280743_bdf8ae0594a8005b8f70f213a24afea0_largeየህጻናትን ጤንነት እና እድገት የሚፈታተኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለተወለዱ ሕጻናት ጥሩ የሆነ እድገት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች ፍቅር የተሞላው ወላጅነት… ሓላፊነት የተሞላው የቅርብ ክትትል ማድረግ… የተመጣጠነ ምግብ መመገብ… ምቹ የሆነ የአየር ጸባይ… ጥሩ የእረፍት ጊዜ እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናት በእድገታቸው ዘመን ጤናማ እንዲሆኑ ገና ከጅምሩ ጥሩ ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጨቅላዎቹ በአካባቢያቸው ሊፈጠሩ ለሚችሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ሁሉ እንዳይጋለጡ ተገቢው ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

ልጆቹ በአመጋገባቸው፣ በሕክምና ክትትል፣ በንጽህና አጠባበቅ… በመሳሰሉት ሁሉ ከእናት ወይም ቤተሰብ አሊያም በእንክብካቤ ከሚያሳድጉ ሁሉ ያላሰለሰ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ሕጻናቱ በትክክል እንዲያድጉ ኃላፊነቱ የወላጆች የቤተሰብ የጤና ባለሙያዎች እና ልጆችን ለማሳደግ ኃላፊነት የሚወስዱ አካላት ሁሉ ነው፡፡
Infant health &development/http://www.eHow.com
ሕጻናት አመጋገባቸው ፣ የጤና አጠባበቃቸው በምን ደረጃ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል? ለሚለው ምላሹን በጋንዲ ሆስፒታል የእናቶችና ሕጻናት ጤና አጠባበቅ አስተባባሪ ከሆኑት ከሲስተር ጸሐይ መሐሪ አግኝተናል፡፡ በሆስፒታሉ ልጅ ወልደው አልጋ ይዘው ያገኘናቸው ሁለት እናቶችም የየራሳቸውን እውቀት አካፍለውናል፡፡
“ፍሬሕይወት ንጉሱ እባላለሁ፡፡ እድሜዬ 22 ነው፡፡ አሁን የወለድኩት ሁለተኛ ልጄን ሲሆን የመጀመሪያው ልጄ 4 አመቱ ነው፡፡ ያንኛውን ልጅም የወለድኩት በዚሁ በጋንዲ ሆስፒታል ሲሆን ገና ከመውለዴ በፊት ጀምሮ ትምህርት ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ አሁንም በእርግዝና ክትትል ወቅት ጀምሮ ትምህርቱ ተሰጥቶናል። ልጅ ተወልዶ እስከ ስድስት ወር ድረስ ከእኔ ከእናቱ ጡት በስተቀር ምንም ምግብ መሰጠት የለበትም ስለተባልኩ እኔም ያደረግሁት ያንኑ ነበር፡፡ ጤንነቱን በሚመለከት ከሐኪም ጋር በቅርብ መመካከር እንደሚገባኝም ተምሬ ስለነበር ልጄን በተነገረኝ መሰረት በትክክል አሳድጌ አሁን በጣም ጤነኛ ነው፡፡ እና ከገጠር መጥታ ስታርሰኝ… እንኩዋንስ ለልጄ ለእኔም ምግብ ሲሰራልኝ በምን መንገድ እንደሆነ እነግራት ነበር፡፡ ምክንያቱም አኔም ብሆን ክብደን ጨምሬ ወይም ጤናዬ እንዲዛባ አልፈልግም ነበር፡፡ ስለዚህ የተቻለኝን ጥንቃቄ አድርጌያለሁ፡፡ ለልጄም ውሀ ሆነ ቅቤ ወይንም ከሞሜላ ምንም ነገር ሳልሰጥ ቆይቼ ስድስት ወር ካለፈው በሁዋላ ግን በተነገረኝ መሰረት ተጨማሪ ምግብ መግቤ አሳድጌዋለሁ፡፡ አሁን የወለድኩትንም ልጅ በዚሁ መንገድ ነው የማሳድገው”
“ቤቲ ተስፋ ነው ስሜ፡፡ እድሜዬ 22 አመት ነው። የወለደኩት ዛሬ ለሊት ነው፡፡ ልጄም ወንድ ነው፡፡ እኔ ለመውለድ ወደ ጋንዲ ሆስፒታል መጣሁ እንጂ በእርግዝናዬ ጊዜ ክትትል ሳደርግ የነበረው በጤና ጣቢያ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት ትምህርት አላገኘሁም፡፡ ስለዚህ ልጄን አሁን በሚነግሩኝ ምክር መሰረት ለማሳደግ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ልጅ ስወልድ ገና የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ሐኪሞቹ ከሚነግሩኝ በስተቀር የማንንም ምክር አልቀበልም”
ኢሶግ፡ የሕጻናት ጤነኛ ሆኖ የማደግ ዘዴውና ትምህርቱ ለእናትየው መሰጠት የሚጀምረው መቼ ነው?
ሲ/ር፡ ትምህርት መስጠት የሚጀመረው በቅድመ ወሊድ ማለትም በእርግዝና ክትትል ወቅት ነው፡፡ በቅድመ ወሊድ ጊዜ እናቶች ጡታቸውን የማዘጋጀት ስራን ይማራሉ፡፡ ምናልባትም ችግር ቢያጋጠማቸው የጤና ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚችሉ ይነገራቸዋል፡፡ የሚወለደው ልጅ በወሊድ ጊዜ ቲታነስ እንዳይይዘው እናትየው በእርግዝና ክትትል ወቅት ጸረ ቲታነስ ክትባት እንድትከተብ ይደረጋል፡፡ ሕጻኑ ቲታነስ ሊይዘው የሚችለው እትብቱ በሚቆረጥበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ስለሕጻኑ ጤንነትና እድገት የተማሩት እናቶች በተለይም ጡታቸውን እንዲያጠቡና እስከስድስት ወር ድረስም ሌላ ተጨማሪ ምግብ መስጠት እንደሌለባቸው ይነገራቸዋል፡፡
ኢሶግ፡ የእናት ጡት ደረጃው በምን ይለካል?
ሲ/ር፡ የእናት ጡት ወተት ከማንኛውም ወተት ይበልጣል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በአለማችን ዙሪያ የሚሰሩ ሰው ሰራሽ ወተቶች በጭራሽ የእናት ጡት ወተትን አይተኩም፡፡ የእናት ጡት ወተት ከማንኛውም ወተት ጋር ለውድድር የማይቀርብ ሲሆን ጥቅሙም በተለይም የመጀመሪያው እንገር የተባለው ወተት የህጻኑን አንጀት እንቅስቃሴ ማስተካከል የሚችል እና በሆዳቸው ውስጥ ያለው ጥቁር ነገር እንዲወጣ የሚያደርግ ነው፡፡ የእናት ጡት ወተት ልጁን ከተለያየ አለርጂክ… ቆዳ በሽታ …መተንፈሻ ቡዋንቡዋ የመሳሰሉት አካላት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ሊከላከል የሚችል ጤናማ ምግብ ነው፡፡
ኢሶግ፡ ሕጻናቱ በየስንት ሰአቱ ልዩነት ጡት ሊጠቡ ይገባል?
ሲ/ር፡ ሕጻኑ የእናቱን ጡት መጥባት ያለበት በመጀመሪያ በተወለደ ከ30/ደቂቃ ጀምሮ ሲሆን በመቀጠል ግን በየሁለት ሰአት ቢዘገይ ደግሞ በየሶስት ሰአት ልዩነት መሆን አለበት። ባጠቃላይም በሀያ አራት ሰአት ውስጥ ከ8-12 ጊዜ መጥባት እንዳለበት እናቶች ገና በእርግዝና ጊዜያቸው መረጃው ይሰጣቸዋል ፡፡
ኢሶግ፡ የጡት መጥቢያ ሰአት በልጁ እንቅልፍ ምክንያት ቢዛባስ?
ሲ/ር፡ አንዲት እናት ህጻን ልጅዋ በእንቅልፍ ቢያዝ እንኩዋን ተኝቷል ብላ የመጥቢያ ሰአቱን ልታዛባበት አይገባም። የተኛውን ልጅ የሽንት ጨርቁን ለመለወጥ በመሞከር ወይንም ልብሱን ገለጥ ገለጥ አድርጎ አየር እንዲያገኝ በማድረግ እንዲነቃ አድርጎ ጡት መስጠት ይቻላል፡፡ በዚህ መንገድ ካልተሳካም አይኑን ቢጨፍንም እንኩዋን አቅፎ በመያዝ ጡቱን ማጥባት ተገቢ ነው፡፡ የእናት ጡት ወተት እስከስድስት ወር ድረስ ከተጠባ በሁዋላ የህጻኑም እድገት ስለሚጨምር እና የወተቱ መጠንም ስለሚቀንስ ሌላ ተጨማሪ ምግብ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ህጻኑ አድጎ ወደ አንድ አመት ሲሆነው ደግሞ የአዋቂዎችን ምግብ መመገብ የሚጀምርበት ወቅት ስለሚሆን ቀስ በቀስ ማለማመድ ያስፈልጋል፡፡
ኢሶግ፡ የቢሮ ሰራተኛ የሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን በምን መንገድ መርዳት ይችላሉ?
ሲ/ር፡ ሕጻናት በየሁለት ሰአቱ እስከስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ መጠጣት አለባቸው የሚለው በአለም አቀፍ ስምምነት የተደረሰበት ቢሆንም በሀገራችን ግን የእናቶች የወሊድ ፈቃድ እስከ ሁለት ወር ድረስ ብቻ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ መተግበር አይቻልም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች በሐኪም እረፍት እንዲሁም የወር ፈቃዳቸውን በማጠራቀም በችግር ልጆቻቸውን ለመርዳት ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህንን እድል ስለማያገኙ ሕጻናቱ ተገቢውን የእናት ጡት ወተት እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ ስራ የሚሰሩ እናቶች ልጆቻቸውን መርዳት የሚችሉት ጡታቸውን እያለቡ በቤት በመተው በጡጦ እንዲጠቡ ወይንም በስኒ እንዲጠጡ በማድረግ ነው። የታለበው ወተት ከሰባት ሰአት በላይ የሚቀመጥ ከሆነ በፍሪጅ በማስቀመጥ ማጠጣት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ወተቱ የሚቀመጥበትና ለልጁ የሚሰጥበት እቃ ንጽህናው በትክክል የተረጋገጠ መሆን ይገባዋል፡፡
ኢሶግ፡ ሰራተኛ ለሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን በስራ አካባቢያቸው የሚያቆዩበት ሁኔታ ቢመቻችስ?
ሲ/ር፡ ሕጻናት ከሁለት ወር እድሜያቸው ወይንም እናቶቻቸው ሲለዩአቸው ጀምሮ የሚቆዩበት ቦታ በጣም በጠባቡ አሁንም ቢኖርም እንኩዋን ነገር ግን በስፋት ቢለመድ ጥሩ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግን ሰራተኛ የሆኑት ሴቶች አቅም በራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ የልጅ ማቆያው የሚጠይቀውን ገንዘብ እንኩዋንስ ለማቀያው መክፈል ይቅርና እራስዋም በጠቅላላው ገቢዋ በወር ሰርታ የማታገኝ እናት መኖሩዋን ያህል ለልጁ የሚሰጠውን እንክብካቤም በጥንቃቄ መመልከት የሚገባው ነው፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ አስቸጋሪ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ልጅን ማሳደግ ያለባት እናት ናት፡፡
ኢሶግ፡ ለስራ ወደመስክ የሚሄዱ እናቶች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?
ሲ/ር፡ ጡት ካልተጠባ ወተት አያመነጭም፡፡ ስለዚህ እናትየው ለአንድ ሳምንት ወይንም ከዚያ በላይ ለሆነ ቀን ሳታጠባ የቆየች ከሆነች ጡትዋን ለልጁዋ ብትሰጥ ወተት አይኖራትም ። ስለዚህ በተቻለ መጠን እናት…ልጁዋ ስድስት ወር ያልሞላውና ተጨማሪ ምግብ መውሰድ ያልጀመረ ከሆነ ወደመስክ ለስራ ባትወጣ ይመረጣል፡፡
ኢሶግ፡ ሁሉም ሕጻናት ጡት መጥባት እንዲችሉ መፍትሔው ምን ይመስልዎታል?
ሲ/ር፡ ምርጥ ምርጡን ለህጻናት ሲባል ለህጻናት ከምርጥም በላይ ምርጥ የእናት ጡት ወተት ነው፡፡ እናቶች ልጆቻቸውን በተገቢው የጡት ወተት መግበው እንዲያሳድጉ የሚያስችል ፖሊሲ ቢቀረጽ ጤነኛ ሕጻናትን ለማፍራት ያስችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ እናቶች ቢያንስ ቢያንስ እስከ ስድስት ወር ድረስ ከልጆቻቸው እንዳይለዩ የሚያስችል መመሪያ ቢነደፍ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡
Source- addisadmassnews

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.