ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
አዲስ አድማስ ሚያዚያ 25 ቀን 2006 ዓ.ም

ድንገት ከጎረቤት አለያም መንገድ ላይ ባልና ሚስት ዱላ ቀረሽ ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተው አሰተውለን ይሆን? … ጭቅጭቁ ከፋ ብሎ ዱላ የጨመረ ከሆነስ ….. አ  አ
እዚህ ከተማ ውስጥ ብዙ ሰው ነፍሠ ጡር ሴቶችን ሲመለከተ ታክሲ ውስጥ ከሆነ የተሻለውን ወንበር፣ ሠልፍም ከሆነ ቅድሚያ የመስጠት ሁኔታ ይስተዋላል። በአንፃራዊ ነፍሠ ጡር ባልሆኑ ሴቶች ይልቅ ነፍሠ ጡር የሆኑ ሴቶች የተሻለ እንክብካቤ የማግኘት እድል አላቸው፡፡ አንዳንድ ወንዶችማ ነፍሠ ጡሯን እንዳይነኩ ሲሣቀቁ ሁሉ ይስተዋላሉ፡፡ 


pregnancy sexየተለያዩ ጥናቶች ዋቢ አድርገን በእርግዝና ጊዜ ስለሚደርስ ጾታዊ፣ የሥነ ልቦናና አካላዊ ጥቃቶችን በተመለከተ ትንሽ እናውጋ፡፡ እንዲህ ያለው ርዕሠ ጉዳይ ተነስቶ ጥናት ሲደረግ በአሜሪካን ሀገር ከጠቅላላው ሴቶች ቁጥር 52 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በህይወት ዘመናቸው አካላዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ አለያም ጾታዊ ጥቃት በቅርብ ባሉ ባሎቻቸው አለያም አብረዋቸው በሚኖር ሠው በእርግዝና ጊዜ ይደርስባቸዋል፡፡ በአመት እስከ 4 ሚሊዮን የሚሠርሱ ነፍሠ ጡር ሴቶች ጥቃት ያገኛቸዋል። በአቅራቢያ ሩዋንዳ እስከ 35 በመቶ የሚደርሱ ሴቶች በተመሣሣይ ሁኔታ በእርግዝናቸው ወቅት በባሎቻቸው /በአብዛኛው/ የአንዱ አይነት ጥቃት ሠለባ ናቸው፡፡ የሚገርመው 35 በመቶ በሚሆኑ ሴቶች ላይ በተሠራ ሀገር አቀፍ ጥናት በህንድ ሁሉም ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት ምንም አይነት ጥቃት እንዳልደረሠባቸው ገልፀዋል፡፡ …ንዴት ያሉ ወንዶች ናቸው? አላላችሁስ? 


“ሲጀመር” እርግዝና እንኳንስ ትንኮሳ፣ ጥቃት፣ ማንጓጠጥ፣ ጫና ማጣጣልና ችላ መባል ታክሎበት በራሱ እርግዝናው በሚያሳድረው ጫና /አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ለውጥ/ ምክንያት ነፍሠ ጡር ሴቶች አስቸጋሪ ጊዜ እንዲያሳልፉ ይገደዳሉ፡፡ እርግዝናውን ተከትለው የሚከሠቱ አንዳንድ ለውጦችን ለምሣሌ እንመልከት ብንል የጡት እድገት፣ የሠውነት መጨመር፣ የቆዳ መወጣጠርና ለውጥ፣ የድካም ሥሜት፣የትንፋሽ ማጠር፣ የመኝታና የወንበር አለመመቸት፣ ደም ግፊትና ስኳር መጨመር /በተለይ ችግሩ ካለ/ የምግብ አለመስማማት፣ የእግርና ፊት ማበጥ… ብዙ መቀጠል ይቻላል፡፡ እነዚህን አካላዊ ለውጦች ተከትሎ ደግሞ ሥነ ልቦናዊ ለውጥም ይከተላል፡፡ 


ስሜቷ በቀላሉ ይረበሻል፣ ድብርት ውስጥ ትገባለች፣ የውኃ መቅጠን ብቻ ለሥሜቷ መረበሽ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ደግሞ ልንሟገተው ወይም ልናጠይቀው ብዙ አስፈላጊ አይመስልም ምክንያቱም ራሷ ነፍሰ ጡሯም ልትቆጣጠረው የማትችለው አይነት ስሜት ነው፡፡ 


ልጁን ወይም ፅንሱን እንዳላጣ የሚል ሥጋት ወይም መረበሽ ሥሜት ይመጣል፣ የመርሣትና ሁኔታዎችን በስርዓቱ አለመቆጣጠር አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እነዚህ ስሜቶች ሁሉ እንደ እርዝግናው ጊዜ በተለያዩ ወቅቶች የሚታዩና ነፍሠ ጡሯ ሁኔታውን እየተለማመደችው ሠውነትም ራሱን እያስተካከለ ሲመጣ እየከሠሙ የሚሄዱ ክስተቶች ናቸው፡፡ 


ይህ በእንዲህ እንዳለ /እንበልና እንደ ሬዲዮ ጋዜጠኛ/ ወደ ቀደመው ጉዳይ ሥንመለስ በእርግዝና ጊዜ በባሎች አለያም አብረው በሚኖሩ የቅርብ ሠዎች በነፍሠ ጡር ሴቶች ላይ የሚደርሱ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ጾታዊ ጥቃቶች የሚያስከትሉት ተፅህኖ ከቀደመው “ተፈጥሯዊ” ክስተት ጋር ተጨማሪ ይሆናል፡፡ 


አካላዊ ጥቃት ስንል ዱላ ነው፡፡ ከጥፊ እስከ ሆድ መርገጥ ይደርሳል /ቦክስና  ካልቾ በዚሁ መሃል የሚገኙ ናቸው/፡፡ ጾታዊ ጥቃት ሲባል ደግሞ ወሲባዊ ጥቃትን ይመለከታል፡፡ ታዲያ የባሎች እንዴት ወሲባዊ ጥቃት ይሆናል? ያለ ነፍሠ ጡሯ ፈቃድ ሲፈፀም ጥቃት ይሆናል፡፡ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ደግሞ መሣደብ፣ ማንጓጠጥ፣ ማግለል፣ እንክብካቤ መንፈግ፣ ዛቻ /በተለይ የመግደል/፣ መደበኛ እንቅስቃሴአቸውን ወይም ዘወትር ከሚያከናውኗቸው ድርጊቶች መገደብ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል /ፍላጎትን አለማሟላት/፣ ማጥላላት፣ ጫናና ቁጥጥር ማብዛት፣ እነዚህና የመሣሠሉት ናቸው፡፡ 
በተለይ ይህ ጥቃት መዘዙ በጣም የከፋ ነው ብለን አንዱን ለይተን ከጥቃት ጥቃት ልናገዝፍ ባንችልም እንኳ እያንዳንዱ ጥቃት በተፈፀመበት በዚያ የእርግዝና ወቅት ለነፍሠ ጡሯ እናት ሸክሙ ቀላል ባለመሆኑ በተገለፀበት መንፈስ መዘዛቸውን ብንመለከት የተሻለ ይመስላል፡፡ 


አካላዊ ጥቃቱ አንዳንዴ ነፍሠ ጡር እናቶችን እስከመግደል የሚደርስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመለስ በነፍሠ ጡር ሴቶች ላይ የሚደርስ አካላዊ ጥቃት /ድብደባ/ ያልተጠበቀን ደም መፍሠሥ፣ የፅንሱ መቋረጥ ወይም ፅንሱ እንዲወጣ የመገደድ፣ ያለ ጊዜው ምጥ የመከሠት ሁኔታና  ከሚጠበቅባቸው (እርግዝና መደበኛ ጊዜ) ጊዜ በፊት መወለድ የፅንሡ (የልጁ) ክብደት መጠን ከተገቢው በታች በጣም መወረድ የእንኩላሊት ቁስለት (ኢንፌክሽን) እና ሌሎችም በአካላዊ ጥቃት ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ 


ሌላው የፆታ ጥቃት ብለን የገለፅነው የወሲብ ጥቃት ነው፡፡ የዚህ መሠረታዊ ችግር በመጀመሪያ ነፍሰ ጡር ሴቶች በባሎቻቸው ከፈቃዳቸው ውጭ ሲፈጸም ተገቢ አይደለም ብለው አይወስዱም፡፡ ይልቁን የሚጠበቅና መደረግ ያለበት ነው ብለው ይገምታሉ። ከዚህ አንፃር ተገቢ በሆነ ጊዜም ይሁን ተገቢ ባልሆነ፣ መደበኛም ይሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ፣ ነፍሰ ጡሯ ፈልጋም ይሁን ሳትፈልግ ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል፡፡ ቀደም ሲል በእርግዝናው ወቅት የሚለውጡትን እንግዳ ስሜቶች እያስተናገደች ባለበችበት ሙድ ወዲህና ወዲያ በሚዋዥቅበት በዚህ የእርግዝና ወቅት እንደገና ተገዶ ወሲብ መፈጸም ሌላ ጫና ይሆናል፡፡ 


    ከዚህ ውጭ ነፍሠ ጡር ሴቶች ሁሉ ባለ ትዳሮች ናቸው ብለን መቼም አናስብም፡፡ ታዲያ በአንድና በሌላ አጋጣሚ ከእርግዝና በኋላ ፍቺ ቢያጋጥም በቀድሞ ባል እንደዚሁ የወሲብ ጥቃት ይደርሳል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ያላገቡ ወጣቶች በፍቅር ጓዳኞቻቸው ወይም ከሌላ ፈልገው ወይም ሳይፈልጉ እርግዝና ይከሠታል (በእርግጥ ይህን ክስተት አንዳንዴ በማለት ገለፅኩት እንጂ አንዳንድ ጊዜ  ላይሆን ይችላል) እነዚህ  ሴቶች ደግሞ በእርዝናውም ጊዜ ሌላ የወሲብ ጥቃት ሲከተልባቸው ይችላል፡፡ ከዚህ በተረፈ የጎዳና፣ በስደተኛ ካምፖች የሚገኙ ሴቶችም ቀደም ሲል እንደገለፅኩት በፍላጎትም ያለ ፍላጎትም አንዴ እርግዝና ከተከሰተ በኋላ በዚያው የእርግዝና ጊዜ በተመሳሳይ ሰው ወይም በሌላ ወሲብ ጥቃት ሊያገኛቸው ይሻላል፡፡ ከእነዚህ ከላይ ከገለፅኳቸው ከአካልና ከፆታ (ወሲባዊ) ጥቃት ጋር ተያይዞ የሚከሠት የሥነ ልቦና መታወክ ችግር ደግሞ ሶስተኛው ችግር ነው፡፡


በእርግዝና ወቅት ሴቶች የሚያደርስባቸውን የሥ ልቦና ጥቃት አብዛኞች ልብ ላይሉት ወይም ጥቃት ነው ብለው ላይፈረጁት ይችላሉ፡፡ (በእርግዝና ወቅት ሴቶች ጭንቀትና ድብርት ውስጥ የሚገቡበትና አስጨናቂዎቹ ክስተቶች ወደ አእምሮ እየተመላለሡ ረፍት የሚነሱበት ጊዜ ነው፡፡ ለዚህም ነው የቤተሰብ፣ የጓደኛ፣ የህክምናና የሥነ ልቦና ባለሞያዎች እገዛና እንክብካቤ የሚሹትና የሚያስፈልጋቸው) ሆኖም በዚህ እርግዝና ወቅት የሚደርሱ የስነ ልቦና ጥቃቶች ነፍሠ ጡር ሴቶችን ለስሜት መረበሻና ድብርት፣ ጭንቀት እንዲሁም ጭንቀቱ ወደሚወልደው መታወክ (anxiety disorder) ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከፍ ያለ ጭንቀት ደግሞ ራሱን ወደ ማጥፋት ሙከራና አደጋ ይገፋል ይሉናል ጥናቶቹ፡፡ 


የሥነ ልቦና  ጥቃት ሥንል በነፍሠ ጡር ሴቶች ላይ የሚደርስ ጫና በቀጥታ ከመሰደብ፣ ከዛቻ፣ እንክብካቤ ከመንፈግና ከመሳሰሉት ብቻ የሚወለድ ሣይሆን ቀደም ሲል ከገለፅናቸው የአካልና የፆታ ጥቃቶችም የስነ ልቦና መታወክም ማስከተላቸው የማቀር ነው፡፡ 


በእርግዝና ወቅት ጥቃት ይቀንሳል ብለን ልናስብ እንችላለን- አዎ የአንዳንድ ጥናት ውጤቶች ይህን ውጤት በአንዳንድ ሀገራት ላይ ያመላክቱ እንጂ በሌሎች ደግሞ በእርግዝና ወቅት ጥቃት ማየሉን ይጠቁማሉ፡፡ 


ከጥቃቶቹ ጋር የተያያዘው አንድ አቢይ ችግር ግን ጥቃቱ የሚደርሠው በባሎችና በቅርብ አብረው በሚኖሩ ሠዎች አማካኝነት በመሆኑ ነፍሠ ጡር ሴቶች ድርጊቱን ደፋ አያደርጉም፣ ቢጠየቁም ይክዳሉ፡፡ 


እንግዲህ እንዲህ ያሉ ክስተቶች መፍትሄዎቻቸው ይህ ነው ብሎ መደምደም አይቻለም፡፡ የሥነ ልቦናና የህክምና ባለሞያዎች ድርጊቶች ከመከሰታቸውም በፊት ይሁን ከተከሠቱ በኋላ እርዳታና ህክምና ለመሰጠት የሚያስችሉ የየራሳቸው መንገድ አላቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ በጉዳዩ ላይ እውቀት መፍጠርና እያንዳንዱ ሠው ሊወስድ የሚችለውን ጥንቃቄ መወሰዱ ዋነኛው የመፍትሄ አካል ሲሆን ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ የህግ መሻሻልና የዚህንም ከለላ ማግኘት ወሳኝ መሆኑ ይታመንበታል፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.