ፎሮፎር (Dandruff) ምንድነው?

ፎሮፎር

dandruffበጭንቅላታችን ቆዳ ላይ የሚገኙ ሴሎች ተፈጥሮአዊ በሆነ ዑደት በየጊዜው እየሞቱ በአዳዲስ ሴሎች እየተተኩ ይሄዳሉ፡፡ ይህ የሴሎች የመተካከት ሂደት በጤነኛና የፎሮፎር ችግር በሌለባቸው ሠዎች ላይ እስከ 1 ወር የሚደርስ ጊዜን ሊወስድ ይችላል በዚህ ጊዜ ውስጥም የሞቱት ሴሎች ቀስ በቀስ ከቆዳ ላይ እየተወገዱና እየተተኩ ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን በተለያዩና በእርግጠኛነት ይህ ነው በማይባል ምክንያት አዳዲስ የጭንቅላት ቆዳ ሴሎች በብዛትና በፍጥነት እየተፈጠሩ ይሞታሉ እነዚህ ሴሎች ከትክክለኛው ተፈጥሮአዊ የመተካከያ በጣም ባነሠ ጊዜ ውስጥ ስለሚፈጠሩና ስለሚሞቱ እየተገፉ ወደ ላይኛው የጭንቅላታችን የቆዳ ክፍል በብዛት ይወጣሉ በቆዳችን ላይ ባለው ተፈጥሮአዊ ቅባት ምክንያትም እነዚህ የሞቱ ሴሎች እርስ በእርሳቸው በመጠባበቅ በመጠን እያደጉ ነጫጭ ርጋፊዎችን በመፍጠር በፎሮፎር መልክ ከፀጉራችን ላይ ይረግፋሉ፡፡ ይህ የሞቱ ሴሎች ከጭንቅላት ላይ የመርገፍ ሂደት በጤነኛና ፎሮፎር በሌለባቸው ሠዎችም ላይ የሚከሠተ ቢሆንም አዲስ የሚፈጠሩና የሚሞቱት ሴሎች መጠን ተመጣጣኝ ስለሆነ ሣይስተዋሉ ከፀጉር ላይ ይወገዳሉ፡፡ የፎሮፎር ችግር ባለባቸው ሠዎች ላይ የሚስተዋለው በከፍተኛ መጠን የጭንቅላት የቆዳ ሴሎች መፈጠርና መሞት እንዲከሠት ከሚያደርጉ ምክንቶች ውስጥ Malassezia (ማላሴዚያ) የተባለው የፈንገስ አይነት አንዱ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያሣያሉ ይህ ተዋህሣያን ጉዳት ሳያስከትል በጭንቅላታችን ቆዳ ላይ የሚኖር ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ በመራባትና ተፈጥሮአዊውን የቆዳችንን ቅባት በማብላላት የሚፈጥረው ኬሚካል ቆዳችን እንዲቆጣና የተለያዩ ለውጦች እንዲከሠቱ በማድረግ ከላይ ያየነውን ያልተመጣጠነነና ጊዜውን ያልጠበቀ የሴሎች መተካካት እንዲኖርና ፎሮፎር እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡
ፎሮፎር በሁሉም የእድሜ ክልል ላይ የሚከሠት ችግር ቢሆንም በበለጠ መልኩ ግን ወጣቶችና ጐልማሶች ለችግሩ ተጋላጮች ናቸው የተለያዩ ጥናቶች ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በፎሮፎር እንደሚጠቁ አሣይተዋል፡፡
ፎሮፎር እንዲባባስ የሚያደርጉ ምክንያቶች
ፎሮፎር ከላይ ባየነው መልኩ መፈጠር ከጀመረ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች አማካኝነት እየተባባሠ ሊሄድ ይችላል ከእነዚህም ውስጥ
በተለያዩ የፀጉር መንከባከብያ ምርቶች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ኬሚካሎች በተለይም በጄሎች፣ እስኘሬዎች፣ ሻምፖዎችና ቅባቶች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ከቆዳችን አይነት ጋር ላይስማሙ ስለሚችሉ አለርጂኮችን ይፈጥራሉ በዚህም ምክንያት የጭንቅላት ቆዳ ላይ መቅላት፣ መቁሠልና ማሣከክ የመሣሠሉት ሁኔታዎች ይኖራሉ ይህም ፎሮፎርን ለማባባስ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል በመሆኑም እነዚህን ምርቶች ስንጠቀም እንደቆዳችን አይነት የሚስማማንን በአግባቡ መርጠን መሆን ይኖርበታል
ፎ ሮ ፎ ር
♦♦ በተፈጥሮ የጭንቅላታችን ቆዳ በጣም ደረቃማ ወይም ቅባታማ መሆን ችግሩን እንደሚያባብሠው የተለያየ ጥናቶች ያሣያሉ በመሆኑም እነዚህን የቆዳ
ችግሮች ለመቆጣጠር የቆዳ ህክምና ባለሙያ በማማከር አስፈላጊውን ምክርና ህክምና ማግኘቱ የፎሮፎር ችግር እንዳይባባስ ይረዳል፡፡
♦♦ ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ቀዝቃዛማ አየር ችግሩን ሊያባብሠው ይችላል በተለይም በዚህ የአየር ንብረት ወቅት ፀጉርን አጅለው የሚሸፍኑ ከፍያዎችና
ስካርፎችን መጠቀም የችግሩን መጠን ከፍ እንደሚያደርገው ጥናቶች ያሣያሉ፡፡ ከቀዝቃዛ አየር በተጨማሪም ከፍተኛ ሙቀትም የችግሩን መባባስ ያስከትላል፡፡
♦♦ የተለያዩ ከቆዳ ጋር ተያይዘው የሚከሠቱ ህመሞች በተለይም seborrheic dermatitis (ሴቦሪክ ዳርማታይቲስ)፣ Eczema (ኤክዚማ)፣ Psoriasis(ሶሪያሲስ)
የመሣሠሉት ፎሮፎርን ያባብሣሉ
♦♦ ከነርቭ ጋር ተያይዘው የሚከሠቱ ህመሞች እንዲሁም ፖርኪንሠኒዝም (parkinsonism) ያለባቸው ሠዎች ከሌላው በተለየ መልኩ ለችግሩ የመጋለጥ
እድላቸው ከፍተኛ ነው በተጨማሪም የሠውነትን በሽታ የመከላከል አቅም (Immunity) የሚጐዱ ህመሞች ያሉባቸው ሠዎችም ችግሩ ሊባባስባቸውና
ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡
♦♦ ደካማና ተከታታይነት የሌለው የፀጉር ንፅህና አጠባበቅ ለፎሮፎር መባባስ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በየጊዜው በሚስማሙን የፀጉር ንፅህና
መጠበቂያዎች አማካኝነት ፀጉራችንን መታጠብና ማፅዳት ይኖርብናል በተለይም ከፍተኛ ላብን ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች በኋላ በአግባቡ የፀጉርን ንፅህና
መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
♦♦ አመጋገብ፡- በቫይታሚን ቢ ኮምፕሌክስ (Vitamin B complex) እና ዚንክ የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትሮ አለመመገብ ችግሩን ሊያባብሠው ይችላል በአንፃሩ
ስኳርን አብዝቶ መጠቀም ደግሞ ፎሮፎርን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር የተለያዩ ጥናቶች አሣይተዋል፡፡
♦♦ጭንቀት፡- ጭንቀት በጤናችን ላይ የተለያዩ ችግሮች እንዲከሠቱ የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል ከዚህም ጋር ተያይዘው በሚከሠቱ የተለያዩ ኬሚካላዊ
ለውጦች ምክንያት ፎሮፎርን እንዲባባስ የማድረግ አቅም አለው፡፡
ፎሮፎርን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መንገዶች
የፎሮፎር ችግርን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም በተለያዩ መንገዶች በደንብ መቆጣጠር ይቻላል የመጀመሪያው መንገድ የፀጉርን ንፅህና በአግባቡ
መጠበቅ ሲሆን ከፀጉራችን አይነት ጋር ተስማሚ የሆኑ መታጠቢያ ሳሙናዎችና ሻምፖዎችን አንዲሁም የፀጉር ቅባቶችን በመምረጥ መጠቀም ይኖርብናል
ወዛም ቆዳና ቅባትማ ፀጉር ያላቸው ሠዎች ደረቃማ ቆዳ ካላቸው ሠዎች የተለየ የፀጉር ንፅህና መጠበቂያዎችን መጠቀም ያለባቸው ሲሆን ለፀጉሬ አይነት
የትኛው ይስማማኛል የሚለውን ለመምረጥ በምርቶቹ ላይ የሚጻፈውን ማብራሪያ በደንብ ማንበብና መረዳት ይኖርብናል ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ
ባለሙያዎችን ጠይቆ መረዳትና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ተጨማሪ መዋቢያዎችን ለፀጉራችን የምንጠቀም ከሆነ ለተወሠነ ጊዜ ማቆምና ለውጡን ማየት
ይኖርብናል በተጨማሪም የሚከተሉት ነጥቦች ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ መንገድን ሊፈጥሩልን ይችላሉ
• የምንወስደውን የዚንክ (Zinc) መጠን ከፍ ማድረግ፡- ዚንክ ለፎሮፎር ምክንያት የሆነውን ፈንገስ ለማጥፋት ከማስቻሉም ባሻገር የጭንቅላታችን ቆዳ
የሚያመነጨው ቅባት ተመጣጣኝ እንዲሆን በማድረግ ፎሮፎርን ይቆጣጠራል፡፡ ዚንክን ከአሣ፣ የስብ መጠኑ ትንሽ ከሆነ ስጋ፣ ከስንዴ፣ ከለውዝ፣ ከዱባ
ፍሬ፣ እንዲሁም ከአጃ ልናገኘው እንችላለን
• በቫይታሚን ቢ ኮምኘሌክስ (vitaminB complex) የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትሮ መጠቀም ፎሮፎርን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል የተያዩ ጥናቶች ያሣያሉ
ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ጥራጥሬዎች እንዲሁም አሣ፣ ጉበት ጥሩ ምንጮች በመሆናቸው በአመጋገባችን ውስጥ አካተን
መጠቀም ይኖርብናል በተጨማሪም በአሣ ውስጥ የሚገኘው ኦሜጋ 3 (Omega 3) የተባለው ጠቃሚ የቅባት አይነትም ተጨማሪ የመከላከል ጥቅምን
ያጐናጽፋል
• የምንጠቀመውን የስኳር መጠን መቀነስ ፡-ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር መጠቀም የተለያዩ የፈንገስ አይነቶች እንዲራቡ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር ስለሚችል
ብሎም ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮችን ስለሚያስከትል በመጠን መጠቀሙ ይመከራል
• ጭንቀትን ማስወገድ፡- የተለያዩ የስነልቦናና የጤና ባለሙያዎችን በማማከር የጭንቀት ምንጮችን ለማስወገድ መሞከር ይኖርብናል ይህንን ማድረጉ በብዙ ሠዎች ላይ ፎሮፎርን በአግባቡ ለመቆጣጠር ማስቻሉ ይታወቃል፡፡
• ፀጉርን በኮፍያና በሻሽ ወይም በተለያዩ ነገሮች ጥብቅ አድርጐ መሸፈን ፎሮፎር እንዲባባስ ያደርጋል ፀጉራችን በቂ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝና እንዲናፈስ ማድረግ የበለጠ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለተለያዩ የፀጉር እንክብካቤ የምንጠቀምባቸው ምርቶች በውስጣቸው አልኮል የማይዙ ቢሆን ተመራጭ ነው ምክንያቱም አልኮል የጭንቅላት ቆዳ እንዲደርቅና ችግሩ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል፡፡
• በፎሮፎሩ ምክንያት የሚፈጠር ማሣከክ ሲኖር ቆዳን በሚጐዳና በከፍተኛ ሁኔታ በጥፍር ማከክ ቁስለትና ተያያዥ ኢንፌክሽኖች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
• በነጭና ቀይ ሽንኩርት ውስጥ የሚገኘው Alicin (አሊሲን) የተባለው ንጥረ ነገር ፀረ ፈንገሣዊ ባህሪ ስላለው በምግብ ስርዓታችን ውስጥ ማካተቱ ተጨማሪ ጥቅም አለው፡፡
ውድ አንባብያን እነዚህንና የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመን ፎሮፎሩ ለውጥ ካላመጣ ወይም እየተባባሠ ከሄደ ለፎሮፎር ህክምና ተብለው የሚዘጋጁ ሻምፖዎችን መጠቀም ይኖርብናል እነዚህ የህክምና ሻምፖዎች በውስጣቸው የተለያዩ አይነት የመድኃኒት ይዘት ያላቸውን ኬሚካሎችን የሚይዙ ሲሆን በህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት ታዘው ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ሻምፖዎቹ በተለያዩ መንገዶች ፎሮፎርን የሚቆጣጠሩ ሲሆን የጭንቅላት ቆዳ ሴሎችን የመብዛት ሂደት በመቀነስ፣ የሚመነጨውን የቅባት መጠን በማስተካከል፣ በሚሞቱ ሴሎች መካከል የሚፈጠረውን መጠባበቅ በማስቀረት በቀላሉ ከቆዳ ላይ ተላቀው እንዲረግፉ በማድረግና Malassesia(ማላሴዝያ) የተባለውን ፈንገስ በማጥፋት የፎሮፎር ችግርን በዘላቂነት ለመቆጣጠር ያስችላሉ፡፡ እነዚህ ሻምፖዎች ከታዘዙልን በኋላ በትዕዛዙ መሠረት በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል በተነገረን መጠንና የአጠቃቀም ጊዜ ተከታታይነት ባለው መልኩ መጠቀም ከፍተኛ ለውጥን ያመጣል፡፡ ፎሮፎሩን በደንብ ለመቆጣጠር ረዘም ያለ ጊዜን ሊወስድብን ስለሚችል በአግባቡ ሣንሠላች ተፈላጊው ለውጥ እስኪመጣ ድረስ መጠቀም ይኖርብናል፡፡
የሻምፖዎቹ አጠቃቀም
– በመጀመሪያ ከመታጠባችን በፊት ፀጉርን በደንብ ማበጠሩ ፎሮፎሩ እንዲረግፍና በሻምፖዎቹ ስንታጠብ በቀላሉ እንዲወገድ ይረዳናል፡፡
– በመቀጠል በሚስማማን የማፅጃ ሳሙና ወይም ሻምፖ ፀጉርና የጭንቅላት ቆዳን በደንብ ማጠብና ማፅዳት ይኖርብናል፡፡
– የታዘዘልንን የህክምና ሻምፖ በታዘዘልን መጠን የጭንቅላት ቆዳችንን በደንብ መቀባትና ፀጉርን እየከፋፈቱ ውስጥ ውስጡን በደንብ ማዳረስ ያስፈልጋል፡፡
♦ ♦ሻምፖውን ለተነገረን ደቂቃዎች ያህል የጭንቅላት ቆዳችን ላይ በጣቶቻችን እያሸን ማቆየት፡፡ ከተባልነው ደቂቃ በላይ ሻምፖዎቹን በጭንቅላት ቆዳ ላይ ማቆየቱ የማቃጠል ስሜትን ሊፈጥርና ቆዳችንንና ፀጉራችንን ሊጐዳ ስለሚችል በታዘዝነው መሠረት ብቻ መጠቀም ይኖርብናል፡፡
♦ ♦ልክ የያዝነው ደቂቃ ሲያበቃ ፀጉራችንን በድጋሜ መታጠብ ይኖርብናል ሻምፖውን ከፀጉራችን ላይ ስናፀዳ ወደ አይናችን እንዳይገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡
♦ ♦በመጨረሻ ፀጉርን በአግባቡ ማድረቅ ይገባል፡፡
እነዚህን የህክምና ሻምፖዎች መጠቀም ከጀመርን በኋላ የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ በተወሠነ ጊዜ ውስጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ፎሮፎሩ ሙሉ ለሙሉ ጠፋ ማለት ስላልሆነ ሻምፖዎቹን መጠቀም ማቋረጥ የለብንም ፎሮፎሩን በአግባቡ ከተቆጣጠርነው በኅላም ቢሆን ለተወሠነ ጊዘ ያህል መቀጠል ይኖርብናል፡፡ የፎሮፎሩ መጠን እየቀነሠ ሲመጣ የምንጠቀመውን የሻምፖ መጠንም ሆነ ድግግሞሽ እየቀነስን መምጣት እንችላለን፡፡ ሻምፖውን እየተጠቀምን ፎሮፎሩ ለውጥ ካላመጣ ወደ ሀኪማችን በመሄድ ሌላ አይነት ሻምፖ እንዲቀየርልን ማድረግና መሞከር ይኖርብናል ምክንያቱም የተለያዩ ሻምፖዎች በተለያዩ መንገዶች ስለሚሠሩ አንዱ ያልተቆጣጠረልንን ሌላኛው ሊቆጣጠረው ይችላልና፡፡ እነዚህን የህክምና ሻምፖዎች ስንጠቀም የተለያዩ የአለርጂክ ምልክቶች ማለትም የተቀባነው ቆዳና አካባቢው ላይ መቅላት፣ ማበጥ መቁሠል የመሣሠሉት ሁኔታዎች ከተከሠቱ በተጨማሪም የፀጉር መሠባበር እንዲሁም መነቃቀል ሁኔታዎች ካሉ በአፋጣኝ ሻምፖዎቹን ማቆምና ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መፍትሔ ማግኘት ይኖርብናል፡፡
ውድ አንባብያን ባቀረብንላችሁ አጠር ያለ ጽሑፍ ስለ ፎሮፎር ምንነትና መቆጣጠሪያ መንገዶቹ አጠር ያለ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ተስፋ በማድረግ ወደ ፊት በሚኖሩት ዕትሞቻችን ላይ የቆዳ ህክምና ስፔሻሊስቶችን በማቅረብ የተለያዩ በቤት ውስጥ ልናዘጋጃቸው የምንችላቸውን የፎሮፎር መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ይዘንላችሁ እንደምንቀርብ ቃል እንገባለን፡

ከፋርማኔት መፅሔት የተወሰደ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.