broken loveሕሊናዬን እያስጨነቀኝ ያለ አንድ ሀሳብ አለ እንደሚከተለው ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጓደኛነት ስመሰርት በአይን ለረጅም ጊዜ ከወደድኩዋት ልጅ ጋር በአጋጣሚ ተዋውቀን፤ ከዚያም ተነጋግረን በጓደኝነት 1 ዓመት ያህል ከዘለቅን በኋላ አንድ ስሜቴን የሚጎዳ ነገር ገጠመኝ፡፡ ፀጉሬን እየተስተካከልኩ ሳለ የማላውቃቸው ሰዎች ስለእሷ መጥፎ ነገር ሲያወሩ ሰማሁ፤ ከዚያም የራሴን የጥናት ስራ ሰርቼ አረጋገጥኩኝ፡፡ ከዚያም ለመለያየት በቃን፤ አሁን ከተለያየን 1 ዓመት ሆኖናል፡፡

አሁን ደግሞ ለእኔ እጅግ አሳቢ ልጅ ጋር ተዋውቄ የበፊቱን ፍቅሬን እጅግ በጣም አስረስታኛለች፡፡ ከ1 ዓመት በኋላ ግን እኔ ጣዕም አጥቼያለሁ፡፡ ለምን እንደሆነ አላወቀኩትም፤ እባካችሁን መፍትሄውን ስጡኝ፡፡ የመጀመሪያዋን ማሰብ ጀምሬያለሁ፡፡ ከሁለቱም ጋር ምንም አይነት የወሲብ ግንኙነት አላደረግንም፡፡

ዮናስ

ውድ የዚህ አምድ ተሳታፊያችን

ለአምዳችን ስኬት ጉልህ ሚና የሚጫወቱት እንደ አንተ መሰል ተሳታፊዎቻችን በመሆናቸው ጥያቄህን ከወፍራም ምስጋናና ሰላምታ ጋር ተቀብለናል፡፡ በአንድ ወቅት የአይን ፍቅር ከያዘህ ልጅ ጋር በፍቅር ጥንዶች ሆናችሁ ለአንድ ዓመት ያህል እንደቆያችሁ፤ ድንገት ፀጉር ቤት ሆነህ ስለ እርሷ መጥፎ ባህሪ እንደሰማህ፤ እውነታውንም አረጋግጠህ ካንተ ውጪ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንደምትወጣ ካወቅህ በኋላ እንደተለያያችሁ ከደብዳቤህ ማወቅ ችለናል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለአንተና ለፍቅራችሁ በጣም አሳቢ፣ እንዲሁም ያለፈውን ጥሩ ያልሆነ ትዝታህን የምታስረሳህ ልጅ እንዳገኘህም ነግረኸኛል፡፡ ግን ከበፊቷም ሆነ ከአዲሲቷ ጋር ምንም አይነት ወሲብ ግንኙነት እንደሌለህ ጭምር ለማወቅ ችለናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከጋብቻ በፊት ወሲብ ባለማድረግህ ሳናደንቅህ አናልፍህም፤ ለሌሎችም አርአያ እንድትሆን ግፋበት እንላለን፡፡ ይሁንና ለምን እንደሆነ ባታውቀውም በዚህ ጊዜ ሌላ አንድ ዓመት አብሮ መሆኑ እንደሚያሰለችህና እንደሚያደክምህ ገልፀህልናል፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ? ላልከው መፅሐፍት አጣቅሰን፣ የራሳችንንም የህይወት ተሞክሮና ምክር አክለን መፍትሄውን እነሆ ብለናል፡፡

ምንም እንኳ ያለፈው ታሪክህ ለዛሬ መሰረትና መነሻህ፣ ለወደፊቱም አመላካች መሆኑ ባይካድም ትላንት ያጋጠመህ ነገር በሙሉ ዛሬም ይከሰታል ብለህ መገመት ያለብህ አይመስለንም፡፡ ዛሬ ሌላ ቀን ነው፤ ነገም እንዲሁ! ለጥያቄህም መልስ ከመስጠታችን በፊት የሚከተሉትን ማወቅና መረዳት ተገቢ ነው እንላለን፡፡ ለመሆኑ ከአዲሲቷ ጓደኛህ ጋር መሆኑ ያስፈለገህ ዘላቂ የትዳር ጓደኛህ እንድትሆን ነው? ወይስ እንዲያው የበፊቷን እንድታስረሳህ? በግንኙነታችሁ ውስጥ የመጨረሻ ግብህ ምንድነው? ያለምንም በቂና አሳማኝ ምክንያት ብዙ ጊዜ እንድትቆዩ ባንመክርህም፤ ለአጭር ጊዜ መሆኑም ደግሞ የራሱ የሆነ ጉዳት አለው፡፡ በእርግጠኝነት የምንነግርህ ግን ቀጣይነት ላለው የኑሮ ምዕራፍ ለሚዘጋጁ ጓደኛማቾች አንድ ዓመት አብሮ መቆየታቸው ቢያንስ እንጂ የሚበዛ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ከበፊቷ ልጅ ጋር መለያየትህ የማይታይ በረከት እንጂ ክስረትና ጉዳት አይደለም፡፡ ጊዜህን፣ ጉልበትህን፣ ገንዘብህን ልታጠፋ ትችል ይሆናል፤ ግን ወደ ፊት አብራ በመሆኗ ልታደርስብህ ከምትችለው ጉዳት አይበልጥም፡፡ ደግሞም የአንተ ካልሆነችው ልጅ ጋርም ጊዜህን ማጥፋት ላንተም ለሷም መልካም አይመስለንም፡፡

ውድ ተሳታፊያችን አንድ ነገር ልታጤን የሚገባው አዲሲቷ ልጅ ላንተም ሆነ ለፍቅራችሁ አሳቢ እንደሆነች ነው፡፡ ይህ ደግሞ መልካም፣ ለወደፊት ህይወታችሁ ገንቢና መሰረት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ላይ ያንተም ሀሳብና ምላሽ ተመሳሳይ ካልሆነ ችግሩ ወደ እናንተም ግንኙነት እንደሚመጣ ሌላ ምልክት ወይም ተአምር መጠበቅ አያሻም፡፡ ደግሞ መልካም ከሆነና መጥፎ የሆነው ታሪካችንን ከሚያስረሳ ሰው ጋር እረጅም ጊዜ መቆየት የሚጠላ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ለብዙም ሆነ ለአጭር ጊዜ በጓደኝነት መቆየቱ የራሱ የሆነ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም የጊዜው ጉዳይ ከጥንዶች ጥንዶች አንፃራዊ ስለሆነ ዋናው የምንቆየው ለምንድነው? የሚለውን መመለሱ ላይ ነው፡፡ ከቆይታው በስተጀርባ ያለውን ፍላጎት /Motive/ ማወቅም ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ለመሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮ በጓደኝነት መቆየቱ ጠቀሜታው ምንድነው?

አብሮ ማደግን ስለሚያስከትል ነው፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ ጥንዶቹ (ለምሳሌ ከተጫጩ በኋላ ቢያንስ ለአንድ ዓመት አሊያም ከተዋወቁ 18 ወራት ያላነሰ) ጊዜ የነበራቸው ሊጣጣም የሚችል መንፈሳዊ እምነት ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂነት ላለው የጋራ እድገት አቅም ይሆናቸዋል፤ በጋራ ማደግን መቀጠል ከቻሉ ደግሞ በደስታ አብሮ ለመቆየት አያስቸግራቸውም፡፡ ስለዚህ መልካም ግንኙነት እድገት ተኮር ስለሆነ ሁለታችሁም እየተማራችሁ የምትለወጡበት፣ ከግለሰባዊ አካሄድ ወደ ጥንድ አስተሳሰብ የምትራመዱበት የህይወት መድረክ ነው፡፡ ይህ ግን በመዳከምና በመሰልቸት የሚመጣ አይደለም፤ እንደውም ከሁለታችሁም በኩል ቁርጠኝነትን፣ ትዕግስትን፣ ትኩረት መስጠትንና መከባበርን ይጠይቃል፡፡

መተሳሰብን ያጎለብታል፡፡ ፍቅር የሁለትዮሽ ግንኙነት ነው፡፡ እርሷ ብቻ የምትወድህ ከሆነና ተመጣጣኝ ምላሽ ካንተ ካላገኘች ችግርና በአንድ እጅ የማጨብጨብ አይነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን መተሳሰቡ በተዋወቅካት ማግስት ይምጣ ማለት አይደለም፡፡ ጊዜያት ባለፉ ቁጥር እርስ በርስ የመተዋወቁ፤ የመናበቡ ሁኔታ እየተሻሻለ እንደሚመጣ ግልፅ ነው፡፡ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ፍቅራችሁን የምትገልፁበትን መንገድ በመፈለግ እርስ በርስ እንድትተሳሰቡ፣ ፍቅራችሁንም እያሳደጋችሁ ከመጥፎ ነገር እንድትጠበቁ ያስችላችኋል፡፡ ጊዜው ደግሞ በደንብ እንድትተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ያልተስተካከለ ባህሪና ልማድ ካለም የምትተራረሙበት ወቅት ነው፡፡

የረጅም ጊዜ እቅድ እንዲኖርህ ያደርግሃል፡፡ መቼም ጤነኛ አእምሮ እንዳለው ማንኛውም ሰው ይብዛም ይነስም በህይወቱ እንዲሳካለት የሚፈልገው ነገር ይኖረዋል፤ ለዚህም መሳካት ደግሞ ሰው የራሱ የሆኑ የአጭር ወይም የረጅም ጊዜ እቅዶችን ያቅዳል፡፡ እንዲሆንልን እንደምንፈልገው ነገር ደግሞ የሚጠይቀንም ጊዜ የዚያኑ ያህል ይለያያል፡፡ የምንፈልገው ነገር ከባድና ዘላቂነት ያለው ከሆነ የረጅም ጊዜን እቅድንና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ አይካድም፡፡ ይህ ደግሞ አላማ ያለው ህይወት እንድትኖር ከማድረጉም ባሻገር ውጤታማ ያደርግሃል፡፡ የመጨረሻው ውሳኔ ያንተ ቢሆንም እኛ ደግሞ ወደፊት ህይወትህ እንዲቃና መልካም ናቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች እናመላክትሃለን፡፡ ስለዚህ ስለምታስበው የወደፊቱ ግንኙነትህ ከእድል ጋር በምንም ሁኔታ ሳታያይዝ አብዛኛው ጉዳይህ አሁን በምታስበው፣ በምትቆጣጠረውና ከሁሉም በላይ ደግሞ መጨረሻህም እንዴትና ምን እንዲሆን እንደምትፈልግ በምታደርገው ጥረት ላይ እንደሚወሰን እወቅ፡፡

እንግዲህ ወንድማችን ማንኛውንም ሰው በሚኖርበት አካባቢ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ነጋዴዎች እንኳ የደንበኞችን እምነት ለማግኘትና የረጅም ጊዜ ትስስርን ለመመስረት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይ እኛ ደግሞ ወደ ፊት የህይወት ጊዜያችንን ልንጋራው ከምንሻው ሰው ጋር ምን አይነት ግንኙነት መፍጠር ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እንዴት ልናቆየው እንችላለን የሚለው ላይ ማተኮር ተገቢ ይመስለናል፡፡ ነገሮችን ካከበድክ ይገዝፍብሃል፤ ነገር ግን ወዴት እንደምትሄድ ካወቅክና ለምን እንደምታደርገው ከተገነዘብክ የሚያስቸግርህ የሚያሰለችህ አይመስለንም፡፡ ለማንኛውም አንተ ውደዳት እንጂ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ ብታደርግ ከውጤታማ የሆነ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ሳትሰላች ከምትወዳት ልጅ ጋር ይኖርሃል እንላለን፡፡

  1. ከሌላ ሰው ጋር አታነፃፅር፡፡

የእያንዳንዱ ጥንድ ግንኙነት አጀማመሩም ሆነ አካሄዱ፤ አጨራረሱም የተለያየ እንደሆነ አስብ፡፡ አሁን ያለህን ግንኙነት ‹‹ፍፁም›› ነው ብለህ ከምታስባቸው ከሌሎች ጓደኞችህ ቤተሰቦችህ ጥንዶች ጋር በፍፁም አታነፃፅር፡፡ እያንዳንዳቸው ጥንዶች በግንኙነታቸው ውስጥ የራሳቸው የሆነ የፍቅር ስምምነት፤ ልማድና ደንብ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ ወንድሜ በራሳችሁ (በአንተና በርሷ) ላይ ትኩረት አድርገህ ግንኙነታችሁን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነቱ በሁለታችሁም እጅ ነው፡፡ የጎንህ አጥንት እርሷ ከሆነች ሌሎቹ ምንም ያህል ያማሩ መስለው ቢታዩህም ይወጉሃል፤ ያሳምሙሃል፤ ዕድሜህን ያሳጥሩታል፤ እግዚአብሔርም ካዘጋጀልህ መልካም ነገር ላይ እንዳትደርስ ያደርጉሃል፡፡ ስለዚህ የአንተ የአንተ ነች፤ ልትቀይረው የምትችለው ሊቀየር የሚችለውን ባህሪዋን ብቻ ነው፡፡

  1. ልዩነታችሁን አክብር፡፡

መቼም ሁለታችሁም ከአንድ ቤት ውስጥ እንደ አለመውጣችሁ፤ የተለያየ የኑሮ ዘይቤና አስተዳደግ እንዲሁም የሀሳብ ልዩነት ይኖራችኋል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ነገሮችን ከራስህ አቅጣጫ ብቻ አትመልከት፣ ሁሉም ነገር እኔ እንደምፈልገውም ብቻ ይሁንም አትበል፡፡ እሷም የራሷ የሆነ አመለካከት እንዳላት እወቅ፡፡ የማትስማማበት ነገርና የሀሳብ ልዩነት እንኳ ቢፈጠር በማክበር ተቀበለው፡፡ ስለዚህም ጓደኛህን ለማድመጥ፣ ለመረዳትና በመሀከላችሁም ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት አድርግ፡፡ ምክንያቱም ውጤታማ ግንኙነት ከሁለቱም በኩል ፈቃደኝነትንና መተሳሰብን ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን በጣም አጥብቀህ የምትፈልገው ነገር ተሟልቶ እስካላገኘህ ድረስና የማታውቀው ቅራኔ በመሀከላችሁ ኖሮ ካልተፈታ ወደፊትም ችግሩ መነሳቱ ስለማይቀር ግንኙነቱን ባትቀጥለው እንመርጣለን፡፡

  1. ውስጣዊ ማንነትህን እንድታውቅ አድርጋት፡፡

ከጓደኛህ ጋር የምታሳልፋቸው እያንዳንዳቸው ጊዜያት ወይም ደረጃዎች በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን አትዘንጋ፡፡ ስለ ጓደኛህ የበለጠ እንድታውቅ ከማድረጉም ባሻገር ከእርሷ ጋር ያለህን ስሜትና ግንኙነት ትክክል ስለመሆኑ ያረጋግጥልሃል፡፡ አካልህን ብቻ ሳይሆን ከልብህ ያለውን ነገርህን አሳውቃት፡፡ ጊዜና አቅም በፈቀደ መጠንም ትርጉም ያለውና ጠለቅ ያለ ንግግር በተወሰነ ወቅት ይኑራችሁ፡፡ በደስታዋም ሆነ በሀዘኗ ጊዜ በሀሳብ፣ በአካልም ሆነ በስሜትህ ቅርብ ሁንላት፡፡ አብራችሁ የምታደርጓቸው ነገሮች ብዙ ሰዓት የሚፈጁ ከሆነ ጊዜያችሁ አጠር ስለሚል ቀልጣፋና የማያሰለች ይሆናል፡፡ ለሌላ ጊዜም እንድትገናኙና እንድትነፋፈቁ መንገድ ይከፍትላችኋል፡፡

  1. ይቅርታ ማድረግንና መርሳትን ሞክር፡፡

ሰዎች እስከሆንን ድረስ አንዳንድ ስራዎችን ሰንሰራ እንሳሳታለን፡፡ ስለዚህ በግንኙነታችሁ ወቅት ትክክል ያልሆነ ነገር ቢገጥምህ ለጓደኛህ ይቅር ማለትን ተማር፡፡ መቼም ቢሆን ረስህን ትክክለኛና ፃድቅ አድርገህ በመግለፅ፣ ጓደኛህን እንደ ጥፋተኛ አታድርግ፡፡ ስህተትን በእውነት ለመርሳት ሞክር፡፡ የተሻለ ነገር በማሰብ ወደፊት ተራመድ፡፡ መፅሐፉስ የሚለው ‹‹…በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ…›› አይደል የሚለው! ስለዚህ በግንኙነት ውስጥ መልካምና ዘላቂ የሆነ ነገር ለማግኘት ይቅርታ ጠይቅ፤ ከልብም ይቅር በል፡፡ ከእያንዳንዱ ጥላችሁና ክርክራችሁ በስተጀርባ ግንኙነታችሁን ማቋረጥ ወይም መለያየት እንደመፍትሄ የምታስብ ከሆነ መቼም ቢሆን ችግርህ መፍታት የምትችል አይመስለንም፡፡ ይልቁኑ የሚያስጨንቃችሁን ነገር ወደ ጠረጴዛ ላይ በማምጣት መፍትሄ እስክታገኙና ሁለታችሁም ወደ ቀድሞው መልካም ጓደኛችሁ እስክትገናኙ ድረስ ደጋግማችሁ ተነጋገሩበት፡፡

  1. በመሀከላችሁ መተማመንን አዳብሩ፡፡

በጥንዶች መካከል ያለ መተማመን አንድ ግንኙነት ዘላቂና ወደ ተሻለ ደረጃ ከሚያደርሱ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡ ማንም የማንንም የግል ገመና አሳልፎ ለሌላ ሰው እንደማይሰጥ፤ አንዳችሁ ሌላኛውን ጓደኛችሁን እንደማታታልሉ እርግጠኛ መሆን መቻል አለባችሁ፡፡ ለነገሩ ወደ ፊት ከኛ ጋር አንድ ይሆናል ብለን የምናስበውን ሰው አለማመናችን የወደፊቱን ግንኙነታችንን ከማቀጨጩም ባሻገር፤ እምነት በጓደኛችን ላይ ጥለን የምናገኘውን ደስታና ሰላም በራሳችን ምርጫ እንገፋለን፡፡ እንግዲህ ህይወት በምርጫ የተሞላች ናት፡፡ እኛ የራሳችንን መክረናል፡፡ አንዱንና የሚያዋጣውን መምረጥ ያንተ የባለታሪኩ መብት ድርሻ ነው፡፡

ከላይ ከጠቀስናቸው አምስት ነጥቦች ባሻገር ምክንያታዊ የሆኑ ግቦችን ብታቅድና ብታስቀምጥ (ለምንድነው ግንኙነት መመስረት ያስፈለገኝ ብለህ ራስህን ጠይቀህ)፣ ቁርጠኝነትህን የሚገልፅ አባባል/ፅሑፍ ብታዘጋጅና ለተፈፃሚነቱ ክትትል ብታደርግ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጓደኛህን/እጮኛህን ማመንና ማክበር ብትጀምር፣ ያልተከፋፈለ ትኩረት ለጓደኛህ መስጠትን ብትማር፣ ሳትሰለች ጊዜ እየሰጠሃት የበለጠ እርሷን ለመርዳት ብትሞክር እንዲሁም በቆይታህ ለሚገጥሙህ ያላሰብካቸው ችግሮች/ገጠመኞች ታጋሽ ብትሆን ግንኙነትህ የተሳካ ይሆናል እንልሃለን፡፡ ሞክረው፡፡

አብዛኛዎቹ የስነ ልቦና ምሁራን እንደሚገልፁት ሁሉም ሰው መልካም የሆነ ግንኙነት የመፍጠርና ይዞ የመቀጠል ፍላጎት አለው፡፡ እንደነዚህ አገላለፅ ሰዎች የተረጋጋ ግንኙነትና አመርቂ መስተጋብር አብረዋቸው ካሉ ሰዎች ጋር መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ሰዎች ለብቸኝነት፣ ለድብርት፣ ለጭንቀትና ደስተኛ ላለመሆን ይጋለጣሉ፡፡

ውድ የዚህ አምድ ተሳታፊያችን ስለ ግንኙነት (Relation ship) የተጠኑ የተለያዩ ንድፈ ሀሳቦች አሉ፡፡ አሁን ያለህበት ሁኔታ ከነዚህ አስተሳሰቦች ውስጥ በየትኛው ንድፈ ሀሳብ ተፅዕኖ ውስጥ እንደሆንክ ማወቅ የምትችለው ራስህ ስለሆንክ ጥያቄዎቹን መመለስ ላንተው ትተነዋል፡፡

Attachment theory:-

ይህ ንድፈ ሀሳብ ግንኙነትን የሚመለከተው በህፃንነታችን ወቅት ከነበረን ከቤተሰባችን ጋር ያለንን ቁርኝትና ቅርርብነት ጋር ነው፡፡ በዚያ ወቅት የነበረን መልካምም ሆነ መጥፎ ግንኙነት እያደግንም ስንመጣ በጎልማሳነት እድሜያችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድርብናል፡፡ እንዴት ነበር አስተዳደግህ?

Social Exchange Theory:-

ይህ ንድፈ ሀሳብ ደግሞ ግንኙነትን የሚመለከተው ከጥቅም ልውውጥ ጋር ነው፡፡ ሰዎች ግንኙነቱን የሚመለከቱት በመካከላቸው ካለው ግንኙነት የተነሳ የሚመጣነው ስጦታ ወይም ሽልማት በመመልከት ነው፡፡ አንተ የምትፈልገው ነገር ኖሮህ ከርሷ አጥተሃል? አንተስ መስጠት የሚገባህን ነገር ሰጥተሃል?

Equity theory:-

በሁለተኛ ተራ ቁጥር ያለውን በመቃወም የመጣ ንድፈ ሀሳብ ሲሆን ሰዎች ግንኙነትን የሚመለከቱት ፍትህና እኩልነትን በመፈለግ ነው፡፡ ስለዚህ ከስጦታ መለዋወጥ ይበልጥ እንደሚተሳሰቡ ይናገራሉ፡፡

Relational Dialect:-

እነኚህ ደግሞ ግንኙነትን የሚመለከቱት እንደ ቋሚና የማይለዋወጥ ነገር ሳይሆን ተቀያያሪና ቀጣይነት ያለው ሂደት እንደሆነ ነው፡፡ ግንኙነታችሁ ቀስ በቀስ እየተቀየረ እንደሚመጣ ተረድተሃል? በነገራችን ላይ ዶ/ር የሺጥላ መንግስቱ የሚገባው ማንን ነው በሚል መጽሐፋቸውና ሴቶች በአሰሳ ጊዜ ከወንዶች ምን ጥቃሉ በሚለው ጽሑፋቸው ላ እንደገለፁት ሴቶች ከወንዶች ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀስ በቀስ እንዲያድግ እንጂ ፍጥነት እንዲኖረው አይሹም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነገሮችን ሁሉ መቆጣጠር እንዲችሉና መረጋጋት እንዲኖራቸው ቀጠሮውንም ሆነ በወቅቱ ስለሚደረጉ ነገሮች ቀደም ብለው ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡

እንግዲህ እንደማንኛውም ህይወት እንዳለው ፍጡር ግንኙነት አጀማመር፣ የተወሰነ ፍጡር ግንኙነት አጀማመር፣ የተወሰነ የህይወት ቆይታና መጨረሻ አለው፡፡ ሰዎች እርስ በርስ እየተዋወቁና በስሜትም እየተቀራረቡ በመጡ ቁጥር ግንኙነታቸው እያደገ ይሻሻላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን እያሻሹና ሌላ ግንኙነት መመስረት ሲጀምሩ ግንኑነታቸው እየከሰመና እየጠፋ ይሄዳል፡፡ George levinger የተባሉ የስነ ልቦና ምሁር በ‹‹Development and change›› በተሰኘ ጽሑፋቸው ላይ የግንኙነት እድገት ደረጃዎችን እንደሚከተለው ያስቀምጡአቸዋል፡፡

Acquaintance (ትውውቅ)

ከሰዎች ጋር ስንተዋወቅ ከአሁን በፊት የነበረን ግንኙነትና ቅርርብነት፣ እንዲሁም ስለዛ ሰው በመጀመሪያ በሚኖረን ግምትና ሌሎች ተዛማች ክስተቶች ሊወሰን ይችላል፡፡ ሰዎቹ ከተዋደዱና ቀልባቸው ከተፈቃቀደ ቀጣይነት ያለው መስተጋብራቸው ወደ ሌላኛው ደረጃ ያሻግራቸዋል፡፡

Build-up (መጠንከር)

በዚህ ጊዜ ሰዎች እርስ በርስ መተሳሰብን፣ መግባባትና መተማመን ይጀምራሉ፡፡ በተለያዩ ነገሮችም መጣጣም መቻላቸውና አለመቻቻላቸው የወደፊቱ ግንኙነታቸውን ይወስነዋል፡፡ ለዚህም መወያየትና መነጋጋር ይጠይቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዶ/ር የሺጥላ መንግስቱ ይህ ወቅት ‹‹ህልምና ራዕያችሁ አብሮ ይሄድ አይሄድ እንደሆነ የምትመዝኑበት ጊዜ ነው›› ይላሉ፡፡

Continuation (መቀጠል)

ይህ ደረጃ ጓደኛማቾቹ በጋራ ኃላፊነት የሚወስዱበት ወይም ረዘም ወዳለ ግንኙነት፤ የፍቅር ትስስርና ጋብቻ ቁርጠኛ ሀሳብ የሚይዙበት ነው፡፡ ይህ ጊዜ ሊረዝምና በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ሊሆን ይችላል፡፡ የማያቋርጥ እድገትና ለውጥም በዚሁ ጊዜ ይከሰታል፡፡ ይህ ወቅት መደጋገፍና መረዳዳት እንደሚቻል የምታውቁበት፤ አንዳችሁም ከሌላው ተለይታችሁ ለመኖር አለመቻላችሁን የምትገንዘቡበት ጊዜ ስለሆን ግንኙነታችሁና ፍቅራችሁ አንዳችሁ ለሌለው በምታደርጉት ጥንቃቄና እንክብካቤ ይገለፃል፡፡

Detrioration (መዳከም/መቀነስ)

እዚህ ላይ ሁሉም ግንኙነቶች ይቀንሳሉ ማለት አይደለም፡፡ ይሁንና በግንኙነት ወቅት መሰላቸት፣ አለመረጋጋት፣ አለመደሰትና ሌሎች ተዛማች የሆኑ የችግሮች ምልክቶች ካሉ መቀነሱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሰዎች ግንኙነታቸውን የመቀነስ አንዳንዴም እራሳቸውን የመግለፅ ሁኔታ ያስወግዳሉ፡፡ ይህም ነገር እየቀጠለ በሄደ ቁጥር አለመተማመንና ክህደት እያነገሰ ይሄዳል፡፡

Termination (መፈፀም)

ይህ ጊዜ የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን ግንኙነታቸው መልካም ከነበረ በሞት አሊያም ደግሞ በመለያየት የሚያበቃበት ነው፡፡

እንግዲህ ወንድማችን አንተ የትኛው ደረጃ ላይ እንዳለህ የምታውቀው አንተ ነህ፡፡ ምንም እንኳ የግድ እነዚህን ደረጃዎች ማለፍ አለብህ ባንልም ከአንደኛው ደረጃ ወደ መጨረሻው በአንድ ጊዜ መድረስ ብትፈልግ ጤና አይስለንም፡፡ ቀደም ብለን ከላይ ያስቀመጥናቸውን ምክሮች በደንብ አስተውል፡፡ በግንኙነታችሁም የቆይታ ጊዜ ተለማመዳቸው፡ ረዘም ያለ ግንኙነቱን አትጥላው፤ ቢጠቅምህ እንጂ አይጎዳህም፡፡ የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል አይደል የሚባለው? በተረፈ ከሁኔታዎች በላይ የሆነው አምላክ ይርዳህ፡፡ መፅሐፉስ …እኛ ባሪያዎቹ እንሰራለን፤ የሰማዩም አምላክ ያከናውንልንል ነው አይደል የሚለው? ለዛሬ አበቃን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

Source:: Zehabesha

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.