ቶንሲል ህመም ለኩላሊት መድከም ለልብ ህመምና ለሞት ሊዳርግ ይችላል
የቀዘቀዘ ምግብን ወይም መጠጥን አብዝቶ መጠቀም አሊያም በሃይለኛ የፀሐይ ሙቀት በመመታት ይከሰታል ተብሎ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የሚታሰበው የቶንሲል ህመም መነሻ ምክንያቱ ከእዚህ በእጅጉ የተለየና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ካላገኘም እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ የጤና ችግር ነው፡፡ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች በፀሐይ ላይ መመገብ፣ እንደ አይስክሬም ያሉ የቀዘቀዙ ምግቦችን በተለይ ለህፃናት መስጠትና በከባድ ፀሐይ መመታት፤ ከቶንሲል ህመም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና በሽታው በባክቴሪያና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር እንደሆነም የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር አብርሃም የሺዋስ ይናገራሉ፡፡
በጉሮሮአችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል እጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡና ሲያብጡ የሚከሰተው ህመም ቶልሲላይተስ ተብሎ ይጠራል፡፡ እነዚህ ቶንሲሎቻችን እንዲቆጡና እንዲያብጡ በማድረግ ህመም እንዲሰማን የሚያደርጉት ባክሬቴሪያና ቫይረሶች ናቸው፡፡ የቶንሲል ህመም (ቶንሲላይተስ) በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እጅግ የተለመደና በየጊዜው የሚያጋጥም የህመም አይነት ነው፡፡ አንድ ሰው በየዓመቱ በአማካይ እስከ አራት ጊዜ ያህል በቶንሲል ህመም ሊጠቃ ወይንም ቶንሲላይትስ ሊይዘው ይችላል፡፡


የቶንሲል ህመም በቫይረስና በባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰት ህመም ሲሆን ቫይረስ አመጣሹ ቶንሲላይት በአብዛኛው በቀላል የቤት ውስጥ ህክምናዎች ማለትም ጨው በተቀላቀለበት ሞቅ ያለ ውሃና በሎሚ ጭማቂ ደጋግሞ የጉሮሮ ውስጠኛውን ክፍል በማፅዳት፣ በዝንጅብል የተፈላ ሻይና ትኩስ ነገሮችን ደጋግሞ በመጠጣት ሊድን የሚችልና ምንም ዓይነት መዘዝን የማያስከትል ህመም ሲሆን በባክቴሪያዎች በተለይም ደግሞ ስትሬፕቶኮክስ ፓዮጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ የሚመጣው የቶንሲላት አይነት ግን ለከፍተኛ ህመምና ሥቃይ የሚዳርግ ከመሆኑን በላይ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል መዘዝ የሚያስከትል ነው፡፡


የቶንሲል ህመም መንስኤ የሆነው ቫይረስ ወይንም በባክቴሪያ በተለያየ መንገድ ወደ ሰውነታችን ገብቶ ቶንሲሎቻችንን ከበከለ በኋላ ባሉት ሁለትኛ ሶስት ቀናት በህመምተኛው ላይ የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡ ምልክቶቹም ሃይለና ትኩሳት፣ ከባድ የራስ ምታት፣ መጥፎ ጠረን ያለው ትንፋሽ፣ የጉሮሮ ህመም፣ ለመዋጥ መቸገርና በአክት ግራና ቀኝ አካባቢ በእጅ ሲነካ የህመም ስሜት መኖር ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ህመምተኛው አፉን እንዲከፍት በማድረግ ጉሮሮው በሚታይበት ጊዜ ከምላሱ ኋላ በግራና ቀኝ የጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ እብጠትና ቅላት ይታያል፡፡ እነዚህ የጉሮሮ ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ የሚገኙ የቶንሲል እጢዎች እብጠታቸው አንዳንዴ ከፍተኛ ይሆንና ጉሮሮን ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ ይችላሉ፡፡ ባክቴሪያ ወለዱ ቶንሲላይት ከመደበኛው የቶንሲል ህመሞች ምልክቶች በተጨማሪ ከሚኖረው የበሽታው ምልክት መካከል በጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ በሚኖረው እብጠት ላይ ነጫጭ አይብ መሰል ነጠብጣቦች /ችፍታዎች/ ሊታዩበት ይችላሉ፡፡ የቶንሲል ህመም በትንፋሽ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና ህፃናትን በይበልጥ የሚያጠቃ የበሽታ ዓይነት ነው፡


የቶንሲል ህመም (ቶንጀሲላይትስ) ከፍተኛ ሥቃይ ያለው ህመም ቢሆንም ከህመሙ በላይ አስከፊው ነገር በሽታው ካልታከመ የሚያስከትለው መዘዝ እንደሆነ ዶክተር አብርሃም ይናገራሉ፡፡ ስትሬፕቶኮከስ ፓዪጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ በሚመጣው የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው በአግባቡና በወቅቱ ህክምናውን ካላገኘ ከኩላሊት መድከም (ኩላሊት ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆም) እስከ ልብ ህመም ብሎም እስከሞት ሊያደርሱ የሚችሉ መዘዞችን ያስከትላል፡፡ በባክቴሪያ ወለዱ የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው ተገቢውን ህክምና ካላገኘ ቶንሲሎቹ ዙሪያቸውን ያብጡና መግል ይቋጥራሉ፡፡ የህመምተኛው አንገትም ይበልጥ መግል ወደተቋጠረበት አቅጣጫ ያዘማል፡፡ ይህም የማጅራት አለመታዘዝንና መንጋጋን እንደልብ መክፈት አለመቻልን ከማስከተሉም በላይ ታማሚው ህክምና ካላገኘ ባክቴሪያው በደም ውስጥ በመሰራጨት የኩላሊትና የልብን መደበኛ ስራ በማስተጓጎል ታማሚውን ለሞት ሊዳርገው እንደሚችል ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡ ባክቴሪያ አመጣሹ ቶንሲላይተስ ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል አጣዳፊ የኩላሊት መድከም፣ የልብ ህመም፣ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) የቆዳና የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች፣ ጥቂቶቹ እንደሆኑም ዶክተር አብርሃም ተናግረዋል፡፡


ስትሬፕቶከክስ ፓዮዲኒስ በተባለው የባክቴሪያ አይነት ሳቢያ የሚከሰተውን እና እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን የሚያስከትለውን የቶንሲል አይነት ቫይረስ አመጣሽ ከሆነውና በቀላሉ ከሚድነው የቶንሲል አይነት መለየቱ አስቸጋሪ ነው፤ ያሉት ዶክተሩ ሁሉም ዓይነት የቶንሲል ህመሞች በአግባቡና በወቅቱ ህክምና ማግኘት አለባቸው፤ የሚባለውም ለዚሁ ነው ብለዋል፡፡ በቶንሲል ህመም ሳቢያ የሚመጡ የህመም ስሜቶች በሽተኛው ህክምናውን ባገኘ ሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ ሊጠፉ እንደሚችሉና ቶንሲላይትን በቶሎ አለመታከም ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ የሚቆይበትን ጊዜ በማራዘም ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉንም በዛው መጠን እንዲጨምረው ተናግረዋል፡፡ በሽታው ከፍተኛ ሥቃይ ያለው ህመም ቢሆንም ከህመሙ ይልቅ በወቅቱ ህክምና ካላገኘ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ አስከፊ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ በአግባቡና በጊዜው ህክምናውን በማድረግ በሽታው ከሚያስከትለው የከፋ ጉዳት መዳን ይቻላል ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.