የእርግዝና የአደጋ ምልክቶች

2

በሌላ ጊዜ ሚያሳስቡ የነበሩ ስሜቶች በእርግዝና ወቅት በሰውነትሽ ላይ በሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ለውጦች ምክንያት የሚጠበቁና ብዙም የማያስደነግጡ ይሆናሉ። ለምሳሌ የመድከምና ቶሎ ቶሎ የመተንፈስ ስሜት፣ ማቅለሽለሽና ማስታወክ፣ የሙቀት ስሜትና ላብ በእርግዝና ወቅት ሌላ ምንም አይነት ችግር ሳይኖር ልናያቸው የምንችላቸው ስሜቶች ናቸው።

 

embarazoectopicoበአንፃሩ እርግዝና ባይኖር ብዙ የማያስደነግጡ ግን ከእርግዝና ጋር አንድ ላይ ሲከሰቱ ከፍተኛ አደጋ ሊመጣ እንደሚችል የሚያመላክቱ የእርግዝና ምልክቶች አሉ። ሆኖም ከጥርጣሬ አረጋግጦ መተማመን ስለሚሻል እንግዳ ስሜት ሲሰማ የእርግዝና ሃኪምሽን ማማከሩ ይመረጣል። በድህረ ገፃችን ላይ ባለው ፎረም ላይም ጥያቄሽን በማስቀመጥ ከባለሙያዎች ምላሽ ልታገኚ ትችያለሽ።

በእርግዝና ጊዜ በፍፁም ሊታለፉ የማይገባቸውን የአደጋ ምልክቶች እስቲ አንድ በአንድ ተንትነን እንመልካታቸው፤

በማህፀን ደም መፍሰስ

በማንኛውም ወር ሲከሰት ይህ ምልክት ከፍተኛ አደጋን ያመላክታል። በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውርጃን፣ ከከፍተኛ የሆድ ህመም ጋር አብሮ ሲከሰት ደግሞ ከማህፀን ውጪ የተከሰት እርግዝና ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁኔታዎች የጽንሱን ብቻ ሳይሆን የእናቲቱንም ህይወት አደጋ ውስጥ ይከታሉ።  በመጨረሻዎቹ ወራት ቢከሰት የእንግዴ ልጅ ያለጊዜው ከማህፀን ግርግዳ እየተላቀቀ ስለሆነ ሊሆን ይችላል።

ደም መፍሰስ ሁልጊዜም ከባድ ምልክት ስለሆነ ወዲያውኑ እንደታየሽ ወደ ምትከታተልሽ ሃኪም በፍጥነት ሂጂ።
(link to bleeding in pregnancy)

በጣም የከፋ ማቅለሽለሽና ማስታወክ

በተለይ በእርግዝና መጀመሪያ ላይ የተወሰነ ጠዋት ላይ የሚብስ ማቅለሽለሽና ማስታወክ የሚጠበቅ ሁኔታ ቢሆንም ከመጠን አልፎ ምንም ነገር ሆድ ውስጥ ቁጭ ማለት ሲያቅተው ግን አደገኛ ሁኔታ ነው። የበላሽውን ሁሉ ሙሉ ቀን የሚያስታውክሽ እንደሆነ በሰውነትሽ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ እና ነጥረ ነገር ጨርሶት ለሰውነት መመንመን (malnutrition) እና ለሰውነት ድርቀት (dehydration) ያጋልጥሻል።

እነዚህ ሁለት ሁኔታዎች ደግሞ የፅንስ የአፈጣጠር ችግር፣ ከጊዜው ቀድሞ የሚመጣ ምጥ ወ.ዘ.ተ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ስለዚህም ከፍተኛ የሆነ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ሲገጥምሽ ሃኪምሽን ማማከር ይኖርብሻል።
(link to hyperemesis gravidarum)

የልጅ እንቅስቃሴ መቀነስ ወይም መቆም

ልጅሽ ከእንግዴ ልጁ በቂ ምግብና በተለይም አየር (ኦክስጅን) ሳያገኝ ሲቀር በመጀመሪያ የሚታይሽ ምልክት የእንቅስቃሴው መቀነስ ነው። እየተንከባለለችና እየተራገጠች ሰላም ስትነሳሽ የነበረችው ልጅ በድንገት እንቅስቃሴዋ ሲቀንስብሽ ትንሽ ጉልበት የሚሰጥ የሚጠጣ ወይም የሚበላ ነገር ቀመስ አድርጊና በጎንሽ ጋደም ብለሽ እንደገና መንቀሳቀስ መጀመሯን አጣሪ።

እንቅሰቃሴዋን መቁጠርም ሊረዳ ይችላል። ይህ ነው የሚባል የተቆረጠ ቁጥር መስጠትም ባይቻልም በሁለት ሰዓታት ውስጥ 10 ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ የተንቀሳቀሰች እንደሆነ አያሳስብም። በ12 ሰዓታት ውስጥ ግን ከአስር ጊዜ በታች የተንቀሳቀሰች እንደሆነ ልጅሽ የመታፈኗ እድል ከፍተኛ ስለሆነ በፍጥነት ወደ ሃኪምሽ በመሄድ ምርመራዎች እንዲደረጉልሽ አስፈላጊ ነው።

ሃኪምሽ ልጅሽ በጤናማ ሁኔታ እያደገችና እየተንቀሳቀሰች መሆኗን በአልትራሳውንድ እንዲሁም በሌሎች ምርመራዎች ያረጋግጥልሻል።

ከጊዜው በፊት የሚሰማ የመጫን ስሜት

ይህ ከጊዜው ቀድሞ የመጣ የምጥ ስሜት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ብዙ የመጀመሪያ ጊዜ እናቶች እውነተኛ የምጥ ስሜትን ከውሽት የምጥ ስሜት መለየት አይችሉም። የውሽት ምጥ መጫን (Braxton-Hicks contractions) ጊዜ የማይጠብቅ ፣ ዘፈቀደ የሆነና ቀስ በቀስ እየባሰ የማይሄድ የመጫን ስሜት ነው። በአንፃሩ እውነተኛ የምጥ መጫን በየ10 ደቂቃው ወይም ከዛ በታች እየደጋገመ የሚመጣ እና ቀስ በቀስ እየባሰ የሚሄድ አይነት የመጫን ስሜት ነው።

በዚህ ሁኔታ ግን ምጥ ይዞኛል ብለሽ ከተጠራጠርሽ ወደ ሃኪምሽ በመሂድ ማጣራት ላንቺም ሆነ ለልጅሽ ጤና የተሻለ አማራጭ ነው። ያለጊዜው የመጣም ምጥ ይዞሽ እንደሆነ ምጡን ለማስቆም የሚቻልበትን ሁኔታ ከሃኪምሽ ጋር መወያየት ትችያለሽ።

የሽርት ውሃ መፍሰስ

በአገር ሰላም እየተንቀሳቀሽ እያለ ውሃ በእግርሽ ላይ ሲፈስ ቢሰማሽ፤ በእርግጥ የሽርት ውሃሽ ፈሶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በእርግዝና ወቅት ማህፀን የሽንት ፊኛን በጣም ስለሚጫነው ሳይታወቅሽ የፈሰሰሽ ሽንትሽ ሊሆንም ይችላል። የሽርት ውሃ ሲፈስ በሚያስደነግጥ ሁኔታ “ቷ” ብሎ ፈንድቶም አልያም ብዙም ሳያስታውቅ ትንሽ ትንሽ ጠብ ጠብ እያለም ነው።

ፈሳሹ ሽንት ይሁን የሽርት ውሃ ለማረጋገጥ አንድ ጊዜ ወደ ሽንት ቤት ጎራ ብለሽ ፊኛሽን ባዶ አድርጊው። ከዚህ በኋላ መፍሰሱ ከቀጠለ ወደ ክትትል ቦታሽ ሄደሽ ሃኪምሽ እንዲያይሽ ይመከራል።
(link to PROM)

ኃይለኛ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ የእይታ ብዥ ማለት እንዲሁም የሰውነት ማበጥ

እነዚህ ምልክቶች በእርግዝና ምክንያት የሚመጣ የደም ግፊት በሽታ አስከፊ ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚታዩ ምልክቶች ናቸው። በእርግዝና ምክንያት የሚመጣ የደም ግፊት በሽታ የእንግዴ ልጅ መላቀቅ፣ የፅንስ ሞት፣ የሚጥል በሽታ አይነት ድንገተኛ ማንቀጥቀጥ እና የእናት ሞት ሁሉ የሚያስከስት አደገኛ በሽታ ስለሆነ እንዚህ ስሜቶች ከተሰሙ በፍጥነት ወደ ሃኪም ቤት በመሄድ ሃኪምሽን ማማከር ግድ ነው።

ከእርግዝና ጋር የሚከሰት የደም ግፊት በሽታ የሚታወቀው የደም ግፊት መጨመርና በሽንት ውስጥ መኖር የሌለበት ፕሮቲን በብዛት መገኘት ከሰውነት እብጠት ጋር ሲኖሩ ነው።

ይህን በሽታ በጊዜ ለማግኘት እና ለመቆጣጠር ታድያ ቀጠሮ ሳይዘሉ የእርግዝና ክትትል ማድረግ ከፍተኛ ሚና አለው።
(link to Preclampsia)

ትኩሳት

ትኩሳት የተላላፊ በሽታዎች ዋና ምልክት ነው። የትኩሳቱ መንስኤ ጉንፋን ቢሆን ራሱ በእርጉዝ እናቶች ላይ፣ ሌላ ሰው ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ የበለጠ ስለሚኖረው ይህን ምልክት በጊዜ አስተውሎ ከሐኪም ጋር መማከር አስፈላጊ ነው።

2 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.