በቅድሚያ ለጥያቄዬ መልስ ለመስጠት በመቻላችሁ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ እንዴት ናችሁ? ጤና ይስልኝ፡፡ ስሜ ሃና ይባላል፡፡ ዕድሜዬ 28 ነው፡፡ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ በሶሲዮሎጂ ተመርቄ በሙያዬ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ የምኖረው ከቤተሰቦቼ ጋር ነው፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የማውቀው አንድ ጓደኛ አለኝ፡፡ ምንም እንኳን ሁለታችንም ከልጅነት ጀምሮ በፍቅር መፈላለጉ ውስጣችን እንዳለ ብናውቅም አንዳችንም አፍ አውጥተን ስሜታችንን ለመግለፅ ባለመቻላችን ምክንያት እንዲሁ በጓደኝነት ብቻ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተናል፡፡ ቅርብ ጊዜ ግን በጋራ አብረን የምናሳልፋቸው ጊዜያት በመጨመራቸው ሁለታችንም ለዓመታት አፍነን ያቆየነውን ስሜት አፍረጥርጠን ለመነጋገር ችለናል፡፡ እርሱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ቀለበት ያሰረላት ልጅ አለች፡፡ እርሷ ደግሞ የምትኖረው እንግሊዝ ሀገር ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ትመጣና ተጋብተን እኔም ወደዛው አመራለሁ የሚል ሀሳብ አለው፡፡ እርሱ እንደዚህ ይበል እንጂ ተጋብተው ለመሄድ ግን እስከዛሬ ድረስ ለእኔም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት አልቻሉም፡፡
ታዲያ መገናኘቱ እና አብሮ ማምሸቱ እየጨመረ ሲመጣ ስሜታችንን መቆጣጠሩ ለሁለታችንም አስቸጋሪ ሆነና አብረን ማደር ጭምር ጀመርን፡፡ በዚህ መልኩ ለጥቂት ጊዜያት እንደቆየን እያደረግን ያለነው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ተነጋግረን ተለያየን፡፡ ምንም እንኳን እንለያይ፤ ከዚህ በኋላ አንገናኝ የሚል ውሳኔ ከእርሱ ሲመጣ እኔም አጨብጭቤ ብቀበለውም ስሜቴ ግን በጣም ነበር የተጎዳው፡፡ ለበርካታ ቀናት ደብሮኝ፣ ሰው ማግኘት አስጠልቶኝ መኝታ ቤቴን ዘግቼ አለቀስኩ፡፡ እንደምንም መጎዳቴን አባብዬ አሁን ቆረጠልኝ ስል በድጋሚ መደወል እና እንገናኝ ማለት እርሱ አመጣ፡፡ አይሆንም ማለት ደግሞ እኔ አልቻልኩም፡፡
‹‹በዚህ ሁኔታ እስከመቼ እንቀጥላለን? ግልፅ አድርግላትና ተለያይታችሁ አብረን እንሁን ለቤተሰብም እናሳውቅ›› ብለው እርሱ እምቢ አለ፡፡ ሌላው ቀርቶ በግልፅ ለመወያየት እንኳን ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ይህ ጠባዩ ግራ ቢያጋባኝም፣ ቢያናድደኝም ከልቤ ስለምወደው ግን ሁለተኛ አይንህን ማየት አልፈልግም ማለት አልቻልኩም፡፡ ነገ አብረን እንሁን አንሁን ግልፅ መሆን ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ አብረን መሆኑ ያማል፤ ጨርሶ ከእርሱ መራቁም እንዲሁ ከብዶኛል፡፡ ከዚህ ግራ አጋቢና አስጨናቂ ግንኙነት እወጣ ዘንድ ምን ትመክሩኛላችሁ፡፡
ሐና ነኝ ምስጋና ጋር

Boring-marriage
የኢሳያስ ከበደ ምላሽ፦ ውድ ሐና፣ ጤና ይስጥልን! እንዲህ አይነቱን በጣም የግል የሆነውን ጥያቄ ለመጠየቅ ድፍረት ስላገኘሽ ላመሰግንሽ እወዳለሁ፡፡ በደብዳቤሽ ውስጥ የተጠቀሰውን መረጃ መሰረት በማድረግ ለጉዳይሽ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
የፍቅር አካሄድ ውጣ ውረድ የተሞላበት መንገድ ነው አንዳንድ ጊዜ ፍቅር ሰው በሚፈልገው መንገድ ላይሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህ የተፈለገው ባይገኝ ከተገኘው ጋር ወዳጅነትን መመስረት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ የማግባት ፍላጎት ካለሽ (ከደብዳቤሽ መንፈስ ለማግባት ፍላጎት ያለሽ ይመስላል) ምቹ ሁኔታ አለሽ፡፡ ዕድሜሽ ለጋብቻ ደርሷል፤ ስራና የገቢ ምንጭ አለሽ፣ ወንድን የመውደድ ችሎታና ልምድ አለሽ፡፡

ስለ አንቺ የተቃራኒ ፆታ የፍቅር ጉዞ ምን እንደሚመስል ከደብዳቤሽ ዝርዝር መግለጫ ባይኖርም የወደድሽውን ወንድ ‹‹እወድሃለሁ›› ብሎ በልብሽ ውስጥ ያለውን ሐሳብሽን መግለፅ እንደሚከብድሽ መገመት ይቻላል፡፡ አሁን የፍቅር ጓደኛሽ ከሆነው ወንድ ጋር ከልጅነት እስከ ወጣትነት ዕድሜሽ ድረስ ብታፈቅሪውም እንደምትወጂው መናገር አልቻልሽም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ የአንቺ ሊሆን የሚችለው ሰው በሌላ ሴት ተይዟል፡፡ ልብሽ እየፈቀደ፣ አንደበትሽ ግን አልከፈት በማለቱ ዕድሉ ሊያመልጥሽ ሆነ፡፡ ይህ ስለአንቺ ሁኔታ የሚናገረው መልዕክት አለው፡፡ የተሰማሽን ስሜት፣ ያሰብሽውን ሀሳብ ለመናገር የሚያስቸግርሽ ይመስላል፡፡ አዕምሮሽን የሞላውን ሀሳብ ይዘሽ የማያዳግም ውሳኔ ለመወሰን ትቸገሪያለሽ፡፡

የሚጠቅምሽን ነገር ለማግኘት በተገቢው ጊዜ መወሰን አለመቻል ብቻም ሳይሆን የሚጎዳሽንም ነገር ለመተው ቆራጥ ውሳኔ ለማድረግ እየተቸገርሽ ነው፡፡ የአንቺ ጓደኛ ከአንቺ ጋር በፍቅር ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው በግልፅ ነግሮሻል፡፡ አንቺ ግን በጣም ስለወደድሽው የእርሱን ፍላጎት እያረካሽ ከእርሱ ጋር አለሽ፡፡ እርሱ ሌላይቱን ለሚስትነት እየጠበቃት ከአንቺ ጋር ጊዜያዊ ስሜቱን እያረካ ይገኛል፡፡

በእኔ መረዳት አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ የማስባቸው ሐሳቦችን ልጥቀስ፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ሀሳብ ይህ ጓደኛሽ የወደፊት ባልሽ ሆኖ በዘላቂነት ከአንቺ ጋር ባይኖርም የፍቅር ግንኙነቱን ከእርሱ ጋር መቀጠል ነው፡፡ በዚህ አማራጭ መፍትሄ መሰረት ወዳጅሽ በእንግሊዝ ሀገር ያለችውን እጮኛውን እስኪያገባት ድረስ ለጊዜው ከእርሱ ጋር መቆየት ትችያለሽ፡፡ በዚህ አይነት ከእርሱ ጋር መቆየት ትችያለሽ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ከምትወጂው ሰው ጋር በፍቅር መኖ ትችያለሽ፡፡ ድብርት አይሰማሽም፡፡ ሆኖም ይህ ፍቅርና ወዳጅነት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ይቆያል፡፡ እርሱ ወደ ዘላቂ ግንኙነቱ ሲሄድ አንቺ ብቻሽን ትቀሪያለሽ፡፡ ያን ጊዜ የስሜት መጎዳት ያጋጥምሻል፤ አሁን ከእርሱ በራቅሽ ቁጥር የሚሰማሽ ድብርቱና ሀዘኑ ያን ጊዜ እጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የመፍትሄ መንገድ ነገ ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት ሳያስቡ በጭፍን የዛሬውን ስሜት ብቻ ተከትሎ መሄድ ነው፡፡
ሁለተኛው አማራጭ ሐሳብ ደግሞ ወዳጅሽን ከእጮኛው መለየት ነው፡፡ ከዚህ በፊትም አንዳንድ ሙከራዎችን አድርገሻል፡፡ ከእርሷ ጋር ያለውን ግንኙነት ማቋረጥ የሚችልበትን መንገዶች መፈለግና ይህ ከተሳካ ከእርሱ ጋር መጋባት ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ይህን ለማድረግ የተመቻቸ አይመስልም፡፡ በወዳጅሽና በአንቺ መካከል ያለው የፍቅር ስበት ኃይል በእርሱና በእጮኛው መካከል ካለው የስበት ኃይል የበለጠ አይመስልም፡፡ የወዳጅሽ ልብ ከአንቺ ጋር ሳይሆን ከእጮኛው ጋር ነው፡፡ በእርግጥ እርሷን ስለወደዳት ወይስ እንግሊዝ ሀገር ለመሄድ ከእርሷ ጋር እንደተጣበቀ አይታወቅም፡፡ ከሁለቱ አንዱ ወይም ሁለቱም ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ ከልጅነት ጀምሮ የሚያውቅሽና የሚወድሽ (አንቺ እንዳልሽው ከሆነ) ቢሆንም ልቡ ለአንቺ አልተሸነፈም፡፡ ከእርሱ ጋር አብረሽ አድረሽም ልቡ አልተማረከም፡፡ ከዚህ በላይ እርሱን መማረክ የሚያስችል ጥበብ ካለሽ መሞከር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እርሱ ከልጅቷ ጋር ያለው ወዳጅነት ቀለበት ማሰር ደርሷል፡፡ ይህ ማለት ምናልባት ቤተሰብም አውቋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንቺን ቢወድሽም እንኳ ከቤተሰብ ጋር ያለው ግንኙነቱ እንዳይበላሽ ፈርቶ አቋሙን ላይቀይርም ይችላል፡፡ ይህ ቢሳካስ ለአንቺ ምን ያህል የአዕምሮ እርካታ ይሰጥሻል? አንቺ ራስሽን በልጅቷ ስፍራ ብታስቀምጪ፣ የአንቺን እጮኛ ሌላ ሴት ብትቀማሽ ምን ይሰማሻል? ይህ ተቀምቶ የመጣ ባልስ፣ ነገ በሌላ ሴት ተታሎ ከእርሷ ጋር የማይሄድበት ምን ዋስትና ይኖራል?

ሶስተኛው አማራጭ ሐሳብ ከወዳጅሽ ጋር ያለውን የፍቅር ግንኙነት ማቋረጥ ነው፡፡ ይህ ሰው ለጊዜው የፍቅር ፍላጎትሽን ቢያሟላም በዘላቂነት ከአንቺ ጋር አይቆይም፡፡ ከእርሱ መለየት የስሜት ጉዳት ሊያስከትልብሽ ይችላል፡፡ አሁንም ቢሆን ከእርሱ ለመለየት ወስነሽ ለተወሰነ ጊዜ ስትቆዪ የሚሰማሽ ድብርት፣ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ አለ፡፡ ከእርሱ መለየት የሚያስከትለውን የስሜት ጉዳት ፈርተሽ ከእርሱ ጋር መቆየትሽ መፍትሄ አይሆንም፡፡ አንድ ቀን እርሱ ከእጮኛው ጋር ተጋብቶ በዘላቂነት ከአንቺ ሲለይ የስሜት ስብራትሽ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ከእርሱ ጋር በፍቅር ጓደኝነት መቆየትሽ የአንቺን የስሜት ጉዳት ተጋላጭነትን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ አንቺ ሌላ አማራጭ እያለሽ ከእርሱ ጋር በከንቱ ጊዜሽን ማጥፋት የዋህነት ይመስላል፡፡ የአንድ ወገን ፍቅር ዘላቂ የፍቅር ወዳጅነትን አይመሰርትም፡፡ አንቺ በጣም ትወጅዋለሽ፤ አንቺ ለልብ ወዳጅነት ትፈልጊዋለሽ፤ እርሱ ግን አንቺን ለዘላቂ ወዳጅነት ሳይሆን ለጊዜው ከአንቺ ጋር ስሜቱን ለማርካት ነው የሚፈልግሽ፤ የሚደውልልሽም፡፡ ወዳጅነቱን ቢፈልግማ ኖሮ ከዚያች ጋር ያለውን ግንኙነቱን ትቶ ከአንቺ ጋር ይጋባ ነበር፡፡ አሁን ግን እርሱ በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንቺ ጋር መነጋገርም አይፈልግም፡፡ ስለዚህ አንቺ ስራ ያለሽ፣ ዕድሜሽ ደህና ሁኔታ ላይ ሆኖ፣ የሚደግፉሽ ቤተሰብ እያለሽ አንቺ ለጊዜው ብቻ ከሚፈልግሽ ሰው ጋር ለምን እንደምትንከራተች ራስሽን መጠየቅ ይገባሻል፡፡ ይህ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳብ ለጊዜው የስሜት ጉዳት ቢኖውም፣ በዘላቂነት ግን ህይወትሽን ሊጎዳ ከሚችል ግንኙነት አርነት ያወጣሻል፡፡ በዚህ ውሳኔ ሌላ ከአንቺ ጋር ዘላቂ ግንኙነት ሊመሰርት የሚችል ወዳጅ መፈለግ ትችያለሽ፡፡

‹‹ነገ አብረን እንሁን አንሁን ግልፅ መሆን ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ አብረን መሆኑ ያማል፤ ጨርሶ ከእርሱ መራቁም እንዲሁ ከብዶኛል›› ከሚለው ሁኔታ ለመውጣት ቁልፉ ያለው በእጅሽ ነው፡፡ ከሁለቱ የትኛው የስሜት ህመም ይበልጣል?›› እንግዲህ ‹‹ከዚህ ግራ አጋቢና አስጨናቂ ግንኙነት›› ለመውጣት ከላይ ከተሰጡ አማራጭ የመፍትሄ ሐሳቦች አንዱን መምረጥ ይረዳል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.