ይህንን ሱስ ለማሸነፍ የሚከፈለው ዋጋ ሱሱ ውስጥ በመቆየት ከሚከፈለው ዋጋ እጅግ ያነሰ ነው፡፡

sex-addiction-counselor    በዚህ ዘመን ከመረጃ መረብ መስፋፋትና ከግለሰቦች የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ጋር ተያይዞ እየተስፋፋ የመጣው አንዱ ችግር የሰዎች ለግልፅ ወሲብ ምስሎችና ፊልሞች ተጋላጭ መሆን ነው፡፡ በማማከር አገልግሎት ከሚያጋጥሙ ጉዳዮች በመነሳት የግልፅ ወሲብ ምስሎች/ፊልሞች ሱሰኛ የሆኑ በርካታ ወጣቶች እና ጎልማሶች እንዳሉ መገመት ይቻላል፡፡ ባለሙያዎችም የሚከተለውን መፍትሄ ይለግሳሉ፡፡

ችግርን ለባለሙያ ማማከር አያሳፍርም

በቅድሚያ ለችግር መፍትሄ ለማግኘት በራስ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሩ ከአቅም በላይ ከሆነ ባለሙያ ማማከር አስፈላጊ ርምጃ ነው፡፡ የሙያው ስነምግባር የሚያከብርና ብቃት ያለውን የሥነ-ልቦና አማካሪ ማማከር አያሳፍርም፡፡ በስነ ልቡና አማካሪዎች ዘንድ ግለሰቦች ማንኛውንም የሥነ-ልቡና ችግርና ህይወታችንን ያለምንም ሀፍረት ማማከር እንዲሁም መወያየት ይቻላል፡፡ ሐፍረትን ፈርቶ ከችግር ጋር ከመኖር ይልቅ የሚያሳፍርን ነገር ተናግሮ መፍትሄ ማግኘት የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ በአውዳችንም ‹‹በሽታውን የሚደብቅ መድሃኒት አያገኝም›› እንደሚባል ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በራስ መፍታት ያልቻሉትን ችግር ወደ ባለሙያ መውሰድ የተሻለ ነው፡፡

ያልተሟላ ፍላጎትን መፈለግ

የወሲብ ፊልም ሱሰኛ እንድንሆን የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ከነዚህ መካከልም ያልተሟላ ፍላጎት አንዱ ነው፡፡ በጤናማ መንገድ ያልተሟላን የወሲብ ዕርካታ  የወሲብ ፊልሙ እየሞላ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ግን ዘላቂ እርካታ ሊሰጥ እንደማይችል እውነት ነው፡፡ ይልቁንም ገንዘብን፣ ጊዜን፣ የአዕምሮ ትኩረትን፣ ከሴቶች ጋር የሚኖርን ግንኙነት፣ አስተሳሰብንና ህሊናን እያበላሸ እንደሆነ መረዳት ያሻል፡፡

የወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችንና ፊልሞችን መመልከት በሕይወት ውስጥ የሚፈለገውን እርካታ አይሰጥም፡፡ በመጀመሪያ ጥቂት መመልከት እርካታ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ ከዚያ በኋላ እንደ መጀመሪያው እያረካ አይሄድም፡፡ ስለዚህ የተለየ ነገር መፈለግ ይጀመራል፡፡ እንዲሁም ከመለማመድ አንፃር ብዙ ካልታየ እርካታ ላይ መድረስ ላይቻል ይችላል፡፡ ከህይወት ጋር ያለው ክፍተትም እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ውስጣዊ ባዶነትም እየተሰማ ይመጣል፡፡

ስለዚህ መፍትሄ የሚሆነው እነዚህን ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች የሚታዩበትን ምክንያት ማወቅ ነው፡፡ ከነዚህ ፊልሞች የሚገኘውን ጥቅምና እርካታ ምን እንደሆነ መፈተሽ ጠቃሚ ነው፡፡ የወሲብ ፊልሞች ዋነኛ አላማ ተገንዘብ፡፡ በአብዛኛው ለገንዘብ ተብለው እንጅ ለትምህርት የሚሰሩ አይደሉም፡፡…. የወሲብ ፊልሞች በቲያትር መልክ ለሽያጭ የቀረቡ ሸቀጦች ናቸው እንጅ እውነተኛውን ባህልና ወግ እንዲሁም ነባራዊ እውነታውን አያሳዩም፡፡ … እናም ያልተሟላ ፍላጎትን አውቆ በተፈጥሮአዊው መንገድ ለማሟላት መጣር መልካም ነው፡፡

ወደ ተጨባጭ ነባራዊ እውነታ መመለስ

በወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች ውስጥ የሚታዩ ሴቶች በጣም ውብና ማራኪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ለገበያ የተቀለሰ ስልት ነው፡፡ ስለዚህ በአካባቢያችን የምናገኛቸው ሴቶች ከእነሱ እኩል ቆንጆ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በፊልም የሚታዩ ሴቶችንም እንደ ፍቅር ጓደኛ መሳል ይመጣል፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ እነዚያ ሴቶች በልብ ወለድ ውስጥ እንደምናያቸው ገፀ ባህርያት ናቸው እንጂ በነባራዊ እውነታው ውስጥ የሚገኙ አይደሉም፡፡

በወሲብ ፊልሞች ውስጥ ያሉት የቃላት ልውውጦችና የወሲብ ክንውኖች ከፍቅር ጓደኛ ጋር ከሚደረገው የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚያ ትያትር እየሰሩ እንደሆነ አስብ፡፡ ስለዚህ በፊልም ውስጥ እንደሚታየው ያለ ወሲብ በተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ላይገኝ ይችላል፡፡ አስተውል በተለይም ባህላችን ለእንስሳዊ ልቅ ወሲብ ክፍት አይደለም፡፡ ወደራስህ ተመለስ፡፡

ሱስ ካለብህ ቀስበቀስ ቀንስ

የሱሰኝነት አንዱ ባህሪ በየጊዜው መጠኑ ካልጨመረ በስተቀር እርካታ አለመስጠቱ ነው፡፡ ስለዚህ ሱስ ያለበት ሰው በትናንቱ መጠን እርካታ አያገኝም፡፡ የመውጫ መንገዱ ይህንን እየጨመረ የሚሄደውን መጠን በየጊዜው እየቀነሱ መሄድ ነው፡፡ የመጠን መቀነስ ለጊዜው ጥሩ ስሜት ባይሰጥም ይህንን በመቋቋም ከሱስ መውጣት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት በሱስ ላይ አለቃ መሆን ማለት ነው፡፡

ሌሎች አስደሳች ስራዎችን መፈለግ

የወሲብ ፊልሞች በምታይበት ጊዜ ሌሎችን ተኪ፣ አስደሳችና አዝናኝ ስራዎችን ፈልግ፡፡ ፊልሙን እይ፣ እይ የሚል ውስጣዊ ስሜት ሲጎተጉትህ በሌሎች ስራዎች ተጠመድ፡፡

የልብ ጓደኛ ይኑርህ

ለአማካሪ መንገር ካልተቻለ ለልብ ጓደኛ መንገር ጠቃሚ ነው፡፡ ከወንድ ጓደኞችህ መካከል ላንተ ቅርበት ያለው፣ ሚስጥር ጠባቂና በጎ ነገር የሚያስብ፣ እውነትን ሳይደብቅ በመልካም አቀራረብ ሊነግርህ የሚችል ጓደኛህን እየታገለህ ስላለው ስሜት ንገረው፡፡ ይህ ሰው ከአንተ ጋር ፊልሞችን የሚያይ መሆን የለበትም፡፡

ከወሰንህ ከችግርህ መውጣት ትችላለህ

ከልብ ከወሰንህ ከዚህ ሱስ መውጣት ትችላለህ፡፡ በራሳችን ላይ አለቃ እንዲሆን ያደረግነውን ሱስ ዳግም ባሪያ ማድረግ እንችላለን፡፡ ሽንፈትና ማሸነፍ በውሳኔያችን ቆራጥነት እና ተግባራዊነት ላይ የሚወሰን ይሆናል፡፡

ምንጭ፡- ጤና ስጥልኝ (ለድረ-ገፅ ንባብ እንዲመች በጥቂቱ የተስተካከለ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.