ህጻናት ከአዋቂዎች በላይ ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው። ምንም እንኳን ህጻናትን የሚያጠቁ በሽታዎች ለክፉ የማይሰጡ እና በተገቢው እንክብካቤ እና ህክምና በቀላሉ የሚድኑ ቢሆኑም ብዙ ወላጆች ግን ካለማወቅ የተነሳ ሲቸገሩ ይስተዋላል።

ልጆት በቀን ለብዙ ጊዜ ቀጭን ሰገራ ካለው ተቅማጥ አለው ይባላል፡፡ በሆድ እቃቸው ውስጥ ኢንፌክሽን ሲኖር ወይም ለተለያዩ ምግቦች አለርጂክ ሲሆኑ ይመጣል፡፡ ብዙ ጊዜ ከተቅማጡ ጋር ትውከትና የሆድ ህመም ተያያዥነት አላቸው፡፡

በሽንት ጨርቅ ምክንያት የሚመጣ ሽፍታ (Diaper rash) በማንኛውም በሽንት ጨርቅ በተሸፈነ ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ነው፡፡ይኼ ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ የሚችል ቢሆንም አብዛኛውን ግዜ የተለመደው ምክንያት ግን በሽንት እና በሰገራ የቆሸሸ የሽንት ጨርቅ ከቆዳ ጋር የሚኖረው ፍትግትግ ነው፡፡

ከጥቂት ሰአታት በፊት ደህና የነበረ ልጅ ወዲያው ሀይለኛ ትኩሳት ከተሰማው፣ በጣም ከደከመና ጉሮሮዬን አመመኝ ካለ ቶንሲል እደያዘው ይገምቱ:: ቶንሲል በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከባክቴሪያ ይልቅ ቫይረሶች ያስከትሉታል፡፡ እነኝህ ጀርሞች ጉሮሯችን ውስጥ በጥገኝነት ይኖራሉ፡፡ ህፃናቶች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ስላልጠነከረ እነዚህ ጉዳት የሌላቸው ጀርሞች በተደጋጋሚ ያጠቋቸዋል፡፡

የጆሮ ኢንፌክሽን ብዙ ጊዜ የላይኛውን የአየር ቧንቧ ከሚያጠቁ በሽታዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡የላይኛውን የአየር ቧንቧ የሚያጠቁ በሽታዎች በሚኖሩ ጊዜ የጆሮን የመካከለኛውን ክፍል እና ጉሮሮን የሚያገናኘው ቱቦ (eustachian tube) ያብጥና አየር ወደመካከለኛው የጆሮ ክፍል እንዳይገባ ያደርጋል፡፡

የሳምባ ምች በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጣ በሽታ ሲሆን የህፃናትን ሳምባ ያጠቃል፡፡ በብዛት በባክቴሪያ የሚከሰት ሲሆን አንዳንዴም የበሉት ምግብ ወይም ጨጓራቸው ውስጥ ያለው ነገር ወደላይ ተመልሶ የአየር ቧንቧቸው ውስጥ ሲገባ ሊከሰት ይችላል፡፡

 

ህፃናት ላይ ከሚታዩ በሽታዎች ሁሉ በብዛት የሚያጋጥመው ጉንፋን ነው። በላይኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ በቫይረስ ምክንያት የሚከሰት በሽታ ሲሆን ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ቫይረሶች ሊያስከትሉት ይችላሉ።

ክሩፕ በብዛት የሚታይ የህፃናት የትንፋሽ ቧንቧ ችግር ነው። በብዛት በበልግ እና በክረምት የሚከሰት ሲሆን ዋና ምልክቱም ደረቅ የበግ (ውሻ) አይነት ሳል ነው። ክሩፕ ወደ ሳንባ በሚወርዱት የትንፋሽ ቧንቧዎች እና በድምፅ መፍጠሪያ ሳጥን ላይ እብጠት በማስከሰት የታመመው ህፃን ለመተንፈስ እንዲቸገር ያደርገዋል።ልጆች በክሩፕ ሲያዙ በጣም ቢያስደነግጥም በብዛት ለከፋ አደጋ የሚሰጥ ሁኔታ አይደለም። በቤት ውስጥ እረፍት እና እንክብካቤ ካገኙ ልጆች በቀናት ውስጥ በሽታው ይሻላቸዋል።

የዚህ በሽታ መንሳኤዎች ብዙ ቢሆኑም በብዛት አገራችን ላይ ችግር የሚያስከትሉት ግን ቫይረስና ባክቴሪያ ናቸው። እነዚህ ጀርሞች የጭንቅላታችንን ሽፋኖች በማቁሰል ለከፋ ችግር ይጋልጣሉ። በሽታው በትንፋሽ መተላለፉ ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ለማጥቃት ያስችለዋል። በበሽታው ለመያዝ ተጋላጭ የሆኑት በሽታው ከያዘው ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው፣ በቅርቡ ሌላ ኢንፌክሽን ያጋጠማቸው እና በድህነት ብዙ ሰው ተጨናንቆ በሚኖርበት ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። በሽታው በህፃናት ላይ፣ በተለይም ከአንድ ዓመት በታች ባሉት ላይ ሲከሰት አስከፊ ችግሮችን አያይዞ ይመጣል።

ይህ በባክቴሪያ የሚመጣ በሽታ ሲሆን ከ1-5 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናትን ያጠቃል። በሽታው ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ በመተላለፉ ህፃናት በብዛት በአንድ ቦታ በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች፣ ለምሣሌ በትምህርት ቤቶች ላይ በቀላሉ ይተላለፋል።

የጉድፍ በሽታ በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ሲሆን በአብዛኛው ከ10 አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ያጠቃል። በተለይም ብዙ ልጆች በብዛት በሚኖሩበት ስፍራ በትንፋሽ እንዲሁም በንክኪ በቀላሉ ይተላለፋል። በክረምትና በበልግ ወራትም በብዛት ይታያል። አንድ ሰው በቫይረሱ በተጠቃ በ 14 ቀናት ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል።

 

ምንጭ — አዲስ ጤና

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.