የሆድ ህመም መንስኤዎች ከብዛታቸው የተነሳ ይኼ ነው ለማለት ይከብዳሉ፡፡ የሆድ ህመም በብዛት ቀላል ችግሮችን ቢያመላክትም አንዳንዴ ግን ጠንከር ያሉ በሽዎች መገለጫ ነው፡፡

 

Fotolia_39594141_XS-aabfe4d483ትክክለኛውን ምክንያት ከህመሙ ብቻ ተነስቶ ማወቅ ቢከብድም ሌሎች ተጨማሪ የበሽታ ምልክቶች ካሉብህ እና ከሆድህ ህመም ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮችን በማየት ከህመሙ ጀርባ ያለውን ምክንያት ማወቅ ይቻላል፡፡

የሆድ ህመም አንድ ቦታን ለይቶ አሊያም እንዳለ ሆድህን አጠቃሎ ሊያም ይችላል፡፡ ከግማሽ በላይ የሆነውን ክፍል የሚያመው አይነት የሆድ ህመም በቀላል የህክምና ክትትል ሊድን የሚችል ሲሆን እንደ የምግብ አለመፈጨት( Indigestion)ባሉ በአብዛኛው በሚታዩ ችግሮች ይነሳል፡፡ አንድ ቦታን ብቻ ለይቶ ካመመህ ደግሞ ከበድ ያለ ችግርን ያመላክታል፡፡ ለምሳሌ እንደትርፍ አንጀት (appendicitis) እና የጨጓራ ቁስል የመሳሰሉ በሽታዎች ዋነኛ ምልክት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሆድ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ የአካል ክፍሎች- ጉበት እና ጣፊያ በሽታዎችም በዚህ መልኩ ይገለፃሉ፡፡

የሆድ ቁርጠት (እየመጣ የሚሄድ አይነት ህመም) ከፈስ እና ሰገራ መጠራቀም ጋር ተያይዞ ይመጣል፡፡ ብዙ ሴቶችም ይኼኛውን አይነት ህመም የወር አበባቸው በሚታያችው ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ከተቅማጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሆድ ቁርጠት ምንም እንኳን ሀይለኛ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ለክፉ አይሰጥም፡፡ በድንገት የሚነሳ ሃይለኛ ህመም ደግሞ አንጀት መቀደድን፣ኩላሊት ጠጠርን፣ የሃሞት ከረጢት በሽታዎችን፣ የሴት እንቁላል ማምረቻ (ovaries) ወይም የወንድ የዘር ፍሬ ማማረቻ (testis) መቋጠርን (torsion) አሊያም የትልልቅ የደም ቧንቧ ችግርን ተከትሎ ይመጣል፡፡ እንደዚህ አይነቱ ህመም አስቸኳይ ህክምና ስለሚያስፈልገው በፍጥነት ወደሆስፒታል መሄድ አለብህ፡፡

በትርፍ አንጀት እና በሃሞት ከረጢት በሽታዎች የሚመጣው ህመም እንቅስቃሴና ሳል ጋር ይብሳል፡፡አንዳንዴም ከከፍተኛ እንቅስቃሴ በኋላ የሚኖር የጡንቻዎች መኮማተር (ስትራፖ) የዚህ አይነቱን ህመም ሊያስከተል ይችላል፡፡

ሆድ ላይ የሚደርስ አደጋን (ግጭት፣ ምት) ተከትሎ ህመም፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ የበሽታ ምልክቶች ግን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይሻሻላሉ፡፡ ከደቂቃዎች ባለፈ የሚቀጥሉ ከሆነ ሆድ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ አካላት ጉዳትን ያመላክታል፡፡ ስለዚህም ወደሆስፒታል መሄድ አለብህ፡፡

ብዙ መድሃኒቶችም ለሆድ ህመም አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንደድርቀት የመሳሰሉ ያልተፈለጉ ችግሮችን በማምጣት የሆድ ህመም እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡

የሆድ ህመምን የሚያመጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሁሉም ሰው በህይወቱ ከአንድ ጊዜ በላይ የሆድ ህመም ያጋጥመዋል፡፡ የሆድ ህመም በጣም በብዛት የሚታይና ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ችግር ነው። ምንም እንኳን የሆድ ህመም በየጊዜው የሚከሰት ነገር ቢሆንም ዋናው ነገር ከጀርባው ያለውን ምክንያት አውቆ እራስን መጠበቅ ነው፡፡ ከዛም ባለፈ ህመሙ መቼ የተደበቀ በሽታን እንደሚያመላክት አውቆ በፍጥነት ወደሆስፒታል መሄድ ተገቢ ነገር ነው፡፡

የሆድ ህመምን ከሚያመጡ ነገሮች መካከል የሚከተሉት በብዛት የሚታዩት እና ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

 • የምግብ አለመፈጨት(Indigestion)
 • የሆድ ድርቀት(Constipation)
 • ኢንፌክሽን
 • የወር አበባ
 • የምግብ አለርጂ
 • የፈስ እና የሰገራ መጠራቀም
 • የጨጓራ ቁስል
 • ቡአ (Hernia) ?
 • Lactose intolerance?
 • የሃሞት ጠጠር(Gallstones)
 • የኩላሊት ጠጠር(Kidney stones)
 • የአሲድ ከጨጓራ ወደ ላይ መመለስGastroesophageal reflux disease (GERD)
 • የትርፍ አንጀት በሽታ (Appendicitis)
 • የምግብ መመረዝ( Food Poisoning)
 • የተለያዩ ሆድ ውስጥ የሚኖሩ ረቂቅ ህዋሳት – አሜባ፣ ጂያርዲያ

የሆድ ህመም መቼ ሊያሰጋኝ ይገባል?

በጣም ሀይለኛ የሆድ ህመም ካለብህ አሊያም ከሚከተሉት ምልክቶች ጋር የተያያዘ ከሆነ በፍጥነት ዶክተርህን ማማከር አለብህ ምክንያቱም ጠንከር ካለ በሽታ ጋር ሊያያዙ ይችላሉ እና፡፡

 • ትኩሳት
 • ማስታወክ
 • የሆድ ድርቀት
 • ደም ካስታወክህ
 • ደም የቀላቀለ ሰገራ
 • መተንፈስ ማቃት
 • ሽንት ከመሽናት ጋር የተያየዘ ህመም እና ቶሎ ቶሎ መሽናት
 • የቆዳ ቢጫ መሆን
 • በእርግዝና ጊዜ የመጣ የሆድ ህመም
 • ሆድህ ስትነካውም የሚያምህ ከሆነ
 • ቀደም ብሎ አደጋ ከደረሰብህ
 • ለብዙ ቀናት የቆየ የሆድ ህመም

የሆድ ህመም ህክምና ምንድን ነው?

የሆድ ህመም ህክምና እንደመንስኤው ይለያያል፡፡ ሚዋጡ መድሃኒቶች ፣ አንቲባዮቲክስ ፣ የአኗኗር ዘዴን ማሻሻል አሊየም ኦፕሬሽን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የምግብ አለመፈጨት (Indigestion)

የምግብ አለመፈጨት ብዙ ጊዜ ከጨጓራ ቁስለት፣ የሀሞት ከረጢት በሽታዎች ወይም የአሲድ መብዛት ጋር ይያያዛል፡፡ ከምግብ በኋላ ወይም ምግብ በምትበላ ጊዜ በሚኖር የሆድ መነፋት እና ምቾት ማጣት የሚገለፅ ሲሆን አንዳንዴም የማቃጠል እና የህመም ስሜት አብሮት ይኖራል፡፡

የምግብ አለመፈጨት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የምግብ አለመፈጨት ምክልቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች በጭንቀት እና ስራ በሚበዛበት ግዜ የመጨመር ባህሪ አላቸው፡፡

 • የሆድ መነፋት 
 • ማግሳት እና የፈስ መብዛት 
 • ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ
 • የማቃጠል ስሜት 
 • የሆድ ህመም
 • የሆድ መጮህ
 • የማቃጠል ስሜቱ ጨጓራ ውስጥ የሚገኘው አሲድ ወደላይ ሲመለስ እና ለአሲድ ምቹ ያልሆነ ሽፋን ያለውን የጉሮሮ ክፍልን ሲያቃጥል ይከሰታል፡፡

የምግብ አለመፈጨት ማን ላይ ይከሰታል?

ይሄ ችግር በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሴቶችንም ወንዶችንም ያጠቃል፡፡ አልኮል በብዛት መጠጣት፣ ጨጓራን የሚጎዱ እንደ አስፕሪን ያሉ መድሃኒቶችን በብዛት መጠቀም እንዲሁም የጨጓራ ቁስለት እና ጭንቀት ወይም ድብርት( depression) የመሳሰሉ በሽታዎች ያለበት ሰው ለዚህ ችግር ተጋላጭ ነው፡፡.

የምግብ አለመፈጨት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

የጨጓራ ቁስል፣ የአሲድ ከጨጓራ ወደ ጉሮሮ መምጣት፣ የጨጓራ ካንሰር፣ በስኳር ህመም የሚመጣ የጨጓራ በሽታ፣ የሆድ ኢንፌክሽኖች፣ የጣፊያ በሽታ የመሳሰሉ በሽታዎች ሊያመጡት ይችላል፡፡ ከመድሃኒቶች ደግሞ እንደ አስፕሪን እና አስፕሪንን የመሳሰሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒን፣ ለእንቅርት በሽታ የሚወሰዱ መድሃኒቶች፣ አንዳንድ አንቲባዮቲክስ ሊያመጡት ይችላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአኗኗር ዘይቤህም ይወስነዋል፡፡ በፍጥነት መብላት፣ በአንድ ጊዜ ብዙ መብላት፣ብዙ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ጭንቀት ሊያመጡት ይችላሉ፡፡

በእርግዝና ወቅት መሃል አካባቢ አሊያም ወደመጨረሻ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይኼም ከሆርሞን ለውጥ እና እያደገ ያለው ማህፀን በምግብ መፍጫ አካላት ላይ ከሚያስከትለው ጫና ጋር ይያያዛል፡፡ አንዳንዴ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ጋር የማይያያዝ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የምግብ አለመፈጨት ያጋጥማል፡፡

የምግብ አለመፈጨት ችግር ሲያጋጥመኝ ምን ላድርግ?

የምግብ አለመፈጨት ምልክቶች እየታዩብህ ከሆነ ወደሆስፒታል ሄደህ መታየት አለብህ፡፡ ምክንያቱም የምግብ አለመፈጨት በብዙ አይነት ምክንያቶች የሚመጣ ከመሆኑ አንፃር ተገቢውን ምርመራ ማድረግን እንመክራለን፡፡ ምንም እንኳን ብዙም አሳሳቢ ምክንያቶች ሊከሰት ቢችልም በዚያው መጠን በጣም የከፉ በሽታዎች መገለጫም ስለሆነ ወደ ዶክተርሀ ሄደህ መታየት አማራጭ የሌለው ተግባርህ አድርገው፡፡ ከዚያ ባለፈ ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል አለማብዛት እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ(በአይነትም በመጠንም) መመገብ ችግርህን ሊቀርፍልህ ይችላል፡፡

አሜባ

አሜባ ምንድን ነው?

አሜባ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ በማጉያ መነፅር ብቻ በሚታይና በትናንሽ ረቂቅ ህዋሳት አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ አሜባ አንጀት ውስጥ የሚኖር ሲሆን ከአንጀት አልፎ እንደጉበት ያሉ አካላትን ያጠቃል፡፡ ዘጠና ከመቶ የሚሆኑ አሜባ ሆዳቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የበሽታውን ምልክት የማያሳዩ ሲሆን በተቀሩት አስር በመቶ ብቻ ተቅማጥ እና ሆድ ቁርጠት የመሳሰሉ ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡

አሜባ እንዴት ሊይዘኝ ይችላል?

በአሜባ የተበከለ ውሃ እና ምግብ ዋና መተላለፊያ መንገዶቹ ናቸው፡፡ ከሰውነት ከወጣ በኋላ ለሳምንታት ምንም ሳይሆን የመቆየት ችሎታ ያለው ሲሆን ያልበሰሉ ምግቦች በተለይም አትክልት መመገብ ለበሽታው ያጋልጣል፡፡

የአሜባ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ምንም እኳን አሜባ ሆድህ ውስጥ ቢገኝም ምንም ምልክት ላታሳይ አሊያም አልፎ አልፎ ብቻ ሊያስቀምጥህ ይችላል፡፡ የሆድ ቁርጠት እና ደም የቀላቀለ ተቅማጥ ጠና ባለህመም ጊዜ ይታያሉ፡፡ ከአንጀት ውጭ ሌላ አካልህን ካጠቃ ደግሞ ሆድ ቁርጠት፣ ትኩሳት እና በአጠቃላይ ጤናህ ይጎዳል፡፡ አንዴ አሜባ ከያዘህ ለአመታት አብሮህ ሊኖር ይችላል፡፡

የጉበት አሜባ ምንድን ነው?

አንጀት ውስጥ የነበረው አሜባ በደም አማካኝነት ተሰራጭቶ ጉበትን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ጉበት ውስጥ ከገባ በኋላ መግል ይፈጥራል፡፡ በቀኙ የላይኛው የሆድ ክፍል የሚሰማ ህመም እና ትኩሳት ዋናዎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በሽታው ከአንጀት ቢነሳም ተቅማጥ የሚታየው በጣም ጥቂት በሽተኞች ላይ ነው፡፡ ጉበት ውስጥ የተፈጠረው መግል ወደሳምባም ሊዛመት ይችላል፡፡ ከሳምባ እና ጉበት በተጨማሪ ወደልብም ይሄዳል፡፡ ለአሜባ የሚሰጡ መድሃኒቶች የሚያድኑት ሲሆን ተጨማሪ መዘዞችን ካመጣ ወይም ደግሞ በመድሃኒቶቹ ካልዳነ ኦፕሬሽን መሰራት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

አሜባን ምን በማድረግ መከላከል እችላለሁ?

ምግብህን በፅዱ ሁኔታ በማዘጋጀት ይህንን በሽታ ልትከላከል ትችላለህ፡፡ አሜባ ከሰውነት ውጭ ብዙ አይነት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የመኖር አቅም ቢኖረውም ሀይለኛ ሙቀትን ስለማይቋቋም የሚጠጣ ውሃን ማፍላት እና ምግቦችን በተለይ አትክልትን በደንብ አብስለህ መመገብ በበሽታው ከመያዝ ይጠብቅሃል፡፡ ንፁህ ውሃ መጠጣት በበሽታው የመያዝ እድልህን በትልቁ ይቀንሰዋል፡፡ ሽንት ቤት ከተጠቀምክ በኋላ እጅህን መታጠብንም ልማድ አድርገው፡፡

ጃርዲያ

ጂርዲያ ምንድን ነው?

ጂያርዲያ አንጀትን የሚያጠቃ በአይን የማይታይ ረቂቅ ህዋስ ነው፡፡

ጃርዲያ እንዴት ሊይዘኝ ይችላል?

ጃርዲያ ከሰገራ ጋር አብሮ የሚወጣ ሲሆን በዚህ አይነት ሰገራ የተበከለ ውሃ እና ምግብ መተላለፊያ መንገዶቹ ናቸው፡፡

የጃርዲያ በሽታ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

ጃርዲያ ተቅማጥ፣ ሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ እና የሆድ መነፋትን ያስከትላል፡፡ እነዚህን ምልክቶች በተደጋጋሚ ልታይ አሊያም እየመጡ እና እየሄዱ ሊያገጥሙህ ይችላሉ፡፡ከዚህ ውጪ ምንም ችግር የማያሰከትል ሲሆን በመድሃኒቶች ይድናል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ምልክቶች ስታይ ዶክተርህን አማክረው፡፡

ከጃርዲያ እራሴን እንዴት ልከላከል?

እንደ አሜባ ሁሉ የምግብ ፅዳትን በመጠበቅ፣ ምግብህን በደንብ በማብሰል እና ሽንት ቤት ከተጠቀምክ በኋላ እጅህን በአግባቡ በመታጠብ እራስህን ከዚህ በሽታ ልትከላከል ትችላለህ፡፡

Source- addishealth

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.