ወደ ጥርስ ሐኪም መሄድ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

toothዘመናዊው የጥርስ ሕክምና ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ከወጣትነታቸው ጀምሮ በጥርስ ሕመምና በጥርስ መውለቅ ይቸገሩ ነበር። ብዙ ሰዎች የጥርስ መበለዝ፣ መወላገድ ወይም መውለቅ ውበታቸውን ይቀንስባቸው ነበር። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ማኘክ ስለሚቸግራቸው ለተመጣጣነ ምግብ እጥረት ይዳረጋሉ እንዲሁም ያለ ጊዜያቸው ይሞታሉ። በዛሬው ጊዜ በርካታ የጥርስ ሕመምተኞች ከሕመማቸው ነጻ መሆን፣ ዕድሜያቸውን ሙሉ የጥርሳቸውን ጤንነት መጠበቅና ጥርሳቸው ውበቱን እንደያዘ እንዲቆይ ማድረግ ችለዋል። ዘመናዊው የጥርስ ሕክምና እነዚህ ሦስት አስደናቂ ስኬቶች ላይ መድረስ የቻለው እንዴት ነው?

ትምህርት በመስጠትና በየጊዜው ምርምራ በማድረግ ላይ የተመሠረተው በመከላከል ላይ ያተኮረ የጥርስ ሕክምና የጥርስ ሕመምንና የጥርስ መውለቅን ለማስወገድ የሚረዳ ወሳኝ መንገድ ነው። ኢየሱስ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም” ብሏል። (ሉቃስ 5:31) በመሆኑም አንዳንዶች ስለ ጥርስ ንጽሕና አጠባበቅ ያገኙት ትምህርት በእጅጉ ስለጠቀማቸው እምብዛም ሐኪም ቤት መሄድ አላስፈለጋቸውም።* የሆነ ሆኖ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች ወደ ጥርስ ሐኪም መሄድ አይፈልጉም። አንዳንዶች እንዲህ የሚያደርጉት ሁኔታው ስለማያሳስባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው ስለማይፈቅድላቸው ነው። ከዚህም በላይ መታከም ፈርተው ወደ ጥርስ ሐኪም የማይሄዱ ሰዎች አሉ። አንተ ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅህ ተገቢ ነው:- ‘የጥርስ ሐኪሙ ምን ሊረዳኝ ይችላል? ወደ እርሱ መሄዴ ጥቅም ይኖረዋል?’ ለጥርሳችን ቅድመ ጥንቃቄ የማድረጉን አስፈላጊነት ለመገንዘብ የጥርስ ሐኪሞች ለማስወገድ የሚሞክሩት ምንን እንደሆነ ማወቃችን ጠቃሚ ነው።

ጥርስ መጎዳት የሚጀምረው እንዴት ነው?

የጥርስ ሐኪሞች የጥርስ ሕመምና የጥርስ መውለቅ የሚያስከትለውን ሥቃይ ማስቀረት እንድትችል ሊረዱህ ይችላሉ። የአንተ ትብብር ታክሎበት ሐኪሞቹ በጥርስህ ላይ በመጣበቅ ባክቴሪያ የሚፈጥሩ ቆሻሻዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለማስወገድ ይሞክራሉ። ባክቴሪያዎች ጥርስ ውስጥ ተሰግስጎ የሚቀረው ምግብ ስለሚመቻቸው እንደልብ ይራባሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች በምግቦቹ ውስጥ የሚገኘውን ስኳር ወደ አሲድነት የሚለውጡት ሲሆን አሲዱ የጥርስን መስተዋት በመጉዳት ጥቃቅን ቀዳዳዎችን ይፈጥራል። ቀዳዳው ቀስ በቀስ ሰፍቶ ጥርስህ መቦርቦር ደረጃ ላይ ሲደርስ ጥርስህ መበስበስ ይጀምራል። በዚህ ወቅት ምንም ሕመም አይሰማህም፤ ነገር ግን ጥርስህ እየተቦረቦረ ሄዶ የጥርስህ ማዕከላዊ ክፍል ላይ ሲደርስ ኃይለኛ የሕመም ስሜት ይሰማሃል።

በቆሻሻው ምክንያት የሚፈጠረው ባክቴሪያ ሌላም ጉዳት አለው። ቆሻሻው በጥንቃቄ ካልተወገደ በስተቀር ድድን ሊያስቆጣና ከቦታው እንዲሸሽ ሊያደርግ የሚችል ታርታር የተባለ ጠንካራ የቆሻሻ ክምችት ይፈጥራል። ይህ ደግሞ በጥርስህና በድድህ መካከል ክፍተት እንዲኖር በማድረግ ድድህን የሚጎዱ ባክቴሪያዎች እንዲራቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። የጥርስ ሐኪምህ ችግሩ እንዲስተካከል ማድረግ ይችላል። ሁኔታውን ችላ ካልከው ግን ጥርስህን አቅፎ በያዘው በድድህ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስበትና ጥርስህ መውለቅ ሊጀምር ይችላል። በጥርስ መቦርቦር ምክንያት ከሚወልቀው ይልቅ በድድ መጎዳት ሳቢያ የሚወልቀው ጥርስ ይበልጣል።

ባክቴሪያዎች ከሁለት አቅጣጫ የሚሰነዝሩትን ጥቃት በመከላከል ረገድ ምራቅህ የሚጫወተው ሚና አለ። እስክትጠግብ ድረስ በምትበላበትም ሆነ ትንሽ ጣፋጭ በምትቀምስበት ጊዜ ምራቅህ የምግብ ትርፍራፊዎችን አስወግዶ በጥርስህ ቆሻሻ ላይ ያሉትን አሲዶች ለመበረዝ ከ15-45 ደቂቃ ይወስድበታል። ጊዜውን የሚወስነው በጥርስህ ላይ ተጣብቆ የቀረው የስኳር ወይም የምግብ መጠን ነው። ጥርስህ ጉዳት የሚደርስበት በእነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ይመስላል። በመሆኑም በጥርስህ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የተመካው በምትበላው የስኳር መጠን ላይ አይደለም ማለት ነው፤ ከዚህ ይልቅ ቶሎ ቶሎ የምትመገብ ከሆነና ስኳርነት ያላቸውን ምግቦች የምታዘወትር ከሆነ ጥርስህ ሊጎዳ ይችላል። በእንቅልፍ ወቅት አፍህ የሚያመነጨው የምራቅ መጠን ስለሚቀንስ ጣፋጭነት ያላቸውን ምግቦች ወይም መጠጦች ከተመገብክና ከጠጣህ በኋላ ጥርስህን ሳትቦርሽ የምትተኛ ከሆነ በጥርስህ ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ታስከትላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ከምግብ በኋላ ስኳር አልባ ማስቲካ ማኘክ የምራቅህን መጠን ስለሚጨምር ጥርስህን ከጉዳት ለመከላከል ይረዳሃል።

በመከላከል ላይ ያተኮረ የጥርስ ሕክምና

የጥርስ ሐኪሞች እንደ ጥርስህ ሁኔታ በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ምርመራ ማድረግ ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። በምርመራው ወቅት ሐኪምህ ጥርስህን ራጅ ሊያነሳና የጥርስ መበስበስ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጥንቃቄ የታከለበት ምርመራ ሊያደርግ ይችላል። ሕመም ባለበት ቦታ ላይ ማደንዘዣ በማድረግና በከፍተኛ ፍጥነት የሚንቀሳቀሱ የጥርስ መሰርሰሪያዎችን በመጠቀም የተቦረቦረ ቦታ ካለ ምንም ሳያሳምምህ ይሞላዋል። አንዳንድ ሐኪሞች ይህ ዓይነቱን ሕክምና የሚፈሩ ሰዎችን ለመርዳት ጨረር ወይም ጥርስ ላይ ያለውን ቆሻሻ ለማሟሟት የሚረዳ ቅባት መጠቀም ጀምረዋል፤ ይህ ደግሞ ማደንዘዣንም ሆነ የጥርስ መሰርሰሪያዎችን መጠቀምን ሙሉ በሙሉ አሊያም በከፊል የሚያስቀር ነው። ከልጆች ጋር በተያያዘ ሐኪሞች ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት አዲስ ለሚበቅሉ የመንጋጋ ጥርሶች ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ጥርሶች ምግብ በሚታኘክበት በኩል ለማጽዳት የሚያስቸግር ስንጥቅ ወይም ጎድጎድ ያለ ቦታ ሊኖራቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካለ ሐኪሞች የላይኛውን የጥርስ ክፍል ለጥ ያለ እንዲሆንና በቀላሉ ለማጽዳት እንዲመች ለማድረግ ሲሉ ቦታው እንዲሞላ ሐሳብ ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው እርምጃ ጥርሱ እንዳይበሰብስ ለመከላከል ይረዳል።

አዋቂዎችን በተመለከተ ደግሞ የጥርስ ሐኪሞች ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት የድድ በሽታ እንዳይከሰት መከላከል በሚችሉበት መንገድ ላይ ነው። በምርመራ ወቅት የተከማቸና ጠጣር የሆነ የጥርስ ቆሻሻ ካገኙ ያጸዱታል። አብዛኞቹ ሰዎች ጥርሳቸውን በሚቦርሹበት ጊዜ አንዳንድ ጥርሶችን ትኩረት ሰጥተው አያጸዷቸውም፤ በመሆኑም ሐኪሞች ጥርስ የማጽዳት ችሎታችንን እንዴት ማሻሻል እንደምንችል ሊጠቁሙን ይችላል። አንዳንድ የጥርስ ሐኪሞች ታካሚዎቻቸው ይህን ጠቃሚ ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ በጥርስ ንጽሕና አጠባበቅ ወደ ሠለጠኑ ሰዎች ይልኳቸዋል።

የተጎዱ ጥርሶችን ወደቀድሞ ሁኔታቸው መመለስ

የተበላሸ፣ የወለቀ ወይም የተወላገደ ጥርስ ካለህ የጥርስ ሐኪሞች ጥርሶችህን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ብዙ አዳዲስ ዘዴዎች እንዳላቸው ማወቅህ ያስደስትህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ሕክምና ውድ በመሆኑ ከአቅምህ በላይ እንዳታወጣ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። የሆነ ሆኖ ብዙ ሰዎች እንዲህ ላለው ሕክምና ምንም ያህል ገንዘብ ቢወጣ የሚያስቆጭ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ምናልባት ሐኪሙ በጥርስህ እንደገና ማኘክ እንድትጀምር ሊረዳህ ይችላል። አሊያም ስትስቅ ደስ የሚል ጥርስ እንዲኖርህ ያደርግ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም የተበላሸ ጥርስ በሕይወትህ የምታገኘውን ደስታ ሊቀንስብህ ይችላል።

ሐኪሞች የተሸረፉ ወይም የበለዙ የፊት ጥርሶችን ከተፈጥሯዊው የጥርስ መስተዋት ጋር በሚመሳሰል አንጸባራቂ ንጥረ ነገር መሸፈን ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። ንጥረ ነገሩ በተጎዳው ጥርስ ላይ ተጣብቆ የጥርሱን ቅርጽና መልክ ይለውጠዋል። ጥርሱ በጣም የተጎዳ ከሆነ ሐኪሞች ብዙውን ጊዜ ክራውን ተብሎ የሚጠራ በጥርስ መልክ የሚሠራ ሽፋን እንዲለብስ ሊያዝዙ ይችላሉ። ይህ ሽፋን ሽራፊውን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍነው ከመሆኑም በላይ ጥርሱ የወርቅ ወይም የተፈጥሮ ጥርስ መልክ እንዲኖረው ያደርጋል።

የተወሰኑት ጥርሶችህ ቢረግፉ ሐኪምህ በምን መንገድ ሊረዳህ ይችላል? ሰው ሠራሽ የሆነ ሊወልቅ የሚችል ጥርስ ሊገጥምልህ አሊያም ከወለቀው ቦታ ግራና ቀኝ ባሉት ጥርሶች ላይ ተሰክቶ አንድ ወይም ሁለት ሰው ሠራሽ ጥርሶችን ደግፎ የሚይዝ እንደ ማቀፊያ ያለ ነገር (fixed bridge) በቋሚነት ሊገጥምልህ ይችላል። ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ያለው ሌላው አማራጭ ደግሞ አዲስ ጥርስ ማስተከል ነው። ሐኪሙ ጥርሶችህ በነበሩበት መንጋጋ ውስጥ ከቲታንየም የተሠራ የጥርስ መቀበያ ይቀብርና አጥንትህና ድድህ ሲያገግም ሰው ሠራሽ ጥርሱን አስቀድሞ ድድ ውስጥ በተቀበረው መቀበያ ላይ ያስረዋል። ይህ ዓይነቱ ሰው ሠራሽ ጥርስ እውነተኛውን ጥርስ ይመስላል።

የተወለጋገዱ ጥርሶች የሚያሳፍሩ ከመሆናቸውም በላይ ለማጽዳት ስለሚያስቸግሩ በቀላሉ ለበሽታ ሊጋለጡ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ጥርሶች በትክክል ካልተደረደሩ ሕመም ሊያስከትሉና ማኘክ አስቸጋሪ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ። ደስ የሚለው ግን፣ የጥርስ ሐኪሞች የጥርስ ማሰሪያ ሽቦዎችን በመጠቀም ችግሩን ማስተካከል የሚችሉ መሆናቸው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሽቦዎቹ ንድፍ ላይ በታየው እድገት የተነሳ ዘመናዊዎቹ የጥርስ ማሰሪያዎች ብዙም የማይታዩና ማስተካከያ የማይፈልጉ ሆነዋል።

አንዳንድ የጥርስ ሐኪሞች መጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ብዙ ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረን የሚያስቸግራቸው አልፎ አልፎ ሲሆን አንዳንዶች ግን ዘወትር ያጋጥማቸዋል። መጥፎ የአፍ ጠረን እንዲኖር የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዳንድ የጥርስ ሐኪሞች የችግሩን መንስዔ ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ መሣሪያዎች አሏቸው። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ችግር የሚከሰተው በምላስ የኋለኛ ክፍል አካባቢ በሚፈጠሩ ባክቴሪያዎች አማካኝነት ነው። ስኳር አልባ ማስቲካ በማኘክ የምራቅህን መጠን መጨመርህ ችግሩን ለማስወገድ እንደሚረዳህ ሁሉ ምላስህን መቦረሽህም ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የወተት ተዋጽኦዎችን፣ ሥጋ ወይም ዓሣ ከተመገብክ በኋላ ጥርስህን ማጽዳትህ በጣም አስፈላጊ ነው።

የሚሰማህን ፍርሃት ማሸነፍ

ወደ ጥርስ ሐኪም መሄድ የሚያስፈራህ ከሆነ ሐኪምህ ይህንን ፍርሃትህን ማሸነፍ እንድትችል ሊረዳህ ይችላል። ስለዚህ ምን እንደሚሰማህ ንገረው። በሕክምናው ወቅት እንዳመመህ ወይም እንደፈራህ ለመጠቆም በእጅህ ምልክት መስጠት ትችል እንደሆነ ጠይቀው። ብዙ ታካሚዎች እንደዚህ ማድረጋቸው ፍርሃታቸውን ለመቋቋም ረድቷቸዋል።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሐኪሙ ይቆጣኛል ብለህ ትፈራ ይሆናል። እንዲሁም ለጥርስህ ጥሩ እንክብካቤ አላደረግህም ብሎ ያንቋሽሸኛል ብለህ ትጨነቅ ይሆናል። ነገር ግን ሐኪሞች እንዲህ ማድረጋቸው ገበያቸውን እንደሚዘጋባቸው አውቀው ጥንቃቄ ስለሚያደርጉ መፍራት አይኖርብህም። አብዛኞቹ የጥርስ ሐኪሞች ከታካሚዎቻቸው ጋር በደግነት የመነጋገር ፍላጎት አላቸው።

ብዙ ሰዎች ደግሞ ክፍያውን በመፍራት ወደ ጥርስ ሐኪሞች አይሄዱም። ነገር ግን አሁኑኑ ምርመራ የምታደርግ ከሆነ ከጊዜ በኋላ ለከፋ ችግር ከመጋለጥና ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረግ ልትድን ትችላለህ። በየአካባቢው እንደየሰዉ አቅም የጥርስ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት አሉ። በደረጃ ዝቅ ያሉ ናቸው የሚባሉት የጥርስ ሕክምና መስጫ ተቋማት እንኳ ራጅ ማንሻና በከፍተኛ ፍጥነት የሚንቀሳቀሱ የጥርስ መሰርሰሪያ መሣሪያዎች አያጡም። የጥርስ ሐኪሞች አብዛኛውን የሕክምና ሂደት በታካሚዎቻቸው ላይ እምብዛም ሕመም በማያስከትል መንገድ ማካሄድ ይችላሉ። ለማደንዘዣ የሚከፈለው ክፍያም ቢሆን ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሰዎች አቅም በላይ አይደለም።

የጥርስ ሐኪሞች ተግተው የሚሠሩት በሽታህን ለማስወገድ እንጂ ለማባበስ አይደለም። በዛሬው ጊዜ የሚሰጠው የጥርስ ሕክምና በአያቶችህ ዘመን እንደነበረው ለከፍተኛ ሥቃይ የሚዳርግ መሆኑ አብቅቷል። ጥርስህ ጤናማ መሆኑ፣ ለጠቅላላው ጤንነትህ የሚበጅህ እንዲሁም በሕይወትህ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን የሚረዳህ ከሆነ ለምን የጥርስ ሐኪም ዘንድ አትሄድም? የሚያስደስት ሁኔታ ያጋጥምህ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

ይህ ርዕስ የጥርስ ሐኪም ሕመምተኛውን ለመርዳት በሚያደርጋቸው ነገሮች ላይ የሚያተኩር ነው። የጥርስህን ጤንነት ለመጠበቅ በግልህ ማድረግ የምትችላቸውን ነገሮች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በኅዳር 8, 2005 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የጥርስህን ውበት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ማንበብ ትችላለህ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የጤናማ ጥርስ ገጽታዎች

የጥርስ አናት (Crown)

የጥርስ መስተዋት

ዴንቲን

ነርቮችና የደም ሥሮች ያሉበት የጥርስ ውስጠኛ ክፍል

ሥር

የድድ ኅብረ ሕዋስ (gingiva)

አጥንት

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የበሰበሰ ጥርስ

የተቦረቦረ ጥርስ

የተቦረቦረን ጥርስ ማስሞላት ቀዳዳው እንዳይሰፋ ይረዳል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የድድ በሽታ

የጥርስ ቆሻሻ መጽዳት ይኖርበታል

የጠጠረን የጥርስ ቆሻሻ ማስወገድ ከባድ ሲሆን ይህ ቆሻሻ ድድ እንዲሸሽ ያደርጋል

የሸሸ ድድ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የተጎዱ ጥርሶችን ለማስተካከል የሚረዱ ዘዴዎች

የተሸረፈ ጥርስ ላይ የሚለጠፍ ሽፋን

የጥርስ ክዳን

የሚተከል ጥርስ

በግራና በቀኝ በኩል ባሉት ጥርሶች ላይ ተሰክቶ ሰው ሠራሽ ጥርሱን ደግፎ የሚይዝ እንደ ማቀፊያ ያለ ነገር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.