የጀርባ ህመም

4

back-pain-kidneyዛሬ በጀርባ ህመም ላይ ምክሮች እንሰጥዎታለን፡፡ ስለጀርባ ህመምም ይሁን ስለሌላ የጤና ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጉ 8896 ሃሎ ዶክተር ላይ በመደወል በቂ ልምድና ሙያ ያላቸዉን ሀኪሞቻችንን ያማክሩ፡፡ እርስዎን ለማማከር ሁሌም ዝግጁ ናቸዉ፡፡

ሰዎች በህይወት ዘመናቸዉ አንድ ጊዜና ከዚያ ጊዜ በላይ ከመቀመጫ ከፍ ብሎ ባለዉ የጀርባ ክፍል የጀርባ ህመም( low back pain) ሊኖራቸዉ የሚችል ሲሆን ይህ ችግር ብዙ ጊዜ ሰዎችን ወደ ህክምና ተቛም በተደጋጋሚ የሚያመላልስ ወይም ከስራ የሚያስቀር የህመም አይነት ነዉ፡፡

የህመሙ ምልክቶች
የህመሙ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸዉ
• የጡንቻ ላይ ህመም
• እንደ ዉጋት ያለ ህመም
• ወደ እግርዎ የሚሰራጭ ህመም
• እንደ ልብዎ ለመታጠፍ ያለመቻል
• ቀጥ ብሎ መቆም ያለመቻል

የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያለብዎ መቼ ነዉ?
ብዙዉን ጊዜ የጀርባ ህመም ቤት ዉስጥ በሚደረግ ህክምና እንክብካቤ ቀስ በቀስ ይሻሻላል፡፡ ህመሙ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሙሉ ለሙሉ ለመጥፋት ብዙ ሳምንታትን የሚወስድ ቢሆንም ለራስዎ እንክብካቤ ካደረጉ ህመሙ በ72 ሰዓታት ዉስጥ የተወሰነ መሻሻል ያሳያል/ይገበዋል፡፡ይህ ካልሆነ ግን የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ይገባዎታል፡፡

አንዳንዴ የጀርባ ህመም ከፍ ያለ የህክምና ችግርን ሊያመለክት ይችላል፡፡የሚከተሉት ምልክቶችን ካዩ ባስቸኳይ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ፡-
• አዲስ የመጣ የሽንት ወይም የአንጀት ስርዓት መታወክ ካለ (የሽንት ማምለጥ/ሰገራ የመቛጠር ችግር)
• ትኩሳት፣የሚመታ የሆድ ዉስጥ ህመም ካለ ( throbbing (pulsation) in the abdomen)
• የጀርባ ህመሙ መዉደቅን ወይም መመታትንም ይሁን ማንኛዉንም አደጋ ተከትሎ ከመጣ
በተጨማሪ የሚከተሉት ነገሮች ካለዎ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ
• በተለይ ማታ ማታ ወይም ተንጋለሁ በሚተኙበት ወቅት የማያቛርጥ/ከፍ ያለ ህመም ካለዎት
• ህመሙ ወደ አንዱ ወይም ሁለቱም እግርዎ በተለይ ከጉልበትዎ በታች የሚሰራጭ ከሆነ
• የመደንዘዝ፣የመስነፍ፣ወይም እንደ መርፌ የመጠቅጠቅ የህመም ስሜት በአንዱ ወይም በሁለቱም እግርዎ ላይ ከተሰማዎ
• በሌላ ምክንያት ሊገለፅ የማይቻል የክብደት መቀነስ ካለዎ
• የማበጥ ወይም የመቅላት ስሜት በጀርባዎ ላይ ካለዎ
• ከ50 ዓመት በላይ ከሆኑና ለመጀመሪያ ጊዜ የጀርባ ህመም ከተሰማዎ
• የካንሰር ህመም ካለዎ፣የአጥንት መሳሳት ችግር ካለዎ፣ ስቴሮይድ መድሃኒት የሚወስዱ ከሆነና አደንዛዥ ዕፅ ወይም አልኮል የሚጠጡ ከሆነ

የጀርባ ህመምን የሚያመጡ ነገሮች
የጀርባ ህመም ያለምንም ሁነኛ መንስዔ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም የሚከተሉት ምክንያቶች ብዙዉን ጊዜ ከጀርባ ህመም ጋር ይያያዛሉ፡-
• የጡንቻ ወይም ጅማት መወጠር በሚከሰትበት ወቅት፡- ከባድ ነገር በሚያነሱበት ወቅት ወይም በድንገት ያልተገባ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት የጀርባ ጡንቻዎችና ጅማቶች ስለሚወጠሩ ህመምን ሊያመጡ ይችላሉ
• የዲስክ መንሸራተት/መሰበር፡-ዲስክ በሁለት የጀርባ አጥንቶች መካከል የሚገኝ ሲሆን ዲስኩ በሚሰበርበት/በሚወጠርበት ወይም በሚንሸራተትበት ወቅት በህብለ ሰረሰሩ ላይ ወይም ከህብለ ሰረሰር ወጥተዉ ወደ ሰዉነታችን ክፍሎች በሚሰራጩ ነርቮች ላይ ጭነትን ስለሚፈጥር የህመም ስሜት ሊኖር ይችላል
• አርትራይትስ፡-ኦስቲዎአርትራይትስ የሚባለዉ የአጥንት ህመም አይነት በህብለሰረሰር ዙሪያ ያለዉን ቦታ ስለሚያጠበዉ ህመም እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል፡፡
• የጀርባ አጥንት ችግሮች፡-አንድ ሰዉ ካለዉ የጀርባ አጥንት አቀማመጥ ዉጭ በሚሆንበት ወቅት ለምሳሌ የመጉበጥ፣ጀርባችን ወደቀኝ ወይም ግራ በሚጎብጥበት ወቅት( Scoliosis) የጀርባ ህመም ሊከሰት ይችላል፡፡
• የአጥንት መሳሳት( Osteoporosis)፡-የአጥንት መሳሳት በሚከሰትበት ወቅት አጥንቶች በቀላሉ የመሰበር አደጋ ስለሚደርስባቸዉ ለህመም መከሰት ምክንያት ይሆናሉ

የህክምና ባለሙያዉ ዘንድ እስኪሄዱ ድረስ ምን ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ?
የህክምና ቀጠሮዎ እስኪደርስ ድረስ
• ሙቀት ያለዉ ነገር በቦታዉ ላይ መያዝ(ሙቅ ሻወር/የሞቀ ፓድ)
• ቀዝቃዛ/በረዶ በቦታዉ ላይ መያዝ ህመምን ሊያስታግስ ይችላል
• ስራዎ ከባድ ነገሮችን ማንሳት ካልሆነ በስተቀር በታቻሎት መጠን ዕለታዊ እንቅስቃሴዎትን ማካሄድ/መተግበር፡፡ ነገር ግን ህመሙን የሚቀሰቅስብዎ የተወሰነ የእንቅስቃሴ አይነት ከሆነ ያንን እንቅስቃሴ መተዉ፡፡

ሊደረጉ የሚችሉ መርመራዎች
• ራጅ መነሳት፡-የአጥንትዎን አቀማመጥ፣የአጥንት ችግሮች መኖራቸዉን ለማየት
• ሲቲ ወይም ኤምአርአይ፡-የዲስከ መንሸራተትን፣በአጥንት፤ነርቮች፣ጡንቻዎችና ጅማቶች ላይ ችግር መኖር ያለመኖሩን ለማየት
• ቦን ስካን፡-የአጥንት ካንሰርን፣ስብራትን ለማየት
• የነርቭ ጥናቶች/ምርመራዎቸ(ኤሌክትሮማዮግራፊ)፡-ይህ ምርመራ በዲስክ መንሸራተትም ይሁን በነርቮች መተላለፊያ መንገድ ላይ ጥበት መከሰት ምክንያት የሚመጣዉን የነርቮች ላይ ጉዳት( compression) ለማወቅ ይጠቅማል፡፡

ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
ብዙዉን ጊዜ የጀርባ ህመም ለተወሰነ ሳምንታት የቤት ዉስጥ ህክምና ከተደረገና ትኩረት ከተሰጠዉ ሊሻሻል ይችላል፡፡ ምናልባትም ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድሃኒቶች ብቻ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የተወሰኑ ቀናት እረፍት ቢደረግ ችግር ባይኖረዉም ለረጅም ጊዜ ዕረፍት ማድረግ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ስለሆነም እንቅስቃሴዉ ለህመሙ መቀስቀስ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር እንቅስቃሴዎን አያቛርጡ፡፡ በተጨማሪም ወክ ማድረግ ወይም የእለት ተዕለት እንቅስቃሴዎን ማካሄድ ይመከራል፡፡ እየወሰዱት ያለዉ የህመም ማስታገሻ ካልሰራ የህክምና ባለሙያዎ የተሸለና ጠንከር ያለ የህመም ማስታገሻን ጨምሮ ሌሎች ህክምናዎችን ሊያደርግልዎ ስለሚችል ወደ ጤና ተቛም መሄድ ይመከራል፡፡

መድሃኒቶች
የጀርባ ህመምን ሊያስታግሱ የሚችሉ የተለያዩ መድሃኖቶች ያሉ ሲሆን እነርሱም
• አሴታሚኖፌን
• አይቡፕሮፌን/አድቪል
• መስል ሪላክሳንት
• ናርኮቲክስ(ኮዴን፣ሃይድሮኮዴን)
• አንታይዲፕሬሳንት(አሚትሪፕትሊን) የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ በህክምና ባለሙያዎ እንደአስፈላጊነቱ የሚታዘዙ ናቸዉ፡፡
ያለ ሃኪም ትዕዛዝ ሊሚወሰዱ የሚችሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች በጨጓራ፣በኩላሊትና በሌሎች የሰዉነት ክፍልዎ ላይ ጉዳት ሊያመጡ ስለሚችሉ ያለሃኪም ክትትል ለረጅም ጊዜ ባይወስዱ ይመከራል፡፡

ፊዝዮቴራፒና የአካል እንቅስቃሴ
ፊዝዮቴራፒና የአካል እንቅስቃሴ የህክምናዉ ዋናዉ አካል ናቸዉ፡፡ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዉ የተለያዩ መንገዶችን ለመጠቀም ይችላል (ሙቀት፣አልትራሳዉንድ፣ኤሌክትሪካል ስቲሙሌሽን)፡፡ ህመሙ ሲሻሻል ባለሙያዉ ህመሙ ተመልሶ እንዳይመጣ ምን አይነት የአካል እንቅስቃሴ ቢያደርጉ እንደሚመረጥ ያስተምሮታል፡፡

በመርፌ የሚሰጡ ህክምናዎች
ሌሎች ህክምናዎች ስቃዩን ሊያሻሽሉ/ሊያስታግሱ ካልቻሉና ህመሙ ወደ እግርዎ የሚሰራጭ ከሆነ የህክምና ባለሙያዎ ህመሙ ባለበት አካበቢ መድሃኒት እንዲወጉ ሊያዝሎት ይችላል፡፡

የቀዶ ጥገና
የጀርባ ህመም ካለቸዉ ዉስጥ የተወሰኑ ሰዎች የቀዶ ጥገና ሊያስፈልጋቸዉ ይችላል፡፡

አማራጭ ህክምናዎች
የጀርባ ህመሞትን ሊያስታግስልዎ የሚችሉ የተለያዩ አማረጭ ህክምናዎች ያሉ ሲሆን እነዚህን አማራጮች ከመጠቀምዎ በፊት የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ይመረጣል፡፡
• ካይሮፕራክቲክ ኬር
• የደረቅ መርፌ ህክምና( Acupuncture)
• ማሳጅ
• ዮጋ

የጀርባ ህመምን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ጀረባዎትን ጠንካራና ጤናማ ማድረግ
• የአካል እንቅስቃሴ፡- ተከታታይ የሆነ ቀለል ያሉ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴ ሆኖ በጀርባዎ ላይ ከፍተኛ ጫና የማይፈጥር ሆኖ ጡንቻዎ በደንብ እንዲሰራና ጀርባዎ ጥንካሬ እንዲገኝ የሚያደርግ ቢሆን ይመረጣል፡፡
• የጡንቻዎን ጥንካሬና መተጣጠፍ ማጎልበት፡- የሆድንና የጀርባ ጡንቻዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ይህን ለማጎልበት የሚረዳዎ ሲሆን የትኞቹ እንቅስቃሴዎች ይህን ሊረዱ እንደሚችሉ የአካል እንቅስቃሴ/ፊዚዎቴራፒስትዎን ያማክሩ፡፡
• የተስተካከለ ክብደት እንዲኖሮት ማድረግ፡- ዉፍረት በጀርባዎ ጡናቻዎች ላይ ጫና እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ክብደትዎን በመቀነስ የጀርባ ህመምዎን መከላከል ይቻለል፡፡

የተስተካከለ የሰዉነት ዘዴ/ሜካኒክስ
• በአግባቡ መቆም (ስታንድ ስማርት)፡- በሚቆሙበት ወቅት የዳሌ አቀማመጥ ተፈጥሮያዊ ቦታዉን እንዲይዝ ማድግ፡፡ለረጅም ሰዓት የሚቁሙ ከሆነ ትንሽ ድኳ/አጭር የእግር መረገጫ በማዘጋጅት እግሮዎን እያቀያየሩ በማስቀመጥ በታችኛዉ ጀርባዎ ላይ ያለዉን ክብደት/ጫና መቀነስ፡፡
• በአግባቡ መቀመጥ (ሲት ስማርት)፡- በሚቀመጡበት ወቅት የሚቀመጡበት መቀመጫ የታችኛዉን የጀርባ ክፍል የሚደግፍ መሆን አለበት፡፡ጀርባዎ ትክክለኛዉን ቅርፅ( to maintain its normal curve) እንዲይዝ ትንሽ ትራስ ወይም የተጠቀለለ ፎጣ ጀርባዎና በመቀመጫዉ መሃል ያስገቡ፡፡ ጉልበትዎና የዳሌ አጥንትዎ በኩል ደረጃ እንዲሆኑ ማድረግ፤የአቀማመጥ አቅጣጫዎን በተደጋጋሚ መቀያየር(ከተቻለ በየ30 ደቂቃዉ)፡፡
• በአግባቡ ማንሳት (ሊፍት ስማርት)፡- የሚያነሱትን ዕቃ ወደ ሰዉነትዎ በማስጠጋት፤ጉልበትዎን አጠፍ በማድረግና ወገብዎን ቀጥ በማድረግ፤ባንዴ ለማንሳትና ለመታጠፍ ሳይሞክሩና የሚያነሱት ዕቃ ከባድ ከሆነ ረዳት በመፈለግ የጀርባ ህመም እንዳይከሰት ያድርጉ፡፡

4 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.