የአከርካሪ አጥንት በተለይም የአከርካሪ አጥንት ዲስክ / Spinal Disc/ መነሻና ችግሮችን አስመልክቶ የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች የተለያየ አይነት አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ይስተዋላል። እነዚህ በተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ የተለያዩ አስተያየቶችም በዚሁ በአከርካሪ አጥንት ችግሮች የተጠቁ ህመምተኞችን ግራ መጋባት ውስጥ ሲከቱም ይታያል። በመሠረቱ በአከርካሪ አጥንት ዙሪያ የሚከሰቱ የህመም አይነቶች ተመሳሳይነት የሚታይባቸው ነገር ግን የተለያየ የመነሻ ምክንያትና ስያሜ ያላቸው መሆኑ ለሚፈጠሩት አለመግባባቶች እንደምክንያት ይጠቀሳል። በተለይ ዲስክ የተመለከቱት የህመም አይነቶች ውስብስብና በርካታ ሲሆኑ ለመጥቀስ ያህልም የነርቭ መጨፍለቅ / pinched nerve/ ፣ ዲጀነሬትድ ዲስክ / defenerated disc/፣ የዲስክ መንሸራተት /Slipped disc/፣ /Herniated disc, bulfing disc… የሚባሉ የህመም መነሻ ዓይነቶች /ምክንያቶች አሉ።
lower-back-pain-treatment-virginia-beach-300x220
የአከርካሪ ዲስክ ክብ ሆኖ ከላይና ከታች ጠፍጣፋ ቅርፅ ያለው ሲሆን፤ በእያንዳንዱ የአከርካሪ አጥንቶቻችን / Vertebrae/ መገጣጠሚያ መሐል ይገኛል።

እነዚህ ዲስኮች በተለይ በአከርካሪ አጥንቶቻችን ላይ የሚከሰትን መርገብገብ ለመቀነስ /Shock absorption/ ያገለግላሉ።

የበሽታዎች ምልክቶች እና መነሻ ምክንያት

ከአከርካሪ አጥንት ዲስክ ጋር የተገናኘ ህመም በሚገጥመን ወቅት የተለያዩ የበሽታውን ምልክቶች ማየት የሚቻል ሲሆን የምልክቶቹም አይነት እንደተጐዳው የዲስክ አይነትና ዲስኩ እንደሚገኝበት ቦታ ሊለያይ ይችላል። ይህም ህመም የተከሰተው በዲስኩ ላይ ብቻ ከሆነ ቀለል ያለ የህመም ምልክትን ብቻ ማሳየት ሲችል የነርቭ ስሮችን የሚነካ ከሆነ ግን የህመሙ መጠን ከፍተኛ ይሆናል።

በዲስክ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ህመሞችም ሆነ በአጠቃላይ የወገብ ህመም ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በእርጅና ወቅት የሚከሰት የዲስክ ህመም በአብዛኛው ከመንሸራተት ጋር የተገናኘ ሳይሆን በዲስኩ ረጅም ጊዜ ማገልገል የሚከሰት ድርቀት የአከርካሪ አጥንት እንደፈለገው እንዳይተጣጠፍ / እንዳይንቀሳቀስ/ ማድረግ ስለሚጀምር ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመንቀጥቀጥ/ ንዝረትን የመቆጣጠር /Shock absorption/ ሥራውን በአግባቡ መወጣት አለመቻሉ ለችግሩ መከሰት ምክንያት ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዲስክ ጋር የተያያዙም ሆኑ ሌሎች የጀርባ ህመሞች በቀን ተቀን ህይወታችን በምንተገብራቸው እንቅስቃሴዎች አማካኝነት ይከሰታል። በተለይ የአቀማመጥ ሁኔታችን እንዲሁም ክብደት ያላቸው እቃዎችን ከመሬት ለማንሳት የምናደርገው ትክክለኛ ያልሆነ እንቅስቃሴ ለችግሩ ሊያጋልጠን ይችላል።

በጀርባ ህመም የተጠቃ ሰው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ጣቢያዎች ማምራት የሚገባው ከመሆኑም በላይ የህክምና ባለሙያውም ከዚህ ቀደም የነበረውን የህመምተኛውን የጤና ታሪክ፣ አሁን እየተሰማው ያለውን የህመም ምልክቶች እንዲሁም ሌሎች ሳይንሳዊ መመርመሪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ምርመራ ሊያደርግለት ይገባል።

የጀርባ ህመሞች ካላቸው በርካታ መነሾዎች አንፃር ህመሙን በተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶች ማከም የተለመደ ነው። X-ray ከእነዚህ የመመርመሪያ መሳሪያዎች ተርታ ተሰልፎ የቆየ ቢሆንም ቲሹዎችን /Soft tissue/ በግልፅ ለማሳየት አለመቻሉ ተመራጭ አያደርገውም። ከዚህ ይልቅ Magnetic resonance imagind (MRI) በተሠኙ መሳሪያዎች ወይም tomography (CT) ስካን መጠቀም / መመርመር/ ይረዳል።

ህክምናው

በአብዛኛው የጀርባ ህመም በሚያጋጥም ወቅት ቀዶ ጥገና ማድረግ እምብዛም አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚናገሩ የህክምና ባለሙያዎች አሉ። በቀደሙት ዘመናት ለጀርባ ህመም ‹መኝታ› ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ ተደርጐም ይታሰብ ነበር። በእርግጥ ‹‹ቀላል›› ለሚባሉ የጀርባ ህመም አይነቶች የአንድና የሁለት ቀን መኝታ ጠቃሚ እንደሆነ አሁንም ቢሆን በሳይንሳዊ መንገድ የሚመከሩ ባለሙያዎች አሉ።

ይሁን እንጂ ‹‹ከባድ›› ወደሚባለው የጀርባ ህመም አይነት ስንመጣ እንደጀርባ ህመሙ አይነት የተለያዩ ህክምናዎች የሚሰጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ፡-

Transoutaneous Electrical Nerve Stimulation (TENS)

ይህ የህክምና አይነት በተለይ ከዲስክ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የህመም አይነቶች የሚሰጥ ሲሆን፤ አነስተኛ መጠን ያለውን የኤሌክትሪክ ከረንት በተፈላጊው ቦታ ላይ በመልቀቅ የሚሰጥ ህክምና ነው። ይህ ህክምና ህክምናውን ለመስጠት በተዘጋጀ በራሱ መሳሪያ የሚሰጥ ሲሆን ህክምናው ምንም አይነት ህመም የለውም። የአሜሪካ የኒውሮሎጂ አካዳሚ ይህ ህክምና ውጤታማ ቢሆንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለደረሰና ወገብ አካባቢ ላለ ህመም ፍቱንነቱ አናሳ መሆኑን ይገልፃል።

Acupunctur /የደረቅ መርፌ ህክምና/

ከቀዶ ህክምና ነፃ የሆነና በፍቱንነቱም ተመራጭ የሆነው የጀርባ ህመም ህክምና ‹አኩፓንቸር› ተብሎ ሲጠራ ብዛት ያላቸውን ደረቅ መርፌዎችን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በመሰካት የሚደረግ ህክምና ነው። በእርግጥ ይህ የደረቅ መርፌ ህክምና በምን መንገድ እንደሚሰራ እስካሁን በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ህክምናውን የወሰዱና የዚሁ የጀርባ ህመም ተጠቂ የነበሩ ሰዎች ከህክምናው በኋላ ፈውስ ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ስለህክምናው የሚሰጠው አስተያየት የተለያየ ነው።

እነዚህን ሁለት አይነት የጀርባ ህመም መፈወሻ መንገዶችን ለምሳሌነት አነሳን እንጂ Epidurals steroid Injections (ESI)፣ Diskectumy፣ Spinal Fusion፣ Laminotomy ፣ የሚባሉ የህክምና አይነቶች ሲኖሩ መለስተኛና ሙሉ የቀዶጥገና ህክምናም የጀርባ ህመምን ለማከም በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ የህክምና አይነቶች ውስጥ ይመደባሉ።

እንዴት መከላከል ይቻላል?

የጀርባ ህመም ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በዕድሜም ሆነ በሥራ ጫና ሊፈጠር የሚችለው እድል ሠፊ እንደመሆኑ መጠን፡-

– ዕድሜ ሲገፋ የሚከሰትን የጀርባ ህመም ለመከላከል አዘውትሮ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣

– አቀማመጥን እና የመኝታ ሁኔታችንን ማስተካከል

– ከባድ እቃዎችን ከመሬት በምናነሳ ወቅት አንድ እግራችንን ሸብረክ በማድረግ የእቃውን ክብደት ከጀርባችን ይልቅ በእግራችን ላይ እንዲያርፍ አድርጐ ማንሳት ከብዙዎቹ ምክሮች ጥቂቶቹ ናቸው።

 

ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.