አንዳንድ ጥንዶች የሴቷ ማርገዝ በወሲብ ህይወታቸው ላይ ምንም አይነት ለውጥ ባይፈጥርባቸውም በአብዛኛው እርግዝና የወንዱንም ሆነ የሴቷን የወሲብ ፍላጎት ይቀይረዋል። የተወሰኑ ጥንዶች እርግዝና የተሻለ የወሲብ ህይወት እንደሰጣቸው ሲመሰክሩ ሌሎች ከባድ ጊዜ ሊያሳልፉ ይችላሉ። ሆኖም በተለይ ከወሊድ በኋላ ብዙዎች ረዘም ያለ እረፍት ይወስዳሉ።
 

pregnancy-sexበዚህ ወቅት በፊት የነበራችሁ ጥሩ የወሲብ ህይወት በጣም እንዳይቀየር ዋናው መፍትሄ ስለምትፈልጉት እና ስለሚሰማችሁ ነገር በግልፅ መወያየት ነው። ሁለታችሁንም የሚያረካ መፍትሄ ፈልጉ። ከዚህ በታች ብዙ ጥንዶች ስለ ወሲብ የሚያሳስቧቸው ነገሮች ተዘርዝረዋል። በሃገራችን ባህል ስለነዚህ ጉዳዮች በግልጽ ማውራት ሊከብድ ይችላል። ይህ ከሆነ ከባለቤትሽ/ባለቤትህ ጋር በመሆን ይህንን ፅሁፍ ማንበብ ነገሮችን ሊያቀል ይችላል።

የግብረ ሥጋ ግንኙነት በእርግዝና ወቅት በእናቲቱ ወይም በልጁ ላይ ችግር ይፈጥር ይሆን?

ይህ ጥያቄ ብዙዎችን የሚያሳስብ ነው። በአጠቃላይ መልሱም በፍፁም ነው። ሴቷ በወሲብ ወቅት በምትረካበት ጊዜ በማህፀን ላይ የመኮማተር (የመጫን) ስሜት ሊፈጥር ይችላል። የእምስ ግርግዳ ስለሚሳሳ በግንኙነት ወቅት በትንሹ ሊደማ ይችላል። እኚህ ሁኔታዎች ባይመቹም በብዛት አደጋ የላቸውም። ለመጀመሪያ ጊዜ የደማሽ እንደሆነ ወይም አደማምሽ ካሳሰበሽ ሃኪምሽን አማክሪ። የደማሽው መጠኑ ብዙ ከሆነ ግን በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ሂጂ። በባለቤትሽ ብልትና በልጅሽ መካከል ብዙ ርቀት ስላለ በተጨማሪም ልጅሽ በማህፀን ግርግዳ፣ እንዲሁም የማህፀን በሩን ዘግቶ ባክቴሪያና የውንዱ የዘር ህዋስ እንዳይገባ በያዘው ዝልግልግ መድፈኛ ከዚያም አልፎ በክርታሱና ውስጡ ባለው የሽርት ውኃ ተከልሎ ስለሚገኝ ወሲብ ልጅሽ ላይ የሚፈጥርበት ችግር አይኖርም።

ጥሩ ግንኙነት ስለመፈፀም

ብዙ እናቶች በእርግዝና ምክንያት በሰውናታቸው ውስጥ ባሉ ሆርሞኖች አማካኝነት እና የብልት ግርግዳዎች ስለሚለሰልሱ በወሲብ ወቅት በቀላሉ ለመራስ ይችላሉ። ስለዚህም በዚህ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ይመቻቸዋል። በጣም ጥሩው ጊዜ በተለይ የመጀመሪያው ሶስት ወር (ብዙ ማቅለሽለሽ የሚሰማበት) ካለፈ በኋላ ፅንሱ ትልቅ ሆኖ ሆድ በጣም እስከሚገፋ በመኃል ያለው ነው።

ሆድሽ ወደፊት ሲገፋስ?

ሆድሽ በሚገፋበት ጊዜ ለወሲብ የሚመች አኳኋን ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ዋናው ነገር የሚመቻችሁን አይነት መንገድ እስክታገኙ መሞከር ነው። ሴቷ በጎኗ ብትተኛ ወይም በጉልበቷ ብትንበረከክ የበለጠ ሊመቻችሁ ይችላል።

ወደ እርግዝና መጨረሻ

በዚህ ጊዜ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። ጉልብት የበዛው ግንኙነት ማድረግ አይመከርም። ቢሆንም አንደኛው ወገን ወሲብ ማድረግ ፈልጎ ሊላኛው ወገን ባይፈልግ ሌሎች ፍቅርን ለመግለፅ ሊደረጉ የሚችሉ ነገሮች አሉና መረሳት የለባቸውም።

ከወሊድ በኋላ

ወሊድ በእያንዳንዷ እናት ላይ የሚፈጥረው ስሜት ይለያያል። ቀላል ወሊድ ከነበረ በቶሎ ወደነበረው ሁኔታ ለመመለስ ይቀላታል። ከባድ ወሊድ ያሳለፈች እናት ደግም አእሮዋም ሆነ ሰውነቷ ዝግጁ እስኪሆን ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድባት ይችላል። በወሊድ ወቅት የማህፀን መውጫ እና አካባቢው ሊቆስልና ህመም ሊሰማ ይችላል። ሆኖም ይሄ የሚድን ሁኔታ ነውና ሊያሳስብሽ አይገባም። በሰውነትሽ ውስጥ ያለው የኤስትሮጅን መጠንም ይቀንሳል። በዚህ ምክንያትም እንደበፊቱ እርጥበት ላይሰማሽ ይችላል፤ ነገር ግን ይሄ የተለመደ ነው። ሊረዳሽ የሚችል ቅባት በፋርማሲዎች ስለሚገኝ ሐኪምሽን ማማከር ትችያለሽ።

ከወሊድ በኋላ ግንኙነት ማድረግ የሚቻለው መቼ ነው?

ከአራት እስከ ስድስት ሳምንት በኋላ ሁኔታዎች በፊት እንደነበሩት ለመመለስ ቢችሉም ብዙ ጥንዶች የበለጠ ጊዜ ይወስድባቸዋል።፡አዲስ ወላጆች እንደመሆናቸው በቤታቸው ለመጣው እንግዳ ህይወት ብዙ ትኩረት ስለሚሰጡ ላያስባቸውም ይችላል። አብሮ በመተኛት እና በመጨዋወት ቀስ በቀስ ድሮ ወደነበረው ፍቅራቸው በሂደት መመለስ ይችላሉ። ይህ እንደገና ለመላመድ እድል ይሰጣቸዋል። ስለስሜታቸው በግልፅ መወያየት በጣም ጥሩ ነው። በተጨማሪ ስለዚህ ጉዳይ ሐኪምን ማማከር ይቻላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.