firut«ዛሬ የበላሁት ምግብ አልተስማማኝም፤ እየረበሸኝ ነው» ያሉበትን ቀን አያስታውሱም? የበሉት ምግብ ውስጥዎን ረብሾዎትና ምቾት አጥተው የዋሉበት ወይም ያደሩበት ቀንስ ትዝ አይሎትም? ትዝ ሊሎት አልያም አጋጥሞት ላያውቅና ትዝ ላይሎት ይችላል፡፡ ሆኖም ብዙዎች በተመገቡት ምግብ ሳቢያ ታመዋል፡፡ ይህ የሚከሰተው አልፎ ተርፎ በተመረዘ ምግብ በሚመጣ ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ የሚመገበው ምግብ የሚያሳምመውና ጤናውን የሚያቃውስበት ሳይሆን ለአካላዊም ሆነ ለአዕምሯዊ ዕድገቱ የማይጠቅም ሊሆን እንደማይገባ አያጠራጥ ርም፡፡ 

የጤና ዘርፍ ጠበብቶቹ እንደሚገልጹት ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ለጤናማነት መሠረት ነው፡፡ ምግብ መመገብ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ምግቡ የያዘው ንጥረ ነገር ለተመጋቢው አስፈላጊና ጠቃሚ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ አለዚያ ትርፉ የርሃብ ስሜትን ማስታገስ ብቻ ይሆናል፡፡ 


ሰዎች በቂና የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዳለባቸው አያከራክርም፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን በቂና የተመጣጠነ ምግብ ስለማግኘት እናስብ ይሆን? ጉዳዩ ከግለሰባዊነትም ያልፋል፤ መንግሥትስ ዜጎች በቂና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ምን ያህል ይተጋል? ሰዎች በቂና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት የማን ነው? የመንግሥትና የራሳቸው የግለሰቦቹ ብቻ ነውን? 
ጉዳዩን በዋናነት የሚወስዱት መንግሥትና ራሳቸው ተመጋቢ ግለሰቦቹ ቢሆኑም ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችም ከምግብ ጋር ተያይዞ እንሠራለን ካሉ እነርሱንም ይመለከታል፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶቹ ከዕለታዊ ዕርዳታ ይልቅ ለዘለቄታው ሕዝቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ሊሠሩ ይገባል፡፡ 


በቅድሚያ ከራሳችን እንነሳ፤ አመጋገባችን እንዴት ነው? በእንጀራ እና ወጥ ላይ የተወሰነ ወይስ ለሰውነት አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የያዙ ምግቦች የተካተቱበት? የሰው ልጅ በየጊዜው የተለያየ ምግብ መብላት አለበት፡፡ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ምግብ መመገቡ ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጤና ላይ ወይም የአዕምሮ መበልጸግ ላይ ችግር ያስከትላልና፡፡ 


መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የተመጣጠነ ምግብ ለአዕምሮ መበልጸግ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ የበለጸገ አዕምሮ ያለው ኅብረተሰብ ሳይኖር የበለጸገ ተቋምንና ያደገች ሃገርን እውን ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በሃገር ደረጃ ከምንም በላይ የተመጣጠነ አመጋገብን የሚከተል ኅብረተሰብን መገንባት ይቀድማል፡፡


መንግሥትስ ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶታል? በግልጽ እንደሚታየው መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ዝናብን ጠብቆ ብቻ ሳይሆን በመስኖም እየተጠቀመ እንዲያለማ እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን የማይዋሽ አንድ ሐቅ አለ፡፡ ለተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች መመረት ቢኖሩባቸውም አርሶ አደሩ በተለምዶ የሚያመርተውን ብቻ አሁንም እያመረተ ነው፡፡ ለምርት ብዛት እንጂ ምርቱ ለሚይዘው ንጥረ ነገር ዓይነትና መጠን ሲታሰብ አይታይም፡፡


አንዳንድ ጊዜ አርሶ አደሩ ከገበያው ጋር ተያይዞ አንድ ዓይነት ምርት ብቻ የሚያመርትበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአብነት አምና ሽንኩርት ከተወደደ በተለይ የመስኖ አምራች አርሶ አደር በሙሉ ሽንኩርት ያመርታል፡፡ ጎመን ፣ቲማቲምና ሌሎችም አትክልቶች አይመረቱም፡፡ ሕዝቡ እንደ ድንችና ጎመን የመሳሰሉ አትክልቶችን ለመመገብ ቢፈልግም በገበያ ላይ አያገኝም፡፡ ከተገኘም ዋጋው እጅግ ይወደዳል፡፡ እዚህ ላይ አርሶ አደሩን በጉዳዩ ላይ የማስተማርና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያመረት በማድረግ በኩል የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር በተጨማሪ ምግብን በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ሊያስቡበት ይገባል፡፡ 


በግብርና ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ፅጌ እንደሚናገሩት ተቋሙ አርሶ አደሩ አመጣጥኖ እንዲያመርት በማድረግ በኩል እስከአሁን የሠራው ሥራ አነስተኛ ነው፡፡ ከእዚህ በኋላ ግን በትኩረት ይሠራበታል፡፡ ከጉዳዩ አስፈላጊነት አንፃርም መንግሥት ወይም የግብርና ሚኒስቴር ብቻውን ሳይሆን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችም ሆኑ በጎ አድራጊዎች ከዕለት ደራሽነታቸው ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ በቀጣይነት ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን እንዲከተል ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው ፡፡ 
«መንግሥት ምርታማነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ፖሊሲዎችን፣ስትራቴጂዎችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኅብረተሰቡ በቂ ምግብ እንዲያገኝ የማድረግ ጥረት ላይ ነው» የሚሉት አቶ ታረቀኝ በ2005 እና 2006 የምርት ዘመን ምርቱን 20 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ይናገራሉ ፡፡ 


በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በሃገር ደረጃ ወደ 277ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው 251 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት መቻሉን ይገልጻሉ፡፡ የመስኖ ልማት በማስፋፋት አትክልት ማምረት ላይ ትኩረት መሰጠቱንም ጭምር፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ በተለመዱ ምርቶች ላይ እንደሚያተኩርና ከፍተኛ ቫይታሚን የያዙ አትክልቶችን ማምረት ላይ ክፍተት መኖሩን ያመለክታሉ፡፡ በፍራፍሬ ምርት በኩልም ግን ትልቅ ዕድገት መኖሩን በመጠ ቆም፡፡


ሕዝቡ በቂ ምግብ እንዲያገኝ እየተሠራ ያለው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ታረቀኝ ፤ ነገር ግን በተለይ የተመጣጠነ ምግብ እንዲገኝ የተከናወነው ሥራ በቂ ነው ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በቀጣይ የተገኘውን ውጤት በማስፋት ስትራቴጂ ተጠቅመው ሕዝቡ በቂና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ እንደሚደረግ ይና ገራሉ፡፡ 
እንደ አቶ ታረቀኝ ገለጻ በዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን ዕቅዱ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብና በሃገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ ታቅዷል፡፡ በመሆኑም በአርሶ አደሩ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢ ውሃን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የእንስሳት ሀብት ልማቱ ላይም እየተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት አንዱን ትቶ ሌላውን እየያዘ ሳይሆን ሁሉም በቂ ምግብ እንዲያገኙና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የተቻለው ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከእዚህ በኋላ ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ላይም ትኩረት የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል፡፡ 


የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ተወካይ አቶ ሐሰን ዓሊ በበኩላቸው በአጠቃላይ ሕዝቡ በተለይ አርሶ አደሩ ፣ ባለሀብቱ ፣ እህል አምራች ድርጅቶችና ዕርዳታ ሰጪዎችም ሆኑ መንግሥት ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖር ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ የሚመረት ምርት ብዛትና ሰዎች የተመገቡት ምግብ መጠን ማደግ ላይ ብቻ ሳይሆን ምርቱ የያዘው ንጥረ ነገር ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡ በእርግጥ ምርት እያደገ መሆኑ ተገቢ ቢሆንም ኅብረተሰቡ የሚያስፈልገውን ንጥረ ነገር እያገኘ ነው? የሚለውን ማየት እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡
በአንድ ወገን ሃገራት በፈጣን ዕድገት ላይ መኖራቸው እየተነገረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሲታመሙና ሲሰቃዩ ይስተዋላል፡፡ ማምረት አንድ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል የተመረተው ምርት የሚይዘው ንጥረ ነገር ማመጣጠን ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ የሚሉት አቶ ሐሰን ከዕድገቱ ጋር ተያይዞ የተሻለ የአመጋገብ ሥርዓት በመፍጠር ጤናማ ማኅበረሰብ መገንባት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ 


እንደ አቶ ሐሰን ገለጻ ምግብ ማጣት ብቻ ሳይሆን ከልክ በላይ ምግብ ተመግቦም የተመጣጠነ ምግብ እጦት በሽታ ያጋጥማል፡፡ ለጤናማ ሰውነት የሚያገለግል ምግብ ሳይመገቡ ያለልክ ከተበላ ከመጠን በላይ በመወፈርም በሽታ ላይ ይወደቃል ፡፡ ስለዚህ ምግብን ማመጣጠን ያስፈልጋል፡፡


የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የአመጋገብ ሥርዓትን የማሻሻል ጉዳይ የአንድ ድርጅት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ መንግሥትና አጋር ድርጅቶች በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በእዚህ በኩል ግንዛቤውን መፍጠር የግድ ነው፡፡ በእዚህ ጉዳይ ላይ ኅብረተሰቡ እንዲነጋገር ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ 


የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅትም ከመሪዎች ጀምሮ እስከ ዝቅተኛው ኅብረተሰብ ድረስ የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በተለይም አሁን ከተመጣጠነ ምግብ እጦት ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ከቀድሞ የብራዚል ፕሬዚዳንት፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን ከፍተኛ የመሪዎች ስብሰባ እንዲካሂድ አድርጎ ነበር ፡፡ 


በወቅቱ የምግብ ዋስትናና የአመጋገብ ሥርዓትን አሻሽሎ መሄድ ፕሮግራም የየሃገሮቹ መሠረታዊ ፕሮግራም መሆን እንዳለበት መሪዎቹ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ላይ ለሙከራ ትግበራ አራት ሃገራት የተመረጡ ሲሆን፤ አንደኛዋ ኢትዮጵያ እንደነበረችም ይናገራሉ፡፡ ሃገሪቱ እስከአሁን በራሷ ያከናወነቻቸው ሥራዎች ለሌሎች ሃገሮች መነሻ እንዲሆንም ታስቧል፡፡ በእዚህ በኩል የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር በዋናነት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሥራት ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


«የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሃገር አቀፍ የተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራሙ እንደገና እንዲከለስ ሲደረግ ግብርናና የአመጋገብ ሥርዓት የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ አሁን የፀደቀው የኢትዮጵያ የአመጋገብ ሥርዓት ፕሮግራም ተግባራዊ ሲደረግ የጤናውም ክፍል ተካቷል፡፡ ሁለቱም ዘርፎች አያይዘው እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ በፊት የተመጣጠነ ምግብ ጉዳይ ሲነሳ የጤና ዘርፍ ጉዳይ ብቻ ነው ይባል ነበር፡፡ የጤናው ዘርፍ በበኩሉ ጉዳዩን ከግብርና ምርት ጋር በማገናኘት ጉዳዩ የግብርና ኃላፊነት እንደሆነ ይቆጥረው ነበር ፡፡አሁን ግን ጉዳዩ የሁለቱም ዘርፎች መሆኑ በግልጽ እንዲታወቅ ተድርጓል» ብለውናል፡፡ 


አቶ ሐሰን እንደሚናገሩት የተመጣጠነ ምግብ ጉዳይ የአስተሳሰብ ጉዳይ በመሆኑ በኅብረተሰቡ አካባቢ የሚሠራው ሥራ ሰፊና ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ለውጥ የሚመጣውም በሂደት ነው፡፡ ስለዚህ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ጤናማ የተመጣጠነ አመጋገብ ለማምጣት በቅድሚያ ኅብረተሰቡን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡


«በኢትዮጵያ ያለ የገጠርም ሆነ የከተማ ተማሪ ሆዱን ሞልቶ እየመጣ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ትምህርት ቤት አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ለተማሪዎች የሚያስፈልገውን ምርት አምርቶ ማቅረብ ከቻለና ትምህርት ቤቱ ያንን ምግብ ከገዛው፤ለተማሪዎቹ በቀላሉ መመገብ ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ማሰብ ይገባል፡፡ እነብራዚል፣ቻይናና ቬትናም በትምህርት ቤት ተማሪዎችን የመመገብ ሥርዓት (school feeding) ፕሮግራምን ተግባራዊ አድርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን በምግብ ራሱን አስችለዋል» ብለዋል፡፡


በማጠቃለያቸውም የተመጣጠነ ምግብ ለጤናማ ኅብረተሰብ ወሳኝ ነው፡፡ ያለጤናማ ኅብረተሰብ ዕድገትም ሆነ ልማት አይታሰብም፡፡ ዕድገትና ልማት ሲታሰብ በዋናነት የተመጣጠነ ምግብ ይታሰብበት ብለዋል፡፡

ምንጭ;- አዲስ ዘመን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.