ሜዲካል ጋዜጣ
ሳይንስ ፌቸር    

ggtራሰ በራ ነዎት? ወይስ ራሰ በራ ሰው በቤትዎ አለ? እርስዎስ ፀጉርዎ ገባ ገባ፤ሸሸት ሸሸት ማለት ጀምሮብዎ ይሆን? ራሰ በራ የሆነ ሰው ሲመለከቱ ምን ይሰማዎት ይሆን? አንዳንዶቻችን መምለጥ የስነልቦና ተፅዕኖ አሳድሮብን ይሆናል፡፡ በተለይ ምዕራባዊያን መላጣ ወንዶች የሴቶችን ቀልብ የመግዛት ግርማቸው እንደሚገፈፍ ያምናሉ፡፡ በእርግጥ ይህ በግልፅ ምክንያቱ ባይታወቅም በኛም ሀገር ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳሉ ከሴቶቻችን ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ ይም ሆነ ይህ መምለጥን አስቀድመን ማስቀረት እንችላለን?

በቅርቡ ለሕትመት የበቃን አንድ ጥናት ባነበብኩ ወቅት ለፅሑፌ መነሻ እንዲሆን ሻትኩ፡፡ ጥናቱ እስከዛሬ ስለራሰ በራነት ያልተነገሩ እውነታዎችን ለማስነበብ በቅቷል፡፡ በመሰረቱ ራሰ በራነት በጥንት ዘመን መጥፋት ሲገባው በትንሽ የዘረመል ስሕተት ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የበቃ ለአብዛኞቹ የራስ ምታት፤ ለዘመኑ ተመራማሪዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆን ችሏል፡፡ አለመታደል ሆኖ ነው እንጂ የራሰ በራነት የዘረመል ቀመር ድሮ የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ውስጥ ሲያልፍ ሊጠፋ ሲገባው በትንሽ አጋጣሚ ከዘር ዘር እየተባዛ አሁን ላይ ላለው በሚልዮን ለሚቆጠረው ወፈሰማይ ሕዝብ መለያ ምልክት ሆኖ ሊቀር ችሏል፡፡

ሰዎች ለምን ፀጉራቸው ይሳሳል በመጨረሻም እንዴት ሊመለጥ ይችላል ብለን ብንጠይቅ አያሌ ምክንያቶችን እንሰማለን፡፡ ነገር ግን የሰው ፀጉር በምንም ዓይነት መልኩ ቢወድም ተመልሶ መብቀል እስከቻለ ድረስ አብዛኞቹ ምክንያቶች ተቀባይነትን ያጣሉ፡፡

አዲሱ ጥናት ምን ይላል?

አብዛኞቹን ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥናቶችን ይደግፋል፡፡ በዚህ መሠረትም አብዛኛው መላጣ ግለሰብ መምለጥ የሚጀምረው ዕድሜ ከ30 ሲሆን ከዛ በፊትም ሊሆን ይችላል ነገር ግን የአብዛኛው መላጣነት አይቀሬ መሆኑ የሚታወቀው ከፊት ፀጉሩ ገባ ገባ ማለት ሲጀምር ነው፡፡ በመቀጠልም ከወደ ኋላ መሳሳት ይጀምራል፡፡ ይህ ዓይነት አመላለጥ በሕክምና እንኳን ላይቆም ይችላል፡፡

በጥናቱ መሠረት ሰዎች ወደ መላጣነት የሚያመሩበት ዋነኛ ምክንያት የወንድ የዘር ፍሬ(ቴስቴስትሮን) ክምችት  በሰውነት ውስጥ መብዛት ነው፡፡ ይህ የዘር ፍሬ ክምችቱ ሲጨምር በሰውነታችን አማካኝነት ወደ ዲሀይድሮቴስቴስትሮን ሆርሞን ይቀየራል  ሆርሞኑም ወደ ራሳችን በማምራት የራስ ቅላችንን የፀጉር ማምረቻ ቀዳዳዎችን በመድፈን አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡብን ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜም ፀጉር መብቀል ይቀራል፡፡ ራሳችንም መምለጡን እንረዳለን፡፡

ሁለተኛውና ብዙዎቹ ጥናቶች የሚደግፉት በዘር የሚተላለፍ መላጣነት ሲሆን፡፡ እስካሁን የመላጣነትን የዘረመል ኮድ ተንትኖ ማብራሪ የሰጠ ተመራማሪ ባለመኖሩ አንዳንድ መላጣዎች በሕክምና መፍትሔ ሲያገኙ ብዙዎቹ ሙከራቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የወንድ የዘር ፍሬ መጠን በሰውነት ውስጥ መጠኑ አለቅጥ መጨመሩ ለመላጣነት ቢዳርግም መኮላሸት ደግሞ ራሰ በራነትን እንደሚከላከል ጥናቱ ደምድሟል፡፡ በእርግጥ የፀጉር ቀዳዳዎች በራሳቸው የሕይወት ዑደት ውስጥ የሚሄዱ ቢሆኑም የዲሀይድሮቴስቴስትሮን ሆርሞን ካገኛቸው ያለምንም ምክንያት ልንመልጥ መቻላችን በመኮላሸት መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል ጥናቱ ቢጠቁምም አብዛኛው መላጣ ግለሰብ የማይቀበለው መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ የተሻለ ሀሳብም በማቅረብ ደረጃ ወሲብን በለጋ ዕድሜ መጀመር ጥሩ እንደሆነ የሚመክሩ ተመራማሪዎችም አልጠፉም፡፡ ነገር ግን ወሲብ ያን ያህል አስተማማኝና ቋሚ ላይሆነ ስለሚችል ይህኛውም መፍትሔ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ እንግዲህ ልብ ይበሉ እነዚህ መፍትሔዎች ሁሉ ገና ላልመለጡና የመምለጥ ስጋት ላለባቸው ነው፡፡

በቫለሪ ሆስሌ የተመራ የተመራማሪዎች ቡድንም በዬል ዩኒቨርሲቲ የራስ ቅል ፀጉር አብቃይ ሕዋሳትን ለመፍጠርና ለማባዛት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡ የራስ ቅል ሕዋሳትን በማውደም ለቀዳዳዎቹ መደፈን ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ብዙ ቢሆኑም፡፡ሕዋሳቶቹን በማነቃቃት የፀጉር መሠረት የሆነ የፕሮጄኒተር ሕዋስ እንዲፈጠር  ማድረግ ችለዋል፡፡ይህ ግኝታቸውም ለሁሉም ራሰ በራዎች የሚሆን መፍትሔ እንዲፈልጉ አነሳስቷቸዋል፡፡

የራሰ በራነት መድሐኒቶች፤ከጥንት እስካሁን

ከ5000 ዓመተ ዓለም ጀምሮ አርቴፊሻል ፀጉር(ዊግ) የሰው ልጅ ይጠቀም እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አሴራዊያን፣ሱሚሪያውያን፣ፋርሳዊያን እና ግሪካዊያን በስፋት እሚጠቀሙበት ሕዝቦች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከዊግ ባሻገርም ራሰ በራነትን ለመከላከል የሚውሉም የባሕል መድሀኒቶችም ነበሩ፡፡ለምሳሌ ያህለ ግብፃውያን 3500 ዓመት የሚሆነው በፓፒረስ ያሰፈሩት የአይረን ኦክሳይድ፣የእርሳስ ማዕድን፣ሽንኩርት፣ማር፣ከእባብ፣አዞ እና አንበሳ ሥጋ የሚሰራ ነገር ግን ለፀሀይ አምላክ ተፀልዮ የሚሰጥ መድሐኒት ብለው ያስቀመጡት ሙከራቸው አንዱ ነው፡፡ ባጠቃላይ የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ መፍትሔ ፍለጋውን አቋርጦ አያውቅም፡፡

በአሁን ዘመን ፀጉርን በቀዶ ጥገና ማስተከል ዝነኛና ውጤታማ እየሆነ የመጣ ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህ የሚሆነው ለጥቂቶቹ ዕድለኞችና ሚልየነሮች ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም ፀጉር ካለው የራስዎ ቅል ወይም ፀጉራም ከሆነ ወዳጅዎ  የፀጉር ቀዳዳ ሕዋሳት ይወሰድና በመላጣው ራስዎ ቦታ ላይ ልክ እንደ ችግኝ ይተከልልዎታል፡፡ በሒደትም ሕዋሳቱ በአካባቢው መስፋፋት ይጀምራሉ፡፡ ራሰ በራነትን መከላከል ይልዎታል ይህ ነው፡፡

አርቴፊሻል ፀጉርንም ማስተከል በአሁን ዘመን ቢቻልም ይህ ለቢልየነሮች ብቻ የሚሆን አማራጭ ነው፡፡ አርቴፊሻል ፀጉር ማስተከል ከመላጣ መላጣ ስለማይለይም ጥሩ መፍትሔ ሆኗል፡፡

አሁን የስነውበት ኢንዱስትሪውን እያጥለቀለቁ ከመጡ ራሰ በራነትን ከሚከላከሉ እንክብሎች መካከል ፕሮፔሺያ የሚባለው ይገኝበታል፡፡ ይህ እንክብል በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን የወንድ የዘር ፍሬ(ቴስሬስትሮን)መጠን በመቀነስ የፀጉራችን ቀዳዳዎች በሆርሞናችን እንዳይደፈን ይደርጋል፡፡ ይህ እንክብል ለቅድመ መከላከል ወይም መምለጥ ለጀመራቸው ጥሩ መፍትሔ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል፡፡

ሌላኛው ዝነኛ መድሐኒት ሚኖዚዲል ይባላል፡፡የንግድ ስያሜው ሮጄን ይባላል፡፡ የደም ፍሰትን በማፋጠን ፕሮስታግላንዲን የተሰኙ የፀጉር ዕድገት አፋጣኝ ኬሚካሎች ስራቸውን እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ይህ ብዙዎቹ ሞክረውት መምለጥ የጀመረው የራስ ቅላቸው ተግባሩን እንዲገታ አድረጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ መድሐኒት ትንንሽ በአማርኛ የአንበሳ ፀጉር የምንላቸውን ብናኝ መሳይ ፀጉሮችን ማብቀል ችሏል፡፡

በቅርብ ጊዜ በመላጣነት ዙሪያ ሳይንስ ትልቅ የሚለውን መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ ብዙ ተመራማሪዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ በተለይ አሁን ስለ ራሰ በራነት ያለው ግንዛቤ ሰፊ በመሆኑ ለሁሉም ራሰ በርሃ የሚሆን መፍትሔ በባዮሎጂ ባለሞያዎች እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ መድሐኒቱም የፀጉር ቀዳዳዎች እንዳይደፈኑና ፋፍተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ከማድረግም በላይ በራሰ በራ ሰዎች የተደፈኑት የፀጉር ቀዳዳዎች እንዳዲስ ተከፍተው ፀጉር ማብቀል እንዲችሉ የሚያደርግ እንደሆነ ተነግርለታል፡፡

እርስዎስ ምን አስበው ይሆን? የተጠቀሱትን መድሐኒቶች መሞከር ይፈልጋሉ ወይስ በራሰ በራነቴ እኮራለሁ ይላሉ? መልሱን ለእርስዎ እየተውኩ እኔ ግን ቸር እንሰንብት እላለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.