ካንሰር ምንድነው ?

ቴዎድሮስ ታደሰ
ምንጭ : ናሽናል ካንሰር ኢኒስትቲዩት

ካንሰር የሚለው ቃል በብዙዎቻችን ውስጥ መጥፎ ስሜትን ከሚያጭሩ ቃላት አንዱ ነው

different types of cancerበሽታ ባይወደድም አንዱ በሽታ ከሌላው ይሻላል ለምሳሌ ቶሎ የሚድን :የህክምና መፍትሄ ያለው : እጅግ ብዙ የማያሰቃይ : በቀላሉ የማይተላለፍ : በአንድ ጊዜ ብዙ ህዝብ የማይጨርስ

ካንሰር ግን እጅግ ክፉ ነው የተለያዩ አይነት የካንሰር በሽታዎች ቢኖሩም በደፈናው ካንሰር ሲባል ውስጣችን ክፉኛ ይረበሻል በአለማችን ላይ ግንባር ቀደም ለሞት የሚዳርጉ ከሚባሉ በሽታዎች ተርታ የሚሰልፍ ነው

ለዛሬ መሰረታዊ የሆነ የካንሰር ግንዛቤ እንዲኖረን ከናሽናል ካንሰር ኢኒስትቲዩት ያገኘነውን መረጃ አጠር አድርገን እናቀርባለን

ካንሰር በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ጤነኛ ያልሆኑ ሴሎች ያለ ምንም ገደብና ቁጥጥር በመብዛት ሌሎች ጤነኛ የሆኑ ሴሎችን ሲወሩ እና መደበኛ ስራቸውን እንዳያከናውኑ እክል ሲፈጥሩ ያለውን ሁኔታ የሚገልፅ ቃል ነው እነኚህ ጤነኛ ያልሆኑ ሴሎች ወደሌላው የሰውነት ክፍል በደም እና በሊምፋቲክ ሲስተም በቀላሉ ይዛመታሉ

ካንሰር አንድ በሽታ አይደለም ከመቶ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አይነት የካንሰር በሽታዎች አሉ አብዛኛዎቹ ካንሰሮች ስያሜያቸውን የሚያገኙት በተነሱበት የሰውነት ክፍል ስም ነው ለምሳሌ ከጡት የሚነሳ ካንሰር የጡት ካንሰር ይባላል ቆዳ ውስጥ ካሉ ሜላኖሳይት ከሚባሉ ሴሎች የሚነሳ ካንሰር ሜላኖማ ከሳንባም የሚጀምር እንደዚሁ የሳንባ ካንሰር ይባላል

የካንሰር በሽታዎች በአምስት ታላላቅ ክፍሎች ይመደባሉ እነዚህም

፩ . ካርሲኖማ (Carcinoma) – ይሄ አይነቱ ከቆዳ ላይ ወይም የውስጥ የሰውነት ክፍሎችን ከሚሸፍኑ ቲሹዎች ላይ የሚነሳ ነው ለምሳሌ ስኳመስ ሴል ካርሲኖማ : ባዛል ሴል ካርሲኖማ : አዲኖ ካርሲኖማ

፪. ሳርኮማ (Sarcoma) – ይህ አይነቱ ካንሰር የሚነሳው ከአጥንት : ከደም ስሮች : ከጡንቻ : ከካርትሌጅ እና ሌሎች ኮኔክቲቭ ቲሹ ከሚባሉት ነው

፫. ሊዩኬሚያ (Leukemia) – ይህ የሚጀምረው የደም ሴሎች ከሚሰሩበት ከአጥንት መቅኔ ነው ከዛም ወደደም ውስጥ በመግባት ጤነኛ የሆኑ የደም ሴሎችን ያውካል

፬. ሊምፎማ እና ማይሎማ (Lymphoma and Myeloma) – ይህ ደግሞ የሚመነጨው የሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅም ወይም ኢሚውን ሲስተም ከሚመሰርቱ ሴሎች ነው

፭. የአይምሮ እና የነርቭ ካንሰር (Central Nervous System Cancers) – ከአይምሮ እና ከስፓይናል ኮርድ ይነሳል

የካንሰር መጀመሪያው የት ነው ?

ካንሰር የሚጀምረው ከሰውነታችን መሰረታዊ አካል ከሆነው ከሴል ነው ስለካንሰር ለመረዳት ጤነኛ የሆኑ ሴሎች ወደ ካንሰር ሴሎች ሲቀየሩ ምን እንደሚፈጠር መረዳት ያሻል

ሰውነታችን በጣም ብዙ ከሆኑ የተለያዩ ሴሎች የተገነባ ነው እነዚህ ሴሎች ሰውነታችንን በጤና ለመጠበቅ ከፍተኛ ቁጥጥር ባለው ሁኔታ በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ መሄድና ማደግ አለባቸው ሴሎች አርጅተው ወይም ተጎድተው በሚሞቱበት ጊዜ በሌላ አዳዲስ ሴሎች መተካት አለባቸው

ይሄ እጅግ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት እድገትና መብዛት አንዳንድ ጊዜ ከቁጥጥር አምልጦ ጤነኛ ያልሆነ መንገድ ሊከተል ይችላል የካንሰር ቁምነገሩ እና መነሾውም እዚህ ላይ ነው በተለያየ ምክንያት በሴል ውስጥ ያለው ዲ. ኤን. ኤ ጉዳት ሊደርስበት ወይንም ሊቀየር ይችላል በመቀጠልም ይህ የተበላሸ ወይንም የተጎዳ ዲ. ኤን. ኤ ጤነኛና መደበኛ ያልሆነ የሴል ዲቪዥን ወይም ክፍፍልን ይፈጥራል

መሞት የሚገባቸው ሴሎች ሳይሞቱ ይቀራሉ አልያም ሰውነት የሚፈልጋቸው ጠቃሚ አዳዲስ ሴሎች ሳይፈጠሩ ይቀራሉ እነኚህ ጤነኛ ያልሆኑ ሴሎች ይበዙና ትዩመር (tumor) ይባላሉ

ነገር ግን ሁሉም ትዩመሮች ካንሰርን ያመጣሉ ማለት አይደለም ካንሰርን የማያስከትሉት በናይን (benign) ትዩመርስ ይባላሉ እነኝህ በቀላሉ ተቆርጠው ሊወጡ ይችላሉ ተመልሰውም አይመጡም ወደሌላ የሰውነት ክፍልም አይዛመቱም

ካንሰርን የሚያስከትሉት ደግሞ ማሊግናንት (malignant) ትዩመርስ ይባላሉ እነዚህ በጣም አደገኛዎቹ እና ጎረቤት ያሉ ሴሎችን የሚወሩ ወደሌላም የሰውነት ክፍል በቀላሉ የሚዛመቱ ናቸው የካንሰር ሴሎች ከአንዱ የሰውነት ክፍል ወደሌላው በቀላሉ የሚዛመቱበት ሂደት ሜታስታሲስ (metastasis) ይባላል

ስለካንሰር ጥቂት ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን በሌላ ጊዜ ስለተለያዩ አይነት ካንሰሮች ባህሪ እና ስለሚኖራቸው ሕክምና እንዲሁም ከካንሰር ጋር ተዛማች ስለሆኑ ጉዳዮች ጠቃሚ መረጃ እናሰፍራለን

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.