ሴቶች በስትሮክ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው


የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት ውስጥ ሰቃይ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ቆይታ አጠናቆ ሊመረቅ የወራት እድሜ ቀርተውታል፡፡ 


strokeወላጆቹ የቤቱ የበኩር ልጅ የሆነውን ይህን ወጣት በታላቅ ተስፋ ነው የሚጠባበቁት፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት የድህነት ኑሮ የሚታደጋቸው፣ ለታናናሽ ወንድምና እህቶቹ ተስፋ የሚሆናቸው እሱው እንደሆነ በማመን፣ ያቺን የምረቃ ጊዜውን የሚጠብቁት በጉጉት ነው፡፡ ጊዜው የፈተና ወቅት በመሆኑ፣ ዮናስ ቀንና ሌሊት በጥናትና በመመረቂያ ፅሁፍ ዝግጅት ላይ ተጠምዶ ሰንብቷል፡፡ አልፎ አልፎ ከባድ ራስ ምታት ህመም ይሰማው የጀመረውም በዛው ሰሞን ነበር፡፡ ሆኖም የህመም ስሜቱም የከፋ ጉዳት ሊያስከትልበት የሚችል ጠቋሚ ምልክት እንደነበር ፈፅሞ አልገመተም፡፡ ህመም በተሰማው ጊዜ ወፍራም ቡና በመጠጣት፣ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች በመውሰድ፣ ስሜቱን ለማስወገድ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዛው ሰሞን አንድ ሌሊት ለሰዓታት ከእንቅልፍ ጋር እየታገለ ሲሰራ ቆየ፡፡ ቀጣዩ ቀን የመመረቂያ ፅሑፉን ለአማካሪው የሚያቀርብበት ዕለት በመሆኑ ሃሣብ ገብቶታል፡፡ ወደ መኝታው ያመራው ሌሊቱ ከተጋመሰ በኋላ ነበር። ቀሪ ስራዎቹን ደግሞ በሌሊት ተነስቶ ለማጠናቀቅ በማሰብ፣ መፅሃፍቶቹን እንኳን ሳይሰበስብ ወደ መኝታው አመራ፡፡ የጠዋቱ ሰዓት እየገፋ ቢመጣም፣ የዮናስ የመኝታ ክፍል አለመከፈት ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ፤ በሩን በተደጋጋሚ አንኳኩ፡፡ ምላሽ የለም፤ ከውስጥ የሚሰማ የማንቋረርና የማቃሰት ድምፅ ክፉኛ አስደነገጣቸው፡፡  በሩን ሰብረው ሲገቡም ዮናስ ከመኝታው ተንሸራቶ በወደቀበት ሥፍራ ላይ ሆኖ ያንቋርራል፡፡ አይኖቹ ፈጠዋል። እጅና እግሮቹ ይንቀጠቀጣሉ፡፡ እየተጯጯሁ ወደ ክሊኒክ ወሰዱት፡፡ በአቅራቢያቸው ያለው ክሊኒክ፤ ችግሩ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ በመግለፅ ወደ ሆስፒታል እንዲሄዱ መከራቸው፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዱ፡፡ ምርመራ ያደረጉለት ሃኪሞችም ዮናስ የስትሮክ ችግር እንደገጠመው ግምት እንዳላቸው ጠቁመው፤ አስቸኳይ የሲቲ ስካን ምርመራ አዘዙለት፡፡ የምርመራው ውጤትም የቀኝ የአንጎሉ ክፍል ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የሚያሳይ ሆነ፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ ለዚህ ችግር መነሻ ምክንያቱ ዮናስ ለቀናት በውጥረትና በጭንቀት የተሞላ ጊዜ ማሳለፉ እንደሆነ ተናገሩ። ሃኪሞቹም ሆኑ ቤተሰቦቹ ዮናስ ባጋጠመው ክፉ እጣ እጅግ አዘኑ የዮናስን ህይወት ለማትረፍና የደረሰበትን ዘላቂ የአካል ጉዳት ለመቀነስ፣ ሃኪሞቹ ከፍተኛ ጥረት አደረጉ፡፡ የሃያ ሁለት ዓመቱ ወጣት፣ በዚህ እድሜው ግማሽ የሰውነቱን ክፍል ለማዘዝ አለመቻሉና አንደበቱ መያዙ ልብ የሚሰብር ገጠመኝ ነበር፡፡ የማሰብና የማስታወስ ችሎታውም በከፍተኛ መጠን ቀንሷል፡፡ ለቤተሰቦቹ አጋርና ደጋፊ ይሆናል ተብሎ ተሰፋ የተጣለበት ይህ ወጣት በ 22 ዓመት ዕድሜው ያለሰው ድጋፍ የማይንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ሆነ፡፡ ሀሳቡን በአንደበቱ ብቻ ሳይሆን በፅሁፍ እንኳን መግለፅ አለመቻሉ የዮናስን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቹንና በቅርብ የሚያውቁትን ሰዎች ሁሉ ልብ የሰበረ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህንን የዮናስን አሳዛኝ ታሪክ ያጫወተኝ ለፊዚዮቴራፒ ህክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል በየጊዜው የሚያመላልሰው ታናሽ ወንድሙ ነው፡፡ (የዚህን ወጣት ገጠመኝ ማግኘት እንድችል የተባበሩኝ ሲስተር ትዕግስት አስቻለውን በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡) 


ዛሬ የእነዮናስ ቤት ተስፋ የራቀውና የሃዘን ድባብ ያረበበበት ቤት ሆኗል፡፡ ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ ተስፋቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ለራሱ፣ ለቤተሰቦቹና ለአገሩ ብዙ ማድረግ ይችል የነበረው ወጣት፤ ገና ሩጫውን በጀመረበት የወጣትነት ዕድሜው የአልጋ ቁራኛ የመሆን ክፉ እጣ ወደቀበት፡፡ አሁን አሁን በዮናስ ዓይነት በሽታ የሚጠቁ ወጣት ኢትዮጵያውያን ቁጥር መበራከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጠቅላላ ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ዳዊት አብርሃም እንደሚናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በስትሮክ ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡና ዘላቂ ለሆነ የአካል ጉዳት የሚጋለጡ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ 


ዶ/ር ዳዊት ከአመታት በፊት Characteristics and outcomes of Stroke at Trkur Anbesa teaching Hospital Ethiopia” በሚል ርዕሰ በሆስፒታሉ የተካሄደን ጥናት ጠቅሰው እንደሚናገሩት፤ የስትሮክ ችግር ገጥሟቸው ወደሆስፒታሉ ከመጡ ህሙማን መካከል አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው የወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ስትሮክ የበርካታ ወጣቶችን ህይወት በመቅጠፍ እና ለአካል ጉዳት በመዳረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ያመለከተው ጥናቱ፤ በወጣትነት ዕድሜያቸው የስትሮክ ችግር ገጥሟቸው ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ህሙማን መካከል ወደ አርባ በመቶ የሚጠጉት በዚሁ ችግር ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይጠቁማል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ለመጣው የስትሮክ ችግር ዋንኛ መንስኤዎቹ፡- ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብ ህዋሳትና የደም ቧንቧዎች በቅባትና በሌሎች ነገሮች መዘጋት፣ በተደጋጋሚ የሚያጋጥምና በአግባቡ ታክመው ያልዳኑት የቶንሲል ህመም፣ የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን፣ ከልክ ያለፈ ክብደትና እንቅስቃሴ አለማድረግ እንደሆኑ ባለሙያው ገልፀው፤ በተለያዩ ሱሶች መጠመድና የአልኮል ሱሰኝነትም ለስትሮክ ተጋላጭነትን በእጥፍ እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ 


ወደጭንቅላታችን የሚደርሰው የደም ኦክሲጂንና ንጥር ምግቦች በተለያዩ ምክንያቶች ሲቋረጡ የሚፈጠረው የጭንቅላት ህዋሳት መሞት (ስትሮክ) ሁለት አይነቶች ናቸው፡፡ ኢስኬ ሚክ ስትሮክ እና ሄሞራጂክ ስትሮክ በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡

 

ኢስኬሚክ ስትሮክ የምንለው፣ ኦክሲጂንና ንጥረ ምግቦችን ወደ ጭንቅላታችን የሚያስተላልፉት የደም ቧንቧዎች፣ በረጋ ደም ሳቢያ ሲዘጉና ደም የማስተላለፍ አቅም ሲያጡ የሚከተሉት የስትሮክ አይነት ሲሆን ጭንቅላት ኦክሲጂንና ንጥረ ምግቦችን ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ስራውን በአግባቡ ለመስራት አይችልም፡፡ በዚህ ጊዜ ስትሮክ ተፈጠረ ይባላል፡፡ ሌላው ሄሞራጂክ ስትሮክ የሚባለውና በጭንቅላት ውስጥና በዙሪያው ያሉ የደም ቧንቧዎች በድገት በመፈንዳታቸው ምክንያት በሚከሰት የደም መፍሰስ ሳቢያ የሚከሰት ነው፡፡ ይህ በጭንቅላታችን ውስጥ የፈሰሰው ደም፣ ለጉዳት እጅግ ቅርብ በሆነው የጭንቅላት ህዋሳቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ጉዳቱም ህዋሳቶቹን ለሞት ይዳርጋቸዋል። የሞቱ የጭንቅላት ህዋሳት ደግሞ ህይወት ዘርተው ወደ ቀድሞ ተግባራቸው የመመለስ እድላቸው፣ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በህክምና እርዳታ ሊደረግ የሚችለው ከሞቱት ህዋሳት አቅራቢያ ያሉትን በማከም፣ ለማዳንና ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ በማድረግ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ በመጣር እንደሆነ ዶክተር ዳዊት ይገልፃሉ፡፡ 


ስትሮክ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ የመከሰት ዕድሉም በዛው መጠን እየጨመረ የሚሄድ ችግር እንደነበር የጠቆሙት ዶክተር ዳዊት፤ በአሁኑ ወቅት ግን በወጣቶች ላይ በስፋት መታየቱ ችግሩን አሳሳቢ አድርጐታል ብለዋል፡፡ በተለይ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ በስፋት እየታየ ያለው የስትሮክ ችግር ዋንኛ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ዶ/ር ዳዊት ከጠቆሟአቸው ጉዳዮች መካከል በውጥረት የተሞላና ያልተረጋጋ ህይወትን መምራት፣ በበርካታ ሃላፊነቶች በመወጠር አዕምሮን የሚያስጨንቁ ስራዎችን መስራት፣ የአልኮል መጠጥና የተለያዩ እፆች ሱሰኛ መሆን የጤና ምርመራዎችን አለማድረግ ዋንኞቹ ናቸው፡፡


 በድንገት በመከሰትና ያለማስጠንቀቂያ ለሞትና ለአካል ጉዳት በመዳረግ የሚታወቀው ስትሮክ ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት ወይንም ሰዓታት በፊት የሚያሳያቸው ምልክቶች እንዳሉ የገለፁት ዶ/ር ዳዊት፤ እነዚህም ከፍተኛ ራስ ምታት፣ የመደንዘዝ ስሜት፣ ትኩረት ማድረግ አለመቻል፣ መፍዘዝና መሰል ስሜቶች ችግሩ እየመጣ መሆኑን አመላካቾች ናቸው ብለዋል፡፡ 


በቀድው ዘመናት፣ ያደጉት አገራት ህዝቦች ሥጋት የነበረውና በበለፀጉት አገራት ህዝቦች ዘንድ በስፋት የሚታየው ስትሮክ፤ ዛሬ በአብዛኛው የታዳጊ አገራት የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በድሃ አገራት ህዝቦች ላይ ባደረገውና በ2012 ይፋ በሆነው ጥናት እንዳመለከተው፤ ስትሮክ በድሃ አገራት ህዝቦች ላይ በስፋት የሚከሰት የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን ጠቁሞ፤ ችግሩ ሞትና ዘላቂ የአካል ጉዳት የማስከተል ዕድሉም ከአደጉት አገራት በአራት እጥፍ እንደሚበልጥ አመልክቷል። በእነዚህ አገራት ከሚኖሩ 100ሺ ሰዎች መካከል ሃያ አምስት የሚሆኑት በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ በስትሮክ የመጠቃት እድል እንደሚገጥማቸውም ገልጿል፡፡ 


ስትሮክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን የጠቆመው የጤና ድርጅቱ፤ ከወንዶች ይልቃ ሴቶች ለስትሮክ ችግር የበለጠ እንደሚጋለጡም ገልጿል፡፡ ስትሮክን አክሞ ማዳን እንደማይቻል የሚናገሩት የህክምና ባለሙያው፤ ይህ ታውቆ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት በመከላከሉ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ይላሉ። ስትሮክ እንዳያጋጥም ለማድረግም የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል፣ የደም ግፊት፣ የኮሌስትሮልና የስኳር መጠንን መቆጣጠር፣ የልብ ህመምን፣ ያልተስተካከለ የሰውነት ክብደትን ማስወገድ፣ የቶንሲል ህመም በሚያጋጥም ወቅት ህክምናውን በአግባቡ ተከታትሎ ማዳን፣ ከአልኮልና ከዕፅ ሱሰኝነት መራቅ፣ አጠቃላይ የጤና ምርመራዎችን በየጊዜው ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል – ባለሙያው፡፡ 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.