ኪንታሮት በሽታ በትክክል ከታከመ ተመልሶ አይመጣም

3

ዶ/ር አሰፋ ወልዱ
safe_image

በጤና ለመኖር ጤናን መጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ጤንነትን ለመጠበቅ በቂ ውሃ መጠጣትና የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ፣ ንፅህናን መጠበቅና አመጋገብን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ። የዛሬው እንግዳችን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃውን ሄሞሮይድ በተለምዶ « ኪንታሮት» ከሚባለው ህመም ለመጠበቅ በርካታ ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደ ሚያስፈልግ አጥብቀው ይመክራሉ። እንግዳችን ዶክተር አሰፋ ወልዱ ይባላሉ። የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሲሆኑ፤ በሀልስተድ ከፍተኛ ክሊኒክ እያገለገሉ ይገኛሉ። ለዛሬ ማብራሪያ የሚሰጡን ህዝብ ሊያውቀውና አስቀድሞ ጥንቃቄ ሊያደርግበት ይገባል ያሉትን በፊንጢጣ አካባቢ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል «ሄሞሮይድ» የሚባለውን የበሽታ አይነት ነው፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 ሄሞሮይድ በተለምዶ « ኪንታ ሮት» ምን አይነት በሽታ ነው?

ሄሞሮይድ በፊንጢጣ አካባቢ የሚከሰት በሽታ ሲሆን ህዝባችን በተለምዶ ኪንታሮት በሚል ይጠራዋል። «ኪንታሮት» በሚለው አጠራር እኔ አልስ ማማም። ምክንያቱም በፊንጢጣ አካባቢ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች አንደኛ፤ አንድ አይነት ብቻ አይደሉም። ብዙ በሽታዎች ናቸው። ስለዚህ ለሁሉም አንድ አይነት ስያሜ መሰጠት የለበትም። ሁለተኛ፤ ኪንታሮት የሚባለው ብዙ ጊዜ በልጆች ቆዳ እጅ ፣ እግርና ፊት ላይ የሚወጣ ነው። በልጅነት «ኪንታሮት ነው አትንኩት ከተነካ ይባዛል» እየተባልን ነው የኖርነው። ስለዚህ አሁንም በፊንጢጣ አካባቢ የሚፈጠረውን ህመም «ኪንታሮት ነው አትንኩ» እየተባለ ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደከፋ የጤና ችግር የሚሸጋ ገሩበት ሁኔታ አለ።ስለዚህ « ኪንታሮት» የሚለው አጠራር ተገቢ አይደለም።
በዘመናዊ ህክምና ሄሞሮይድ የሚባለው ሁለት አይነት ነው። አንደኛው ኤክስተርናል(የውጭ) ሄሞሮይድ የሚባል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኢንተርናል (የውስጥ) ሄሞሮይድ ይባላል። ውጫዊው ሄሞሮይድ የሚፈጠረው በፊንጢጣ ዙሪያ በውጪኛው በላይ በኩል የሚገኙ ቀጫጭን የደም ስሮች አሉ። በተቅማጥ፣ በሀይለኛ ድርቀት ፣ ብዙ ጊዜ በመፀዳጃ ቤት በማማጥ ከቆዳው ስር ያሉ ደም ስሮች ይለጠጣሉ። እነዚህ በውጪ በኩል የሚገኙ ለስላሳ እና ትርፍ ስጋ መስለው በፊንጢጣ ዙሪያ ሊበቅሉ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። እነዚህ በውሃና በሳሙና እየታጠቡ በንፅህና እስከተያዙ ድረስ ብዙ ችግር የሚያመጡ አይደሉም።

ነገር ግን ከተፀዳዱ በኋላ በውሃና በሳሙና ካልታጠቡ እንደቆዳ ተንጠልጥለው ቆሻሻ ይደብቃሉ። ከሙቀት ጋር ላብ ይፈጠራል፣ ማሳከክና መጥፎ ጠረን የማምጣት ሁኔታ ይኖራል። ከእዚህም አልፎ ኃይለኛ ድርቀትና ተቅማጥ ሲኖር ማማጥ ከበዛ ከቆዳው ስር ያሉ ደም ስሮች ይበጠሱና በጓጎለ ደም ይወጠራሉ። ይህ «ትሮምቦስድ ኤክስተርናል ሄሞሮይድ» ይባላል ። በፊንጢጣ ዙሪያ በድንገት የሚፈጠር ጠጣር እባጭ ነገር ሲሆን የእብጠቱ መጠን በውስጥ እንደፈሰሰው የደም መጠን ሊለያይ ይችላል። በጣም ህመም ይፈጥራል። ለመቀመጥና ተነስቶ ለመራመድ ያስቸግራል። ይህ በጊዜ ካልታከመ በላዩ ላይ ያለው ቆዳ ተወጥሮ ይቆይና እስከ መቁሰልና መድማት «አልሰሬትድ ኤክስተርናል ሄሞሮይድ» ደረጃ ይደርሳል።

ሌላው ኢንተርናል ሄሞሮይድ ነው። ይሄ በፊንጢጣ በውስጠኛው ክፍል የሚገኝ ሲሆን ፤ በተፈጥሮ አልፎ አልፎ ወጣ ወጣ ያሉ( አናልኩሸነስ) የተባሉ አካላት አሉት። እነዚህ ፊንጢጣው ቆንጥጦ መያዝ ከሚችለው አቅም በላይ ሲሆን አጋዥ አካላት ናቸው ተብሎ ይታመናል። በግራ በኩል መሀል ላይ በቀኝ በኩል ከፊትና ከኋላ ይገኛሉ። ደረቅ አይነምድር ሲኖር ፣ ረጅም ሰዓት መፀዳጃ ቤት በመቀመጥ፣ ብዙ ተቅማጥ ሲኖር ፣ ከእርግዝናና ወሊድ እንዲሁም ከዕድሜ ጋር በተያያዘ እዚያ አካባቢ ያሉ ደም ስሮች እየላሉ ሲመጡ ፊንጢጣ ውስጥ መንጠልጠል ይጀምራሉ።

የኢንተርናል ሄሞሮይድ መገለጫው አንዱ መድማት ነው። ህመምተኛው ተፀዳድቶ ሲጨርስ ጠብጠብ የሚል ቀይ ደም መድማት ነው። ሌላው ደግሞ ወደ ውጪ መውጣት አለመውጣት ነው። ይሄ እንደየደረጃው በአራት ድግሪ ይመደባል። የመጀመሪያው ዲግሪ በውስጥ በኩል ተንጠልጥሎ ወደ ውጪ የማይወጣ ነው። ሁለተኛ ዲግሪ ህመምተኛው ሲያምጥ ብቅ ይልና አምጦ ሲጨርስ በራሱ ጊዜ የሚመለስ ነው። ሦስተኛ ዲግሪ ሄሞሮይድ የሚባለው ህመምተኛው ሲያምጥ ጉልጉል ብሎ ይወጣና በእጅ ካልተገፋ ወደ ውስጥ አይመለስም። አራተኛው ደረጃ ደግሞ ውጪ እንደወጣ የሚቀር በእጅም የማይመለስ ነው። ከዚህ ባሻገር የተወሳሰበ ሁኔታ ከተፈጠረ በሀይለኛ ተቅማጥ ተጎልጉሎ ሲወጣ የፊንጢጣ መቆጣጠሪያ ጡንቻ ከኋላ ቆንጥጦ ከያዘ «ፕሮላፕስድ ኤንድ ስትራንጉሌትድ ሄሞሮይድ ወይም ሄሞሮይዳል ክራይስስ» የተባለ ውስብስብ የጤና ችግር ይፈጠራል። ይሄ ከፍተኛ ህመም ያስከትላል። በሽተኛው ለመፀዳዳት ይቸገራል። ይሄ በወቅቱ መፍትሄ ካላገኘ ጋንግሪን እና መበስበስ ደረጃ ይደርሳል።

 

 ሄሞሮይድመንስኤው ምንድንነው?

የሄሞሮይድ መንስኤው የሆድ ድርቀት ነው። መፀዳጃ ቤት ውስጥ ለረጅም ሰዓት ተቀምጦ ማሳለፍ፣ረጅም ጊዜ ትንፋሽን አፍኖ ማማጥ ፣ የእድሜ መጨመር፣ ሴቶች በእርግዝና ወቅት እና በወሊድ ጊዜ እህታ ሲጨመር ችግሩ ይባባሳል።

ድርቀትን ለመከላከል የኢትዮጵያውያን አመጋገብ ከሌላው ዓለም ህዝቦች (ካደጉት ሀገራት) በተለየ ተጠቃሚ ነን። ጤፍ የማይፈተግ ምግብ ነው። ስለማይፈተግ ገለባ አለው። ፓስታ መኮረኒ የመሳሰሉ የፋብሪካ ውጤቶች ገለባ የላቸውም። በምግብ ላይ ገለባ መኖር ከአፍ ጀምሮ እስከ ፊንጢጣ ድረስ ለጤነንት ጥሩ ነው። ከብዙ በሽታዎች ይከላከላል። አሰር ያላቸውን ቅጠላ ቅጠል መመገብ ጥሩ ነው።

ሌላው ለድርቀት ምክንያቱ በቂ ውሃ አለመጠጣት ነው።አንድ ሰው በቀን በሚያቃጥለው ካሎሪ እኩል ውሃ መጠጣት አለበት። ስለዚህ አንድ ሰው በቀን ከሁለት እስከ ሁለት ሊትር ተኩል ( ከስምንት እስከ አስር ብርጭቆ ውሃ መጠጣት) አለበት። ይህ ሲሆን ድርቀትን ይከላከላል።

ሌላው ችግር ደግሞ ማስማጥ ነው። ይህን ችግር ከሚያስከትለው አንዱ በርበሬና ቅመማ ቅመም የበዛበት ምግብ መመገብ ነው። የሰው ልጅ ለመፀዳዳት ቤት ውስጥ መጠበቅ ያለበት ቢበዛ አምስት ደቂቃ ነው። ብዙ ሰዎች ግን የሚነበብ ይዘው ይገባሉ፤ ኮምፒዩተር ይዘው ረጅም ሰዓት ይቀመጣሉ። ይህ አይመከርም። የመፀዳዳት ሰዓታችን ለመታጠብና ለመድረቅ በሚቻልበት ሰዓት ላይ እንዲሆን ማስለመድ ያስፈልጋል። በመፀዳዳት ወቅትም ድንጋይ፣ ቅጠል ፣ ወረቀት ፣ ሶፍት፣ ጋዜጣና የመሳሰሉትን ከመጠቀም ይልቅ በውሃና ሳሙና በመታጠብ ንፅህናን መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህ ለሄሞሮይድ ብቻም ሳይሆን ለሌሎች ፊንጢጣ አካባቢ ለሚከሰቱ የህመም ችግሮች መፍትሄ ነው።

ሄሞሮይድ የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ያጠቃል?

ሄሞሮይድ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያጠቃል። ወንድ፣ ሴት ፣ልጅ፣ አዋቂ አይመርጥም። ከተማ ገጠር አይለይም። ሆኖም ብዙ ጊዜ ህፃናት ላይ አይታይም።  ሄሞሮይድ በዘመናዊ ህክምና የሚድን ህመም ነው።

ሕክምናው ምንድን ነው?

የውጪው ሄሞሮይድ «ኤክስተርናል ሄሞሮይድ ትሮንቦስት» ካልሆነ ወይም የጓጎለ ደም ተፈጥሮ መቁሰልና መድማት ደረጃ ካልደረሰ በስተቀር በእንክብካቤ መያዝ ይቻላል። ዙሪያው አበጥ አበጥ ሲል በመሀሉ ቆሻሻ እየደበቀ ካልታጠበ የመርጠብና የማሳከክ ችግር ይፈጥራል። ስለዚህ ያንን አካባቢ በውሃና በሳሙና የምንታጠብ ከሆነ ችግር አይሆንም። አልፎ አልፎ ችግር ሲኖር ለብ ባለ ውሃና ጨው ተዘፍዝፎ መታጠብ ጥሩ ነው። ስለዚህ ችግሩን በዚህ መልኩ መንከባከብ ይቻላል። ነገር ግን ትሮንቦስት ሄሞሮይድ ከተፈጠረና ቁስሉ መድማት ከጀመረ በቀዶ ህክምና ማስወገድ ይቻላል።

ኢንተርናል ሄሞሮይድ ደግሞ እንደየደረጃው የተለያዩ የህክምና አማራጮች አሉት። የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ላይ ካሉና እየደማ ለህይወት በሚያሰጋ ደረጃ ላይ ካልሆነ አስፈላጊ የሆኑትን ጥንቃቄዎች በማድረግ፣ አመጋገብን በማስተካከል፣ የሰውነት እንቅስቃሴ በመስራት፣ የግል ንፅህና በመጠበቅ፣ ድርቀትን በመከላከል እንዲሁም ሰገራን የሚያለሰልሱ፣ አካባቢን የሚያረጥቡ፣ የህመም ማስታገሻ በመውሰድ መንከባከብ ይቻላል። ከዚህ አልፎ ከሄደ ግን ለማስወገድ የተለያዩ አማራጮች አሉ።

ለምሳሌ በአንደኛና በሁለተኛ ዲግሪ ላሉ ህመሞች በ«ባንድላይጌሽን» ህክምና ይደረጋል። ይህ ህክምና ሄሞሮይዶችን በአንድ ላይ በላስቲክ ማሰር ነው። በሙቀትና በሀይለኛ ቅዝቃዜ ማቃጠል እንዲሁም በኢንፍራሬድ መሳሪያ ማቃጠል ነው። ነገር ግን የህመም ደረጃው ሶስተኛና አራተኛ ዲግሪ ላይ ከደረሰ የቀዶህክምና ይደረግና ተቆርጦ ይወጣል። ስለዚህ የውስጥም ሆነ የውጪው ሄሞሮይድ በዘመናዊ ህክምና በመድኃኒት እና በቆዶ ህክምና የመዳን ዕድል አለው።

ሄሞሮይድስ በቀዶ ህክምና ከወጣ በኃላ እንደገና ይተካል የሚሉ ወገኖች አሉ ።ይሄ ምን ያህል እውነትነት አለው?

በትክክል ቀዶ ህክምና ከተሰራ እና ቀደም ሲል ለሄሞሮይድ መከሰት መንስኤ ናቸው ያልናቸው እንዳይከሰቱ በሚገባ ጥንቃቄ ካደረግን ሄሞሮይድ አይተካም።

 አንዳንድ ሰዎች ከዘመናዊ ህክምና ይልቅ ባህላዊውን ይመርጣሉ። ባህላዊ ህክምና ሙሉ ለሙሉ ያድናል የሚሉም አሉ ። ይሄ ምን ያህል ተቀባይነት አለው?

ባህላዊ ህክምና በሀገራችን ለረጅም ዘመን አብሮን የኖሮ ነው። ዘመናዊ ህክምና ወደ ህብረተሰቡ የደረሰው አሁን ነው። ስለዚህ ህዝቡ ዘንድ ሊኖር የሚችል ተቀባይነት አለ። ምንያህል ውጤታማ ነው? የሚለውን ለመናገር ጥናት ያስፈልጋል። ምንያህል ጉዳት አለው የሚለውንም ጭምር። ነገር ግን እኔ በስራ ላይ ያሚያጋጥሙኝ «ባህላዊ ህክምና ሄደን ነው…» የሚሉ ለተወሳሰበ ችግር የተዳረጉ ሰዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ምንነቱ የማይታወቅ የተቀመመ ነገር ተጨምሮባቸው ተጎድተውና ሰገራቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ይመጣሉ። የአይነምድር መውጫቸው ተደፍኖባቸው መፀዳዳት አቅቷቸው የሚመጡ ሰዎችም አሉ። ብዙ አይነት ችግሮችን ይዘው ነው የሚመጡት።

ባህላዊ ህክምና ሁሉም ነገር ድብቅ ሆኖ ነው የሚሰራው። የትኛው ባህላዊ ሀኪም ያድናል የትኛው አያድንም የሚለውንም ማወቅ አይቻልም። እንዲሁም የሚሰጡት መድሀኒቶች ከንፅህና ጋር ተያይዞ የሚደረገው ጥንቃቄስ ምን ያህል ነው? የሚለው ሁሉ አጠያያቂ ነው። የባህል ሀኪሙ ስለተፈጥሮ በሚገባ ያውቃል ወይ? የሚያነባቸው መጻህፍት አሉ ወይ? የሚለውን ማወቅ ይከብዳል። እንደ አጠቃላይ ግን «ባህላዊ ህክምና ሄደን ነው» የሚሉና ብዙ ችግር የገጠማቸው ሰዎች መኖራቸውን መናገር ይቻላል።

ህመምተኞች ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው?

ህመምተኞች ለሄሞሮይድስ መንስኤ ናቸው ያልናቸውን ሁሉ ጥንቃቄዎች ማድረግ አለባቸው። ገለባ ያለባቸውን ምግቦች መመገብ፣ ድርቀትን መከላከል፣ በቂ ውሀ መጠጣት፣ በውሀና በሳሙና መታጠብና ንፅህናን መጠበቅ፣ ረጅም ሰዓት መፀዳጃ ቤት አለመቀመጥ የሚሉትንና ሌሎችንም ተግባራዊ ማድረግ ነው።

 የፊንጢጣ አካባቢን ለማፅዳት ምን አይነት ሳሙና መጠቀም ያስፈልጋል?

በየምግብ ቤቱ ሁሉ «ጥሩ ነው» በሚል አጃክስና የልብስ ማጠቢያ ሳሙና ለእጅ መታጠቢያነት ሲውል ይታያል። ይህ ስህተት ነው። ለልብስ እና ለሌላ ነገር የተሰራው ሳሙና ያለው የኬሚካል አይነትና መጠን የልብስ ቆሻሻን ለማስለቀቅ ነው። ስለዚህ ቆዳን ይጎዳል። አሁንም በውሀና በሳሙና ሲባል በገላ መታጠቢያ ሳሙና ማለት ነው። በማንኛውም ሳሙና ገላን መታጠብ ቢቻል ኖሮ የልብስ የገላ ተብሎ ሳሙና አይፈበረክም ነበር።

– See more at: http://www.tenaadam.com/amharic/archives/1460#sthash.1rRBmIci.dpuf

3 COMMENTS

 1. መቸስ እግዚአብሄር ይስጥልኝ ከማለት የዘለለ ስጦታ የለኝም እንጂ መከፈልስ ያለበት ለዚህ ትምህርታዊ ፅሁፍ ነበር፡፡አመስግናሎህ፡፡ግን አንድ ቅሬታ አለኝ ቅሬታው የተፈጠረብኝ ኢትጱያውያን ለኪንታሮት የተጋለጡት በፈንጢጣቸው ባህሪ አልያም በሚመገቡት ምግብ ብዛት ገለመለ የሚሉ የተዛቡ ቃለመጠይቆች በ ኢቲቪ ኣዳምጨ ነበር ድሮ ነው ኢቲቢ ኢቢሲ ሳይባል፡፡
  ይሄ ፍፅም ስህተት ነው፡፡ኢትዮጱያውያን በዘራችን ያልተሟላን /incomplete/ አይደለንም የሚል ሐሳብ ነበረኝ አሁን ያነበብኩት ፅሁፍ ማካካሻ ሆኖልኛል ::የምንመገበው ምግብ ጤፍ ስለሆነ አልያም ብዙ ስለሆነ ጥራት ስለሌለውም አይደለም ብየ ስለማምን በዛሬው እለት ትክክለኛ ሙሁራዊ ትንተና /ማብራሪያ/ ስላገኘሁ ደስታየ ከፍተኛ ነው፡፡ከበሽታው የዳንኩ ያህል ተሰማኝ፡፡ እኔ ስግብግብ ነጋዴዎች ወይም ሙሰኛ የዩኒበርሲቲ አመራር ያመጡብኝ እንጂ በተፈሮ ወይም ደግሞ በዘር አለመሆኑ አምናሎህና፡፡
  ኢትዮዩያውያን በኪንታሮት የመያዝ ሰለባ እንዲሆኑ ካደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት ንፁህ መፀዳጃቤት ፣ንፁህ መኝታቤት፣ንፁህ አከባቢ ስለሌላቸው ነው ባይ ነኝ፡፡ምግብ በልተን ምግብ ቤቶቹ ሽንት ቤት ከሌላቸው ፣ ቤት ተከራይተን የተከራየነው ቤት ሽንት ቤት ከሌለው ፣የምንሰራበት መስራቤት በሰዓት እንድንገባና ሙሉ የስራ ሰዓታችን በስራ እንድናሳልፍ ተፈልጎ ነገር ግን ንፁህ ሽንት ቤት ከሌለው ባንታመም ነው የሚገርመው፡፡ሽንት ቤት አለ ቢባልም የስራ አስኪያጁ ለብቻው ይፀዳና/ይታጠብና/ ሌላው ሽንት ቤት አይፀዳም/አይታጠብም/ ውሃም የለውም የሚመለከተው የጤና ተቋም የላካቸው ባለሙያዎች ሊጎበኙ በሄዱበት የመስክ ስራ ሙስና በልተው የሚፈለገው ጉብኝት አካሂደው የሚፈለግ ሪፖርት አያቀርቡም፡፡ ንፁህ እና ጤናማ ሽንት ቤቶች ፣ንጡህና ጤናማ ሻወር ቤቶች ፣ንጡህና ጤናማ ምግብ ቤቶች ሲገነቡ ብቻ ነው ጤናማ ትውልድ ሊኖረን የሚችለው ብየ እከራከራሎህ፡፡
  ክርክሬ የሚያጠነጥነው በዚህ ዌብሳይት ለተፃፉ ሳይንሳዊ ማብራሪዎች አደለም፡፡ልብ በሉኝ እኔ የታመምሁት በድርቀት ነው !! በትክክል ተገልፀዋል ድርቀትም የያዘኝ በአንድ ወቅት ዩኒበርሲቲ እየተማርሁ በነበርሁበት ውሃና ሽንትቤት ስላልነበረ ነው ፡፡በጣም እየተፈታተነኝ ያለውም ምግብ በልቸ እምፅዳዳበት ውሃ ያለው ሽንት ቤት በከተማው ስለሌለ ነው ፡፡እኔን ተውኝ በርካታ ምርታማ የህብረተሰብ ክፍል በሽተኛ ያደረጉ እና በሽተኛ ለማድረግ የተዘጋጁ እነዚህ ምግብ ቤቶት የቆለፉት ሽንት ቤት ከፍተው ምግብ የሚገዛላቸውን ህብረተሰብ ጤንነት ሊጠብቁ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
  ሙሰኛው የሳኒተሪ ባለሙያ ህዝቡ ከሌለ ዶመዙ እንደማያጀኝ ቢያውቅልኝ ደስ ይለኛል፡፡ህዝቡ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ጤናማ እና ምርታማ ካልሆም ጭምር የሚበላው ሙስና የለውም የሚከፈለው ዶመዝም አይኖርም፡፡
  በየመስሪያቤቱ ያሉ የውሃ ቧምቧዎች በሳምንት ይበላሻሉ አልያም ጥራት ባለው እቃ አልተሰሩም ወይም ደግሞ ተተቃሚው ብጥንቃቄ አይይዛቸውም፡፡ምን በመሰለ ዘመናዊ ሽንት ቤት የውሃ ማሸጊያ ላስቲክ /በተለምዶ የሀይላንድ ኮዳ/ እና የተፅዳዳበት ሽንጽ ቤት ቀዳዳ ላይ ይከታል፡፡እኔ በጣም እገረማሎህ ፡፡ ከ30 ብር እማትበልጥ የውሀ ቧንቧ አፍ አውልቆም ይወስዳል፡፡ ታድያ የቱ ጋ ነው የኢትዮጱያውያን ኩሩነት ፣ ጭውነት፣ መልካምነት? ከዘፈን የዘለለ መካም ተግባር ቢኖረን ጥሩ ነው እላህ፡፡
  ይቅርታ አጀንዳየ ከጤና አልፎ ማሕበራዊ ጉዳይ ገባ መሰለኝ ፡፡ማሕበራዊ ኑሮአችን በጤናችን ጉዳት እያመጣ ስለሀነ ነው፡፡

 2. I found It is very important and informative for the community to take the major actions and cares before the Worest comes.but would you please let me know the location of halseted higher clinic?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.