‹‹ወንዶች አካላዊ ፍላጎታቸውን ለማስታገስ፤ ሴቶች ደግሞ ለተለያዩ ስሜታዊ ምክንያቶች ይወሰልታሉ›› ሲባል ሰምተው ይሆናል፡፡ ጥቂትም እውነትነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ በቅርቡ ሴቶች በፍቅረኞቻቸው ላይ የሚወሰልቱባቸውን ምክንያቶች ለማወቅ በሚል አንድ ጥናት ተደርጓል፡፡ ‹‹አሳሳሙ ይደብረኛል…›› ከሚለው እስከ ‹‹ለበቀል ነው›› የሚሉ ምላሾች ተገኝተዋል፡፡ ጥናቱ እንስቶችን ለመወስለት ያነሳሳሉ ያላቸውን ሰባት ምክንያቶች እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡ 1. ፍቅር ስሜት አልባ ሊሆን ‹‹…ከጆን ጋር ለሶስት ዓመታት አብረን ኖረናል፡፡ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ አብሬው መሆን ያስደስተኛል፡፡ ይሁን እና ፍቅራችን ስሜት አልባ ነው፡፡ አብዛኞቹ የምናውቃቸው ሰዎች የተጋቡ ወይንም ለመጋባት የተጫጩ ናቸው፡፡ ጆን ሳይፈልግ ቀርቶ ሳይሆን ጉዳዩን ሲያነሳው ወዲያው ወሬ ስለምቀይርበት ነው፡፡ ወደ አውስትራሊያ በስራ ምክንያት ሁሌም ከሚማርከኝ የስራ ባልደረባዬ ጋር ተጓዝኩ፡፡ በጣም አስደሳች ወቅትም አሳለፍን፡፡ ከጆን ጋር የተለያየሁት እንደተመለስኩ ነበር፡፡ የሰራሁት ተግባር ደረቴን አስነፍቶ የሚያኮራኝ ባይሆንም ከጆን ያጣሁትን ከዚህ ልጅ አግኝቼ ነበር፡፡ ለሶስት ዓመታት በፍቅር ከቆየን በኋላ አሁን ተጋብተን በደስታ በመኖር ላይ ነን›› ስትል ጊሴል የተባለች የ30 ዓመት ወጣት በቀድሞ ፍቅረኛዋ ላይ እንድትሄድ የገፋፋትን ምክንያት ገልፃለች፡፡

2. ፍቅር ካለቀ በኋላ ለመለየት መፈለግን ደፍሮ አለመናገር ‹‹ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ከሾን ጋር ከመለያየታችን በፊት በጣም የሚወዳት ውሻው ሞታበት ልቡም በጣም ተሰብሮ ስለነበር ካንተ ጋ ያለኝ የፍቅር ግንኙነት አልቆለታል… መለያየት አለብን›› ብዬ ብነግረው ጭካኔ ይሆንብኛል ብዬ በማሰቤ ስሜቱ እስኪስተካከል ድረስ ለወር ወይንም ከዚያ ለበለጠ ጊዜ ልጠብቀው ወሰንኩ፡፡ ሞራሉ ጥሩ በሆነበት፣ ነገሮች የተስተካከሉ በመሰሉበት እና እኔም ለመንገር በተዘጋጀሁበት ወቅት ደግሞ ከስራው ተባረረ፡፡ በድጋሚ ኑሮው እስኪስተካከል መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ በዚህ መሀል ‹‹ፍቅርስ ከዚህ ጋር… ብዬ የምመኘውን አይነት ሰው አገኘሁና አብሬው መሆን ጀመርኩ፡፡ በጊዜ ሂደት ለሾን የሚሰማኝን ነግሬ ተለየሁት፡፡ ከሱ ጋር እያለሁ ከሌላ ሰው ጋር ፍቅር መጀመሬ ግን አልነገርኩትም ነበር፡፡ ይህን ቢያውቅ ኖሮ የሱን ስሜት ለመጠበቅ ብዬ ያደረኩትን ነገር ሁሉ ከታላቅ ክህደት ይቆጥረው ነበር፡፡ ለሱ ያለኝ ስሜት ተንጠፍጥፎ ባለቀበት ወቅት መንገር እንደነበረብኝ ኋላ ላይ ተሰምቶኛል›› ስቴሲ 30 ዓመት ዕድሜ ያላት የሌክሲንግተን ኗሪ፡፡


3. ርቀት ለፍቅርና ለታማኝነት ጠንቅ ነው
‹‹ከምንኖርበት ስፍራ 320 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ኮሌጅ ስኮላርሺፕ አግኝቼ ስሄድ ከፍቅረኛዬ ከክሬግ ጋር ፍቅርን በሩቁ ማስኬድ የምንችል መስሎኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ነገሮችን ባሰብኩበት መንገድ ማስኬድ ችዬ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀናት እየገፉ በሄዱ ቁጥር ላብራቶሪ ውስጥ አብሮኝ ከሚማረው ሄንሪ ከተባለ ወጣት ጋር ፍቅር እንደያዘኝ ተረዳሁ፡፡ እንደቀልድ የተጀመረ ልፊያ ቀስበቀስ ወደ አንሶላ መጋፈፍ አደረሰን፡፡ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ግሬክ እቅፍ ተመልሼ ገባሁ፡፡ ነገር ግን ከሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ አዳጋቻ ሆነብኝ፤ ይሁንና እሱንም ስለምወደው ልለየው አልፈለግኩም፡፡ ሄነሪን በተደጋጋሚ ብጎበኘውም ለኔ የሚሆን አይነት ሰው እንዳልሆነ ሳውቅ ከሱ ጋር ያለንን ግንኙነት አቋረጥኩ፡፡ ስለውስልትናዬ ለግሬክ ምንም አለመናገሬ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያድርብኝ አድርጎኛል፡፡ ይህን ስህተቴንም ባለማወቅ በልጅነት አዕምሮ የተፈፀመ ብዬ ራሴን ለመሸንገል ሞክሬያለሁ፡፡ ኮርሱን ካጠናቀቅኩ ከአራት ዓመታት በኋላ አሁንም ከግሬክ ጋር ነኝ›› ታማራ በፖርትላንድ የምትኖር የ33 ዓመት ሴት ናት፡፡

4. ብቸኝነት እና የማንም አለመሆንን መፍራት ‹‹የሁለት ዓመት ፍቅረኛዬ ዴቭ አልፈልግሽም ብሎ ከተለየኝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከኤሪክ ጋር መውጣት ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ ስሜቴ በጣም ተጎድቶ ስለነበር ኤሪክ ዋነኛው አጽናኜ ነበር፡፡ ከኤሪክ ጋር ለአምስት ወራት እንደቆየሁ ዴቭ ተመልሶ በመምጣት አብሮኝ መሆን እንደሚፈልግ ነገረኝ፡፡ በጣም ናፍቆኝ ስለነበር አብሬው መሆን ጀመርኩ፡፡ ይህን የማደርገው ከኤሪክ ሳልለያይ ነበር፡፡ ይህን ወድጄ ያደረኩት አይደለም፡፡ ምናልባት ዴቭ መልሶ ቢከዳኝ ከኤሪክ ጋር ለመቀጠል እንዲመቸኝ የቀድሞ ጉዳቴ ያስተማረኝ ጥንቃቄ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን አልተሳካልኝም፡፡ ዴቭ አሁንም ከዳኝ ኤሪክ ደግሞ የኔንና የዴቭን ነገር ከጓደኛቹ ሰማ፡፡ ሌላኛውን ትምህርት በሚያም መልኩ ተማርኩ- ከሁለት ወንዶች ጋር ግንኙነት መጀመር ትርፉ ከሁለቱም ሳይሆኑ መቅረት እንደሆነ›› ጄን የ28 ዓመት ወጣት ስትሆን በኦክፓርክ ከተማ ኗሪ ነች፡፡

5. ከመጥፎ ግንኙነት ለመውጣት መሻት ‹‹ኢታን ከሚባልና ሁሌም ከሚተቸኝ ልጅ ጋር ግንኙነት ጀምሬ ነበር፡፡ በየጊዜው ስለክብደቴ፣ ስለ አለባበሴ እና ደባሪ ስለመሆኔ እያነሳ ይተቸኝና ያሸማቅቀኝ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ በጣም ቢጠሉትም፣ እኔን እያበሻቀጠ የፈለገውን ቢለኝም እኔ ግን ከሱ መለየትን አልፈለኩም፡፡ በአንድ የሳምንቱ መጨረሻ ዕለት ፓርቲ ላይ ዊልን ተዋወቅሁት፡፡ ከኢታን ፍፁም የተለየ ደግ፣ ጣፋጭ እና ለጋስ እንዲሁም ፍፁም የተረጋጋና አብረውት ቢውሉ የማይሰለች አይነት ልጅ ነው፡፡ የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት በሙሉ አብረን ካሳለፍን በኋላ ከበሰሉ ወጣቶች ጋ ፍቅር እንዲህ አስደሳች ነው ስል አሰብኩ፡፡ እሁድ ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ ዊልን ሳምኩት፡፡ ብዙም ሳልቆይ ከኢታን ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋረጥኩ፡፡ ከዊል ጋር ለሶስት ዓመታት በፍቅረኝነት ከቆየን በኋላ በጋብቻ ተጠቃለልን፡፡›› አሊሰን የኒውዮርክ ኗሪ ስትሆን የ30 ዓመት ወጣት ነች፡፡

6. ከማንነት ጋር የሚስማማንን ሰው ፍለጋ ‹‹የፍሎሪዳ ተወላጅ በመሆኔ በባህር ዳርቻዎችና በጀልባዎች ላይ መንሸራሸር እወዳለሁ፡፡ የመሀል ሀገር ልጅ የሆነው የቀድሞ ፍቅረኛዬ ክሪስ ደግሞ ይንንን ይጠላ ነበር፡፡ በየጊዜው የት ሄደን መዝናናት እንዳለብን እያነሳን እንጨቃጨቅ ነበር፡፡ ሁልጊዜም እሱ አሸናፊ ነበር፡፡ ለስምንት ወራት ያህል አብረን ከቆየን በኋላ አንድ ዕለት ከጓደኞቼ ጋር ጀልባ ተከራይተን ኪይዌስት ወደተባለ ስፍራ ሄድን፡፡ የጀልባዋ ካፒቴን የባህር ዳርቻዎችን የሚወድ፣ ሳቢና መልከመልካም ወጣት ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ከሱ ጋር ስጫወት አሳለፍኩ፡፡ ያን ዕለት ምሽትም ለብቻችን ጥሩ ጊዜ አሳለፍን፡፡ ወደ ቤቴ ስመለስ ለክሪስ ስለሆነው ምንም አልነገርኩትም፤ እኔም የጥፋተኝነት ስሜት አልተሰማኝም፡፡ ግማሹ እኔነቴ ክሪስ በጣም ግትር በመሆኑ በሱ ላይ መሄዴ ይገባዋል የሚል ስሜት ነበረው፡፡ ከክሪስ ጋር አብረን መዝለቅ አልቻልንም፡፡ ከተለያየን በኋላ የምይዛቸው ወንድ ጓደኞች የባህር ዳርቻን የማያፈቅሩ ከሆነ እርቃቸዋለሁ›› ሊዝ ቺካጎ የምትኖር የ32 ዓመት ሴት ነች፡፡

7. መቃጠልና መንገብገብ ምን እንደሚመስል ይየው የቀድሞ ፍቅረኛዬ የለየለት ሴሰኛ ነበር፡፡ እቀይረዋለሁ ብዬ አስቤ የነበረ ቢሆንም ልክ አልነበርኩም፡፡ አብረን እያለን ሌሎች ሴቶችን እንደሚያወጣ ወሬ ብሰማም ስጠይቀው ሁሌ ሽምጥጥ አድርጎ ይክዳል፡፡ አንድ ምሽት አንዲት ልጅ ደወለችልኝና ከፍቅረኛዬ ጋር ሶስት ወር የሞላው ግንኙነት እንዳላቸው፤ ከሌላ ሴት ጋርም ግንኙነት እንዳለው ማወቋን ስትነግረኝ በንዴት ጦፍኩ፡፡ እጅግ በመናደዴም ሽቅርቅር ብዬ ለብሼ ጓደኞቼ ዘንድ ሄድኩ፡፡ ምሽቱንም ከአንድ መልከመልካም ወጣት ጋር አሳለፍኩ፡፡ ለፍቅረኛዬ ያንምሽት ያደረኩትን ነገር እንዲሁም ስለሌሎቹም ሴቶች ማወቄን ስገልጽለት ፊቱ ላይ ያየሁት ነገር ትልቅ እርካታ ሰጠኝ፡፡ ወራዳና የማይረባ መሆኑን ነግሬም አባረርኩት፡፡›› አሻንቴ በኮሌጅ ፓርክ የምትኖር የ25 ዓመት ወጣት ነች፡፡ ከላይ በእውነተኛ ታሪክ ተደግፈው የቀረቡትና ሴቶችን ለውስልትና የሚገፋፉ ድርጊቶች አብዛኞቹ በወንዶቹ ስህተት እና የእውቀት ማነስ የተነሳ የተከሰቱ ናቸው፡፡ ሴቶችን በማንነታቸው ማክበርና ማፍቅር እንዲሁም ማንነታቸውን መቀበል ለዘላቂ ፍቅር ዋነኛው መሰረት ነው፡፡

Source- Zehabesha.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.