በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ታትሞ የወጣ

ኮሌስትሮል የሁሉም እንስሳት ህዋሳት አካል የሆነ የማይሟሟ ነጭ የቅባት አይነት ሲሆን በበርካታ የሰውነት ተግባራት ውስጥ ቁልፍ ስራዎችን ያከናውናል፡፡ ሆርሞን ዝግጅት ውስጥ አለ፤ ሰውነት ቫይታሚን ዲ መጠቀም እንዲችል በመርዳቱም ይታወቃል፡፡ የሴቶችና የወንዶችን ፆታዎች ሆርሞኖች ቴስቴስቴሮን እና ኤስትሮጅን እንዲሁም ሀይል አጠቃቀማችንን የሚያስተካክለው አድሬናል ሆርሞን ምርትም ግብአት ነው፡፡ ቅባት ነክ ምግቦችን ስንመገብ ለመፍጨት የሚያገለግለው ሀሞትም ከኮሌስትሮል ነው የሚዘጋጀው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የህዋሳቶቻችን ሽፋኖችም እንዲሁ ስሪታቸው ኮሌስትሮል ነው፡፡ ነርቭ ጫፎችን በመሸፈንም የነርቭ መልዕክቶች የተቀላጠፈ እንዲሆኑ ይረዳል፡፡

ኮሌስትሮል ራሱ የሚዘጋጀው በዋናነት በጉበት ውስጥ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሰውነት ህዋሳቶችም ኮሌስትሮልን ይሰራሉ፡፡ በደም ውስጥ ሊፖፕሮቲንስ በተሰኙ ተሸካሚዎች ይዘዋወራል፡፡
cholestorl
የኮሌስትሮል ምንጮች

ያለው በቂ በመሆኑም ከሰውነት ውጪ የሚመጣ ኮሌስትሮል አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከውስጥ ተጨማሪ ምግብ አያስፈልግም፡፡ ይሁንና የምንወስዳቸው ምግቦች ውስጥ ቅባት ስለሚገኝ ጤናማውን ምጣኔ በአመጋገባችን ምክንያት እናዛባዋለን፡፡ ከእነዚህ ኮሌስትሮል በብዛት ከምንወስድባቸው ምግቦች መካከል እንቁላል፣ ስጋና ሌሎች ሙሉ ቅባት ያላቸው የእንስሳት ተዋፅኦ ውጤቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ሁሉም ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦች ኮሌስትሮልን የሚይዙ ሲሆን ከኮሌስትሮል ነፃ የሆኑት ከእፀዋት የሚገኙ ምግቦች ብቻ ናቸው፡፡

በተለይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኙት እንቁላል፣ ስጋ እና ቅቤ የምቾት ምግቦች ተብለው ስለሚቆጠሩ የሚበዛው ሰው ትንሽ ገንዘብ ሲያገኝ እነዚሁኑ ምግቦች ይሸምትና ይጠቀማል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተማ አካባቢ ብዙ መቀመጥ እና ኮሌስትሮል በዝቶ የሚገኝባቸውን ፈጣን ምግችና ጥብሳ ጥብሶችን የመመገብ ልምዶች እየሰፉ በመምጣታቸውም ኮሌስትሮል ጉዳቱ በቅጡ ሳይታወቅ ለበርካቶች የጤና ጠንቅ እየሆነ መምጣቱን ባለሞያዎች ይገልፃሉ፡፡

ጥሩ ኮሌስትሮል፣ መጥፎ ኮሌስትሮል

ኮሌስትሮል በሰውነት ውስጥ የሚዘዋወርበት ዋነኛ ሁለት መልክ ያለው ሲሆን አንደኛው ‹‹ጥሩ›› ሌላኛው ‹‹መጥፎ›› ተብለው በተለምዶ ይጠራሉ፡፡ መጥፎ የሚባለው አይነት የኮሌስትሮል መልክ ዝቅተኛ ግዝፈት ያለው ኮሌስትሮል ሲሆን ከጉበት ወደ ህዋሳት የሚደርሰው ኮሌስትሮል በዚህ መልክ ይገኛል፡፡ በደም ውስጥ መጠኑ ከልክ ሲያልፍ የደም መተላለፊያ መስመሩን ሊደፍን ስለሚችል ነው መጥፎ የተባለው፡፡ የደም ቧንቧዎቹ መደፈን ደግሞ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚደርሰው ደም እንዲገታ እና ለልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች እንድንጋለጥ ያደርጋሉ፡፡

ጥሩው የሚባለው ከፍተኛ ግዝፈት (ዴንሲቲ) ያለው ኮሌስትሮል መልክ የደም ቧንቧዎችን ጨምሮ በህዋሳት ውስጥ የተጠራቀመውን ትርፍ ኮሌስትሮል መጥጦ ወደ ጉበት የሚያስወግድ በመሆኑ በጥሩነቱ ይነሳል፡፡ ጥሩም መጥፎም ለመባል መጠኑ ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ባለሞያዎች የኮሌስትሮል ልኬትን ተለክቶ ማወቅና ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጨምረው ይገልፃሉ፡፡

ጤናማ የኮሌስትሮል

መጠን ምን ያህል ነው?
ኮሌስትሮል ለተለያዩ የሰውነት ወሳኝ ተግባራት አስፈላጊ እንደመሆኑ በሰውነት ውስጥ እንዲገኝ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ኮሌስትሮል ያስፈልገናል የሚለው እና መጠኑም በጤናማ ክልል ውስጥ ስለመገኘቱ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ጤናማ የኮሌስትሮል መጠን በሐኪሞቹም ዘንድ ቁርጥ ያለ ቁጥር የሚቀመጥለት አይደለም፡፡ በአማካይ ግን በደም ውስጥ የሚገኝ የኮሌስትሮል መጠን በሊትር ከ5.5 ሚሊሞል መብለጥ እንደሌለበት ስምምነት አለ፡፡ ይህ መጠን የሚፈቀደው ግን ሙሉ ጤነኛ ለሆኑና በተለያዩ ምክንያቶች ለልብና ተያያዥ ህመሞች ተጋላጭነት ለሌላቸው ሰዎች ነው፡፡ ፆታ፣ ዕድሜ፣ በቤተሰብ ውስጥ ያለ የልብ ህመም ታሪክ፣ ሲጋራ የማጨስ ልምድ፣ ከልክ ያለፈ ክብደት እንዲሁም ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም ስኳር ህመም በመጠኑ ላይ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሁኔታዎች በአንድ ሰው ላይ የሚስተዋሉ ከሆነ ዝቅተኛ ግዝፈት ያለው ኮሌስትሮል (መጥፎ ኮሌስትሮል) መጠን ከ2.5 ሚሊሞል በሊትር መብለጥ አይኖርበትም፡፡

በመሆኑም የአንድ ሰው የኮሌስትሮል መጠን በተለያዩ ተጨማሪ አጋዥ ምክንያቶችም የሚወሰን በመሆኑ ለሁሉም ሰው የሚሰራ ምጣኔ ማስቀመጥ በባለሞያዎቹ አይመከርም፡፡ ይህ ግለሰብ በሐኪም ታይቶ ሊወሰን የሚገባ እንደሆነም ይጠቆማል፡፡ ነገር ግን ማንም በሊትር ከ6 ሚሊሞል በላይ ኮሌስትሮል በደሙ የሚገኝ ሰው በባለሞያ ክትትል ሊደረግለት ይገባል፡፡

የኮሌስትሮል ጠንቆች

በሰውነት ውስጥ ኮሌስትሮል በጉበት ውስጥ ስለሚመረት ተጨማሪ ኮሌስትሮል ከምግብ ማግኘት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሰውነት ለራሱ ተግባራት በቂ ኮሌስትሮል ያዘጋጃል፡፡ ይሁንና የተለያዩ የእንስሳት ተዋፅኦ ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት የምንወስዳቸው ቅባቶች በሰውነታችን ከተመረተው ኮሌስትሮል ጋር በጉበት አማካይነት ተቀላቅለው በሊፕሮቲን መልክ ወደ ደም ዝውውር ስርዓት ይቀላቀላሉ፡፡

በደም ዝውውር ውስጥ የእነዚህ ውህዶች መጠኑን ባለፈ ሁኔታ መገኘት ቅባቶች በደም ቧንቧዎች ውስጥ እንዲጠራቀሙ ያደርጋል፡፡ ይህ የቧንቧዎች በቅባት መጠቅጠቅ ቧንቧው እንዲጠብ ቀስ እያለም ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ ያስገድደዋል፡፡ የደም ፍሰቱ መገታት ለከፋ የልብ ህመም እንዲሁም በጭንቅላት የደም መቋረጥ (ስትሮክን) ይዞ ይመጣል፡፡ ስትሮክን ተከትሎ በሚገጥም የመውደቅ፣ የነርቮች መዛበት አሊያም ስራ ማቆም የበረቱ የጤና ችግሮች ይከሰታሉ፡፡

ኮሌስትሮልን መቆጣጠሪያ ስልቶች

ኮሌስትሮል የጤና እክል ከመፍጠሩ በፊት መቆጣጠር መከላከል ይቻላል፡፡ ዋነኞቹ መንገዶችም ከአመጋገብ እና የአኗኗር ስታይል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ቅባት ያላቸውን የተጠበሱ ስጋ እና የስጋ ውጤቶችን መመገብ ይቀንሱ፡፡ የድንች ጥብስ (ቺፕስ)፣ በርገር በተለይ ቺዝ በርገር፣ ኬክ ብስኩትና አጠቃላይ ጥብሳ ጠብሶች የኮሌስትሮል ምንጭ በመሆናቸው ከእነዚህ በሚቻል መጠን መራቅ ይመከራል፡፡

ከምግብ እና መጠጦች በተጨማሪ በሰውነት ውስጥ ያለን የኮሌስትሮል ምጣኔ በመቆጣጠር በኩል የእለት ተዕለት ልምዶችና ባህሪያቶቻችንንም ወሳኝ ናቸው፡፡ አልኮል መጠጦች በተለይ ተቀላቅለው የሚጠጡ መጠጦች የደም ኮሌስትሮልን ሊጨምሩ ስለሚችሉ በቀን ከሁለት በላይ እንዲጠጡ አይመከርም፡፡ ሲጋራም ይከለከላል፡፡ ሲጋራ አደገኛ የሚባለውን ዝቅተኛ ግዝፈት ያለው ኮሌስትሮል ወደ ደም ቧንቧ እንዲገባ በማመቻቸቱ ስለሚታወቅ ሲጋራ አያጭሱ ሲሉ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡ የአካል ብቃት እንቀስቃሴ ጥሩውን ኮሌስትሮል መጠን በሰውነት ውስጥ የጨመረም ጥቅም ስላለው በሳምንት ቢያንስ ለ3 ቀናት ለ30 ደቂቃ ፈጣን እርምጃ ቢያደርጉ እንኳ ኮሌስትሮል ምጣኔን በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ ክብደትዎ በጤናማ ክልል ውስጥ እንዲሆን ይጣሩ፣ የስኳር መጠንዎን መቆጣጠርም ይመከራል፡፡ የእንስሳት ተዋፅኦ ምግቦች ኮሌስትሮል ስላላቸው ተቆጣጠሯቸው ሲባል አይመገቡ ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ የምግብ አይነቶች ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ እንደ ካልሲየም አይነት ንጥረ ነገሮች ስለሚይዙ መጠናቸውን አያብዙ እንጂ ጨርሰው አያስወግዷቸው፡፡

በምግብ እንዲሁም በአኗኗር ስታይል ጤናማነት ኮሌስትሮልን መቆጣጠር ቢቻልም ይህ ይከብደኛል ላሉት ምዕራባውያን የኮሌስትሮል መቀነሻ መድኃኒቶች ተሰርተው ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ከፋርማሲዎች ይሸጥላቸዋል፡፡ የተሻለው ግን ባለሞያ ጋር ቀርቦ ምርመራ እና እርዳታ ማግኘት ተመራጩን መፍትሄም መከተል ተመካሪ ነው፡፡ የአመጋገብ እና አኗኗር ልምዳችን ግን በእጃችን ነውና ጥንቃቄ አይለየን፣ ጤና ሁኑ!

Source- Zehabesha News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.