የልጅሽ እንቅስቃሴ ልጅሽ እድገት እያሳየ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ በተጨማሪም ከአንቺ ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠነክርልሻል።

ልጄ መቼ እንቅስቃሴ ይጀምራል?

Fotoliaከ16ኛው እስከ 25ኛው ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንቅስቃሴውን ልታስተውዪ ትችያለሽ። የመጀመሪያ እርግዝናሽ ከሆነ ከ20ኛው እስክ 25ኛው ሳምንት ላይ ይከሰታል። ከአንድ በላይ የወለዱ ሴቶች ሲያረግዙ በ13ኛው ሳምንትም እንቅስቃሴው ሊሰማቸው ይችላል። የልጁን እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥተሽ መከታተል ከፈለግሽ፤ ጸጥታ በሰፈነበት አካባቢ በተመቻቸ አቀማመጥ መሆን ወይም መጋደም ይኖርብሻል።

የልጅ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ይህንን የተለያዩ እናቶች ተገላበጠ፣ ተራገጠ፣ ወይም ነዘረኝ ሲሉ በተለያየ አነጋገር ይገልጹታል። በመጀመሪያ ልጁ መንቀሳቀሱን ለማወቅ ሊያስቸግርሽ ይችላል፤ እየቆየ ሲሄድ ግን የልጁን እንቅስቃሴ ከረሃብ ስሜት እና ከሌሎች የሆድ ውስጥ እንቅስቃሴዎች መለየት እየቻልሽ ትሄጃለሽ። በተለይም በመጨረሻዎቹ የእርግዝና ሶስት ወራት ምን አይነት እንቅስቃሴ ለምን እያደረገ እንደሆነ ትረጂዋለሽ።

በምን ያክል እንቅስቃሴ ሊሰማኝ ይገባል?

በመጀመሪያዎቹ የእርግዝናሽ ሶስት ወራት ትንሽ ንዝረት ሊሰማሽ ይችላል። በ6ኛው ወር አካባቢ ልጅሽ እድገቱን እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግን የልጁ እንቅስቃሴ ብዛቱና የምቱ መጠን እየጨመረ ይሄዳል።

በመጨረሻዎቹ የእርግዝናሽ ሶስት ወራት ልጁ በሰዓት 30 ጊዜ ይንቀሳቀሳል። ህጻናት በማህጸን ውስጥ እያሉ የሚተኙበት እና የሚነቁበት ጊዜ አላቸው። በተለይ ንቁ ሆነው ብዙ እንቅስቃሴ የሚኖራቸው ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ማታ 1 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የልጆች የመንቃት እና የመተኛት ጊዜያቸው ከእናት የደም የስኳር መጠን መለዋወጥ ጋር የተያያዘ ነው። በማህጸን ውስጥ ያለ ህጻን በአካባቢው የሚካሄዱ የተለያዩ ነገሮችን ተከትሎ ለምሳሌ ለንክኪ እና ለድምጽ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይችላል። ከባለቤትሽ ጋር ተጠጋግታችሁ የምትተኙ ከሆነም ከአባቱ ጋር ያለውን ቅርበት ለማሳየት ህጻኑ ሊራገጥ ይችላል።

የልጄን እንቅስቃሴ መከታተል ይኖርብኛል?

በእርግዝናሽ ከ28ኛው ሳምንት በኋላ እንቅስቃሴውን እንድትከታተዪ እንመክራለን። ይህም ልጅሽ በትክክለኛው መጠን እድገት እያሳየ እንደሆነ ለመገመት ይጠቅማል። የልጅሽን እንቅስቃሴ ለመከታተል ከወሰንሽ ክትትልሽን የምትመዘግቢበት ማስታወሻ ብታዘጋጂ ጥሩ ነው።

ይህንንም ለማድረግ የልጁ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሚሆንበትን ጊዜ በመምረጥ (በተለይም ምግብ ከተመገብሽ በኋላ) በሚመችሽ ወንበር ላይ በምቾት በመቀመጥ አልያም በጎንሽ በመተኛት ቆጠራውን መጀመር ትችያለሽ። ከዚያም ልጅሽ 10 እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የፈጀበትን ጊዜ ተመልከቺ። 10 እንቅስቃሴዎችን በሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ማድረግ ከቻለ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ መገመት ትችያለሽ። ነገር ግን በሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ 10 እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ካልቻለ ቆየት ብለሽ በድጋሚ ቁጠሪ። አሁንም ተመሳሳይ ውጤት ካገኘሽ ልጅሽ በቂ እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ተረድተሽ በአፋጣኝ ወደሐኪምሽ መሄድ ይኖርብሻል። ሐኪምሽ የልጁን የልብ ምት እና እንቅስቃሴ በመመርመር ያለበትን ሁኔታ ያሳውቅሻል።

ልጄ እንቅስቃሴ ከሌለው ምን ላድርግ?

በእርግዝናሽ 20ኛው ሳምንት ላይ ካልደረሽ እና የልጅሽን እንቅስቃሴ ካልሰማሽ ወይም የሚሰማሽ ስሜት የልጅሽ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ከገባሽ፤ ብዙ አትጨነቂ። የልጅሽ እድገቱ በጨመረ ቁጥር እንቅስቃሴዎቹን የበለጠ እየተረዳሽና እየለየሽ ትሄጃለሽ። በተጨማሪም በየትኛው ጊዜ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚኖረውም ትገነዘቢያለሽ። መርሳት የሌለብሽ ነገር ግን አንዳንድ ህጻናት ከሌሎች የበለጠ ወይም ያነሰ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ መቻላቸውን ነው። በተጨማሪም እንቅስቃሴ ያለመኖር የልጅሽን እንቅልፍ ላይ መሆን ሊያሳይ ይችላል። ከ32ኛው ሳምንት በኋላ ልጁ እየፋፋ ስለሚሄድ እንደልቡ ላይንቀሳቀስ ይችላል። በዚህ ጊዜ የእንቅስቃሴው መጠን ከበፊቱ ይቀንሳል።

በትክክለኛው መጠን መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ 10 እንቅስቃሴዎችን በሁለት ሰዓታት ውስጥ ማግኘት ካልቻልሽ ወይም አለወትሮው በከፍተኛ መጠን ከቀነሰብሽ በአፋጣኝ ወደ ሐኪምሽ በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ይጠበቅብሻል።

የልጅ እንቅስቃሴ መከታተያ ጊዜያት

ልጅሽ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በዚህ መሰረት መከታተል ትችያለሽ፡

ሳምንት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች
12ኛ ሳምንት ልጅሽ መንቀሳቀስ ይጀምራል ልጁ በጣም ትንሽ ስለሆነ ግን አይሰማሽም
16ኛ ሳምንት ንዝረት
18/20ኛ ሳምንት መራገጥ
24ኛ ሳምንት ክብደቱ ሁለት ኪሎ አካባቢ ስለሚሆን በደንብ ይሰማሻል
28ኛ ሳምንት በተደጋጋሚ ይሰማሻል ክብደቱም ወደ 3 ኪሎ አካባቢ ይደርሳል። አንዳንዴም ሃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ሊያሳምምሽ ወይም ሊያስደነግጥሽ ይችላል
36ኛ ሳምንት ማህጸንሽ እየጠበበው ሲሄድ እንቅስቃሴውን ይቀንሳል

Source- Addis Health.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.