በ  መስከረም አያሌው

Lifeዓለም ወባ ቀን ለ6ኛ ጊዜ ባለፈው አርብ ተከብሯል። ይህ ቀን ሲከበር የወባ በሽታን ከመቆጣጠር እስከ ማጥፋት በሚለው የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ መሰረት ነው። ልክ እንደሌሎቹ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ሁሉ በ2015 ሀገራት ወባን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠሩ ከቻሉም እንደሚያስወግዱ ነው የተቀመጠው ግብ የሚያመለክተው።

በወባ በሽታ ምክንያት በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ህይወቱ የሚያልፍ ሲሆን፤ ቀሪ በርካታ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰለባዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን የወባ ቀኑን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ይህን እውነታ ለመቀልበስ መንግስታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል።

በእርግጥ መንግስታት ባደረጉት ጥረት በ2008 በወባ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ የነበሩ ህጻናት ቁጥር ከነበረበት 1 ሚሊዮነ ወደ 500ሺ ቀንሷል። ይህም ሊሆን የቻለው 44 ሚሊዮን የአልጋ አጎበሮችን በመጠቀም መሆኑ ተገልጿል።

የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የአለም ኢንቨስትመንት መስፋፋት በመኖሩ በወባ ምክንያት ይጠፋ የነበረን 3.3 ሚሊዮን ህይወትን በ14 ዓመታት ውስጥ ለማዳን እንደተቻለ ነው የአለም ጤና ድርጅት የገለፀው። በድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ማርጋሬት ቻን እንደገለፁትም፣ የወባ በሽታ ወረርሽኝ የሆነባቸው ሀገራትም ይህን ውጤታማነት መገንባት አለባቸው።

ከ2000 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወባ ምክንያት ይመዘገብ የነበረውን የሟቾች ቁጥር 42 በመቶ መቀነስ ተችሏል። በአፍሪካ ደግሞ 43 በመቶ። ይህ የተመዘገበ ውጤትም በከፍተኛ ደረጃ የተጠቂነት ታሪክ ያላቸው ሀገራት ሳይቀሩ በሽታውን ለማጥፋት ጥረት እንዲያደርጉ መንገድ ከፍቶላቸዋል።

እንደ የአለም ጤና ድርጅት ገለፃ ምንም እንኳን በርካታ ሀገራት የወባ በሽታን ለማጥፋት የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን ቢያሳዩም ፣ የቴክኒክና የገንዘብ እንቅፋቶች ግን ግባቸውን እንዳይመቱ አድርጓቸዋል። እነዚህን እንቅፋቶች አልፈው የወባ በሽታን ለማጥፋት የተቃረቡ 19 ሀገራትም በድርጅቱ ተለይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሰባት ተጨማሪ ሀገራት ወባን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የተቃረቡ ተብለው ተቀምጠዋል። ከአምስት ዓመት ወዲህ ደግሞ አራት ሀገራት የወባ በሽታ ያልታየባቸው ሆነው ተገኝተዋል። እነዚህ ሀገራትም የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ሞሮኮ፣ ተርክሜኒስታን እንዲሁም አርሜኒያ ናቸው። በ2012 በወጣ ሪፖርትም 52 ሀገራት የወባ ስርጭን እስከ 2015 (እ.ኤ.አ) 75 በመቶ ለመቀነስ አቅደዋል ሲል ያስቀምጣል ።

በ2012 (እ.ኤ.አ) በአለማችን ላይ 207 ሚሊየን የወባ ኬዞች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን፤ በዚህም ሳቢያ 627ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥም 200 ሚሊዮን የሚሆኑት በየአመቱ የተከሰቱ እና ምርመራ ሳያደርጉ ህይወታቸው ያለፉ ናቸው። በእነዚህ ኬዞች 97 ሀገራት ተጠቂዎች የነበሩ ሲሆን ከፍተኛው ወረርሽኝ የተመዘገበው ግን ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ናቸው። ይህም ከ473ሺ እስከ 789ሺህ የሚሆኑት የአፍሪካ ህጻናት ህይወታቸውን አጥተዋል።

በአፍሪካ በየደቂቃው አንድ ህፃን በወባ ምክንያት ህይወቱን እንደሚያጣ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይም ሆኖ ግን ይህ የአፍሪካ ህፃናት ሞት ከ2000 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ጀምሮ እስከ 2013 (እ.ኤ.አ) ድረስ በ54 ከመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ግማሽ ያህሉ የአለም ህዝብ የወባ በሽታ ያሰጋዋል ይላል የአለም ጤና ድርጅት ዘገባ። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ከወባ ጋር የተያያዘ ሞት የሚከተለው ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ቢሆንም እስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ አውሮፓም በዚህ ስጋት ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ያለውን የወባ ስርጭት ሁኔታ ስንመለከት ከኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት 75 በመቶው ለወባ ተጋላጭ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በእነዚህ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች መካከልም 68 በመቶዎቹ ወባ ያሰጋቸዋል። ይህ ማለት ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስጋት ውስጥ ናቸው። በዚህም መሰረት በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች ከአራት እስከ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በየአመቱ በወባ ይጠቃሉ። በዚህም ሳቢያ ወባ በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ ህመም እና ሞት ከሚያስከትሉ በሽታዎች ተርታ እንዲመደብ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ለወባ መከሰትም ሆነ ስርጭት ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት የተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸው። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከልም የቤት እና ግድግዳ እንዲሁም የጣሪያ እና ወለል መስሪያዎች አይነት፣ ዋና የመጠጥ ውሃ ምንጮች፣ ውሃ ከመኖሪያ ቤት ላይ ያለው ርቀት፣ የመፀዳጃ ቤቶች አለመመቻቸት እንዲሁም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም ፆታ ፣ እድሜ፣ የቤተሰብ መጠን፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቦታዎች ለወባ ስርጭት ከፍተኛ ሚና አላቸው።

እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የተደረገ ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተውም በሀገራችን ያለው የወባ በሽታ ስርጭት የተለያየ ገጽታ አለው። ለአብነት ያህልም የመኖሪያ ቤት ከሚሰራባቸው ግብዓት አንጻር ከደቡብ እና ኦሮሚያ ክልል ህዝብ ይልቅ የአማራ ክልል ለወባ ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል።

የወባ ስርጭት በተለይ ከሰዎች አኗኗር ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። በ2012 (እ.ኤ.አ) በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው ንፁህ ውሃ በሚጠቀሙ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የወባ በሽታ ስርጭት አነስተኛ ሆኖ የተገኘ ሲሆን፣ መኖሪያቸው የጭቃ እና የሳር ቤት በሆነ ማህበረሰብ ዘንድ ደግሞ ስርጭቱ ከፍተኛ ሆኗል።

Life1ከዚህ በተጨማሪም የማህበረሰቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የወባ ስርጭት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የተለያየ ገፅታ እንዲኖረው ያደርገዋል። በዚህም ሳቢያ ዝቅተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በወባ ለመያዝ ከፍተኛ ቀረቤታ አላቸው። በተለይ ለድህነት ቅርብ የሆኑ ሴቶችና ህጻናት ደግሞ ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰብ አባላት ቁጥር በጨመረ ቁጥር በወባ የሚያዘው ሰው ቁጥር 5.1 በመቶ ይጨምራል፤ እንደ ጥናቱ።

በኢትዮጵያ ከፍታቸው በ1ሺ እስከ 2ሺህ ሜትር በላይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የወባ ስርጭቱ ከፍተኛ የሆነ ሲሆን፤ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የወባ ወረርሽኝ የሚከሰተውም በአመት ሁለት ጊዜ ነው። ይኽውም ከመስከረም ወር እስከ ታህሳስ እንዲሁም ከሚያዝያ እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ነው። ይህ ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ የግብርና ስራ የሚከናወንበት ወቅት በመሆኑ በርካቶች በበሽታው ተይዘው ቤት ውስጥ ስለሚቀሩ በስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል። ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በአጠቃላይ ተፅዕኖው የከፋ እንደሆነ ተቀምጧል። ምንም እንኳን የወባ ወረርሽኙ የሚከሰተው ከአምስት እስከ ስምንት ዓመታት ባሉት ጊዜ ውስጥ ቢሆንም ጉዳቱ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህም ሳቢያ የወባ በሽታ የድህነት በሽታ ተብሏል።

በኢትዮጵያ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም እንደመፍትሄ የተቀመጠ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የአልጋ አጎበር መጠቀም፣ የፀረ-ወባ መድሃኒት ርጭት፣ አካባቢን ማፅዳት እና የመሳሰሉት ናቸው። በዚህም የአልጋ አጎበር የሚጠቀሙ ሰዎች ከማይጠቀሙት በ54 በመቶ ለወባ ተጋላጭነታቸው ቀንሶ ተገኝቷል።

በፆታ ረገድ ስንመለከትም ከጭቃ እና ከእንጨት በተሰሩ ቤቶች ውስጥ ከሚኖሩ ወንዶች ይልቅ ሴቶቹ የበለጠ ተጋላጮች ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ በወባ የመያዝ ደግግሞሽ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ ከፍተኛ ሆኗል።

     በአጠቃላይ የወባ በሽታ በቀላሉ በማህበረሰብ ርብርብ ሊገታ የሚችል በሽታ ቢሆንም በርካታ ሀገራት ግን ከችግሩ ጋር እየኖሩ እንደሆነ የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ገልጿል። በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ የመጀመሪያዎቹ የገፈቱ ቀማሾች ናቸው። በአሁኑ ወቅት በወባ ምክንያት የሚሞቱ የአፍሪካ ህጻናትን ቁጥር በግማሽ መቀነስ ቢቻልም፤ አዳዲስ ችግሮች እንዳይቀሰቀሱ መንግስታት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ድርጅቱ አሳስቧል። በወባ ምክንያት በሚከሰተው ችግርም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ከግለሰብ አልፎ እስከ ሀገር የሚደርስ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያስከትላል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.