የትልቁ አንጀት ካንሰር ምልክቶችና ህክምናው

0

ዶ/ር ዓብይ ዓይናለም 

የትልቁ አንጀት ካንሰር እንደ ሌሎች ካንሰሮች ሁሉ፣ ራሱን ሰውነት ውስጥ በማባዛትና በማሰራጨት ሌሎች አካላቶቻችን ስራ እንዳይሰሩ በሚያደርግበት ጊዜ የሚከሰት ነው፡፡

የትልቁ አንጀት ካንሰር በአመዛኙ፣ ከ50 እስከ 70 ዓመት ዕድሜ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚታይ ሲሆን፣ አንዳንዴ ከዚህ የዕድሜ ክልል ዝቅ ብሎም ሊከሰት ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከ20 እስከ 40 ዓመት ዕድሜ በሆኑ ወጣቶች ላይ በብዛት እየታየ ነው፡፡ ለዚህ መንስኤው ምን እንደሆነ በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ ወደፊት ሰፊ ጥናት ተደርጎ ምክንያቱን ማወቅና መጠንቀቅ ያስችለናል ብዬ አስባለሁ፡፡

የትልቁ አንጀት ካንሰር በአደጉት ሀገራት ከሴቶች የጡት ካንሰር በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ በወንዶች ላይ በአንደኝነት በሴቶች ላይ ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ይከሰታል፡፡

በዓለማችን በአማካይ በዓመት አንድ ሚሊየን ሰዎች በበሽታው ይጠቃሉ ተብሎ ሲገመት፣ ከእነዚህም ግማሽ የሚሆኑት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከበሽታው ይድናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

አጋላጭ ምክንያቶቹ

ዕድሜ በጨመረ ቁጥር ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል አለ፡፡ ስለዚህም ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ግለሰቦች ሁሉ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ቢያደርጉና በሽታው ሊሆኑ የሚችሉ ምልክቶችን ካስተዋሉ ቶሎ ሐኪም ዘንድ ቀርበው መታየትና በግልፅ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡

የትልቁ አንጀት ካንሰር ሴቶችም ወንዶችም ላይ ቢከሰትም፣ ከሴቶች ይልቅ በብዛት በወንዶች ላይ ይከሰታል፡፡

አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና አመጋገብ፣ እንደ ማንኛውም ያለፈ ውፍረትና አመጋገብ፣ እንደ ማንኛውም ካንሰር ትልቁን አንጀት ለካንሰር ሊያጋልጠው ይችላል፡፡

በበሽታው የተጠቃ የቤተሰብ ወይም የቅርብ ዘምድ መኖር ወይም የረዥም ጊዜ የአንጀት ቁጣ መደጋገም በበሽታው አማጭነት ይታወቃል፡፡

ምልክቶቹ

የትልቁ አንጀት ካንሰር ምልክቶች እንደ በሽታው ደረጃ እና በሰውነታችን ውስጥ ባለው የስርጭት መጠን ይለያያል፡፡

በሽታው ሲጀማምር ከተለመደው ወጣ ያለ የሆድ ድርቀት፤

የሰገራ መቅጠን ወይም ደም እና ንፍጥ የቀላቀለ የረዥም ጊዜ ተቅማጥ

በእርግጥ እነዚህ ምልክቶች በሌላ በሽታ ምክንያት ለምሳሌ በአንጀት ውስጥ ትላትሎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ምልክቶቹ ታዩ ማለት የትልቁ አንጀት ካንሰር ነው ማለት አይደለም፡፡ ባለሙያ ጋ ቀርቦ በአግባቡ መታየትና መመርመር ያስፈልጋል፡፡

– ከሰገራ በኋላ ደም መኖር

– የሆድ እብጠት፣

– ከፍተኛና ተደጋጋሚ ቁርጠት፣

– ደረጃው እየገፋ በሚሄድበት ጊዜ የምግብ ፍላጎትና የክብደት መቀነስ፣

– የድካም ስሜት

– የጀርባ ህመም እና ሰገራ ለመቀመጥ መቸገር ሊኖር ይችላል፡፡

ህክምናው

አንድ ታማሚ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶችን ሲያሳይና፣ የህክምና ባለሙያው የትልቁ አንጀት ካንሰር ሊሆን ይችላል ብሎ ካሰበ፣ ይሄን ለማረጋገጥና ደረጃውን ለማወቅ ተጨማሪ ምርመራዎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ከዕጢው ላይ ናሙና ወስዶ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማድረግም በፊንጢጣ በኩል የሚገባ መሳሪያ ወይም ቀዶ ጥገና ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቀዶ ጥገናው አንድም በሽታውን ለማረጋገጥ እንዲሁም በሽታውን ለማከም ይረዳል፡፡

በሽታው ከተረጋገጠ በኋላ ደረጃውን ለማወቅና ህክምና ለማስጀመር ተጨማሪ ምርመራዎችን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህም፡-

– የሆድ አልትራሳውንድ

– ሲቲስካን

– ኤም አር አይ

– የደረት ራጅ

– የተለያዩ የደም ምርመራዎች

የትልቁ አንጀት ካንሰር ህክምና፣ እንደ በሽታው ደረጃ የናሙና ውጤት፣ እንደ በሽተኛው ዕድሜና አቋም እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች ይለያል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ የህክምና ዘዴዎች ሲኖሩት ከኦፕሬሽን በተጨማሪ ኬሞቴራፒ፣ የጨረር ህክምና እንዲሁም በሀገራችን ባይለመድም ታርጌትድ ቴራፒ የተባ ህክምናዎች አሉ፡፡

የትኛውን ህክምና መጠቀም አለብን ለሚለው፣ እንደ በሽታው ደረጃ፣ እንደ ባለሙያውና እንደ በሽተኛው ውሳኔ ይለያያል፡፡ ባለሙያው እና በሽተኛው ስለ ጉዳዩ በጥልቀት መወያየትና በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

በሽታው ደረጃ አንድ ወይም ሁለት በሚሆንበት ጊዜ ኦፕሬሽን በቂ ሲሆን፣ የናሙናው ውጤት ታይቶ እንደ አስፈላጊነቱ ኬሞቴራፒ ሊጨመር ይችላል፡፡

ደረጃ ሶስት ላይ በብዛት ኦፕሬሽን በኋላ ደግሞ ኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ ያስፈልገዋል፡፡

በሀገራችን ህክምና አሁን በደረሰበት፣ ደረጃ አራት የአንጀት ካንሰር በሽታን ሙሉ በሙሉ ማዳን ይከብዳል፡፡ እነዚህ በሽተኞች በዋነኛነት የሚታከሙት ኬሞቴራፒ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ህመሙን ለመቀነስና በሽታውን ለመቆጣጠር Radiotherapy Surgery የህክምና አማራጭ ልንጠቀም እንችላለን፡፡

እዚህ ጋ መገንዘብ ያለብን፣ የትልቁ አንጀት ካንሰር በቶሎ ከተገኘ /ደረጃው ሳይገፋ/ እና አስፈላጊው ህክምና ከተደረገለት እንደ ማንኛውም በሽታ ሙሉ በሙሉ መዳንይችላል፡፡ ይሄ እንዲሆን ደግሞ የበሽታው ምልክት ከታየ ቶሎ በሐኪም መታየትና የቅድመ ካንሰር ምርመራ (screening) ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

እንዴት መከላከል እንችላለን?

የትልቁ አንጀት ካንሰርን ለመከላከል፣ በተቻለ መጠን ጤናማ የአመጋገብ እና የህይወት ዘይቤ መከተል ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይኼም ማለትየአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ክብደትን መቆጣጠር፣ አልኮልን አብዝቶ አለመጠጣት፣ አለማጨስ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ ማለታችን ነው፡፡

በእኛ ሀር ባይለመድም ቅድመ ካንሰር ምርመራ በኋላ ሊመጣ ከሚችል በሽታ እጅግ ተመራጭ ቅድመ ጥንቃቄ ዘዴ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.