የሰው ልጅ በተለያዩ ምክንያቶች ጤናው ይስተጓጎላል፡፡ በእኛ ኅብረተሰብ ዘንድ ደግሞ በሽታን አስቀድሞ የመከላከልና ሲከሰትም ቶሎ ወደ ሕክምና ሄዶ የመታከም የዳበረ ልማድ ባለመኖሩ በቀላሉ መዳን በሚችሉ በሽታዎች አማካኝነት ለከፍተኛ የጤና ጉዳት ይዳረጋል። ለሕክምናው የሚወጣው ወጪም የቤተሰብ ብሎም የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡ ችግሩ ባስ ካለ ደግሞ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ያልፋል። 

ሰዎች በተደጋጋሚ ከሚጠቁባቸው በሽታዎች ውስጥ «ሄፖታይተስ ቢ» የተባለ የጉበት በሽታ አንዱ ነው፡፡ ስለሄፖታይተስ ቢ በሽታ ምንነትና መንስኤዎቹ እንዲሁም ሕክምናውን አስመልክቶ በተክለሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፒሻሊስት የሆኑት ዶክተር ኤልያስ ሳሙኤል ማብራሪያ ሰጥተውናል።

ሄፖታይተስ ምንድን ነው?

ሄፖታይተስ ማለት ከጉበት መቆጣት ጋር የተያያዘ የጉበት ጉዳት ማለት ሲሆን ፤ይህ የጉበት መቆጣት በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ድንገተኛ ሄፖታይተስ (አኪዩት) ይባላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ስር የሰደደ የቆየ የጉበት መቆጣት (ክሮኒክ) ሲባል የህመሙ ምልክቶች ስድስት ወርና ከእዚያ በላይ ሲቆይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ድንገተኛው ሄፖታይተስ በቀናት ውስጥ ይጀምርና በሁለት ወይም በሦስት ወራት በዛ ከተባለ በስድስት ወር ውስጥ ህመምተኛው ከበሽታው ያገግማል፡፡ የሄፖታይተስ መንስዔዎች በሁለት ይከፈላሉ። ተላላፊ (ከኢንፊክሽን) ጋር የተያያዙ እና ከኢንፌክሽን ጋር ያልተያያዙ ናቸው፡፡ በአብዛኛው በሽታው የሚከሰተው ግን ከኢንፊክሽን ጋር በተያያዘው መንስዔ ነው፡፡ ከኢንፊክሽን ጋር በተያያዘ ለሚመጣው በሽታ መንስዔ ከሚሆኑት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የአልኮል መጠጥ፣መድሐኒቶች፣ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች፣ መርዛማ ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ 

አልፎ አልፎ የሰውነታችን የውስጥ መከላከያ (ኢሚዩኒቲ) ሲዛባ የእራሳችን የበሽታ መከላከያ ጉበታችንን ይጎዳውና «አውቶ ኢሚዩን» ሄፖታይተስ የተባለውን የጉበት መቆጣት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም መንስኤው የማይታወቅ የጉበት መቆጣት ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህም «ክሪብቶጄኒክ» ሄፖታይተስ ይባላል፡፡


ሄፖታይተስ ቢ ማለትስ?

አብዛኛው ሄፖታይተስ የሚከሰተው በአምስት ዋና ዋና የጉበት ቫይረሶች ማለትም ሄፖታይተስ ኤ፣ቤ፣ሲ፣ዲ እና ኢ ተብለው በሚጠሩ የቫይረስ ዓይነቶች ሲሆን፤ የእያንዳንዳቸው ባህሪና ምንነት የሚታወቀው በውስጣቸው ባለው ጄኔቲክ ማቴርያል ነው፡፡ ከአምስቱ አራቱ ሄፖታይተስ ኤ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ – አር ኤን ኤ ቫይረስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ ቫይረሶች በውስጣቸው ያለው ጄኔቲክ ማቴርያል ባለ ነጠላ እረድፍ ነው፡፡ ሄፖታይተስ ቢ ባለጥንድ ረድፍ ጄኔቲክ ማቴርያል የያዘ በመሆኑ ዲ ኤን ኤ ቫይረስ ይባላል፡፡ በእዚህም ከላይ ከተጠቀሱት የሄፖታይተስ ቫይረሶች ይለያል፡፡ እነዚህ ቫይረሶች በሽታን የሚያመጡበት መንገድ ይለያያል፡፡ ሄፖታይተስ ኤ እና ኢ ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ በተበከለ ውሃና ምግብ አማካኝነት የሚተላለፉ ሲሆን፤ ሄፖታይተስ ቢ፣ሲ እና ዲ ልክ እንደ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ከደምና ከደም ጋር በተያያዙ መንገዶች የሚተላለፉ ናቸው፡፡

እነዚህ ቫይረሶች የሚራቡት ጉበት ውስጥ ሲሆን ፤ከተራቡ በኋላ ወደ ደም ዝውውራችን ይገባሉ። በእዚህ ጊዜ ሰውነታችን ቫይረሱን ለመዋጋት ፀረ ህዋስ (አንቲ ቦዲ) ያመርታል፡፡ ሄፖታይተስ ኤ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ በተዘዋዋሪ መልኩ በምርመራ የሚገኙ ሲሆን ፤ እነዚህ ፀረ ህዋሶች በደማችን ውስጥ በምርመራ በመለየት የትኛው ቫይረስ እንደያዘን ለማወቅ ይቻላል፡፡ ሄፖታይተስ ቢ ከሌሎች ለየት የሚለው የቫይረሱን አካል (አንቲጅን) በምርመራ ከደም ውስጥ በመለየት ቫይረሱ እንዳለብን በቀጥታ ማወቅ ይቻላል፡፡ በቫይረሱ ሽፋን ላይ ያለው አንቲጅን (ሄፖታይተስ ቢ ሰርፊስ አንቲጅን) በደም ውስጥ ከተገኘ ቫይረሱ እንዳለብን ያሳያል፡፡ ከቫይረሱ ውስጠኛው ክፍል የሚመነጭ አንቲጅን (ሄፖታይተስ ቢ ኢ አንቲጅን) በምርመራ ከተገኘ በደም ውስጥ ያለውን የመራባት መጠንና የማስተላለፍ አቅሙን ከፍተኛነት ያሳያል፡፡

የቫይረሱ መጠን በላቦራቶሪ በደም ውስጥ በዝቶ በአንድ ሲሲ ከአሥር ሚሊዮን እስከ መቶ ሚሊዮን ከተገኘ የህመሙን ደረጃ ከፍተኛነት ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ የተለያዩ አንቲጅኖችን በደም ውስጥ በመመርመር የበሽታው ደረጃ ምን ያህል እንደሆነና ዓይነቱን ለማወቅ ይረዳል፡፡

አምስቱም የጉበት ቫይረሶች ድንገተኛ የጉበት መቆጣት ሲያመጡ ተመሳሳይ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ሄፖታይተስ ኤ እና ኢ ድንገተኛ የጉበት መቆጣት ያስከትሉና ጉበታችን በራሱ ጊዜ አገግሞ ሰውነታችንም ቫይረሶቹን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። ስለዚህም በደም ውስጥ አይቆዩም፡፡ ሄፖታይተስ ቢ፣ ሲ እና ዲ ደግሞ ምንም ምልክት ሳያሳዩ በደም ውስጥ ለረዥም ጊዜ በመቀመጥ እየተራቡ ሄደው ስር የሰደደ የጉበት መቆጣት መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የጉበት በሽታና ካንሰርንም ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

ከአምስቱ ቫይረሶች ሄፖታይተስ ዲ ስንኩል በመሆኑ ለብቻው ሰውን የማጥቃት አቅም የለውም፡፡ ሰውን የሚያጠቃው ከሄፖታይተስ ቢ ጋር በመዳበል ወይም ሄፖታይተስ ቢ የተያዘን ሰው ነው፡፡ ሁለቱ አብረው ሲከሰቱ የሚያስከትሉት ጉዳትም የከፋ ነው፡፡

ሄፖታይተስ ቢ በአገሪቱ በከፍተኛ የጉበት በሽታና የጉበት ካንሰር መነሻነት በዋነኛነት የሚጠቀስ ቫይረስ ሲሆን ፤ከኤ እስከ ኤች የሚደርሱ ዝርያዎች (ጅኖታይፕስ) አሉት፡፡ እነዚህ ዝርያዎች በተለያዩ የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሲሆኑ፤ የሚያስከትሉት የህመም መጠን አንዱ ከሌለው ይለያያል፡፡ አንዳንዶቹ በህክምና ቶሎ ሲድኑ አንዳንዶቹ ግን አይድኑም። በእዚህም ምክንያት ሄፖታይተስ ቢን ለህክምና አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ 

በሽታው ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል?

አዎ! በሽታው የሚተላለፈው በቫይረሱ በተበከለ ደም፣ ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት፣ የተበከሉ መርፌዎችና ስለታም ነገሮችን በጋራ በመጠቀም፣ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ በመሳሰሉት መንገዶች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።

ቫይረሱ በበሽታው በከፍተኛ ደረጃ በተጠቁ ሰዎች ውስጥ መጠኑ ይለያይ እንጂ በማንኛውም ፈሳሽ የሚገኝ በመሆኑ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፍ ያስችለዋል፡፡ 

የሄፖታይተስ ቫይረስ ወደ ሰውነታችን ለመግባት ቀዳዳ ይፈልጋል፡፡ ምንም ጉዳት የሌለው ጤነኛ ቆዳ ውስጥ አልፎ አይገባም፡፡ ነገር ግን የዓይናችን የውስጠኛው ሽፋን ያለምንም ችግር ሊያስተላልፈው ስለሚችል ቫይረሱም ያለበት ፈሳሽ ዓይናችን ውስጥ ቢረጭ በበሽታው ለመያዝ መንገድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በቫይረሱ የተጠቁ ሕሙማንን የሚያስታምሙ የቤተሰብ አባላት የተላጠ ወይንም የተሰነጠቀ ማንኛውም ቁስል እጃቸው ላይ ካለ በፕላስተር መሸፈን አለባቸው፡፡ 

ማንኛውም ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ (ላብንና ዕንባንም ጨምሮ) በጥንቃቄ መያዝና መወገድ አለበት፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ሲገባ ከዘጠና እስከ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ የሰውነታችን መከላከያ ኃይል ቫይረሱን ሙሉ ለሙሉ አስወግዶ ቋሚ መከላከያ ይፈጥራል፡፡ ቫይረሱን ይዘው የሚቀሩት ከአንድ እስከ አምስት ከመቶ የሚሆኑ ሕመምተኞች ብቻ ናቸው፡፡ ቫይረሱ ካለባቸው ጥቂቶቹ ስር የሰደደ የጉበት መቆጣት ሲይዛቸው አብዛኞቹ ምንም ምልክት አያሳዩም፡፡ በአጠቃላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ሃያ ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ከፍተኛ የጉበት በሽታ (ክሮኒክ ሊቨር ዲዚዝ) ይይዛቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ከዓመታት በኋላ የጉበት ካንሰር ሊይዛቸው ይችላል፡፡

የሲዲሲ (የተላላፊ በሽታዎች ማዕከል) ጥናት እንደ ሚያሳየው ኢንፌክሽኑ በብዛት የሚታየው ከሃያ እስከ አርባ ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ሲሆን ሕፃናት ላይ እንብዛም አይገኝም፡፡ ከአርባ ዓመት ዕድሜ በላይ ባሉ ሰዎች የበሽታው መጠን የመቀነስ አዝማሚያ ያሳያል፡፡

ቫይረሱ ወደ ሰውነት በሚገባበት ወቅት ድንገተኛ የጉበት መቆጣት የሚያሳየው ምልክት የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት መቀነስ፣ ዐይን ቢጫ መሆን፣ በቀኝ በኩል የላይኛው የሆድ ክፍል የህመም ስሜት የሚሰማ ሲሆን፤ ህመምተኛው ህክምና ከወሰደ በሦስት ወር ውስጥ ያገግማል፡፡ ስድስት ወር ከሞላው ግን ስር ወደ ሰደደ የጉበት በሽታ ይቀየራል፡፡

ሕክምናውስ? 
ለድንገተኛ የጉበት መቆጣት ምንም የሚሰጠው መድኃኒት የለም፡፡ ህመምተኛውም ከፍተኛ ካሎሪ ያላቸው ምግቦችን እንዲመገብና መልቲ ቫይታሚኖችን በመጠቀም ከበሽታው ለማገግም ይችላል፡፡ ሄፖታይተስ ቢ ኢንፌክሽን ህክምና አለው። የህክምናውም ዓላማ በደም ውስጥ ያለውን ቫይረስ እስከመጨረሻ ለመቀነስ ወይም ለማጥፋት እና የጉበት በሽታ እንዳይከሰት ወይም እንዳይባባስ ለማድረግ ነው። ህክምናው ለሁሉም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ሰዎች አይሰጥም። ህክምናውን ለመውሰድ የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ። መስፈርቶቹን የሚያሟሉት ብቻ ናቸው መድኃኒቱን የሚጀምሩት። መድኃኒቱ ከመጀመሩ በፊት በደም ውስጥ ያለው የቫይረሱ መጠንና የቫይረሱ ዝርያ (ጂኖታይፕ) በምርመራ መታወቅ አለበት። ይህ የደም ናሙና ወደ ውጭ ተልኮ የሚሠራ ምርመራ ነው። ወደ ህክምናው ስንመጣ ዋናው ለቫይረሱ የሚሰጠው ህክምና «ኢንተርፌሮን አልፋ» በመባል ይታወቃል። ይህ መድሀኒት በሳምንት 3 ጊዜ ለአራት ወራት በመርፌ መልክ የሚሰጥና እጅግ በጣም ውድ የሆነ ሀገራችን ውስጥ የማይገኝ መድኃኒት ነው። ሙሉ የ4 ወር ህክምናው እስከ 300,000 ብር ይፈጃል። ህክምናው በአብዛኛው ጊዜ ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ከሰውነት ውስጥ ባያጠፋውም በማያገረሽ መልኩ እስከመጨረሻ አዳክሞት ምንም ዓይነት የጉበት በሽታ እንዳይከሰት ያደርጋል።

ሌላው መድኃኒት ለፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና የም ንጠቀምባቸው መድኃኒቶች አንዱ የሆነው «ላሚቩዲን» የተባለ መድኃኒት ነው። ነገር ግን ከእዚህ መድኃኒት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ይህ መድኃኒት ከአንድ ዓመት በላይ ሲሰጥ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መድኃኒቱን ይለማመድና መራባቱን ሊቀጥል ይችላል። ይህ ሁኔታ ቢከሰትም አንዳንድ የህክምና ኤክስፐርቶች ህክምናው ሳይቋርጥ መስጠትን ይመከራሉ። ምክንያቱም መድሀኒቱን ተለማምዶ የሚፈጠረው ቫይረስ የመራባት አቅም የሌለው የከፋ ጉዳት የማያስከትል ደካማ ቫይረስ ስለሚሆን ነው።
ሌላው ከላሚቩዲን ጋር የተያያዘው ችግር ለሄፖታይተስ ቢ ህክምና ተብሎ በ100ሚሊ.ግራም የተዘጋጀ እንክብል በሀገሪቱ ገበያ ላይ ያለመኖር ጉዳይ ነው። ላሚቩዲን ለሄፖታይተስ ቢ ህክምና የሚሰጠው በቀን 100 ሚ.ግ ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ነው። በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በሀገሪቱ ደረጃ የሄፖታይተስ ቢ ህክምና አስቸጋሪና ውስብስብ ያደረጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም የመድሀኒቱ ውድነትና የአቅርቦት ችግር እንዲሁም የተሟላ ምርመራ በሀገሪቱ የለም።በሽታውን እንዴት መከላከል ይቻላል?

በሽታውን በሁለት ዓይነት መንገድ መከላከል ይቻላል። የመጀመሪያው የተፈጥሮ መከላከያ ሲሆን፤ በሽታው ሲከሰት ሰውነታችን የተፈጥሮ መከላከያ በማመንጨት ራሱን የሚያድንበት ነው፡፡ በእዚህ ዓይነት መንገድ የዳኑ ሰዎች ቫይረሱ ከሰውነታቸው ከጠፋ በድጋሚ ለበሽታው አይጋለጡም፡፡ አርቴፊሻሉ መከላከያ ደግሞ በክትባት መልክ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም «ፓሲቭ» እና «አክቲቭ» ተብለው ይጠራሉ፡፡ የፓሲቭ ህክምና ፀረ ህዋሱ በአንቲ ቦዲ መልክ ተዘጋጅቶ ይሰጣል፡፡ አክቲቩ ደግሞ ክትባቱን ከተከተበ በኋላ በደም ውስጥ አንቲ ቦዲ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

በሀገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታው በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

በዓለም ላይ ከሦስት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ቫይረሱ ያለበት እንደሆነ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በየዓመቱ ሃምሳ ሚሊዮን አዳዲስ ሕመምተኞች ይጠቃሉ፡፡ በየዓመቱ አምስት መቶ ሺ ገደማ ሰዎች ከሄፖታይተስ ቢ ጋር በተያያዘ ይሞታሉ፡፡ በሽታው በከፍተኛ ደረጃ በኤስያ እና ከሳህራ በታች ባሉ ሀገራት የሚታይ ነው፡፡ የበሽታው ስርጭት ከአምስት እስከ ሃያ በመቶ ሲሆን፤ የበሽታው ዝቅተኛ ስርጭት ደግሞ በአሜሪካንና በምዕራብ አውሮፓ ሲሆን፤ የበሽታ ስርጭቱ ከዜሮ ነጥብ አንድ እስከ ዜሮ ነጥብ አምስት ይደርሳል፡፡ በኢትዮጵያ በተደረገ ቆየት ባለ ጥናት የበሽታው ስርጭት ከስምንት እስከ አስራሁለት በመቶ ነው፡፡ በበሽታው ከእዚህ በፊት ተይዘው የዳኑ ሰዎች በአንድ ወቅት ቫይረሱ እንደያዛቸው የሚያሳይ ምልክት የተገኘባቸው ደግሞ ሰባ ከመቶ እንደሚደርሱ በጥናቱ ታይቷል፡፡

ሄፖታይተስ ቢ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው፡፡ ከኤች አይቪ ጋር ሲወዳደር ሃምሳ ከመቶ በላይ እጥፍ ነው፡፡ በኤች አይቪ በተበከለ መርፌ አንድ ሰው ቢወጋ በቫይረሱ የመያዝ ዕድሉ ዜሮ ነጥብ ሦስት ከመቶ ሲሆን ፤ በሄፖታይተስ ቢ ከሆነ ግን ከስድስት እስከ ሠላሳ ከመቶ ይደርሳል፡፡

የበሽታው ተጋላጮች የትኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው?

ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ያልተከተቡ ሕፃናት በሽታውን ለመከላከል የተዘጋጀውን ክትባት መከተብ ይኖርባቸዋል። ክትባቱ በሦስት ዙር ማለትም የመጀመሪያ፣ ከወር በኋላ እና ከስድስት ወር በኋላ የሚሰጥ ሲሆን፤ እስከ አሥር ዓመት ድረስ የመቆየት አቅም አለው፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከበርካታ ሰዎች ጋር ልቅ የፆታ ግንኙነት የሚያደርጉ፣በጣም የታመመ የቤተሰብ አባል ያላቸው ቤተሰቦች፣ ቫይረሱ ያለበት የትዳር አጋር ያለው ሰው፣የጤና ባለሞያዎች፣ በጤና ችግር ምክንያት በተደጋጋሚ ደም የሚለገሳቸው ህሙማን ናቸው።

ምን ይመክራሉ? 

እኔ የምመክረው ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ያለበት አንድ ሰው ስለመድኃኒቱ ከመጨነቅ ይልቅ ጉብቱ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች ራሱን እየጠበቀ (እንደ አልኮል ያለ፣ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰድ መድኃኒት፣ ያበሻ መድሀኒት) በተወሰነ ጊዜ ርቀት ቋሚ የህክምና ክትትል ቢያደርግ በቂ ነው እላለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.