በቁምላቸው አባተ (ሜ. ዶክተር)

ሕሙማን ለሚያገኙት የህክምና አገልግሎት የሚወሰዱ ርምጃዎች ክብደት በውሳኔው ላይ መከተል የሚገባንን ጥንቃቄ ያንፀባርቃሉ፡፡ ውስብስብ የምርመራ ድርሻ፣ ያልተረጋገጠ የመድሃኒት አመራረጥ፣ ለማስታረቅ የሚከብድ የህሙማን ምርጫ፣ ከማህበረሰብ እሴትና ከመክፈል አንፃር ሲታይ ደግሞ ውሳኔ አሰጣጡ የማያጠራጥር፣ ክብደቱ የማያጠራጥር መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ለመሆኑ የማከም ውሳኔ ተግባር እንዴት ይገለፃል? ሂደቱንስ ማሻሻል ይቻላል? ‹‹የማያጠራጥር›› ውሳኔ ለመስጠት አማራጭ መንገድ አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

Kas21 ከጥቂት አመታት በፊት በጣት የሚቆጠሩ ምርመራዎችና የማያሻማ የመድሃኒት ምርጫ ይሰጥ የነበረ ህክምና አጠራጣሪ አልነበረም፡፡ ዛሬ ዛሬ ህመሞችን ለመረዳት የሚያስችሉ ግብዓቶች ብርካቴ ለግንዛቤ ስፋቱ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ ለህክምና አሰጣጡ አማራጭ መንገዶች አያሌነትና ለውሳኔው ውስብስብነት የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡

አዳዲስ የህክምና አማራጮች የብዙ ህመሞችን መጨረሻ ያሻሻሉበት ሁኔታ ብሎም የጠፋበት አጋጣሚ እንዳለ ሆኖ በቁጥር ጥቂት የማይባሉ ሕመሞች የሰው ልጅ እድሜውን ሙሉ አብሯቸው ኖሮ በወጉ ያልተረዳቸው፣ ተረድቷቸው ማሻሻል እንጅ ማዳን ያልቻላቸው እንዲሁም መከላልና መቆጣጠር የሚችላቸው ህመሞች መሃል ላይ ለሚገኘው ባለሙያ የህመም ቁጥር መብዛት፣ ወጥ ያልሆኑ የህክምና አማራጮች መጨመር ለህክምና አሰጣጡ የሚሰጠውን ውሳኔ አወሳስቦታል፡፡

እርግጠኛ የማንሆንባቸው ሁኔታዎች በመብዛታቸው በምርመራው ሂደት እጃችን ላይ ባሉ የምርመራ መንገዶች ትክክለኛነት፤ በበሽታው የተፈጥሮ አወራረድ፤ ህክምናው በህመሙ ላይ የሚያሳድረው ለውጥ፤ በማህበረሰብ ላይ ከሚያስከትለው አጠቃላይ ውጤት በመነሳት የውሳኔ አሰጣጡን ውስብስብነት መረዳት ይቻላል፡፡ ለውሳኔው የሚስፈልጉ ግብዓቶችን አወዳድሮ ለመምረጥ ቀርቶ ለመረዳትም ከብዷል፡፡ የሆነው ሆኖ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ውሳኔ የተሻሉ የጥናት ውጤቶችንና የተግባር ልምዶችን ያማክላል፡፡

ውሳኔ 1፡- የመረጃ ምንጮች

ብዙ ሐኪሞች በትምህርታቸውና በልምዳቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ትምህርት በስልጠና ብሎም ከሌላ የሙያ አጋሮቻቸው የቀሰሙት ሊሆን ይችላል፡፡ ልምዱን በተመለከተ ተመሳሳይ ህመም የነበራቸው ህሙማንን ከመርዳት፣ ከመመርመርና ከማከም ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ የተሻሉ መረጃዎችን ወይም አዳዲስ የጥናት ውጤቶችን ለመጠቀም የሕክምና መፃህፍትን፤ የሙያ አጋሮችን በመጠየቅና ሌሎችን የመረጃ ምንጮችን በማመሳከር ክህሎታቸውን ያዳብራሉ፡፡ የጤና መረጃን ለሚፈልጉ ሰዎች ዘመኑ የራሱን አስተፅኦ አበርክቷል፡፡ ከነዚህ መካከል የህትመት ውጤቶችና የኢንተርኔት መረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ለመሰረታዊ የህክምና ምንጭነት ግን የህክምና ባለሞያን መጠቀም አሻሚ አይደለም፡፡ ልዩ ልዩ የጥናት ውጤቶች የተለያየ አይነት የውሳኔ መነሻዎችን ያቀርባሉ፡፡ ህመሞችን ለመረዳት የምርመራ ብቃት ምን ያህል ነው፤ የህመሞች መነሻ ምክንያት ምንድን ነው፤ ሕመሞች በጊዜ ብዛት ምን ያስከትላሉ…የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ይመልሳሉ፡፡

ውሳኔ 2፡- ምርመራ

የህክምና ምርመራ ህመም መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ፤ ህመምን ለማወቅ፤ ደረጃውን ወይም ሥር የመስደድ ልኩን ለመለካት አለበለዚያም ለመከፋፈል እንዲሁም ለሕክምና የሚሰጠውን ምላሽ ለመረዳት ይጠቅማል፡፡

ህመም መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚረዱ ምርመራዎች የሚጠቅሙ አንድ ሰው ህመሙ እንዳለበት ጨርሶውኑ አመላካች ነገር ሳይኖር ነው፡፡ ለምሳሌ አንዲት የ40 ዓመት በላይ የሆነች ሴት በየሁለት ዓመቱ የጡት ራጅ መነሳት አለባት፡፡ የጡት እባጭ ቢኖርም ባይኖርም ማለት ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ምርመራ ህመሞች ቀድመው ከታወቁ ብዙ ሳይደራጁ ሊታከሙ ስለሚችሉ የመሻል እድላቸው የተሻለ ይሆናል በሚለው ሃሳብ ላይ ያጠነጥናል፡፡

ህመምን ለማወቅ የሚጠቅሙ ምርመራዎች ባለሞያው ህመሙ መኖሩን ሲጠረጥር የሚታዘዙ ናቸው፡፡ የሚያስከትሉት ወጭም ይሁን ከምርመራው ጋር የተያያዙ ችግሮች ሕመሙን ከማወቅ ጥቅም ጋር ተመዛዝነው ይታያሉ፡፡

ለውስንንና ውጤታማ የህክምና ርምጃ የህመምን የስርጭት ደረጃ ለማወቅ ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የጉበት ካንሰር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ወደየትኛው የሰውነት ክፍል እንደተሰራጨ ተጨማሪ ምርመራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የህመሙን ለውጥ ለመረዳት ምርመራዎች ይካሄዳሉ፡፡ ምንም እንኳ ለብዙ ሰዎች ምርመራ ማድረግ የህሊና እርካታን የሚሰጥ ቢሆንም ሁሉም ምርመራ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡

የህክምና ባለሙያው ምርመራ ከማዘዙ በፊት ቢያንስ ሶስት ነገሮችን ማሰላሰሉ አይቀርም፡-

  1. ምርመራ ስላዘዘለት በሽታ
  2. ስላዘዘው ምርመራና
  3. ምርመራ ስላዘዘለት ህመም ናቸው፡፡ ከነዚህ ባሻገር ህመሙ እስካለ ድረስ ምርመራው ተመሳሳይ ውጤት ማመልከቱን መገንዘብ፣ ምርመራው በመካሄዱ የሚደርሰውን ጉዳት መረጃው ከሚያበረክተው ጥቅም አኳያ ማስተዋል፣ የምርመራ ውጤቱን በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀት . . . ወዘተ ከባለሙያው ይጠበቃል፡፡ የሚሰጠው ህክምና ላይ አንዳችም ለውጥ የማያመጣ ከሆነ ምርመራ ጨርሶውኑ አያስፈልግም፡፡

ውሳኔ 3. ህክምና፡-

በባለሙያ አለ ተብሎ ለታሰበው ህመም አስፈላጊውን የህክምና ምክር ከመለገስ በፊት ህክምናው ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ከጥቅሙ ጋር ይመዛዘነናል፡፡ ጥቅም ሲባል ስቃዩን በመቀነስ ምልክቶችን ማሻሻል፣ አቅምን ማጎልበት፣ ሙሉ በሙሉ ማዳን ወይም ህመሙን ተከትሎ የሚከሰት ችግርን መቀነስ ሊሆን ይችላል፡፡ የጥናት ውጤቶች የጥቅምና የጉዳትን ነገር በአማካይ ቀመር አይተነትኑም፡፡ አማካይ ቁጥሮች/እድሎች ደግሞ አንድ ግለሰብ ለተሰጠው ህክምና የሚኖረውን ምላሽ ሲያንፀባርቅ (ከግምት አድማስ ውስጥ ሊያስገባ) አይችልም፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ሳይንሳዊ ጥናቶች በተሰጠው ህክምና ተጠቃሚ ወይም ተጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ምን አይነት ባህሪ፣ እድሜ፣ ጾታ፣ የህመም አይነት ወዘተ. . . እንዳላቸው ጥቆማ ያደርጋሉ፡፡

ውሳኔ 4 ተሳትፎ፡-

በህክምና አሰጣጡ የውሳኔ ሂደት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመሳተፍ ሰዎች ከባለሙያው ጋር አብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምርመራም ይሁን የህክምና ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ተጨማሪ መረጃ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ መረጃዎችን ከተለያዩ ምንጮች (ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ብሮሸሮች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ መፅሃፍትና ጋዜጣን ጨምሮ ሌሎች የህትመት ውጤቶችና ድረ-ገፆች. . . ወዘተ) ማግኘት ይቻላል፡፡ ‹‹መረጃ ሁሉ ጥሩ መረጃ›› ላይሆን ስለሚችል በጥንቃቄ ማንበብና ማገናዘብ ይሻል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተጨማሪ አማራጮች ካሉም ባለሙያ ማዋየቱ ለውሳኔው ጥንካሬ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

ውሳኔ 5 እውነታታዎች፡-

ለምርመራም ይሁን ለህክምና ውሳኔ ሁለት አይነተኛ ስራዎችን መከወን ያሻል፡፡ የመጀመርያው ትክክለኛውን የመረጃ ምንጭ መምረጥ ሲሆን፣ ቀጣዩ ደግሞ በተረዱት (በቀሰሙት) መረጃ ታማሚውን እንደምን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ መገንዘብ ነው፡፡ ይሄን ወደ ተግባር መለወጥ ብዙ ውጣ ውረድ ይኖረዋል፡፡ አንደኛው ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ውሳኔዎች በፍጥነት መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ባለሙያው ያሉትን መረጃዎች ሁሉ ለመሰብሰብና አገናዝቦ ጥሩ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ጊዜ አይኖረውም፡፡ ከዚህ ባሻገር የመረጃው የጥራት ደረጃ መታወስ ይኖርበታል፡፡ ከመፅሃፍትና ከኢንተርኔት የተነበበ ሁሉ ትክክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ትክክለኛ መረጃ ሆኖም ለተወሰኑ ህሙማን የሚሆን ለሌሎች ደግሞ የማይሆኑ ይሆናሉ፡፡

ብዙውን ጊዜ አንድ ህመም በሚያስከትለው አደጋና ህክምናው በሚያደርሰው ጫና መሃል ያለው ሚዛን ግልፅ አይደለም፡፡ ባለሙያውና ታካሚው ስለጉዳትና ጥቅም ያላቸው አመለካከት የተለያየ ይሆናል፡፡ ይሄን የአመለካከት ልዩነት የመፍታት ኃላፊነት ደግሞ የሁለቱ በመሆኑ መወያየት አስፈላጊ ነው፡፡ ጉዳትን በወጉ መረዳት አማራጮችን ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ ባለሙያው ይጠቅማሉ ያላቸውን ዘዴዎች ዘርዝሮ ታካሚው በውሳኔው ላይ የበኩሉን እንዲያበረክት ያደርጋል፡፡

ጥቅምና ጉዳትን በማመዛዘን ካሉት ምርጫዎች እንዲሁም ከግል ልምድና እሴት አንፃር በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ላይ መድረስ የውጤታማ ህክምና አገልግሎት መሰረት ነው፡፡

መልካም የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.