ጨጓራ ተልጦ ጥርስ እየረገፈ የለጋነት እድሜ በከንቱ አለፈ፡፡

በጤና በአካል ላይ የሚያስከትለው ጉዳት
Khat2ጫት ለጤና ጠንቅነቱ ለሥነ-ምግባር ብልሹነቱ መንስኤነቱ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ላይ ጎጂነቱ ማንም ሠው የሚያውቀውና የሚመሠክረው እውነታ ለመሆኑ አይደለም ጤነኞችን፣ እብዶችን፣ አዋቂዎችን ሳይሆን መሀይሞችን የማይቅሙትን ሳይሆን ቃሚዎችን መጠየቅና ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ጫት ጉዳት የለውም ብሎ የሚከራከር አይገኝም በጫት የሰከረ ሠካራም ካልሆነ በቀር ጥቅም አለው ቢልም ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሳይረዳ አይቀርም! ለምን ይሆን በዚህ ሡስ ወጣቱ መጠመዱ?
– ሠውነቱን በስፖርት መገንባት ሲችል በጫት መጉዳቱ
– ወርቃማ የወጣትነት ጊዜውን ለመቃሚያ መጀባቱ
– በፈቃደኝነት በገንዘቡ ሥካር መሸመቱ
ጫት ቅሞ ታሞ ከመሟቀቅ ጫት በመተው አስቀድሞ መጠንቀቅ ጫት መቃም መተው ከህይወት ዋስትናዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ያለማደናገር ማመሳከር ሳይዋሹ መናገር በሀቁ መመስከር በማይሆን ነገር አያስፈልግም ክርክር፡፡
-የዛሬ የጫት ደንበኛ
-የነገ የሲጋራ ሡሰኛ
-የነገ ወዲያ የሀሺሽ ቁራኛ
-እንዴት ብዬ ልንገራችሁ
-በምን ቋንቋ ላስረዳችሁ
-በጫት ደንዝዞ አእምሯቸው
-ማስተዋል ተስኖት ህሊናቸው፡፡
ሲያዩት የሚያስቀው ሲያስተውሉት የሚያስለቅሰው ጉዳይ ደግሞ ያየሁት አይቅረኝ የተሠራው ይድረሰኝ ባዮች የሴት ቃሚዎች በሀገራችን መስፋፋታቸው ነው፡፡ ባሎቻቸው 100 ግራም ሲያላምጡ እነሱ 50 ግራም የሚውጡ ባሎቻቸው ሲያጨሱ እነሱ የሚጨሱ የሴት ቃሚና አጫሽ መስፋፋት ነው፡፡
አንዳንድ ሠዎች የጫት ሀራምነት ሲነካባቸው አይናቸው ይፈጣል ጥርሳቸው ይገጣል የደም ግፊታቸው ይበዛል የጨጓራ በሽታቸው ይባባሳል እሚናገሩትን ያጣሉ እራሳቸውን ይስታሉ፡፡ ሀይማኖት እንደተነካ አድርገው ለማሳየት ይጥራሉ፡፡

ግን ከንቱ ልፋት የማይሆን ዘበት በራስ ላይ እቃቃ መጫወት አምታትቶ የሠውን ገንዘብ ለመብላት የሚደረግ ጥረት . . .
እስኪ ንገሩኝ ጫት በየትኛው ሀይማኖት ነው የተፈቀደው? በየትኛው ሳይንስ ነው ጥቅሙ የተረጋገጠው? ሳትዋሹ ተናገሩ ማስረጃችሁን አቅርቡ ደርድሩ ምርጫው ሀናለ ነው “መ” መልስ የለም አመላችሁ ነው፡፡
ጫት ሀላል ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት የሀይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ የጫት ነጋዴዎችና የጫት ሲሰኞች መሆናቸው ተሠምሮበት የሚታለፍ ነጥብ ይሁን፡፡

የእስልምና ኃይማኖት ሊቃውንቶች በሒጅራ አቆጣጠር 1402ኛ አመት 5ተኛ ወር ከ27-30 ቀን በተደረገ ሥብሠባ ጫት በእስልምና ሃይማኖት የተከለከለ አደንዛዥ እፅ መሆኑን ተስማምተው ለሙስሊም አገሮች ጫትን የሚዘራን የሚቅምን የሚነግድን ከፍተኛ ቅጣት እንዲቀጣ መክረው አልፈዋል፡፡
እንዲሁም የሳውዲ ሙፍቲዎች የየመን ዑለማዎች የጫት ሀራምነትን አስመልክቶ ብዙ መጽሐፍ ፅፈዋል፡፡
እጅግ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር አላህን ለመገዛት ተብሎ የተሠራው መስጊድ(የአላህ ቤት) የማንም መቃወሚያና መደለቂያ መሆኑ ነው፡፡
መነሻ የሌላቸው መድረሻ የማይገኝላቸው ተረቶችን በመሠብሠብ ትረካዎችን በመለቃቀም የወልዮች ከራማ የደጋጎች ሥራ እያሉ ተረቶችን መተረት ወሬዎችን ማውራት ትረካዎችን መተረክ አላንስ ብሏቸው ሀድራና መንዙማ እያሉ እየቧረቁና እየደለቁ መስጅድን መጫዎቻና መጨፈሪያ ማላገጫ የሚያደርጉት ዲን/ሀይማኖት/ አወቅን ባዮች መሆናቸው ነው፡፡
{አላህ እንድትከበርና ስሙ በውስጧ እንደወሳ ባዘዘው ቤቶች ውስጥ /አውሱት/ በውስጧ በጧትና በማታ በእርሱ ያጠራሉ፡፡አላህን ከማውሳትና ሠላት ከመስገድ ዘካንም ከመስጠት ንግድም ሽያጭም የማያታልላቸው ልቦችና ዓይኖች በርሱ የሚገላበጡበትን ቀን የሚፈሩ የኾኑ ሰዎች (ያጠሩታል) አል-ኑር 36-37
በነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ዘመን መስጅድ ተከፍቶ የሚያድረው ነብያችን እና የነብያችን ባልደረቦች ሊሠግዱበት ቁርዓን ሊቀርቡት ነው በአሁኑ ሰዓት ግን በተለየ በሀገራችን ብዙ መስጅዶች ተከፍተው የሚያድሩት ሊቃምባቸው ሊጨፈርባቸው ነው፡፡ እቤቱ ዘፍኖ የማያውቀው መስጅድ ሒዶ ሲደልቅ ይታያል፡፡
ይህ ሳያንስ ጫትን የዱዓ መሳሪያ ነው ማለታቸው አይገርምም!!!
ከቁርዐን አግኝተውት ነው ወይስ ከሀዲስ? እስኪ ጠይቋቸው ምንድን ነው መልሳቸው አዎ ነገሩ እንዲህ ነው ሊበሏት ያሠቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይላሉ! እንደሚባለው ነው፡፡
በሙከራ እንደሚታወቀው የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የቃመ ሠው አላህን ሲያሥታውስ ሳይሆን አላህን ሲረሳ ነው የሚታወቀው፡፡ ሶላት ሲያሳልፉ ነው ሚገኘው መርቅኖ ሃይማኖትን ሲሳደብ ነው ሚሰማው፡፡

‹‹በአላህም መንገድ ለግሱ በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደ ጥፋት አትጣሉ በጎ ስራንም ስሩ አላህ በጎ ሠሪዎችን ይወዳል፡፡››አል-በቀራህ 195
ጫት ‹ገዝተው› የሚቅሙት ሠዎች በእጆቻቸው ነፍሶቻቸውን እያጠፉ ነው፡፡ በፍቃደኝነት ስካርና እብደት እየሸመቱ ነው፡፡

-ጫት መቃም ጥርስ ያበላሻል/ያሻግታል/
– ምላስ ያሻክራል
– ኩላሊት ያንኮላሻል
– ጨጓራ ይልጣል
– የምግብ ፍላጎት ይዘጋል
– የወንድነት ስሜት ያጠፋል/ያሳጣል/
– ሰውነትን ያከሳል
– ደም ይቀንሳል ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡
*ወጣቶች ምክር ስሙ ጫት አትቃሙ
*በተለያየ በሽታ እንዳትለቀሙ
በቃሚዎች ላይ
– የሽንት መቆራረጥ መብዛት
– የሰውነት ሀይል ማጣት
– ጊዜን ያለ አግባብ ማጥፋት
– የሆነ ያልሆነ ወሬ ማውራት
– ለሊት እንቅልፍ ማጣት
– ቀን ስራ መፍታት ይስተዋላል፡፡

ጨጓራ ተልጦ ጥርስ እየረገፈ
የለጋነት እድሜ በከንቱ አለፈ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.