ሲጋራ አጫሾችን እንደማበረታታት አይቆጠርብኝ፤ ደግሞም የመረጃ ክፉ የለውምና ዛሬ ስለ ኤሌክትሮኒካዊው ሲጋራ (E-cigarette or Personal Vaporizer (PV)) ላወራችሁ ወደድኩ፡፡

E-cigarateኢ-ሲጋሬት በኣጫጫስ ባህሉ፣ በቅርፁ፣ በመጠኑ፣ በአማማጉ እና በኒኮቲን ንጥረ ነገሩ ልክ እንደማንኛውም የቶባኮ ሲጋራ ቢመስልም ጭስ አልባ፣ ጎጂ ጥቀርሻ  የለሽ (No Tar)፣ አመድ አልባ፣ መጥፎ የአፍጠረን የማይፈጥር፣ ሁለተኛ ወገን ላይ ጉዳት የማያደርስ እና ከባቢ አየር ላይም ካርቦን ሞኖክሳይድ የማይለቅ ነው በማለት አምራቾቹ ይሟገቱለታል፡፡

በጥናት አቅራቢዎች እና በጤና ድርጅቶች አማካኝነት የኢ-ሲጋሬት ጥቅም እና ጉዳት እስካሁን ይህ ነው የሚባል ነገር ላይ ባይደረስም የተጠቃሚው ቁጥር በተለይ የቶባኮ ሲጋራ የህዝብ መገልገያ ቦታዎች ላይ እንዳይጨስ ከተከለከለ ወዲህ የኢ-ሲጋሬት ተጠቃሚ ቁጥረ ይበልጥ እየጨመረ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በእንግሊዝ ብቻ  እ.ኤ.አ 2013 ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ተገንዝበዋል፡፡ ከዚያም በላይ አንዳንድ ተጠቃሚዎች የቶባኮ ሲጋራን ጨርሶ ለመተው እንዳስቻላችውም መስክረውለታል፡፡

የኢሲጋሬትን ቀደምት ታሪክ ስንመለከት ኽርበርት ኢ ጊልበርት እ.ኤ.አ 1963 ላይ እንድ ጭስ አልባ ኢ-ቶባኮዋዊ ሲጋሬት (Smokeless non-tobacco cigarette) መጠቀሚያ መሳሪያ የፈጠረ ሲሆን ይህ መሳሪያ በውስጡ ያለውን ፈሳሽ ኒኮቲን በማሞቅ እንፋሎት እንዲፈጠር በማድረግ እና ወደ ውስጥ በቀላሉ ለመማግ እንዲመች ተደርጎ የተሰራ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ 1967 በፈጠራው የተደነቁ ብዙ ካምፓኒዎች መሳሪያውን ለማምረት እና በይበልጥ ለማስፋፋት ጊልበርትን ቀርበው አነጋግረውትም ነበር፡፡ ይህ ፈጠራ ነው እንግዲህ ለዛሬው ኢ-ሲጋሬት መነሻ ሃሳብ ሆኖ የሚነገርለት፡፡

በኃላም እ.ኤ.አ. 2004  መሳሪያው በቻይና የውስጥ ገበያ የተለመደውን ሲጋራ እንዲተካ እና እስከመጨረሻው ለማቆም እንዲረዳ ተደርጎ ቀረበ፡፡ ሆን ሊክ ይሰራበት የነበረው እና ጎልደን ድራጎን ሆልዲንግስ ተብሎ ይታወቅ የነበረው ቀጥሎም ስሙን በመቀይር ሩያን (Ruyan/Resembling Smoking) የተባለው ካምፓኒ ምርቱን ለውጭ ገበያ እ.ኤ.አ 2005/6 ማቅርብ ጀመረ፡፡ ዓለም አቀፉን የንግድ ፍቃድም እ.ኤ.አ 2007 ላይም አገኘ፡፡

ኢ-ሲጋሬት ሶስት ዋና ዋና ክፍሎችን ይይዛል፡፡ የመጀመሪያው ካርቲሬጅ (Cartridge) ይባላል፡፡ ሞላላ ክብ የሆነና ሁለት ጫፎቹ በፕላስቲክ ወይም በሜታል የተሸፈነና አንደኛው ጫፍ ወደ አፋችን አስገብተን የምንምግበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ፈሳሹን ክፍል በጠብታ ወደ አቶማይዘሩ የሚልክበት ይሆናል፡፡ አንድ ካርትሪጅ የሃያ ሲጋራ ፑፍ (Puff) መጠንን  ይይዛል፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ Atomizer ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ ፈሳሹ በማሞቅ እና ወደ ትነት እንዲቀየር በማድረግ እንዲወጣ የሚያደርገውን ሙቀትን የያዘ ነው፡፡ አቶማይዘሩ መሃል ላይ የሚገኝ ሲሆን ኢ-ሲጋሬትን የሞላላ ክብ (Cylinder) ቅርፅ እንዲኖረው ያደረገው ክፍል ነው፡፡ ከአንዱ ጫፍ ከካርትሪጅ ጋር ሲያያዝ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ከባትሪው ጋር ይገናኛል፡፡ ሶስተኛው እና ትልቁ ክፍል Battery ነው፡፡ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር እና መሙላት (Chargeable) የሚቻል ሲሆን በቆይታቸው የሚታወቁትን ሊቲየምአዮን (Lithium-ion) ባትሪን ይይዛል፡፡ ባትሪው የአየርን ፍሰት የሚያውቅበት ወይም ልክ ተጠቃሚው መማግ ሲጀምር በማወቅ የሚነቃ (Activate) ነው፡፡ አንዳንዶቹም ማብሪያና ማጥፊያን የሚጠቀሙ የኢ ሲጋሬተ አይነቶች አሉ፡፡

ፈሳሹ የተለያየ የኒኮቲን መጠን ሲይዝ ማዓዛውን ለማጣፈጥ ሲባልም በልዩ ልዩ የፍራፍሬ ሽታ ተዘጋጅቶ የቀረበ ኢ-ጁስ (E-Juice or E-Liquid) በማለት የሚጠሩትን የጠረን ቅመም ይጠቀማል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የቶባኮ፣ የቫኔላ፣ የቡና፣ የኮክ ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል፡፡ የኒኮቲን መጠኑ ግን እንደየ አምራቹ ይለያያል፡፡ ኒኮቲን ነፃ የሆኑ ሲጋሬቶችን ማምረትም እየተለመድ መጥቶዋል፡፡

የተሰጡ አስተያየቶች …….

ዶ/ር ቪቪየን ናታንሶን ከ British Medical Association (BMA) ኢ-ሲጋሬት ጉዳት አለው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ “ቀላሉ እና አጭሩ መልሰ እናውቅም ነው” ብለው ነበር ምክንያቱም ጊዜ ወስዶ በተጠቃሚዎቹ ላይ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢ-ሲጋሬት የንግድ ማህበር በበኩሉ “በህክምና የተረጋገጠ ብለን ልንሸጥ አንችልም አሁን ማቅረብ ምንችለው የመደበኛው ሲጋራ ተለዋጭ ብለን ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

ኢ-ሲጋሬት መደበኛውን ሲጋራ እንዳቆም እረድቶኛል ያለችው ስቴፈን “ከዚህ በፊት የተለያዩ ባህላዊ የማቆሚያ ዘዲዎችን ለምሳሌ patch & inhalators ተጠቅሚያለሁ ኢ-ሲጋሬት ግን ከእነርሱ በተሸለ መልኩ ሲጋራ እያጨስኩ እንዲመስለኝ አድርጎኛል” ብላለች፡፡

ሌላዋ የኢ-ሲጋሬት ተጠቃሚ ሊሳ ደግሞ “ኢ-ሲጋሬት እጅግ ግሩም ሃሳብ ነው! የጤና ጥቅም ከማግኘትህም በላይ መጥፎ ጠረን የለውም” ስትል አሞካሽታዋለች፡፡

አንዳንድ የህክምና ሊቆችም ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡ የሮያል ኮሌጅ የህክምና ባለሞያ እና የቶባኮ አማካሪ ቡድን መሪ የሆኑት ፕ/ር ጆን በሪቶን ሲናገሩ “ኒኮቲን በራሱ አደገኛ እፅ አይደለም” ንግግራቸውን በመቀጠል ሲጋራ ላይ ያለ ኒኮቲን ይላሉ ፕ/ር ጆን “ልክ ቡናና ሻይ ላይ የምናገኘውን ንጥረ ነገር በብዛት ስንወስድ ማለት ነው” እንደውም
“እንግሊዝ ውስጥ የሚገኙ አጫሾች ሙሉ በሙሉ ሲጋራን አቁመው ኢ-ሲጋሬትን መጠቀም ቢጀምሩ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሞቶችን እናድን ነበር”ብለዋል፡፡

እንዲያም ሆኖ ኢ-ሲጋሬት አሁንም ከህግ እና ከጤና ተቋማት አከራካሪ ነጥቦች አላመለጠም፡፡ ለምሳሌ ኢ-ሲጋሬትን በህዝብ መገልገያ ቦታዎች እንዲጠቀሙ ይፈቀዳል? ለሚለው ጥያቄ የ UK Fast Internet Storage Company ሲኢኦ የሆነው ላውረንስ ጆንስ ”ይህ በጣም  አምታች ጥያቄ ነው “ ይላል፡፡ ምክንያቱን ሲገልፅ ደግሞ ”በርግጥ ማጨስን ይመስላል ነገር ግን እንድን ሰው እስራስ ቢያኝክ ወይም ጥፍሩን ቢበላ ማስቆም እንችላለን? እኔ በበኩሌ ላሻይ ቡና እረፍት የሚወጡትን ለኢ-ሲጋሬት እረፍት ከሚወጡት ለይቼ አላያቸውም” ብሎል፡፡

ፀረ ሲጋራ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ደግሞ የኢ-ሲጋሬት እየተስፋፋ መምጣት የዘመናት ልፋታቸውን ደቼ እንዳያስግጠው በሚል ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ አጫሽ ላልሆኑ እና ህፃናትን ወደ ኢ-ሲጋሬት ተጠቃሚነት እንዳይከት በማለት ፍራቻቸውን ይገልፃሉ፡፡

የሆነው ሆኖ እውን የተለምዶ ሲጋራን ለማስቆም እና ለጤና የሚያገለግል ሆኖ ከተገኘ ”እሾህን በ እሾህ”  እንዲሉ ”ሲጋራን በ ሲጋራ“ ብያቹኃለው፡፡

ቸር እንሰንብት!

ከበይነመረብ መጽሐፍ አዘጋጆች

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.