quit-smoking-8በአማላይ፣ ሳቢና ማራኪ ማስታወቂያ ታጅቦ ይቀርባል። ጭስ አልባ ፣በተለያየ መዓዛ የተዘጋጀ፣ እንደማስቲካ የሚታኘክ … ሌላም ሌላም በማለት እንኳን ፈላጊውን ስሙን ማንሳት የማይፈልገውን ሰው ልብ ለመሳብ ጥረት ያደርጋል፣ የትምባሆ ኢንዱስትሪ።
ትምባሆ በየትኛው ዓለም በማንኛውም ዜጋ ተወዳጅነትን ያተረፈ አይደለም። ምንም ዓይነት ሣይንሳዊ ጠቀሜታም አልተገኘበትም። ተጠቃሚ እንኳን እየተጠቀመም የሚናገረው ግን ጐጂነቱን ነው። መቼ ነው ከእዚህ ገዳይ ሱስ የምላቀቀው በሚል ስሜት። ይሁን እንጂ የማንኛውም ነገር ሱስ ፈታኝና በአንድ ጊዜ ለማቆም አስቸጋሪ በመሆኑም ብዙዎች ለመተው ይቸገራሉ። ከገቡበት አደጋም ለመውጣት ዳገት የመቧጠጥ ያህል ይሆንባቸዋል።

ግንቦት 23 ቀን በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲጋራ የማይጨስበት ቀን ተብሎ ይከበራል። ይህ ቀን ለብዙዎች ትምባሆ ማጨስን ለማቆም የሚወስኑበት ዕለት ነው። ሌሎች ደግሞ በወሰኑት ውሳኔ ፀንተው የቆዩበት ቃልኪዳናቸውን የሚያድሱበት።
ከትምባሆ አጫሽነት ሱስ ለመላቀቅ ብዙዎች ቢቸገሩም ፣መወሰን ቢያቅታቸውም ጥቂቶች መቻላቸውን በአንደበታቸው መስክረዋል። ወጣት ዮሐንስ መላኩ የወጣትነት ዕድሜው በፈጠረበት ‘የሥልጣኔ’ ስሜት ድንገት ብድግ ብሎ ሲጋራ ማጨስ ጀመረ። በእዚሁም ለአሥር ዓመታት ሳያቋርጥ ማጨሱን ቀጠለ። ሱሰኛ መሆኑን ራሱን አሳመነ።

«ትምባሆ አጫሽ ይሉኝታ የለውም። በቃ አጫሽ ስትሆኚ ደፋር ትሆኛለሽ። ካለሽ ገዝተሽ ታጨሻለሽ። ከሌለሽ ግን የበታች ወይም የበላዬ ከምትይው ሰው ስጠኝ ብለሽ በድፍረት ትቀበያለሽ። በቃ! አጫሽ ዓይን አውጣ ነው። ይሉኝታ የለውም። ለምንም ነገር ልልሽ እችላለሁ። እኔም ይህንኑ ባህሪ ነው ስከተል የኖርኩት» ይላል ተሞክሮውን ሲገልጽ።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ ሲጋራ የማይጨስበት ቀን በመላው ዓለም ታስቦ ሲውል ዮሐንስም ሲጋራ ማጨስ ያቆመበትን ልደት በዓል አክብሯል። ከአንድ ዓመት በላይ ማጨስ ማቆሙን ሲገልጽም ትልቅ ድል አድራጊነት ስሜት እየተሰማው እና ባለፈው ጥፋተኛነቱ እየተፀፀተም ጭምር ነው።

ሲጋራ ማጨስ የጀመረበትን ጊዜ የሚያስታ ውሰው ‘ ፈንድቼ’ ነው በሚለው ቃል ነው። «አንዲት የሴት ጓደኛ ነበረችኝ። አብረን ሲጋራ እናጭስ እና ጫትም እንቃም ብለን ተነሳን። ከዚያ ማቆሚያ አጥተን ቀጠልን። እኔ ለአሥር ዓመታት የሱስ ተገዢ ሆኜ ቆየሁ» ይላል።

ወጣት ዮሐንስ ብስል የሚባል ቀይ ነው። መልከ መልካም ታዛዥና ከሰዎች ጋር ደግሞ ተግባቢ። አንድ ባህሪው ብቻ አይመችም። ቁንጥንጥ ነው። የጀመረውን ቁምነገር ሳይጨርስ ይሰወራል። ደግሞ ይመለሳል። ምድጃ የመሰለው የሰውነት ክፍሉ (ከናፍሮቹ) ግን ማንነቱን ይናገራሉ፡፡ ለምን ጠፋ መለስ እንደሚልም መጠየቅ አያስፈልግም። መለስ ሲል ከአፉ የሚወጣው ጠረን የት እንደነበር ይናገራልና።
ዛሬስ? አልኩት። «ሳቀ» ከናፍሮቹን በእጁ እየደባበሰ አንቺው አይተሽ ፍረጂ ዓይነት ነው ምላሹ። በእውነትም የዮሐንስ ‘ምድጃ’ መሳይ ከናፍሮቹ የተፈጥሮ ቀለማቸውን ይዘዋል፡፡ ከልብሱም ሆነ ከአፉ የሚወጣ ገፍታሪ ጠረን የለም። እርሱም «እግዚአብሔር ይመስገን ሱስ ሲፈትነኝ ሮጬ የምሄድ ወደ እምነት ተቋማት ነው። ሳቆምም ለጊዮርጊስ ነግሬው እርዳኝ ብዬው ነው። ፈተናው ሲበዛም እግሮቼን ወደ ሱቅ፣ እጆቼ ወደ ኪስ ሳይሆን የማደርገው ወደ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ነው። በልመናዬ በፀሎቴ አጽናኝ ስል የእኔ ቆራጥነት እና የአምላክ ዕርዳታም ታክሎበት ከእዚህ ደርሻለሁ» በማለት ሲጋራ ማጨስ መጀመር ቀላል፣ ማቆም ደግሞ ትዕግስትና ቆራጥነትን የሚጠይቅ ከባድ መሆኑን የመሰ ከረው።

ዮሐንስ ዛሬ ላይ ሆኖ መለስ ብሎ ያሳለፈውን ጊዜ ሲያስበው ይገርመዋል። ባለሥልጣን፣ አለቃ፣ ሀብታም፣ ቦዘኔ ብሎ ልዩነት የማይ ደረግበት፤ የተማረ፣ ያልተማረ እኩል የሚሰየሙበት የጫት መቃሚያ እና የሲጋራ ማጨሻ ሥፍራዎች መሆናቸውን ይናገራል።

ትምባሆ አጫሾች ‘ለሲጋራ የሚሆን ገንዘብ አይጠፋም። ለዳቦ እንጂ’ ሲሉ ይደመጣሉ። እውነቱም ይሄው ነው። አንድ ዳቦ የሚበላ (የሚገዛ) ሰው አብሮት ላለው ወዳጁ ዳቦ ሊገዛለት ከቶ አይከጅልም። ሲጋራ ሲገዛ ግን ለጓደኛውም ያስባል። ቢያጣ ደግሞ የጀመረውን የተተረኮሰ ሲጋራ ያጋራዋል። አብረው ይጨሳሉ ያጨሳሉ። ዮሐንስ «ትምባሆ ለማጨስ ፈልጌ ያጣሁበት ቀን የለም» ያለውም ከእዚሁ በመነሳት ነው።
የትምባሆ ጐጂነት በየጊዜው ይነገራል። ይጻፋል። ይሁን እንጂ ትምባሆን ከመሸሽ ይልቅ መቅረቡ ዛሬም ድረስ ጐልቶ ይታያል። ከአጫሹ በማይተናነስ መልኩም ደባል አጫሾች (ቀጥተኛ አጫሽ ያልሆኑ ነገር ግን ጭሱን የሚጋሩ) ሰዎች በጤና መታወክ ተጐጂዎች ናቸው።

በተለይ ሕፃናት እና ሴቶች ደግሞ ችግሩ ገዝፎ የሚታይባቸው ናቸው። ሆኖም ግን ዛሬ ልጆች በሚባለው ዕድሜ ውስጥ ያሉና ሴቶች የትምባሆ አጫሾች ከሚባሉት ጐራ ተቀላቅለዋል። በተለይ ‘ዘመናዊ’ ነን ባይ ወጣቶች።

ወጣት ፌቨን (ስሟ በሌላ ስም ተተክቷል) ትምባሆ ማጨስን ከጀመረች ጥቂት ወራትን ቆጥራለች። መቼና እንዴት እንደጀመረች አታስታውሰውም፡፡ ስታጨስ ግን ደስ የሚል የመነቃቃት ስሜት እንደሚፈጥርላት ትገልጻለች። በተለይ ከጓደኞቿ ጋር ስትሆን ማጨስ ያስደስታታል።

ወጣቷ ሲጋራ ማጨስ በጤና ላይ የሚያስከትላቸው ችግሮች ቢኖሩም ችግሩ ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ አላሰበችም። «ብዙ ሰዎች ሌላው ቀርቶ የሕክምና ባለሙያ የሚባሉት ሳይቀሩ ያጨሳሉ። ታዋቂ ሰዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የሀገር መሪዎች ሁሉ ያጨሳሉ። እና እነርሱ ጐጂነቱን ሳያውቁት ነው?» ስትል የመከላከያ ነጥቧን አነሳች። ዓለም ሁሉ የሚጠቀምበት ጐጂ ስለሆነ አይደለም የሚል እምነት አላት። ደግሞ ትምባሆ በተለያየ መልክ መቅረቡ የጉዳቱን ደረጃ ለመቀነስ ሊሆን እንደሚችል ትገምታለች። ዋነኛ አቋሟ ግን «አይብዛ» እንጂ «አልተወውም» ዓይነት ነው።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወጣት ዮናስ ጣሰው የአጫሽ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ያሳስበዋል። « ምን ያህል ወጣቶች የትምባሆ አጫሽ ሆኑ የሚል ጥናት ባይደረግም በዓይን የሚታዩት ነገሮች ምን ያህል ወጣቱ ለሱስ ተገዢ እየሆነ መምጣቱን ነው» ይላል። በተለይ በየሠፈሩ፣ በየጉራንጉሩ የተከፈቱና የተስፋፉ የጫት መሸጫና መቃሚያ ቤቶችን በማንሳት ጫት ተጠቃሚ (ቃሚ) ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲጋራ አጫሽ ነው። የሲጋራ ጭስ ተጐጂ ነው። ይሄ ደግሞ በጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ በኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጉዳት እንዳለው ይናገራል። ለሱስ የተጋለጠ ወጣት ሱስን ማርካት የሚያስችል ገንዘብ ቢያጣ ሌብነት ውስጥ ይገባል። ማጅራት መቺ አይሆንም ብሎ ማሰብ ከባድ ነው ለወጣት ዮናስ።

ለወጣት አጫሽነት ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ይገልጻል። የአቻ ግፊት፣ ስደትና ሥራ አጥነት፣ አርአያ የሚሏቸውን ታዋቂ ሰዎች ፈለግ መከተል፣ አዲስ ነገርን ለመሞከር የሚደረግ ጉጉት፣ የአዕምሮ መታወክ፣ የአካባቢ ተጽዕኖ እንዲሁም አለማወቅ የሚሉት በምክንያትነት የተነሱ ናቸው።
ለትምባሆ የሚሠሩ ማስታወቂያዎች ለተመልካች ዓይንና ጆሮ ሳቢ ሆኖ መቅረቡ አንዱ ወጣቱን ለሱሰኝነት ከሚዳርጉት ምክንያቶች ጐራ ይሰለፋል። «ላይት፣ ስትሮንግ፣ ሀርድ የተለያየ ፍሌቨር (ጣዕም) ያለው ጭስ አልባው በማስቲካ መልክ የሚታኘክ» የሚሉት ማስታወቂያዎች ወጣቱ እንዲሞክራቸው እና እንዲሳብባቸው የሚጋብዙ ናቸው። 

ይሁን እንጂ ማስታወቂያው አማረ፣ ማሸጊያው ተዋበ ተብሎ ለገዳዩ ትምባሆ እጅ የሚሰጥበት ሳይሆን መራቅ የሚቻልበትን መንገድ መጠቆም ከወጣት ዮናስ የተሰነዘረ ሃሳብ ነበር። «ሰፊ ትምህርቶችን በዘመቻ መልክ ማካሄድ፣ ከፍተኛ ታክስ እንዲጫንበት ማድረግ፣ የማስተዋወቁ ሥራ እንዳይሠራ ማገድ፣ ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ» ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ሳይናገር አላለፈም።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ዲን ዶክተር መስፍን አርአያ በሱስ ተገዢነት ዋነኛ ተጋላጮች ወጣቶቹ መሆናቸውን ይናገራሉ። 80 በመቶ የሚሆኑት የትምባሆ አጫሽ ወጣቶች ዕድሜያቸው ትምባሆን ማጨስ የሚጀምሩት እስከ 18 ዓመት ባለው ዕድሜያቸው መሆ ኑን ይገልጻሉ። 99 በመቶ የሚሆኑ አጫሾች ደግሞ የሚጀምሩበት እስከ 25 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ይሄ ደግሞ አፍላ ወጣትነት የሚባልበት ጊዜ ነው። በዩኒቨርሲቲ አካባቢ በተደረጉ ጥናቶችም ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ሲጋራ ማጨስን ይለማመዳሉ።

‘ዶክተሩ ሲጋራ እያጨሰ አታጭሱ’ ማለት አይቻልም። ይሄ ከሙያ አንፃርም ተገቢ አይደለም ይላሉ። የሕክምና ባለሙያ የሲጋ ራን ጉዳት ጠንቅቆ ያውቃል። አውቆም ያስተምራል ያስረዳል። ስለዚህ እያጨሰ አታጭሱ ሊል አይገባም። ወጣቶችም አርአያ ሞዴል የሚሏቸውን ሰዎች መምረጥ ከተግባሮቻቸው የሚጠ ቅማቸውን መለየት ይኖርባቸዋል የሚል ነው መልዕክቱ።

የዘንድሮ የዓለም ሲጋራ የማይጨስበት ቀን መሪ ቃል «የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት በዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት ትግበራ» የሚል ነው። ይሄ የትምባሆ ፋብሪካዎች የኢኮኖሚ አቅም የገዘፈ በመሆኑ ምርቶቻቸውን በስፋት ለማስተዋወቅ ማሸጊያዎችን ለማሳመር እንዲሁም ውብና ማራኪ የፍራፍሬ ጣዕምና መዓዛ እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ይገኛሉ። መርሁ ይህን ግዙፍ የሆነ ኃይልን እንታገለው የሚል ነው።

በመገናኛ ብዙኃንና በተለያዩ መድረኮች በሲጋራ ጐጂነት ዙሪያ ሰፊ ሥራ መሥራት በመቻሉ በዓለም ላይ አራት ቢሊዮን ሕዝብ ለመታደግ ተችሏል። በመሆኑም የትምባሆን ገዳይነት በመገናኛ ብዙኃን በሚገባ ማስተማር በወጣት አደረጃጀቶች ግንዛቤ የሚፈጠርበትን መድረኮች ማዘጋጀት፣ በሲጋራ መጠቅለያዎች ላይ የሲጋራን አስከፊነት የሚሰብኩ ማስታ ወቂያና ምስሎችን ማድረግ የሚሉና ሌሎችም በመፍትሔ አቅጣጫነት የተነሱ ሃሳቦች ናቸው። «ለሚወዱት ቤተሰብዎ፣ ለልጅዎ እና ለሚስትዎ ከትምባሆ ጭስ ምክንያት በሚመጣ የካንሰር እና ለሌሎች በሽታዎች አይዳርጉ» የሚል ትልቅ ዓለም አቀፍ መልዕክትም ነው።

የትምባሆ ጉዳት ከራስ ቅል እስከ እግር ጥፍር መሆኑን ተረድተው ዛሬውኑ ለማቆም ይወስኑ። አቁመውም ጠንካራነትዎን ይመስክሩ መልዕክታችን ነው። ምንጭ፡- አዲስ ዘመን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.