በፎዚያ ሙህሲን (የምግብ ኢንጅነሪንግ ባለሙያ)

ቆዳችን ያለንበትን የጤና ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መግለፅ የሚችል የአካላችን ክፍል ነው፡፡ ጤናማ ቆዳ በተፈጥሮው በጣም ለስላሳ፣ የሚያበራ(Glow)፣ በሁሉም ቦታ እኩል የውጥረት (Tone) ደረጃ ያለው፣ ከምንም አይነት ሽፍታና የቆዳ እክሎች የጠራ ሆኖ እናያለን፡፡ የተቆጣ ቆዳ በተለይም ፊታችንና እጅ የመሳሰሉት ላይ ሲታይ በጣም ያስጨንቃል ይረብሻል፡፡

      ግን ለምንድን ነው ቆዳ የሚታመመው? ባሉት መረጃዎች መሰረት ይህ ነው የሚባል አንድ መልስ የለም፡፡ ነገር ግን ለቆዳ መቆጣትና ለተለያዩ የቆዳ ችግሮች እንደ መንስኤ ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኛው ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ የሚፈጥሩት ጫናና አካላዊ ውጥረት ቅድሚያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአካባቢ ብክለት በስራዎቻችንና በኑሮአችን ምክንያት የሚፈጠር ውጥረት፤ በምግቦቻችን፣ የመዋቢያና የመፀዳጃ ዕቃዎች ውስጥ የሚገቡት ከጤና አኳያ አላስፈላጊ ኬሚካሎች ወዘተ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ስር የሰደዱ የጤና ችግሮች ካሉ ተደራርቦ የዚህ ሁሉ ጫና ውጤት በቆዳችን ላይ ይንፀባረቃል፡፡

የቆዳችን አገልግሎት

ቆዳን በሰውነታችን ውስጥ ከሚገኙ ክፍሎች እጅግ በጣም ትልቁ ሲሆን በአማካይ ወደ 2.7 ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡ ቆዳችን ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. የመከላከል ስራ (Protection)

 

የመጀመሪያው የቆዳችን ስራ የተለያዩ የአካላችን ክፍሎችን ከውጫዊ  ዓለም ጥቃት መከላለከል ነው፡፡ ቆዳን ሙሉ ለሙሉ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓት (Immune System) ዋና ክፍል ነው፡፡ ቆዳችን በሚገርም ሁኔታ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ በአይን በማይታዩ ባክቴሪያዎች የተሸፈነ ነው፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች በቆዳችን ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳያስከትሉ በሰላም በቆዳችን ላይ ይኖራሉ፡፡ ሌሎች የመከላከል ሥራ አካል የሆኑት ደግሞ በቆዳ ህዋሶች መካከል ተቀብረው አካላችንን የሚጎዱ ህዋሳቶች ሲመጡ ለበሽታ መከላከል ስርዓት መረጃ የሚያቀብሉ ላንገርሃንስ (Langerhans) የሚባሉ የህዋስ አይነቶች አሉት፡፡ በነዚህ ሕዋሶች በመታገዝ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓት አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል፡፡

 

  1. የሰውነት ሙቀት መቆጣጠር

 

ሌላው የቆዳችን ስራና ችሎታ ደግሞ የሰውነትን ሙቀት መቆጣጠር ሲሆን የአካባቢያችን ሙቀት በጣም በትንሹ ቢቀየር በቀላላ መለየት ይችላል፡፡ ታዲያ የአካባቢያችንን የሙቀት መጠን መረጃ ለአዕምሮአችን በመላክ የሰውነት የሙቀት ደረጃ እንዲስተካከል ያደርጋል፡፡

 

በቅዝቃዜ ወቅት ዐዕምሯችን ለቆዳችን ትዕዛዝ በማስተላለፍ በቆዳችን ስር ያሉ የደም ስሮች እንዲጠቡ በማድረግ ከላይኛው የቆዳ ክፍል ርቀው ወደ ታች ዝቅ በማለት ሙቀት ከሰውነታን እንዳይባክን ከማድረግ በተጨማሪ ቅዝቃዜው ሲበረታ ደግሞ ጡንቻዎቻችን እንዲንቀጠቀጡ በማድረግ ሰውነታችን ራሱ ሙቀት እንዲያመነጭ ያደርጋል፡፡

 

በሙቀት ጊዜ ደግሞ በተቃራኒው ለቆዳችን መልዕክት በመላክ ቀጫጭን የደም ስሮቻችን እንዲሰፉ በማድረግ ከልክ ያለፈ ሙቀት በቆዳችን አማካኝነት እንዲወገድ ከማድረግ በተጨማሪ የላብ አመንጪ እጢዎች ላብ እንዲያመነጩ በማድረግ ሠውነት እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል፡፡

 

  1. እንደ ስሜት ህዋስ ያገለግላል

 

በቆዳችን ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነርቮች ሲኖሩ በዋናነት አራት ነገሮችን እንድንለይ ያደርጋሉ፡፡ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ፣ ንክኪና ህመምን፡፡ በንክኪ ብቻ ሸካራ፣ ለስላሳን፣ ግፊትን የመሳሰሉ የተለያ ንክኪዎችን የሚለዩ የነርቭ ህዋሶች አሉ፡፡

 

  1. ቫይታሚን ዲ ማምረት

ሌላው አስደናቂ የቆዳችን ስራ ፀሃይ ስንሞቅ ሙቀቱን ተጠቅሞ ቫይታሚን ዲ ማምረት ነው፡፡ ይህንን የሚሰራው ጠቃሚ ኮሌስትሮልን ወደ ቫይታሚን ዲ 3 በመቀየር ከዚያም በጉበትና ኩላሊት እገዛ አማካኝነት ዲ 3 ወደ አክቲቭ ወደሆነው ስሪቱ እንዲቀየር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የቆዳዎትን ጤንነት አመጋገብዎን በማስተካከል ይጠብቁ፡፡

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.