በልብ የአወቃቀር ይዘት (ስትራክቸር) ወይም በአሰራሩ ላይ ችግር ኖሮ ለሰውነታችን የሚበቃውን ያህል ደም የመርጨት አቅሙ ሲያንስ እና የተለያዩ የበሽታው ምልክቶች ሲታዩ የልብ ድካም ይከሰታል፡፡

congestive-failure-heartየልብ ድካም ሲባል አንድ በሽታን ብቻ የሚገልፅ ሳይሆን የተለያዩ በሽታዎች የመጨረሻ መዳረሻ ነው፡፡ የልብ ድካም ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የመከሰት እድሉም አብሮ የሚጨምር በሽታ ነው፡፡

የጤናማ ሰው ልብ አራት ክፍሎች ሲኖሩት ከነዚህ ክፍሎችም ሁለት ደም የሚወሰዱና ሌሎች ሁለት ደግሞ ደም የሚመልሱ ትልልቅ የደም ቧንቧዎች አሉ፡፡ አራቱ የልብ ክፍሎች የቀኝና የግራ አትሪየም እና የቀኝ እና የግራ ቬንትሪክል ይባላሉ፡፡ ሁለቱም አትሪየሞች ከልብ ውጪ ያለን ደም ተቀብለው ወደ ቬንትሪክል ሲያስተላልፉ ቬንትሪክሎች ደግሞ ይህንኑ ደም ወደሳምባ እና ወደሌላው የሰውነታችን ክፍል ይልኩታል፡፡ ስለዚህም በሁለቱም አትሪየሞች እና በሁለቱ ቬንተሪክሎች መካከል ምንም አይነት የእርስ በእርስ ግንኙነት የለም፡፡ ነገር ግን በቀኝ አትሪየም እና በቀኝ ቬንትሪክል እንዲሁም በግራው አትሪየም እና በግራው ቬንትሪክል መካከል ደም የሚያልፍባቸው በሮች አሉ፡፡ በነዚህ በሮች ላይ ደግሞ ደም ባልተፈለገው አቅጣጫ እንዳይሄድ የሚያደርጉ ክዳኖች(መዝጊያዎች) ይገኛሉ፡፡

ወደሰውነታችን የተረጨ ደም የሰውነታችን ህዋሳት ኦክስጅንን ወስደው እና በካርበንዳይ ኦክሳይድ ተክተው ተጠቅመው ሲያበቁ በላይኛው እና በታችኛው ቬና ካቫ አድርጎ ወደ ቀኙ አትሪየም ይገባል፡፡ ከቀኝ አትሪየም ወደቀኝ ቬንትሪክል ያልፍና በፐልሙነርይ አርተሪ አማካኝነት ወደሳምባ ሄዶ የያዘውን ቆሻሻ ካርበንዳይ ኦክሳይድ በማስወገድ ኦክስጅንን ወስዶ በፑልሞናርይ ቬን ወደግራው አትሪየም ይመለሳል፡፡ በመቀጠልም ይኼው ደም ወደ ግራው ቬንትሪክል በመግባት በአኦርታ አድርጎ ወደሰውነት ክፍላችን ይሰራጫል፡፡ በአኦርታ እና በፐልሞናሪ አርተሪ የደም ቧንቧዎች እና በቀኝ እና በግራ ቬንትሪክል መሃከልም የደም ቧንቧ መዝጊያዎች ይገኛሉ፡፡

የልብ ድካም በሽታን የሚያጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የልብ ድካም በብዙ አይነት በሽታዎች እና ምክንያቶች ይመጣል፡፡ከነዚህም መሃከል ለራሱ ለልቡ የሚያስፈልገው ደም ማነስ( Ischaemic heart disease) ፣ የልብ ጡንቻ ችግሮች (Cardiomyopathy ) እና የደም ግፊት የመጀመሪያውን ሶስቱን ይይዛሉ፡፡ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በማደግ ላዩ ባሉ ሀገራት ደግሞ በብዛት የሚታየው በልብ ቧንቧ መዝጊያዎች ችግር (Valvular heart disease) የሚመጣ የልብ ድካም ነው፡፡ በልብ አፈጣጠር ችግር (ሲወለድ ጀምሮ የነበረ) (Congenital heart disease) ፣ መጠጥ እና የተለያዩ መድሃኒቶች፣ የደም ማነስ (anaemia) ፣ በጣም ብዙ ታይሮይድ ሆርሞን የሚያመርት እንቅርት (thyrotoxicosis ) እና አንዳንድ የሳምባ ችግሮች (COPD) ሊያመጡት ከሚችሉት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የልብ ድካም በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ቶሎ ቶሎ መድከም እና የትንፋሽ ማጠር፣ ያለትራስ በጀርባ ሲተኙ የሚኖር የትንፋሸ ማጠር፣ ለሊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ከባድ የትንፋሽ ማጠር እና ሳል፣ የሰውነት ማበጥ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ሳል፣ የልብ ምት መሰማት፣ ድካም፣ syncope የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡ በሽታው እየባሰ በሄደ ቁጥር የትንፋሽ ማጠር ችግርም አብሮት ይብሳል፡፡ ትንሽ ስራ ሲሰሩ ሀይለኛ የትንፋሽ ማጠር ሊኖር ከሱም አልፎ ያለምንም ስራ ቁጭ ተብሎ እንኳን የትፋሽ ማጠር ይከሰታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የላይኛው የሆድ ክፍል ህመም፣ ማታ ማታ ሽንት በብዛት መሽናትም ተያይዘው ሊታዩ የሚችሉ የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡

የልብ ድካም በሽታን የሚያስነሱ(የሚያባብሱ) ነገሮች ምንድን ናቸው?

ከድሮው በተለየ በልብ ላይ የስራ ጫናን የሚጨምሩ ነገሮች የልብ ድካምን ያባብሳሉ፡፡ የደም ማነስ(anaemia)፣ ኢንፌክሽን፣ እርግዝና፣ በጣም ብዙ ታይሮይድ ሆርሞን የሚያመርት እንቅርት (thyrotoxicosis ) ፣ የተዛባ የልብ ምት (arrhythmias)፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት (obesity)፣ ለልብ ድካም የተሰጠ መድሃኒትን በስርአት አለመውሰድ በሽታውን የሚያባብሱ ነገሮች ናቸው፡፡

የልብ ድካም ከያዘኝ በኋላ ምን አይነት ጥንቃቄ ላድርግ?

የልብ ድካም አንዴ ከያዘ በኋላ ሙሉ ለሙሉ የሚድን በሽታ አይደለም፡፡ በሽታውን ግን በመድሃኒት እና በሌሎች በተለያዩ ነገሮች ልትቆጣጠረው ትችላለህ፡፡ አልኮል መጠጥ በሽታውን ከሚያመጡት በተጨማሪም ከሚያባብሱት ምክንያቶች ውስጥ ስለሚመደብ አልኮል ማቆም አለብህ፡፡ ሲጋራ የማጨስ ልምድ ካለህም ይህንን ባህሪህን አስወግድ፡፡ ከከባድ እንቅስቃሴ እና ስራዎች እራስህን ቆጥብ፡፡ አንዳንድ እንደአስፕሪን ያሉ መድሃኒቶች በሽታውን ስለሚያባብሱት ምንም አይነት መድሃኒት ከመውሰድህ በፊት ሐኪምህን አማክር፡፡ ለበሽታው የተሰጠህን መድሃኒት በአግባቡ መውሰድም ካንተ የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ምንም እንኳን የትንፋሽ ማጠር ከእንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ቢሆንም በሽታው ላልጠናበት ሰው ቀላል እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ መጠነኛ የእግር ጉዞ ይመከራል፡፡ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ከበሽታው ጋር የሚኖርህን ቆይታ ያቃልልሃል፡፡የልብ ድካም ያለበት ሰው የጨው አጠቃቀም ከሌላው ጊዜ በተለየ አናሳ መሆን አለበት፡፡ ውሃ መውሰድም የሚከለከልባቸው አይነት ሁኔታዎች ሊኖሩ ቢችሉም ይህንን ግን ከሀኪምህ ጋር ተማክረህ የምትደርሱበት ውሳኔ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.