ሲጋራ ለማቆም የሚረዳው ተክል

0

በ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ)

quit-smokingይህ ተክል በአማርኛ በትንጀን (ደብርጃን) የሚባል ስም ሲኖረው በዎልፍ ሌስላው የተዘጋጀው የእንግሊኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ‹‹ማደርቻ፣ መደርቻ›› ብሎ ይገልፀዋል፡፡ ለጋራ መግባባት እንዲመቸን በእንግሊዝኛ መጠሪያው ‹‹ኤግፕላንት›› እያልን እንጥራው፡፡

ኤግ ፕላንት ከ10ሩ አወዛጋቢ ምግቦች (10 most controversial foods list) ዝዝር ውስጥ በአብዛኛው ይካተታል፡፡ ይህ የሆነው እንደሱ ያሉ ምገቦች ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጡ ቢሆንም ለሁሉም ሰው እንደማይሆኑ ለመገለፅ ነው፡፡ ኤግፕላንት Nightshade ከሚባለውና ቲማቲምና ድንች ከሚካተትበት የተክሎች ዝርያ ይመደባል፡፡ አበቃቀሉም እንደ ቲማቲም ነው፡፡ አመቱን ሙሉ በገበያ ውስጥ ከሚገኙ ተክሎች አንዱ ሲሆን በጥሩ ሁኔታ የሚበቅለው ከነሃሴ እስከ ጥቅምት ወቅት ባሉት ወራት ነው፡፡

የንጥረ ነገር ይዘት

የምግብ ስልቀጣ ሂደትን የሚያፋጥን (dietary fiber) የተሰኘ ፋይበርና አጥንትን የሚገነባው ማንጋዚን ምርጥ መገኛ ነው፡፡ ቫይታሚን ኬ እና ማግኒዝየም፣ ኮፐር፣ ቫይታሚን ሲ፣ ቫይታሚን ቢ6፣ ፎሌት እና ናያሲንም በከፍተኛ መጠን ይገኙበታል፡፡

የጤና ጠቀሜታዎቹ

ከቫይታሚኖችና ሚንራሎች በተጨማሪ phytonutrients የሚባሉትንና አብዛኛዎቹ አንቲ ኦክሲዳንቶች የሆኑ ንጥረ ነገሮች ይዟል፡፡

ለአንጎል ተስማሚ ነው

በኤግ ፕላንት ሽፋን ላይ . . . በዋናነትም በሽፋኑ ላይ በሚገኘው nasunin የተሰኘ ፓይቶኒውትረንት ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ንጥረ ነገሩ ለአንጎል ጤንነት ጠቃሚ ነው ብሏል፡፡ nasunin ከፍተኛ አቅም ያለው በሽታ ተከላካይ (antioxidant) ሲሆን፤ በተለይ ካንሰር አምጪ የሆኑትን ፍሪ ራዲካልስ እያሳደደ በማጥፋት የሴል ሜምብሬን ጉዳት እንዳይደርስበት ይጠብቃል፡፡ በአንጎል የሴል ሜምብሬን ላይ የሚገኙት ሊፒድስ (lipids) እንዳይጎዱ ይታደጋቸዋል፡፡

በአሜሪካ የግብርና አገልግሎት ተመራማሪዎች የተካሄደ ጥናት ኤግፕላንት እንደ አንቲ ኦክሲዳንቶች ሆነው መስራት የሚችሉት የ (phenolic compounds) ምርጥ መገኛ ነው ብሏል፡፡ እነዚህ ውህዶች ራሳቸውን ከኦክሲዳንት እንዲሁም ከባክቴርያና ፈንገስ ኢንፌክሽኖች መከላከል ይችላሉ፡፡

የልብን ጤንነት ይጠብቃል

ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን የሚገኝባቸው የላብራቶሪ እንስሳት የኤግ ፕላንት ጭማቂ ከተሰጣቸው በኋላ የደም ኮሌስትሮል፣ በደም ግድግዳዎች የሚገኝ ኮሌስትሮል በዋነኛነትም ከልብ ወደ ሰውነት ደም የሚወሰዱት አኦርታዎች (aortas) ላይ የሚገኘው የኮሌስትሮል መጠን ቀንሶ የተገኘ ሲሆን፣ የደም ዝውውሩ በመሻሻሉም የደም ቧንቧዎቻቸው ዘና የማለት ነገር ታይቶባቸዋል፡፡

የብረት መጠንን ይቆጣጠራል

Nasunin ፀረ ራዲካልስ ብቻ ሳይሆን ብረት በዝቶ ጉዳት እንዳያደርስ ይከላከላል፡፡ ብረት በሰውነታችን ውስጥ ኦክስጅንን ለማመላለስ፣ ለበሽታ መከላከል አቅም መዳበር አስፈላጊ ቢሆንም፤ በጣም ከበዛ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ ብረት በሰውነት ውስጥ ከሚፈለገው በላይ ሲገኝ የፍሪ ራዲካልሶችን ብዛት ከመጨመሩም በላይ በልብ በሽታና በካንሰር የመጠቃት እድልንም ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት በየወሩ ብረት የሚያንሳቸው ቢሆንም ከማረጥ እድሜ በኋላ በሁለቱም ጾታዎች ሰውነት ውስጥ ብረት በከፍተኛ መጠን ሊከማች ይችላል፡፡ ኤግ ፕላንት ውስጥ የሚገኘው Nasunin ይህን ክምችት ለመቀነስ ይረዳል፡፡

በካንሰር የመጠቃት እድልን ይቀንሳል

በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ኤግ ፕላንት በርካታ የጤና ጠቀሜታዎችን ይሰጣል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሞች ውስጥም ካንሰርን ማከምና መከላከል መቻሉ አንዱ ነው፡፡ በውስጡ የያዘው ከፍተኛ የፋይበር መጠን በተለይ የትልቁን አንጀት ካንሰርን በማከሙ በኩል ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ፋይበር ካንሰሩ እንዲከሰት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ መርዛማ ንጥረ ነገሮችና ኬሚካሎችን ውጦ ያስቀራቸዋል፡፡

በአንጀት ካንሰር የመጠቃት እድላቸውን ለመቀነስ የሚያስቡ ሰዎች የኤግ ፕላንት ሽፋኑን መጣል ሳይሆን መብላት ነው ያለባቸው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሽፋኑ ከዋናው አካል የበለጠ ፋይበር በመያዙ ነው ብሏል አንድ ጥናት፡፡

ክብደት ለመቀነስ ይረዳል

ከላይ እንደተጠቀሰው ተክሉ ከፍተኛ የፋይበር ይዘት አለው፡፡ ፋይበሩ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ ክብደት እንዲቀንስም ይረዳል፡፡ ፋይበር በተፈጥሮው ብዙ ቦታ ይይዛል፡፡ ክብደት ለመቀነስ የሚሹ ሰዎች ኤግ ፕላንት የተቀላቀለበት ሰላጣ ከምግብ ሰአት አስቀድመው መውሰድ ከቻሉ ፋይበሩ የመጥገብ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፋይበሩ በሆድና የምግብ ስልቀጣ ስርዓት በሚካሄድባቸው አካላት ውስጥ በቀስታ ስለሚንቀሳቀስ የመራብ ስሜትን ያስቀራል፡፡ ይህም ክብደት ለመቀነስ ይረዳል፡፡

ለቆዳ ውበትይጠቅማል

ኤግ ፕላንት ከፍተኛ የውሃ ይዘት ስላለው ለቆዳና ፀጉር ጤንነት ጠቃሚ ነው፡፡ የደረቀ ፀጉር መሰነጣጠቁ አይቀርም፡፡ የደረቀ ቆዳም መጨማደዱና መጎሳቆሉ በቀላሉ ይታያል፡፡ በተክሉ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች በጥሬው ከተወሰደ ለቆዳ ጤንነት የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍ ይላል ብለዋል፡፡

ሌሎች ጥናቶች ደግሞ በውስጡ በከፍተኛ መጠን የያዛቸው ውሃ፣ ቫታሚኖች፣ ሚኒራሎችና ጤናማ ስቦች ለጠንካራና ጤናማ ፀጉር መፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ይላሉ፡፡

ሲጋራ ለማቆም ይረዳል

እስካሁን የፃፍንላቸው ተክሎችና ፍራፍሬዎች ይህን መሳይ ጥቅም ሲሰጡ አልተመለከትንም፡፡ ኤግ ፕላንት ግን በውስጡ ኒኮቲን ይዟል፡፡ ኒኮቲኑ አጫሾችን ቀስ በቀስ ሲጋራ እንዲቆሙ ሊረዳ እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ተክሉ በተፈጥሯዊ መንገድ ማጨስ ማቆም ለሚሹ ተመራጭ ነው፡፡

ማሳሰቢያ፡- አንዳንድ ሰዎች የኤግ ፕላንት አለርጂክ አለባቸው፡፡ ተክሉን ከዚህ በፊት ተመግበው የማያውቁ ሰዎች ለመጀመርያ ጊዜ ሲመገቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ኤግ ፕላንት ከተመገቡ በኋላ በአፍዎና በሌላ የሰውነትዎ አካል ላይ የማሳከክ ስሜት ከተፈጠረ አለርጂክ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ ከተስማማዎ ግን በሳምንት ለጥቂት ጊዜያት ይመገቡት፡፡

በውስጡ oxalates የተሰኘ ንጥረ ነገር የያዘ ሲሆን መጠኑ ሲጨምር ጉዳት ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተለይ የኩላሊትና የሽንት ፊኛ ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዲመገቡት አይመከርም፡፡

 

ምንጭ፡- አዲስ ጉዳይ 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.