ትኩሳትና ህመሞች

0

ሁላችንም ከዚህ በፊት ትኩሳት አጋጥሞን ያውቃል- ቢያንስ በጉንፋን እንኳ ታሞ የማያውቅ የሚኖር አይመስለንምና፡፡ ከመነሻው ስንጀምር ትኩሳት በራሱ በሽታ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእልፍ አዕላፍ በሽታዎች /በተለይም የኢንፌክሽኖች/ ቋሚና ጠቋሚ ምልክት ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ሁላችንም በቅርበት የምናውቀው የበሽታዎቻችን ታርጋ በራሱ ምንድን ነው? በአስገራሚ ሁኔታ እስካሁን የስነ ህይወት ሳይንስ ለዚህ ጥያቄ መቶ በመቶ የሚያስመካ መልስ ለማግኘት አልቻለም፡፡

ibs-gut-pain-peppermint-oil-200በጥቅሉ ተመራማሪዎችን የሚያስማማ አንድ ማብራሪያ አለ፡፡ የሰውነታችን የሙቀት መጠን በጤናማው ክልል ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርገው ‹‹›ሃይፓታላመስ›› የተባለው የአንጎል ክፍል ነው፡፡ ሰውነታችን ውስጥ ኢንፌክሽን ሲፈጥር ለመዋጋት የሚታትሩ ነጭ የደም ህዋሳት የተለያዩ ኬሚካሎችን በደማችን ውስጥ ይለቃሉ፡፡ ከእነዚህ ኬሚካሎች ውስጥ ሁለቱ /IL-1,TNF-1/ ወደ አንጎል በመዝለቅ የአንጎልን አሳር የሚያቀውሱ ሌሎች ኬሚካሎች /prostaglandins/ እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ የተለያዩ የአንጎል ክፍሎች በእነዚህ ኬሚካሎች የተነሳ ይታወካሉ፡፡ በኢንፌክሽን ወቅት የአስተሳሰብ ብዥታና የማገናዘብ ብቃት መውረድ የሚመጡባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ የሰውነት ሙቀት የሚቆጣጠረው ነው ‹‹ሃይፓታለመስ››ም የተመሳሳይ ክስተት ሰለባ ይሆናል፡፡

ሃይፓታለመስ በኬሚካሎቹ ጥቃት ሲደርስበት ጤናማ ብሎ መዝግቦት የነበረው የሙቀት መጠንን ይለውጥና ከዚያ የሚበልጥ ሙቀትን በሰውነት ላይ ለማምጣት ይጥራል፡፡ ብርድ ብርድ ማለትንና መንቀጥቀጥ፣ የጥርስ መንገጫገጭ የሚመጡትም በሃይፓታላመስ የታዘዘውን ከፍ ያለ የሰውነት ሙቀት ለማምጣት ነው፡፡ የሰውነት ህዋሳት ወትሮ በላቀ መልኩ ኢነርጂ የማቃጠል ሂደት ይታይባቸዋል፡፡ በገፍ የተቃጠለው ኢነርጂ ደግሞ ከፍተኛ ሙቀትን /ትኩሳትን/ ያመጣል፡፡ ቀጥሎ የሚታየው በላብ መዘፈቅ ደግሞ ሃይፓታላመስ እየናረ የመጣውን የሰውነት ሙቀት ለማውረድ የሚያደርገው የመልሶ ማቀዝቀዝ ጥረት አካል ነው፡፡ ይህ አይነቱ ውሃ ቅዳን ውሃ መልስ ድግግሞሽ ኢንፌክሽኑ እስካለ ድረስ ይቀጥላል፡፡

ትኩሳትን ሁላችንም የምናየው በፍራቻና በቂም አይን ነው፡፡ ነገር ግን ትኩሳት ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ተፈጥሯዊ ሂደት ደግሞ ከጀርባው የሚያስከትለው ጠቀሜታ አያጣም፡፡ ትኩሳትም በኢንፌክሽን ለተጠቃው ሰውነት የሚያበረክተው ጥቅም ይኖራል፡፡ በአንድ በኩል የናረው የሰውነት ሙቀት በኢንፌክሽን ፈጣሪ ጥቃቅን አካላት /ባክቴሪያና ፓራሳይት/ ርቢ እንዳይፋፋም ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የነጭ ህዋሳት የአመራር ሂደት እንዳይቀላጠፍ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ድካምና እንቅልፍ እንቅልፍ እንዲሰማው በማድረግ ህሙማን ኢነርጂ እንዲቆጥቡም ያስገድዳቸዋል፡፡
ይህ ጠቀሜታ ግን ትኩሳት ከሚያስከትለው መዘዝ ጋር ሲወዳደር ዶሮን በቆቅ እንደመለወጥ ይቆጠራል፡፡ ትኩሳት የሰውነትን የኢነርጂ ጥሬ ክምችት ይፈጃል፡፡ መክሳትና አቅም ማጣትንም ያስከትላል፡፡ የሰውነት የፈሳሽ ክምችትን በሟሟጠጥም ለፈሳሽ እጥረት ይዳርጋል፡፡ ትኩሳቱ ኃይለኛ ከሆነ ደግሞ ራስን መሳትንና የሚጥል ህመምን የሚመስል መንቀጥቀጥ /በተለይ በህፃናት ላይ/ ያመጣል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

እንግዲህ ትኩሳትን በህክምና ለማለዘብ ጥረት የሚደረገውም ለዚህ ነው፡፡ መድኃኒት ከመውሰድዎ በፊት በቤትዎ ሊያደርጓቸው የሚችሉት አንዳንድ እርምጃዎችን እንመልከት፡፡
– ፈሳሽ በብዛት ይውሰዱ፡፡
– በቀዝቃዛ ውሃ በራሰ ጨርቅ ሰውነትዎን ያብሱ
– ፈሳሹ ከውሃ ይልቅ አልኮል /መጠጥን ሳይሆን የህክምናውን አልኮል/ ቢሆን ይመረጣል
– በጣም ስስና ሙቀትን የሚያሳልፍ ልብስ ይልበሱ
– አንሶላ፣ ጋቢ፣ ብርድ ልብስ… ‹‹ብርድ ይመታሃል›› ለሚለው የከተማ አፈታሪክ ከመገዛት ውጭ አይጠቅምዎትም፤ እንዲያውም ትኩሳቱን ያፋፍሙታል፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ግን የትኩሳቱ መንስኤ የሆነውን ዋናውን ህመምዎን መመርመርና መታከም እንዳለብዎ አይዘንጉ፡፡ ትኩሳት ምልክት እንጂ በራሱ ህመም አይደለም፤ እሱን ማስታገስ ለበሽታው መዳን ዋስትና አይሆንም፡፡

ከላይ ያየናቸውን እርምጃዎች ወስደው አሁን ትኩሳትዎ ጋብ ካላለ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ ማስታገሻዎችን ከየትኛውም መድኃኒት ቤት መግዛት ይችላሉ፡፡ ፓራሴታሞል ፍቱን ሲሆን ነገር ግን ያልተፈለጉ የጎንዮሽ ጉዳቶች /side effect/ እምብዛም የሌሉት ግሩም መድኃኒት ነው፡፡ እንደ አስፕሪን እና ዳይክሎ ፌናክ አይነቶቹ መድኃኒቶች ከፓራሴታሞል የበለጠ ፍቱንነት ቢኖራቸውም የጨጓራ ህመምን ከማባባስ ጀምሮ ሌሎች ያልተፈለጉ ውጤቶችን ስለሚያመጡ በሐኪም ካልታዘዘልዎ በቀር ባይወስዷቸው ይመረጣል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.