እርግዝና እና የሰውነት እንቅስቃሴ

0
በእርግዝና ወቅት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ሁሌ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለአጥንቶችና ለጡንቻዎች እድገት እና ጥንካሬ ወሳኝ ነው።
 
Fotolia_39629313_XS-eaf00dbd8fሰውነትሽ እንዲቀልሽና ጤንነት እንዲሰማሽ ይረዳሻል። ስለዚህም በቀን ቢያንስ 30 ደቂቃ የሚሆን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይመከራል። ከዚህ በፊት ምንም አይነት ስፖርት በየጊዜው የማትሰሪ ከነበረ ቀስ ብሎ መጀመሩ ይሻላል። በርግጥ በእርግዝና ወቅት ሰውነትሽ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ለውጦች ስለሚኖሩ፣ ሆድሽ ስለሚገፋና ክብደትሽም ስለሚጨምር በፊት ትሰሪያቸው የነበሩ ስፖርቶች ላይመቹሽ ይችላሉ። ስለዚህ ልታደርጊያቸው ስለምትችያቸው እንቅስቃሴዎች ትንሽ ምክር እንስጥሽ። በእርግዝና ወቅት የሚደረግ እንቅስቃሴ አላማው ጤንነት እንዲሰማሽና ሰውነትሽ ለእርግዝናሽና ለሚጠብቅሽ ወሊድ ብቁ ሁኔታ ላይ እንዲሆን እንጂ ጡንቻ እንድታዳብሪ ወይም ኪሎ እንድትቀንሺ አይደለም። ስለዚህ ሰውነትሽን ማዳመጥና ያለመመቸት ስሜት ሲሰማሽ እንቅስቃሴሽን ማቆም እንዲሁም ሐኪምሽን ማማከር ይኖርብሻል። በዚህ ጊዜ ደስ ሊሉሽ የሚችሉ ብዙ የእንቅስቃሴ አማራጮች አሉሽ። ለምሳሌ መራመድ፣ መዋኘት፣ ሳይክል መንዳት እና ዮጋ የሚጠቀሱ ናቸው።

መራመድ

መራመድ ወይም ዎክ ማድረግ ብዙዎችን የሚስማማ እንቅስቃሴ ነው። ሰውነትሽን ትንሽ ሙቀት እንዲሰማሽ የሚያስችል ቶሎ ቶሎ ያለ ፍጥነት ይዘሽ ለ30ደቂቃ ያህል በሳምንት ሶስት ቀናት ብታደርጊው በጣም በቂ ነው። በተጨማሪም ዎክ ማድረግ ብዙ ዝግጅት የማይጠይቅና በቀንሽ ውስጥ በቀላሉ ጊዜ ልታገኚለት የምትችይው (ለምሳሌ ከስራ ወደ ቤት ስትመለሺ) ቀላል የእንቅስቃሴ ምርጫ ነው።

ሳይክል መንዳት

አዲስ አበባችን ምንም እንኳን ብስክሌት ይዘሽ በከተማው ወይም በፓርኮቿ ዞር ዞር እያሉ ለመንዳት የምትመች ባትሆንም በመዲናችን ምቹ የሆኑ ሳክሎች ያሏቸው ጂሞች ስላሉ አንደኛው ጋር በመመዝገብ በሳምንት የተወሰኑ ቀናት ሳይክል በመንዳት እንቅስቃሴ ማድረግ ትችያለሽ። ይህ ስፖርት በጉልበት፣ ቁርጭምጭሚትና ወገብ ላይ ብዙ ጭነት ስለማይፈጥር ጥሩ ስፖርት ነው። ታድያ ሳይክል በምትነጂበት ወቅት ቆመሽ መሆን የለበትም።

መዋኘት

በመዲናችን አንዳንድ ሆቴሎችና ጥቂት ጂሞች የመዋኛ ገንዳ ስላላቸው ውኃ ውስጥ ገብተሽ ጡንቻዎችሽን እየለጠጥሽ እና ሰውነትሽን ፈታ እያደረግሽ መዋኘት ፍቱን እንቅስቃሴ ሊሆንሽ ይችላል። ስትጀምሪ እስከ አስር ደቂቃ ዋኚና ቀስ በቀስ ጊዜውን እያረዘምሽው ትሄጃለሽ። ይህ እንቅስቃሴ በመገጣጠሚያዎች ላይ የሚኖረው ጫና በጣም አንስተኛ በመሆኑ በተለይ ጅማቶሽ በሆርሞኖች አማካኝነት በሚላሉበት በእርግዝና ወቅት ተመራጭ እንቅስቃሴ ነው።

ኤሮቢክስ

በተለይ ከእርግዝናሽ በፊት ኤሮቢክስ ትሰሪ እንደነበረ አሁን ማቋረጥ አይጠበቅብሽም። ነገር ግን በመገጣጠሚያዎች ላይ ጫና የሚፈጥሩና የሆድ ጡንቻዎችን በብዛት የሚያሰሩ እንቅስቃሴዎችን መጠንቀቅ ይገባል። ስለዚህም የኤሮቢክስ አሰልጣኝሽን ማማከር እና ነፍሰ ጡር እንደሆንሽ መንገር ይገባሻል። በተጨማሪም በተለይ እርግዝና እየገፋ ሲሄድ በጣም የሚጮህ ሙዚቃ ፅንሱ ላይ ተፃዕኖ እንደሚያመጣ የሚያመላክቱ ግኝቶች ስላሉ ይህንንም ግምት ውስጥ ማስገባት ይሻል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.