travel-blog-food-fridays-bakeries-sweet-lady-jane-copyኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩት የጣፋጭ ምግብ ወይም ኬክ ቤቶች በቁጥር ይታወቅ ነበር፡፡ በአሁኑ ግን ቁጥራቸው ልቁጠር የሚያስብል አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን ኅብረተሰቡ ጣፋጭ ምግቦችን ያዘወትራል ለማለት አያስደፍርም፡፡

ዘርፉ ግን የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን አልፎ የውጭ ኢንቨስትመንት እየሳበ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ የውጭ ባለሀብቶችም የተሠማሩት የየአገራቸውን ጣፋጭ ምግቦች መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከተሠማሩት መካከልም የሱዳንና የሶሪያ ባለሀብቶች ይገኙበታል፡፡ የሱዳኑ ባለሀብት የተሠማሩት “ኤቲኢ ምግብና ብስኩት ፋብሪካ ፒኤልሲ”፣ እንዲሁም የሶሪያው ባለሀብት የተንቀሳቀሱት ደግሞ “ሲሪያ ስዊትስ ኤንድ ሬስቶራንት” የሚባሉ ኩባንያዎችን በማቋቋም ነው፡፡

አቶ እስክንድር ዓለማየሁ የኤቲኢ ምግብና ብስኩት ፋብሪካ ወኪል ናቸው፡፡ እንደ ወኪሉ አባባል ከሆነ ፋብሪካው በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አካባቢ ከተቋቋመ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ 21 ዓይነት ኩኪስ፣ ብስኩትና ባቅላባ ያመርታል፡፡ ምርቱን በየሱፐር ማርኬቱ ከማከፋፈሉም ባሻገር አማካይ በሆኑና በተለያዩ ሥፍራዎች አራት የመሸጫ ሱቆችን ከፍቷል፡፡

ፋብሪካው እያመረተ የሚያቀርባቸው ጣፋጭ ምግቦች የመጠቀሚያ፣ ወይም ሼልፍ ላይ የመቆያ ጊዜያቸው ከሁለትና ከሦስት ወራት አይበልጥም፡፡ የተጠቀሰው ጊዜ ካለፈ ይሰበሰቡና እንዲቃጠሉ ይደረጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር የተዘረጋው ኩባንያው ሥራውን በጀመረ ማግስት ነበር፡፡ አሁን ግን ሳይሸጥ የቆየ ለመቃጠል የሚበቃ ኩኪስ፣ ብስኩትና ባቅላባ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡

ኩባንያው 30 ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ በተለይም የሱዳን ባቅላባ በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እያተረፈ መምጣቱን ከአቶ እስክንድር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

አቶ አህመድ አሊ ቢክሪ በዱባይ የሚኖሩ የሶሪያ ዜጋ ሲሆኑ የሲሪያ ስዊትስ ኤንድ ሬስቶራንት መሥራችና ባለሀብት ናቸው፡፡ ድርጅታቸው ከስምንት ዓመት በፊት በዱባይ እንደተቋቋመ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ፣ በፊሊፕንስ፣ በሲሪሊንካ፣ በሶሪያና በሊባኖስ ቅርንጫፎች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ ድርጅታቸውን በአሥር ሚሊዮን ብር ወጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም ያነሳሳቸው “ደማስቆ በሚገኘው የኢትዮጵያ የባህል ምግብ ቤት ማዘውተሬና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ ባደረጉልኝ ምክር፣ ግፊትና ቅስቀሳ ነው፤” ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያና ሶሪያ ለምግብ ዝግጅት የሚጠቀሙባቸው ጥሬ ዕቃዎች ተመሳሳይ መሆኑም አብሮና ተጋግዞ ለመሥራት ቀላል እንደሚሆንላቸው መገንዘባቸውና በኢትዮጵያ ጣፋጭ እምብዛም የተዘወተረ አለመሆኑ በዘርፉ ለመሠማራት ምክንያት ከሆኗቸው ነገሮች ይካተታሉ፡፡

ቃሊቲ አካባቢ ባቋቋሙት የጣፋጭ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከ15 በላይ የሚሆኑ የሶሪያ የባህል ጣፋጭ ምግቦች እንደሚመረቱ፣ ከእነዚህም ምግቦች መካከል ሀላዋና ባቅላባ እንደሚገኙበትና ለስኳር ሕሙማን የሚጠቅሙ ብስኩቶችም እንደሚኖሩበት አስረድተዋል፡፡

ከተጠቀሱም ምግቦች መካከል 60 በመቶ ያህሉ የሚመረቱት ድርጅቱ ለአምስት ወራት ያህል ባሠለጠናቸው 12 ኢትዮጵያውያን ሼፎች ነው፡፡ ሥልጠናውም የተሰጠው ለአምስት ወራት ያህል ሲሆን፣ በጠቅላላው ለ24 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ የደመወዝ ክፍያቸውም ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በሥነ ምግብ ዘርፍ ከተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መካከል አንዳንዶቹ የስኳር ሕሙማን ጣፋጭ ምግቦችን መመገብ ወይም ማዘውተር እንደሌለባቸው ይመክራሉ፡፡ ምክንያቱም እንደነዚህ ዓይነቶቹ ምግቦች ያላቸው ንጥረ ነገር ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት ሲሆን፣ ይህም በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በጣም ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ደግሞ ማኅበረሰቡ ቤት ውስጥ ምግብ አብስሎ ከመመገብ ይልቅ ባለቀላቸው ወይም ለፍጆታ ዝግጁ በሆኑና በታሸጉ ምግቦች ላይ ጥገኛ ሆኗል፡፡ የስኳሩ ባሕሪና ጥሩ መዐዛ የመፍጠሩ ሁኔታ ደግሞ የማኅበረሰቡን ጥገኝነት አጠንክሮታል፡፡

እንደ ባለሙያዎች ማብራሪያ ከሆነ የታሸጉ ጣፋጭ ምግቦችን ከመጠቀም በፊት በእሽጉ ላይ ያለውን ምልክት (ሌብል) ማንበብ ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት አንዳንዶቹ የያዟቸው የስኳር መጠን ትንሽ ወይም ከስኳር ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ሰው እንደ ጤናው ይዞታና እንደፍላጎቱ መጠን እንዲጠቀም ያደርገዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.