A-mother-and-child-sit-un-007የወባ በሽታ በአፍሪካ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ በሽታዎች ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። በተለይ ሕፃናት እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ደግሞ የበሽታው ዋነኛ ተጋላጮች ናቸው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአፍሪካ በወባ በሽታ ከሚሞቱት 90 ከመቶ ያህሉን የሚሸፍኑት ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው።በ45 ደቂቃ ውስጥ አንድ ሕጻን በወባ በሽታ ምክንያት እንደሚሞትም ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የዚህ ሁሉ መነሻ ምክንያት ደግሞ ሕጻናት በሽታውን የመቋቋም አቅማቸው ውስን ስለሆነ ነው።

ከሕፃናት በመቀጠል የወባ በሽታ ተጋላጮች ነፍሰ ጡር ሴቶች ናቸው።ነፍሰ ጡር ሴቶች ከሌሎች አዋቂ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ በበሽታው የመያዝ እድላቸው በአራት እጥፍ ይጨምራል። በበሽታው የመሞት ዕድላቸውም እንዲሁ በሁለት እጅ ይጨምራል፤ ከሌሎች አዋቂ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ማለት ነው። የዚህ መነሻም በእርግዝና ወቅት ከለው የኦስትሮጂንና ከርቲሶል የተባሉ ሆርሞኖች መጠን መጨመር ጋር እንደሚያያዝ መረጃዎች ያሳያሉ።

የወባ ነገር ከተነሳ በሽታው በአገራችንም ከአመታት በፊት ወነኛ ገዳይ በሽታ ነበር። ከገዳይነቱ በተጨማሪ በበሽታው ወረርሽኝ ምክንያት ብዙዎች የአልጋ ቁራኛ በመሆን ምርታማነታቸው እንዲቀንስ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎአቸው እንዲዳከም ምክንያት ነበር፤የወባ በሽታ።ይህ ደግሞ የሰዎችን የዕለት ገቢ ከመቀነስ በተጨማሪ በአገርም ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ነበረው።
መንግስት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሰጠው ትኩረት ዛሬ የወባ በሽታ ገዳይነቱ ቀንሷል።በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተም አመታት ተቆጥረዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ እንደሚያስረዱት ወባን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እና መንግሥት የተለያዩ የወባ መከላከያ ግብአቶችን በመጠቀሙ ላለፉት ሰባት ዓመታት የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ አልተከሰተም።

”በወባ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ቀንሷል።በበሽታው ለሞት የሚዳረጉ ሕሙማን ቁጥርም 55 በመቶ ቀንሷል።” ያሉት አቶ አህመድ የወባ በሽታ በኢትዮጵያ ለሕመም፣ ለስቃይና ለሞት ከሚዳርጉ አስር በሽታዎች መካከል የአንደኝነት ደረጃ ይዞ መቆየቱን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ወደ ስድስተኛ ደረጃ መውረዱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ለሕመምና ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች ውስጥ በያዘው ደረጃ ከአንድ ወደ ስድስት የወረደው በዘርፉ በመንግስትና በባለድርሻ አካላት በተደረገ ርብርብ ነው።በተለይ በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ  የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካይነት ብዙ ሥራ ተሰርቷል።

አቶ አህመድ እንደሚያስረዱት 38 ሺ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ቤት ለቤት በማሰማራት፤ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ሥራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ ሆነዋል።

እንዚህ ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡና ተደራሽነታቸውን ለመሳደግም በመላ አገሪቱ ከ14 ሺ800 በላይ የጤና ኬላዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።ይህም ባለሙያዎቹ በቀላሉ ወደ ህብረተሰቡ ዘልቀው እንዲያስተምሩና ሕብረተሰቡም የጤና አገልግሎቱን በአቅራቢያው እንዲያገኝ አድርጓል።

የወባ በሽታን ስርጭት ለመቀነስና ለመከላከል ብዙ አማራጮች አሉ። የወባ ትንኞች እንዳይናደፉ የሚከላከል መድሃኒት የተነከረ አጎበር መጠቀም፣ የወባ መራቢያ አከባቢዎችን ማጥፋት፣የፀረ-ወባ መድሃኒት ርጭት እና የወባ ክትባት ከመከላከያ ስልቶቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

በየዓመቱ ሚያዚያ 17 ቀን የሚከበረውን የዓለም የወባ ቀን ምክንያት በማድረግ አቶ አህመድ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ በወባማ አካባቢ ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች መካከል 78 ከመቶ በላይ ቤቶች የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ተረጭተዋል። በቀጣዩ አምስት ዓመታት ሽፋኑን ወደ 98 ከመቶ ለማድረስም እየተሰራ ነው።

የወባ በሽታን ለመቆጣጠር ለበሽታው በተጋለጡ አካባቢዎች ለሚኖሩ ቤተሰቦች ከ43 ሚሊዮን በላይ አጎበር የተሰራጨ ሲሆን፤ በሕብረተሰብ ተሣትፎ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ የማዳፈንና የማፅዳት ሥራም ተሰርቷል።

አቶ አህመድ እንደሚናገሩት የምርምር ቁሳቁሶችም በከፍተኛ መጠን እስከ ጤና ኬላ እንዲደርሱ ተደርጓል። የታመሙትን ለማከም ኮአርተም መድኃኒት በበቂ ሁኔታ ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

የዓለም የወባ ቀን በዓለም ለ12ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ «በወባ ላይ የድርሻን በመወጣት ሕይወትን ለማዳን እንረባረብ፤ የተገኙ ውጤቶችን እናስቀጥል» በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።የጉባዔውም ዋና ዓላማም ወባን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ በአገሪቱ የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም የወደፊት አቅጣጫን ለማስቀመጥ ነው።

አቶ አህመድም በወባ መከላከልና ቁጥጥር ዙሪያ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው፣ ሕብረተሰቡም በአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በመሳተፍ አጎበርን በትክክል ሰቅሎ በመጠቀም እንዲሁም ቤቶችን ኬሚካል በማስረጨት ወባን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ የነቃ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የወባ በሽታ በቀላሉ ልንከላከለው የምንችለው ግን ደግሞ የወባ መራቢያ አካባቢዎችን ባለማፅዳት፣የወባ መከላከያ ዛንዚራዎችን በአግባቡ ባለመጠቀምና አካባቢን የፀረ-ወባ መድሃኒት ባለማስረጨት ለሕመምና ለአደጋ የሚዳርግ በሽታ ነው።

ሕብረተሰቡ ስለበሽታው መተላለፊያ መንገዶች ከተረዳ የመከላከሉ ሥራም የዛኑ ያህል ቀላል ይሆናል።ሕብረተሰቡን በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ መንግስት በሽታውን ለማጥፋት የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ ደግሞ የሁሉም ትኩረት እና ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.