2_1ትኩሳትን የሚያመጡ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው?

በሀገራችን ውስጥ ትኩሳትን እንደ ዋና ምልክት በማሳየት ከፍተኛውን ደረጃ የያዙት በሽታዎች ወባ፣ ታይፎይድ፣ ታይፈስ እና ግርሻ (Relapsing Fever) ናቸው። ሌሎች ትኩሳትን አምጪ በሽታዎች የሚከሰቱት በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ ሊሆን ይችላል። ከነዚህም መካከል ቲቢ፣ የሳንባ ምች፣ የኩላሊት ኢንፌክሽን፣ የጉበት በሽታ፣ ካንሰር፣ ማጅራት ገትር፣ የተቅማጥ በሽታዎች ይጠቀሳሉ።

የወባ በሽታ

የወባ በሽታን የምታስተላልፈው የወባ ትንኝ በሞቃትና የረጋ ውሃ ባለባቸው አካባቢዎች በብዛት ትራባለች። በንክሻዋም ከአንድ ሰው ወደሌላ በቀላሉ ታስተላልፋልች። ጥገኛ ህዋሳቱ የደም ሴሎችን በማጥቃት ስራቸውን እንዳያከናውኑ ያግዷቸዋል። በወባ የተጠቃ ሰው ከትኩሳቱ በተጨማሪ የራስ ምታት፣ ትውከት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ድካም እንዲሁም የጡንቻ ህመም ሊያጋጥመው ይችላል።

በበሽታው የተጠቃ ሰው በአፋጣኝ ህክምና ካላገኘ፤ ወደ ጭንቅላት ሊወጣ ወይም ሌሎች በሽታዎች ሊደረቡበት ይችላሉ። በዚህም ምክኒያት የደም ማነስ፣ የደም ስኳር መጠን ማነስ፣ የጥገኛ ሀዋሳት በደም ውስጥ መሰራጨት፣ የሳንባ በሽታ፣ የሰውነት መድማት ባህሪ፣ የሰውነት/አይን ቢጫ መሆን ሊከሰቱ ይችላሉ። የበሽታውን መኖር በቀላል የደም ምርመራ ማረጋገጥ ይቻላል። በሽታው እንዳለ ከተረጋገጠ እንደበሽታው አይነት ከ3-10 ቀናት የሚፈጅ ህክምና ሊሰጥ ይችላል። የበሽታው መዘዞች ችግር ካስከተሉ፤ ለረዥም ጊዜ ሊሰጥ ይችላል።

በሽታው እንዳይከሰት ለመከላከል፤ አጎበር በአልጋ ላይ መጠቀም፣ ማታ ማታ ከቤት አለመውጣት፣ የተባይ ማጥፊያ በቤት ውስጥ መንፋት ይቻላል።

ታይፈስ

ይህ በሽታ በባክቴሪያ የሚከሰት ሲሆን ከጽዳት ማነስ የሚመጡትን ቅማልን የመሳሰሉት ነፍሳት በሽታውን ከሰው ወደሰው ያስተላልፋሉ። የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስምታት፣ ሽፍታ (ከደረት ጀምሮ ሁሉንም የሰውነት ክፍል የሚሸፍን)፣ የዓይን ህመም፣ የምላስ መድረቅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በሽታው በቶሎ ካልታከመ የቆዳ መበላሸት፣ ጋንግሪን፣ የደም መርጋት፣ የሣንባ ምች፣ እንዲሁም የኩላሊትና የልብ በሽታዎችን ሊያመጣ ይችላል። የበሽታውን መኖር በደም ምርመራ ማረጋገጥ ይቻላል። ከዚህም በኋላ ከ7 እስከ 15 ቀን የሚፈጅ የሚዋጥ ፀረ-ተህዋስ መድሀኒት ይሰጣል።

በሽታውን ለመከላከል እንዲያስችል የግል እና የአካባቢ ጽዳት ወሳኝነት አለው። ከዚህም በተጨማሪ፤ ቤትን የተባይ ማጥፊያ በመንፋት አስተላለፊ የሆኑትን ነፍሳት ማስወገድ ይቻላል።

ታይፎይድ

ይህ በሽታ በባክቴሪያ የሚመጣ ሲሆን ዋና ዋና ምልክቶቹም ትኩሳትና የሆድ ህመም ናቸው። በሽታው የሚመጣው ንጽህና የሌለው ምግብ ከመመገብ፣ ያልተጣራ ውሀ ከመጠጣትና እጅን ሳይታጠቡ ምግብ በመመገብ ነው።

የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ ነስር፣ ግራ መጋባት፣ እና ክብደት መቀነስ ናቸው። በሽታው ሳይታከም ከዘገየ የጉበት ኢንፌክሽን፣ ማጅራት ገትር፣ ጆሮ ደግፍ፣ የኩላሊት እና የልብ በሽታ፣ እና የሳንባ ምች በበሽታው ላይ ሊደረቡ ይችላሉ።

የደም እና የሰገራ ምርመራ የበሽታውን መኖር የሚያሳውቁ ዋና ዋና መንገዶች ናቸው። የበሽታው መኖር ከተረጋገጠ ከ10 እስከ 14 ቀን የሚዋጥ መድሀኒት ይታዘዛል።

የግልና የአካባቢ ጽዳት መጠበቅ እንዲሁም ምግብን ከማዘጋጀት በፊት፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስ እንዲሁም ከመመገብ በፊት እጅን መታጠብ፤ በሽታውን ለመካላከል የሚረዱ ወሳኝ ጥንቃቄዎች ናቸው።

ግርሻ (Relapsing Fever)

በባክቴሪያ የሚመጣ በሰውነት ቅማል የሚተላለፍ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ በብዛት የሚገኝ በሽታ ነው።

ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያዎች ህመም፣ ድካም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ውሃ ጥማት፣ የዓይን መቅላት፣ የሆድ ህመም እና ሽፍታ የበሽታው መገለጫዎች ናቸው። በሽታው ሳይታከም ከቆየ የዓይን ቢጫ መሆን እና ግራ መጋባትን ሊያመጣ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ነስር፣ ደም የቀላቀለ አክታ፣ ማጅራት ገትር፣ ያሳንባ ምች፣ የልብ በሽታ እንዲሁም የጣፊያ መፍረስ? ሊያመጣ ይችላል።

ህክምናውን ለመስጠት የደም ምርመራ እንዲሁም የጀርባ ፈሳሽ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ህክምናውም ለ7 ቀናት የሚዋጥ መድሃኒት ይሆናል። በሽታውን ለመከላከል ጽዳት እና ፀረ ተባይ መድሀኒቶች እጅጉን ይረዳሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.