በፍስሀ አምበሉ(BDSC Dentist,ከሆሊ ልዩ የጥርስ ክሊኒክ)

(በኢትዮ ፎርብስ መጽሄት አማካኝነት ለህትመት የበቃ)

mouthበዛሬዉ ፅሁፌ የማነሳዉ ብዙ ሰዎችን ሰላም ሲነሳና በእለት ተእለት ኑሯቸዉ ላይ ጉልህ ተፅእኖ ሰያሳድር ስለሚስተዋለዉ መጥፎ የአፍ ጠረን ችግር(በእንግሊዝኛ halitosis or bad breath ይባላል)ይሆናል፡፡ይህ ከጥርስ መቦርቦር እና ከጥርስ አቃፊ ችግሮች በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ የሰዉን ልጅ ወደ ጥርስ ሀክምና ክሊኒኮች በማመላለስ የሚታወቀዉ መጥፎ የአፍ ጠረን ቀላል ችግር ቢመስልም ተገቢዉ ክትትል ተደርጎ ካለተወገደ ትዳርን እስከማናጋት ሊደርስ እንደሚችል ይነገርለታል፡፡እኔም በጥርስ ህክምና ሙያ ዉስጥ ባሳለፍኳቸዉ የተወሰኑ አመታት ችግሩ የበርካቶችና አሳሳቢ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡
አንድ ሰዉ መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለበት እንዴት ማረጋገጥ ይችላል?

አንድ ሰዉ መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለበት እና እንደሌለበት በዋናነት በሁለት ቀላል መንገዶች በግሉ ሊያረጋገጥ ይችላል፡፡ይህም የሚሆነዉ
1. ንፁህ ማንኪያ ወይም ጠቋሚ ጣታችንንን በመጠቀም ወደ ምላሳችን የመጨረሻ ክፍል በመላክ ከላይ ያለዉን ነጭ ምራቅ መሰል ዝልግልግ ነገር በመፋቅ እና በማሽተት ለሌሎች ሰዎች ሊሸት የሚችለዉን እራሳችን ማወቅ እንችላለን፡፡
2.አፋችንን በመጠኑ በእጃችን መዳፍ በማፈን ትንፋሻችንን ወደ አፍንጫችን እንዲሄድ በማድረግ ያለዉን ጠረን አሽትተን ማረጋገጥ እንችላለን ምንም እንኳ ከላይ እንደተጠቀሰዉ ዘዴ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛዉን ሽታ ሊያሳይ ባይችልም፡፡

በሌላ መልኩ መቸም አንድ የልብ ወዳጅ አይጠፋምና መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለብዎ እና እንደሌለብዎ ወዳጅዎን ጠይቀዉ ሊረዱም ይችላሉ፡፡እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ አንድ በእለት ተእለት ኑሯችን አብሮን ያለ ሰዉ መጠፎ የአፍ ጠረን ችግር ቢኖርበት ችግሩን ከመንገር ወደ ኋላ ማለት እነደሌለብን ነዉ፡፡ ምንም እንኳን በቀጥታ “አፍህ ይሸታል” ብሎ መናገር ቢከብድም ነገሩን አቅልለን ወደ ህክምና በመሄድ መፍትሄ ሊገኝ እነደሚችል በማመላከት መላ እነዲፈልግ ማድረጉ የተሻለ ዉጤት ያመጣል፡፡”ለሰዉ- ሰዉ ነዉ ልብሱ” ይል የለ ብሂላችን::

አፍዎ ባለ ጥሩ መዐዛ ሁኖ ሳይሳቀቁ መሳቅ ከፈለጉ ስለ መንስኤዉና መፍትሄዉ የሚያትተዉን ከዚህ በታች ያለዉን ፅሁፍ አፅንኦት ሰጥቶ ማንበቡ ጠቃሚ ነዉ፡፡

ለመሆኑ መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤዉ ምንድነዉ?

መጥፎ የአፍ ጠረንን አስመልክቶ የተፃፉ አብዛኞቹ መረጃዎች መንስኤዎቹን በሁለት ከፍለዉ ይተነትኑታል፡፡እስኪ ቀለል ባለ ገለፃ አንመልከታቸዉ፡-
1.ከአፍ ዉሰጥ አካላት ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚመጣ መጥፎ የአፍ ጠረን የአብዛኛዉ ሰዉ መጥፎ የአፍ ጠረን ችግር የሚመጣዉ ከአፍ ዉሰጥ የንፅህና ችግሮች ጋር በተያያዘ ነዉ፡፡

ይህም የሚሆነዉ የአፍ እና የጥርስ ንፅህና ባግባቡ በማይጠበቅበት ጊዜ የምግብ ሽርፍራፊዎች በ ጥርስ እና በድድ መሃል እንዲሁም በ ጥርስ እና በ ጥርስ መካከል ሲከማቹ ጎጅ ባክቴሪያዎች ከምራቅ ጋር በመዋሀድ እነዚህን የምግብ ቅሪቶች እንዲሰባበሩ ስለሚያደርጉ ነዉ፡፡ ይህም ሂደት በሚከናዎንበት ጊዜ የሚለቀቀዉ የሰልፈር ጋዝ መጥፎ የአፍ ጠረንን ያስከተላል፡፡

በመሆኑም ከሚከተሉት በአንዱም ሆነ በሌላዉ መንገድ የአፋችን ንፅህና ካልተጠበቀ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊኖር ይችላል፡-

-እንደጥርሳችን ሁሉ ምላሳችንም ባግባቡ ፅዳቱ ካልተጠበቀ ብዙ ሸካራ አና ወጣ ገባ ያሉ ቦታዎች ስላሉት የምግብ ቅሪት እና ባክቴሪያዎች በቀላሉ አጠራቅሞ መጥፎ ጠረን ሊፈጥር ይችላል፡፡

-አፋችን ዉስጥ የተቦረቦረ ጥርስ ካለ በዉስጡ ምግብ እና ባክቴሪያ ሊይዝ ስለሚችል ይህም መጥፎ ጠረን ሊያመጣ ይችላል፡፡
-አፋችን ዉስጥ የሰዉ ሰራሽ ጥርስ ካለና ይህ ጥርስ ባግባቡ ከድድ ጋር ካልገጠመ በመካከል ምግብ እና ባክቴሪያ ሊይዝ ስለሚችል የመጥፎ ጠረን መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡

-በድድ እና በጥርስ አቃፊ አካላት ላይ የጤንነት መጓደል ካለና የድድ መሸሽ፣በጥርስ አቃፊ አካላት መካከል ክፍተት(periodontal pocket) ካለ ይህም ለምግብ አና ባክቴሪያ መከማቸት እድል ስለሚሰጥ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያስከትል ይችላል፡፡

-የአፍ መድረቅ፤ለአፋችን ንፅህና ምራቅ እራሱን የቻለ አስተዋፅኦ አለዉ…ማለትም ምራቅ በበቂ መጠን አፋችን ዉስጥ ካለ ያሉትን የባክቴሪያ እና የምግብ ቅሪቶች በማንሸራተት ወደ ዉስጥ በመላክ ጠረን እነዳይፈጥሩ ይከላከላል፡፡ምራቅ በተገቢዉ መንገድ ሳይመነጭ ቀርቶ አፍ ከደረቀ ግን ለባክቴሪያ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል፡፡

-የጉረሮ፣የእንጥል፣የድድ፣እንዲሁም የምላስ መቁሰል ወይም ኢንፌክሽን ካለ መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡

-ሲጋራ ማጨስና መጠኑ የበዛ አልኮል ማዘዉተርም መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል

-እንዲሁም በተፈጥሮ ከባድ ሽታ ያላቸዉ ምግቦች ለምሳሌ እንደ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት ያሉትን ምግቦች መጠቀም ጊዚያዊ የሆነ የአፍ ጠረን ለዉጥ ሊያስከትል ይችላል ምንም እንኳ እነዚህ ምግቦች የሚያመጡት መጥፎ ጠረን ከተወሰኑ ስአታት በኋላ በራሱ የሚጠፋ ቢሆንም፡፡
2.ከአፍ ዉጭ ባሉ ችግሮች የሚከሰት መጥፎ የአፍ ጠረን

ሁለተኛዉና ከአፍ ዉጭ ባሉ ችግሮች የሚመጣ የአፍ ጠረን ሲባል በዉስጣዊ የሰዉነታችን ክፍሎች ላይ በሚኖር በሽታ ምክንያት የሚከሰተዉን የአፍ ጠረን ለዉጥ ለማመላከት ነዉ፡፡አንድ ሰዉ የኩላሊት፣የስኳር፣የጨጓራ ወይንም የጉበት በሽታ ካለበት ከበሽታዉ ጋር ተያይዞ የሚኖር የአፍ ጠረን ለዉጥ ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዴ የትንፋሽ ጠረን ለውጥ የዉስጣዊ ችግሮች ጠቋሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡እዚህ ላይ ግን ማስተዋል ያለብን መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ ዉስጣዊ በሽታ ሊሆን ይችላል ሲባል ማንኛዉም መጥፎ የአፍ ጠረን ያለበት ሰዉ ሁሉ ዉስጣዊ ችግር አለበት ማለት እንዳልሆነ ነዉ፡፡

መጥፎ የአፍ ጠረን መፍትሄ
መጥፎ የአፍ ጠረን ህክምና በትክክል መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለዉ የጠረኑ መንስኤ በአግባቡ ተለይቶ ታዉቆ ተገቢዉ ህክምና እስከተደረገ ድረስ ብቻ ነዉ፡፡ ከአፍ ዉስጥ አካላት ጉድለቶች ጋር በተያያዘ የሚመጣ የአፍ ጠረን ትክክለኛዉ ህክምና ከተደረገለት ሙሉ ለሙሉ የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለዉ ተጠቂዉ ሀኪም ጋር ቀርቦ ጉድለት የደረሰበትን አካል ሲታከም ነዉ፡፡ ማለትም የተቦረቦረ ጥርስ ካለ በመሙላት፣የተከማቸ ቆሻሻ ካለ በማንሳት፣የአፍ ዉስጥ ኢንፌክሽን ካለ በተገቢዉ መንገድ በማከም እንዲሁም ዉስጣዊ የጤና እክልን በህክምና በማስወገድ ይሆናል፡፡ የአፍ ዉስጥ አካላት ችግሮች ተፈተዉ ጠረኑ ቀጣይነት ካለዉ ከዉስጣዊ ችግሮች ጋር በተያየዘ ሊሆን ስለሚችል ዉስጣዊ አካላት ላይ ምርመራ አካሂዶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በስተመጨረሻ የአፍ ጠረን ቢኖርም ባይኖርም ስለ ጥርስና አፍ ጤና አጠባበቅ ዘዴዎች መክሬ ላገባድ፡-

– ጥዋትና ማታ የጥርስ ሳሙና(የምንጠቀምበት ሳሙና የአገልግሎት ዘመኑ አለማለፉን ማጤን ያሥፈልጋል) ተጠቅሞ በበቂ ሁኔታ ጥርስን ማፅዳት
– ሁሉንም የጥርስ ቦታዎች በለስላሳ ቡርሽ ከ ድድ ወደ ጥርስ መቦረሽ
-ጥርስ ተጸድቶ ካለቀ በኋላ ምላስን ከኋላ ወደ ፊት በደንብ ማጽዳት
-ከቡርሽ በተጨማሪ የጥርስ ማጽጃ ክር(dental floss) ተጠቅሞ ጥርስን ማፅዳት
-በጥርሶች መካከል የተከማቸ ሽህላ(ጠጠር መሰል በጥርሶች መካከል የሚኖር ቆሻሻ) ካለ የጥርስ ሃኪም ጋ ሂዶ ማጽዳት
– በሀኪም የታዘዘ የአፍ መጉመጥመጫ ፈሳሽ ካለ በአግባቡ መጠቀም
– ከስኳር ነጻ የሆኑ ማስቲካዎችን ማኘክ(ማኘክ የምራቅ መመንጨትን ስለሚያበረታታ አፍን ጽዱ የማድረግ አቅም አለዉ)
– ምግብ ከተመገብን በሁዋላ አፍን በንጹህ ዉሃ መጉመጥመጥ
-ሲጋራ አጫሽ ከሆኑ ጭሱ የሚያመጣዉን ዉጫዊ የቀለም ለዉጥ ሊያነሱ የሚችሉ ልዩ የጥርስ ሳሙናዎች ሰላሉ እነሱን መጠቀም፡፡
-የጥርስ ቡርሹ አናት ላይ ያሉ ክብ ለስላሳ ጫፎች ከረገፉ ቡርሹን መቀየር (አንድን ቡርሽ ከሶስት ወር በላይ ባንጠቀምበት መልካም ነዉ)
-ጥርስ ተፀድቶ ከለቀ በኋላ ቡርሹን በንጹህ ዉሀ አለቅልቆ ደረቅ ቦታ ላይ ማስቀመጥ
-የጥርስ ቡርሽና ሳሙና ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ካለ ጥርሥና ድድን ሊጎዱ በማ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here