እርግዝና እና የደም ግፊት በሽታ

0
በእርግዝና ወቅት የደም ግፊት በሽታ ሊከሰት ይችላል። ይህንንም በመገንዘብ እናቶች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል።
 
በእርግዝና ወቅት አራት የተለያዩ የደም ግፊት በሽታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህም፦

  • ፕሪኤክላምፕሲያ (preeclampsia)
  • ከእርግዝናም በፊት የነበረ የደም ግፊት በሽታ (Chronic Hypertension)
  • ፕሪኤክላምሲያ የተደረበበት ከእርግዝናም በፊት የነበረ የደም ግፊት በሽታ (Superimposed Preeclampsia)
  • አላፊ የእርግዝና የደም ግፊት በሽታ (Gestational Hypertension or Transient Hypertension)

ከእርግዝና በፊት የነበረ የደም ግፊት በሽታ

Fotolከሌሎቹ አይነት የደም ግፊት በሽታዎች በተለየ ይኼኛው ከእርግዝና በፊት የሚከሰት ሲሆን ከወሊድ በኋላም ይኖራል፡፡ ከወሊድ በፊት ከነበረ፣ በእርግዝና በመጀመሪያዎቹ 20 ሳምንታን የደም ግፊት መጠን ከመጨመረ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ ከ12 ሳምንት በላይ የሚቆይ ከሆነ በዚህ የደም ግፊት በሽታ ምድብ ውስጥ እንመድበዋለን፡፡ የደም የግፊት መጠን ከ140/90 ሚ.ሜ. በላይ ሆኖ ለረዥም ጊዜ ከቆየ የደም ግፊት በሽታ ይባላል፡፡ የደም ግፊት በሽታ ከሌላው ጊዜ በተለየ በእርግዝና ወቅት ልዩ ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡ ይሄ በሽታ በአንቺም ሆነ በልጅሽ ላይ ብዙ አይነት ችግሮችን የማስከተል አቅም ቢኖረውም በህክምና ክትትል እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤሽን በማስተካከል ልትቆጣጠሪው ትችያለሽ፡፡

ከእርግዝና በፊት ያለ የደም ግፊት በፅንሱ እና በእኔ ላይ ምን ጉዳት ሊያመጣ ይችላል?

በማህፀን ውስጥ የልጅ እድገት መጓተትን ያስከትላል፡፡ ክብደቱ ዝቅ ያለ እንዲሁም ዋና ዋና አካላቱ በደንብ ያልዳበረ ልጅ እንዲፈጠር ከማድረግ በተጨማሪ የተለያዩ የአፈጣጠር ችግሮችንም ያስከትላል፡፡ ከጊዜው ቀድሞ ምጥ እንዲጀምር ሊያደርግ እና የእንግዴ ልጅ ከማህፀን ግድግዳ መለያየትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ እንዲሁም ፕሪኢክላምዢያ ያመጣል፡፡

የደም ግፊት በሽታ ተጠቂ ከሆንኩ ከማርገዜ በፊት እና በእርግዝና ጊዜ ማድረግ ያለብኝ ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው?

የታወቀ የደም ግፊት በሽታ ካለብሽ ከማርገዝሽ በፊት በተቻለ አቅም ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይጠበቅብሻል፡፡ መጀመሪያ ለማርገዝ ስታስቢ ከሐኪምሽ ጋር መማከር አለብሽ፡፡ እርግዝና በሰውነትሽ ላይ የሚያመጣው ጫና ከደም ግፊት በሽታሽ ጋር ተደምሮ የተለያዩ የአካል ክፍሎሽ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለዚህም ዶክተርሽ የተለያዩ ምርመራዎችን ሊያዝልሽ ይችላል፡፡ እነዚህም የአይን፣ የደም፣ የሽንት እና የመሳሰሉት የተለያዩ የአካል ክፍሎችሽን ጉዳት የሚያመላክቱ ምርመራዎች ናቸው፡፡ በእርግዝናሽ ጊዜ በጣም ያልተጋነነ የደም ግፊት መጨመር ከታየብሽ (እንደ ሐኪምሽ ትእዛዝ) መድሃኒት መጠቀም አይጠበቅብሽም፡፡ ነገር ግን አልኮል እና ሲጋራ ከመጠቀም ተቆጠቢ፡፡ጨው አለመጠቀም የሚመከር ሲሆን ከፍተኛ የሰውነት እንቅስቃሴ እና የክብደት መቀነስ ሙከራም ማድረግ አይኖርብሽም፡፡ ሀኪምሽ በሚሰጥሽ ቀጠሮዎች ሁሉ ወደህክምና ቦታው በመሄድ የታዘዙልሽን ምርመራዎች ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ የአይን ብዥታ፣ ክብደት በፍጥነት መጨመር፣ የእጅ እና የፊት እብጠት የመሳሰሉ ምልክቶች ከታዩብሽ በፍጥነት ወደሆስፒታል በመሄድ ዶክተርሽን ማማከር አለብሽ፡፡ የደም ግፊትሽ በጣም ከጨመረ እና ከ180/110ሚ.ሜ ሜርኩሪ በላይ ከሆነ መድሃኒት መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ መድሃኒቶቹም በሐኪምሽ ትእዛዝ መሆን እንዳለባቸው እንዳትዘነጊ፡፡

የደም ግፊት በሽታ ተጠቂ እርጉዝ ሴት ወሊድ ምን ይመስላል?

ይህ በሽታ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ብዙም ችግር አያመጣም፡፡ ቀለል ያለ የደም ግፊት መጠን መጨመር ያለባቸው እናቶች ከ39 እስከ 40 ባሉት ሳምንታት ሊወልዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ካላቸው ከ38 ሳምንት በኋላ ቢሆን ይመከራል፡፡ ከጊዜው ቀድሞ ምጥ ከጀመረ የልጅሽን ሳምባ የእንሽርት ውሀሽን በመመርመር በቂ የእድገት ደረጃ ላይ ካልሆነ የሳምባውን ብቃት የሚጨምሩ መድሃኒቶች ሊሰጡሽ ይችላል፡፡ የደም ግፊት በሸታ ያለባቸው እናቶች ምንም ችግር ሳያጋጥማቸው የመውለድ እድላቸው በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ከላይ የተጠቀሱትን ጥንቃቄዎች በማድረግ እንዲሁም የህክምና ክትትል በማድረግ የጤናማ ልጅ እናት መሆን ትችያለሽ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.