በወሲብ ወቅትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ሴቶች በማህፀን ቲቢ እንዳይጠቁ ምን አይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል?

0

የማህፀን ቲቢ ጉዳይ

– የማህፀን ቲቢ ልክ እንደ ማህፀን ካንሰር የመዛመት ፍጥነቱ ከፍተኛ ነው
– በወሲብ ወቅትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ሴቶች በማህፀን ቲቢ እንዳይጠቁ ምን አይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል?
– የማህፀን ቲቢ ለመካንነትም ሆነ ለወር አበባ መዛባት ዋናው ተጠያቂ እንደሆነስ ያውቃሉ?

ቢ (ቲብርክሎሲስ) ኢንፌክሽን ሲሆን መነሻና መድረሻው ባክቴሪያ ነው፡፡ በሽታው ሲጀምርም ሆነ ሲድን ሰፋ ያለ ጊዜን የሚወስድ ነው፡፡ የቲቢ ኢንፌክሽን የማያጠቃው የሰውነት ክፍል እና የህብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ በአብዛኛው ሳንባን፣ አንጀትን፣ ልብን፣ አንጎልንና ማህፀንን ጨምሮ ቆዳን፣ አጥንትን፣ ጉበትን፣ ጉሮሮን ሌሎችንም የሰውነት ክፍሎችን ያጠቃል፡፡

uterine-cancerአንዳንድ ጊዜም ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ማለት ይቻላል ቲቢን እና ካንሰር በሽታን ለይቶ ለማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ ካንሰር ሰውነትን በማዳከም ለቲቢ በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የቲቢ በሽታ ወደ ካንሰር የመለወጥ እድል የለውም፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ሐኪም በአንድ የጤና ተቋም የገጠማቸው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህም የወር አበባቸው በጤና ችግር ሳቢያ የቆመባቸው አንዲት ተለቅ ያሉ ሴትዮ ለምርመራ ወደ ጤና ተቋሙ ይመጣሉ፡፡ ሴትየዋ ምርመራ ሲደረግላቸው 1 (አንድ) ሊትር የሚሆን መግል በማህፀናቸው ውስጥ ተጠራቅሞባቸው ይገኛል፡፡ እኚህ ሴትዮ ስኳር በሽታ አላቸው፣ በማህፀናቸው ውስጥ መግል አለ፣ የወር አበባቸው ቀርቷልና ሌሎችም በሴትየዋ ላይ የሚታዩት ምልክቶች የሚጠቁሙት የማህፀን ካንሰር አላቸው ተብሎ የሚያስገምት ነው፡፡ ካንሰር ነው የሚለውን በእርግጠኝነት የቀረበ ጥርጣሬ በመያዝ ሐኪሙ ቀዶ ህክምና አድርገው የተጠራቀመውን መግል እንዲወጣ ያደርጋሉ፡፡ ቀጥሎም ከማህፀን ግድግዳው አካባቢ ለባዩብሲ ምርመራ (የቲሹ ምርመራ) ይልካሉ፡፡ የምርመራ ውጤቱ ያመላከተው የማህፀን ካንሰር መሆኑን ሳይሆን የሴትየዋ የጤና ችግር የማህፀን ቲቢ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ከሐኪሙ የስራ ላይ ገጠመኝ መገንዘብ የሚቻለው የማህፀን ቲቢና ካንሰር በጠቋሚ ምልክታቸው በመመሳሰላቸው ሳቢያ ለይቶ ይሄ ነው ለማለት ከባድ መሆኑን ነው፡፡ በመግቢያዬ አካባቢ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የዛሬው ርዕሰ ጉዳይ የማህፀን ቲቢ ነው፡፡ በዚህ በሽታ ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን አንድ የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም አነጋግረናል፡፡ ውይይታችን እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ማህጸን እንዴት ነው በቲቢ የሚጠቃው?

ማህፀን በቲቢ ኢንፌክሽን የሚጠቃው በሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ ይህም በደም ስር አማካኝነት ከሌላ የሰውነት ክፍል በመምጣት ነው፡፡ ይህም ማለት ከቆዳ፣ ከአጥንት፣ ከአንጀት፣ ከሆድዕቃ አካባቢ፣ ከሳንባ እና ከመሳሰሉት የሰውነት ክፍሎች በደም አማካኝነት በመምጣት ማህፀንን ያጠቃል፡፡ አልፎ አልፎም ከራሱ ከማህፀን የሚነሳ ቲቢ ይኖራል፡፡ እንደዚሁም እንደ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ሁሉ በግብረ ስጋ ግንኙነት ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድልም አለው፡፡ ባክቴሪያው አስቀድሞ ወደ ሰውነት የሚገባበት መንገድ ምንድነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የቲቢ ባክቴሪያ ያለበት ህመምተኛ ሰው በሚተነፍስበት ወቅት አየሩን ይበክለዋል፡፡ የተበከለውን አየር ጤናማ የሆነ ሰው በሚስብበት ጊዜ ባክቴሪያውን ወደ ሰውነቱ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ ዋና የመተላለፊያ መንገዱም ትንፋሽ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በሁሉም ሰው ውስጥ የቲቢ ባክቴሪያ ይኖራል፡፡ ባክቴሪያው የሰውነት በሽታዎችን የመከላከል አቅማችን እየተዳከመ በሚሄድበት ወቅት ባክቴሪያው በበሽታ መልክ የመከሰት እድል ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም የቲቢ ባክቴሪያ ወተት ውስጥ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ያልተፈላ ወተት በሚጠጣበት ወቅት ባክቴሪያው በአንጀት በኩል አድርጎ ወደሰውነት ይሰራጫል፡፡ ከሚሰራጭባቸው የአካል ክፍሎች አንዱ ደግሞ ማህፀን ነው፡፡ በተለይም ወደ ማህፀን በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጨው በወተት አማካኝነት ወደ ሰውነት የሚገባው የቲቢ ባክቴሪ ነው፡፡ ሌላው መተላለፊያ ደግሞ መጠኑ አነስተኛም ቢሆን በግብረ ስጋ ግንኙነት ሊተላለፍ የሚችልበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡

ቀደም ብለው እንደገለጹልኝ ከማህጸን ከራሱ የሚነሳ ቲቢ አለ፡፡ እንዴት ነው ቲቢ ከማህፀን የሚነሳው?

መተላለፊያ መንገዱ አንድ አይነት ሆኖ ወደ ሰውነት የገባው ባክቴሪያ በሊንፋቲክስ ወይም በደም ስር አማካኝነት ባክቴሪያው ሌላውን የሰውነት ክፍል ሳይነካ ማህፀን ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ከማህፀን ቱቦ፣ በብልት፣ በማህፀን በር እና ልጅ የሚወጣበት እና የሚያድግበት ካላኒኩላር የሚባል አለ በእነዚህ አካሎች አድርጎ ወደ ማህፀን ይገባና በሽታ ሆኖ ይከሰታል፡፡

ከሌሎች የአካል ክፍሎች ከሚነሳውስ የትኛው ነው በይበልጥ ማህፀንን የማጥቃት እድል ያለው?

ዋናውና ቀዳሚው ያልተፈላ ወተት ተጠጥቶ በአንጀት በኩል የሚተላለፈው ነው፡፡ ሌላ ደግሞ ከግላንድ (ዕጢዎች) እና ከሳንባ የሚነሳው ቲቢ ማህፀንን በማጥቃት ደረጃ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው፡፡

የማህፀን ቲቢ አይነት ካለው ቢገልፁልኝ?

አንዳንዱ ዝም ብሎ የላይኛውን የማህፀን አካል ብቻ የሚያጠቃ አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ልጁ የሚያቅፈውን የውስጠኛውን የማህጸን ክፍል ያጠቃል፡፡ ሌላው ደግሞ የውስጡንም ሆነ የውጭውን ሁሉንም የማህጸን ክፍል የሚያጠቃው አይነትም አለ፡፡ የዘር መተላለፊያ ቱቦዎችንና የዘር ፍሬ መፈጠሪያውን ቦታ ብቻ ለይቶ የሚነካበት ሁኔታም ይከሰታል፡፡ በሌላም በኩል አንዳንዱ ቲቢ ዝም ብሎ ትልቅ እጢ መሰል ነገር ፈጥሮ በእጅ በሚነካ መልኩ የሚፈጠርበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እንደ ምስር አይነት ሆኖ በየቦታው ተሰራጭቶም የሚገኝበት ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ አይነቱም ሆነ ደረጃው የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

በዓለም አቀፍም ሆነ በአገራችን ስርጭቱ ምን ይመስላል?

በአጠቃላይ መልኩ ቲቢ ሰዎችን በበሽታነት መልኩ ተከስቶ የሚያጠቃው የሰውነት መከላከያ አቅም ሲዳከም ነው፡፡ በምግብና በበሽታዎች በተለይም በአሁን ሰዓት የከፋ ችግር እያስከተለ ባለው በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ በኢንፌክሽን፣ በካንሰርና በመሳሰሉት ህመሞች ሳቢያ የሰውነት የመከላከል አቅም በሚዳከምበት ወቅት በዚያው መጠን በቲቢ የመታመማችን እድል የሰፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በአገራችን የስርጭቱን መጠን በትክክል የሚያስገነዝቡ የጥናት ውጤቶች ባይኖሩም ኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ የምግብ እጥረትና በኢንፌክሽን መልክ የሚፈጠሩ በሽታዎች በስፋት የሚታዩ በመሆናቸው እነዚህ ችግሮች ደግሞ ሰውነትን የማድከም እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎች የአካል ክፍሎች የሚከሰተውም ሆነ የማህፀን ቲቢ በአገራችን ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የማህጸን ቲቢ ስርጭት ከአገራችን ሁኔታ ጋር ከሚቀራረቡ ሀገሮች ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ከ2 እስከ 4 በመቶ ይደርሳል፡፡

የማህፀን ቲቢ ሲከሰት የሚያሳያው ምልክቶችስ?

አንዳንዱ ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ለሌላ የጤና ችግር ምርመራ ስናደርግ አልያም በሌላ የጤና ችግር ምክንያት የቀዶ ህክምና በምናደርግበት ጊዜ ጤነኛ ናት ባልናት ሴት ላይ የማህፀን ቲቢ የምናገኝበት ወቅት ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን የማህፀን ቲቢ ምልክት የሚያሳይ ከሆነ ዋና ዋና የሚባሉት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
– እንደማንኛውም ቲቢ ኢንፌክሽን የሰውነት ክብደት በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል
– የምግብ አለመስማማት አልያም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ይታያል
– ሌሊት ሌሊት ማላብ
– ከፍተኛ ተብሎ በሚገለፅ ደረጃ ትኩሳት መኖር
– በማህፀን በአንደኛው ክፍል እብጠት መኖር
– የወር አበባ መዛባት (ይህም ማለት መጠኑ ሊቀንስ፣ ያለጊዜው ሊመጣ ወይም አጠቃላይ ያለመምጣት ሁኔታ ይፈጠራል)
– በማህፀን አካባቢና በማህፀን ቱቦ ላይ መግል የመሰለ ነገር መፈጠር እና
– በተለይም የመውለጃ ዕድሜያቸው ከጀመረ በኋላ መውለድ እንቢ ማለት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ከላይ የገለፅኳቸው ምልክቶች ቲቢ ሊሆን ይችላል ብለን ለመገመት የሚያግዙ ይሆናሉ ማለቴ እንጂ የማህፀን ቲቢ በሽታን በትክክል ይሄ ነው ብሎ ለመወሰን የሚያስችል የታወቀ ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱም ማህፀን አካባቢ የሚታዩ እብጠቶች አልያም የማህፀን ቱቦ መዘጋት ሁሉ ቲቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በተመሳሳይም በማህፀን አካባቢ መግል በመታየቱ ብቻ ቲቢ ነው ማለትም የሚል አይሆንም፡፡ ስለሆነም የማህፀን ቲቢ በሽታ ነው ብሎ የሚታዩትን ጠቋሚ ምልክቶች በሙሉ አሰባስቦ በአግባቡ ማጤንን የግድ የሚል ነው፡፡
በሴቶች ላይ ያለመውለድ ችግር ከሚያመጡ የጤና ችግሮች ጋር ሲነጻፀር የማህፀን ቲቢ ያለው እድል እንዴት ነው? ያለመውለድን ችግር የሚያመጡት በወንድየውም ሆነ ከሴትየዋ አንፃር በርካታ ናቸው፡፡ የሴቶችን ጥቂት አብነቶች ብንወስድ የማህፀን ቱቦንና የሴት ዘር ፍሬ ማመንጫውን (ኦቫሪውን) የሚያጠቁ የጤና ችግሮች ጀምሮ ማህፀን በተፈጥሮ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አለመኖር፣ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ሳይፈጠር መቅረትና የተለያዩ የአባላዘርና የኢንፌክሽን በሽታዎን መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ በኢንፌክሽን መልክ ከሚመጡ የማህፀን አካባቢ በሽታዎች ደግሞ አንዱና ቀዳሚው ቲቢ ነው፡፡ የቲቢ ባክቴሪያ በቀዳሚነት የሚያጠቃው የማህፀንን ቱቦ ነው፡፡ በመሆኑም ቱቦው ሊቆስልና ሊደፈን ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ የሴቷን የወንዱ የዘር ፍሬ መገናኛ ድልድዩ ተቋረጠ (ተሰበረ) ማለት ነው፡፡ የዘር ፍሬዎች መገናኘት ካልቻሉ ደግሞ ፀንሶ መውለድ የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህ የማህፀን ቲቢ ከሌሎች መካንነትን ከሚያመጡ የጤና ችግሮች ሁሉ የቀደመ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡

የማህፀን ቲቢ በምን አይነት ሴቶች ላይ የበለጠ የመከሰት እድል አለው?

የወር አበባ በማየት ላይ ያሉ ሴቶች ሁሉ በማህፀን ቲቢ ይጠቃሉ፡፡ ነገር ግን የወር አበባ ማየት ሲያቆሙ በማህፀን ቲቢ የመጠቃት እድላቸው እየቀነሰ የሚመጣ ነው የሚሆነው፡፡

በበሽታው የተጠቃች አንዲት ሴት በሚያጋጥማት ጉዳቶች ዋና ዋና የሚባሉትን ማየት ብንችል?

– የማያባራና ከፍተኛ የሆነ የማህፀን ህመም ይኖራታል፡፡
– የግብረ ስጋ ግንኙነት በምትፈፅምበት ወቅት ከፍተኛ ህመም ይኖራል፡፡
– የክብደት መጠኗ ከሚጠበቀው መጠን በእጅጉ ያነሰ ስለሚሆን በዕለታዊ እንቅስቃሴዋም ሆነ በስራዋና በትምህርቷ ደካማ ትሆናለች፡፡
– ምግብ የመመገብ ፍላጎት ቢኖራትም ስለማይስማማት መመገብን እንድትጠላ ትገደዳለች፡፡
– ከነጭራሹም የምግብ ፍላጎቷን ልታጣው የምትችልበት አጋጣሚም ሰፋ ያለ ይሆናል፡፡
– መካን ትሆናለች
– ልጅ የሚያቅፈውን የማህፀን ግድግዳ የሚያጠቃው ቲቢ ከሆነም ከፍ ያለ ጠባሳን ያመጣል፡፡ በዚህም ሳቢያ የኋለኛውና የፊተኛው የማህፀን ግድግዳ ይጣበቃል፡፡ በሚጣበቅበት ወቅት የወር አበባ ኡደት እንዲቋረጥ ከማድረጉም በላይ በሴትየዋ ላይ የሞት አደጋን የማምጣት እድል አለው
– ከማህፀን የተነሳ ቲቢ አጠቃላይ የሆድ ዕቃን፣ ሳንባን፣ አጥንትንና አንጎልን ጭምር አጠቃላይ የሰውነት ክፍልን በመበከል አጠቃላይ የሆነ የጤና ቀወስን ሊያስከትል ይላል፡፡

ከማህፀን ከራሱ ላይ የሚነሳ ቲቢ በአብዛኛው የትኞቹን የአካል ክፍሎች ያጠቃል?

– በአግባቡ ሳይታከም ቀርቶ የመዛመት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ከመተላለፊያ መንገዱ ዋነኛው ደም በመሆኑ የማይበክለው የሰውነት ክፍል አለ ለማለት ባይቻልም በቀዳሚነት ሊገለፁ የሚችሉትን ልጥቀስ፡፡
– ሙሉ የሆድ ዕቃን
– ጉበትን
– ሳንባን
– በሰውነት ውስጥ እንደ መረብ የተዘረጉትን ሊንፋቲክስን በአብዛኛው ያጠቃል

ምርመራውስ?

የቲቢውን መነሻ ለማወቅ የላብራቶሪ ምርመራዎችን እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ የአክታ፣ የሳንባ ራጅ እና የዕጢዎች የናሙና ምርመራ እናደርጋለን፡፡ በነዚህ የምርመራ ሂደቶች የምናገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ ሴትየዋ ለህክምና የመጣው በወር አበባዋ ወቅት ከሆነ ከወር አበባዋ ላይ ናሙና በመውሰድ ምርመራ እናደርጋለን፡፡ ብዙ ጊዜ አስተማማኝ የሚሆነውና የሚመከረው ከወር አበባ ላይ የሚወሰደው የናሙና ምርመራ ነው፡፡ ነገር ግን የወር አበባ የሌለበት ወቅት ከሆነ ከማህፀን ግድግዳ ላይ ናሙና በመውሰድ ምርመራ እናደርጋለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያለመውለድ ችግር አለብኝ የምትል ከሆነ የማህፀን ቱቦን ራጅ እናስነሳለን፡፡ ረጅም ቱቦው በቲቢ ባክቴሪያ የተጠቃ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነሱ ካሉ ላለመውለድ ችግሩ ቲቢ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ ሲቲ ስካንም ሆነ ሌሎች ከፍ ያሉ ዘመን ወለድ የመመርመሪያ መሳሪያዎች ምናልባት ማህፀን ውስጥ እብጠት ካለ ካንሰር መሆን አለመሆኑን የመንገር አቅም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የማህፀን ቲቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በመንገር እረገድ ይሄ ነው የሚባል ጠቀሜታ የላቸውም፡፡ ዋናው የማህፀን ቲቢን ለመለየት የሚያስችለን የናሙና ምርመራ ነው፡፡

ህክምናውስ?

ማህጸን ላይም ሆነ ለሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ለሚከሰት ቲቢ በሽታ ዋናውና ተመራጩ ህክምና የመድሃኒት ህክምና ነው፡፡ ለምሳሌ ማህፀን ውስጥ እብጠት ካለ በመድሃኒት ህክምና ሙሽሽ ብሎ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን በሚሰጠው የመድሃኒት ህክምና ማህፀን ውስጥ ያለ እብጠት ላይጠፋ ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ እና በመድሃኒት ህክምናው ተሞክሮ አልጠፋ ያለ ቲቢ ከሆነ የቀዶ ህክምና የግድ የሚል ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ግን ለቲቢ በሽታ የሚታዘዘው ቀዶ ህክምና በመድሃኒት የሚደረገው ህክምና የመጨረሻ ተስፋ አስቆራጭ ሲሆንና ምንም አይነት አማራጮች ሲጠፉ ብቻ ሐኪሙ ተገዶ የሚገባበት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡

ለማህፀን ቲቢ ቀዶ ህክምና የግድ እንዲደረግ የሚያስገድዱ ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

ቅድመ ሀኔታው የጠቋሚ ምልክቶች አለመጥፋት ነው፡፡ ለምሳሌ በመድሃኒት ህክምና ያሉ አማራጮች ሁሉ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ከሆኑ በኋላ የሰውነት ክብደት ካልጨመረ፣ የምግብ ፍላጎት የመስተካከል ሁኔታ ካሳየ፣ በማህፀን ውስጥ የተፈጠረው እብጠት ካልጠፋ፣ ትኩሳትና ሌሊት ሌሊት የማላቡ ሁኔታ እየጠፋ መሄድ ካልቻለ ችግሩን በቀዶ ህክምና ለማስወገድ ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡ ቀዶ ህክምና ሲደረግ ግን ማህፀኑን፣ የዘር ፍሬ መፈጠሪያውን ኦቫሪ፣ ቱቦውን ሙሉ በሙሉ ቆርጦ ለማውጣት ሊያስገድድ ይችላል፡፡ የመድሃኒት ህክምናው ካልተሳካ ባብዛኛው የሚደረገው ቀዶ ህክምና ይሄው ነው፡፡

ህክምናው በሀገራችን ደረጃ ውጤታማ ነው?

በመድሃኒት የሚደረገውም ሆነ የቀዶ ህክምናው በአገራችን ደረጃ አስተማማኝና ውጤታማ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን የቀዶ ህክምናው በሚደረግበት ወቅት በማህፀን አካባቢ ያሉ የሰውነት ክፍሎች ለምሳሌ የአይነ ምድር መውጫ፣ አንጀትና የመሳሰሉ የአካል ክፍሎች ላይ ጉዳት የመድረስ እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ቀዶ ህክምናውን የሚሰራው ሙያተኛ የማህፀን ሐኪምና ልምድ ያለው ቢሆን ይመረጣል፡፡

ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ምን ቢደረግ ይበጃል ይላሉ?

የመጀመሪያውና ትልቁ መከላከያ የቲቢ ባክቴሪያ የሚተላለፍበትን መንገድ ለይቶ በማወቅ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ በምንም መንገድ ቢሆን ያልተፈላ ወተት አለመጠጣት፣ ቲቢ ህመምተኛ በቤተሰብም ሆነ በስራ አካባቢ ካለ በአንድ በኩል ለእራስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህመምተኛው ተገቢውን ህክምና እንዲያደርግ መምከርና ማገዝ ለጋራ ጤና በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚሁም የምንፈፅመው የግብረ ስጋ ግንኙነትን ጤናማና ለየትኛውም አይነት በሽታ የማያጋልጠን መሆኑን ከስሜታዊነት ሰከን ብለን ማሰብ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በማህፀንም ሆነ በሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ የሚፈጠርን ቲቢ በሽታ ለመከላከል መተላለፊያ መንገዶችን ማወቅና መጠንቀቅ መቻል ነው፡፡

Source- Zehabeha.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.