Morengaየሞሪንጋ ዛፍ በኢትዮጵያ በተለምዶ ሽፈራው በሚል የሚታወቅ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ13 በላይ ዝርያዎች ያሉትና በሁለገብ ጠቀሜታቸው ከሚታወቁት ዛፎች መካከል አንዱ ነው። በአለም ላይ ካሉት የሞሪንጋ ዛፍ ዝርያዎች ውስጥ ሰባት የሚሆኑት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በጅቡቲና በሶማሊያ አካባቢዎች ይገኛሉ።

ሽፈራው ከሚለው ስያሜ ባሻገር የጎመን ዛፍ ወይም የአፍሪካ ሞሪንጋ- Moringa stenopetala) ተብሎ የሚጠራው ዛፍ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በዝቅተኛው የስምጥ ሸለቆ ሀይቅ በደረቃማ እና ከፊል-ደረቃማ በሆኑት የአየር ንብረት ክልሎች ማለትም በደራሳ (ጌዲዎ)፤ ሲዳማ፤ ኮንሶ፤ ኦሞ (ወላይታ) ፤ ምዕራብ ጋሞጎፋ፤ ጊዶሎ፣ ቡርጂ፣ ሴይሴና በመሌ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወሎ፤ ሸዋ፤ ሀረርጌና ሲዳማ አካባቢዎች የግብርና ልማትን ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ጋር በማቀናጀት ለሰርቶ ማሳያ እየተተከለ መሆኑን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ሞሪንጋ በፎንተኒና (ወሎ)፣ ዴራ (አርሲ) እንዲሁም በዝዋይ መስኖ እርሻ ለነፋስ መከላከያ አጥር በመሆን ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ደቡባዊው የስምጥ ሸለቆ ክፍል በተለይም በከፋ፣ ጋሞ ጎፋና ሲዳማ አካባቢዎች አንፃራዊ በሆነ መልኩ በተሻለ ስርጭት ይገኛል።

ሞሪንጋ በምድር ወገብ ፈጣን ዕድገት አለው። ይህ ዛፍ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል ለምግብነት፣ ለመድሃኒትነት፣ ለውሃ ማጣሪያነት፣ ለእንስሳት መኖነትና ለንብ ቀሰምነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በደቡብ ክልል የኮንሶ ብሔረሰቦች ለምግብ አገልግሎት ከመጠቀማቸው ባለፈ ከሌሎች ሰብሎች ጋር አሰባጥረው በመትከል ቀጣይነት ባለው የአመራረት ዘይቤ የመሬት ምርትና ምርታማነት እዲጨምር በማድረግ ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ይህ ዛፍ ቅጠሉ በምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው ከሚታወቁት ሰብሎች ማለትም ከካሮት (ቫይታሚን ኤ)፣ ከአተር (ፕሮቲን)፣ ከብርቱካን (ቫይታሚን ሲ)፣ ከወተት (ካልሽየም) እና ከቆስጣ (ብረት) ንጥረ ነገሮች ይዘት እንዳሚበልጥ ጥናቶች ያሳያሉ።

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዝናብ አጠር በሆኑት በዋግኽምራ ዞን (አበርገሌ) እና በሰሜን ሸዋ (እንሳሮ ወረዳ) በተሰሩ የምርምር ስራዎች ሞሪንጋ በአካባቢው መላመድ የሚችልና ውጤታማ ዛፍ መሆኑ ተረጋግጧል፤ በመሆኑም በተመሳሳይ ስነምህዳሮች (አካባቢዎች) እንዲስፋፋ ማድረግ ተገቢ ነው።

የተገኘው የምርምር ሙከራ ውጤት እንደሚያመለክተው የሞሪንጋ ዛፍ በበጋ ወራት ቅጠሉን በመጠኑ የሚያረገፍ ነገር ግን ቅርንጫፉ ከተቆረጠ /ከተከረከመ/ ቅጠሉን ከማርገፍ የሚቆጠብና ብዙ ቅጠል የሚያቆጠቁጥ መሆኑ ታይቷል።

ዛፉ ደረቃማና ከፊል ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች የሚበቅልና የሚያድግ በመሆኑ የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅና ለምግብነት አገልግሎት ስለሚውል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ አስተዋጽዖው የጎላ ነው። ስለዚህ ከባቢያዊ ችግር ባለባቸውና ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ቢለማና መስፋፋት ቢችል ለምግብ ዋስትና ከሚያደርገው አስተዋፅዖ በተጨማሪ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ተመራጭ ዛፍ ያደርገዋል።

የዚህ መዝገበ ዕውቀት ጽሁፍ CCA ስር

ለጓደኛዎ ያካፍሉ (SHARE and Like)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.