የኤሌክትሪክ ሲጋራና መዘዙን በህግ እሰኪለከል ድረስ እኔም ከመምከር አልቆጠብም፡፡ የምትከታተሉ ሰዎች ካላችሁ፣ ህዝቡም እየነቃ፣ መንግሥትም ጠበቅ ያለ ርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ለመሆኑ፣ የዚህ ቬፒንግ ወይም ኢ-ሲጋራ (e-Cigarettes) የሚባለው ጣዕም የሚሠጡ ተጨማሪ ነገሮች እንዴት ሊፈቀዱ ቻሉ?

እንደ ሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ፣ በ2015 FDA, የአሜሪካው የምግብና የመድሐኒት አስተዳደር (e-Cigarettes) የሚጨመሩ ማጣፈጫዎችን ለመከልከል ያደረገው የመጀመሪያው ጥረት በባለሀብቶቹ ታፍኖ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በዚያው አመት፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የትምባሆ ኩባንያ ወኪሎች እና አንዳንድ አነስተኛ ቢዝነስ የሚባሉ ቡድኖች፣ Office of Management and Budget ከሚባለው ድርጅት ባለሥልጣኖች ጋር ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ድርጅት፣ ከፍተኛ የሆኑ ህጎች ሲደነገጉ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትሉትን ግፊት ወይም ውጤት የሚመረምር ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ከተሳተፉት፣ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጠበቆች፣ ለኢ-ሲጋራ ማጣፈጫ የሚያመርቱ ኩባንያ ጠበቆች፣ እናም የምግብና የመድሐኒት አስተዳደሩ FDA በማጣፈዎች ላይ ያደረገውን ጥናት (research) ውድቅ ለማድረግ የሚጥሩ፣ ገንዘብ የሚከፈላቸው ምሁራኖችንም ይጨምራል፡፡ በግንቦት 2016 FDA፣ ትምባሆን በተመለከተ፣ ህግ ሲያወጣ፣ ማጣፈጫዎቹን የሚከለክለውን መመሪያ ትቶ ነበር፡፡ በጊዜው የነበሩት FDA ባለሥልጣኖች፣ ማጣፈጫዎች ቢከለከሉ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሰከትለውን ግፊት ለማጥናት ከፍተኛ ትግል እንዳደረጉ ገለፁ፡፡ ያም በፕሬዚደንት ኦባማ ጊዜ ነበር፡፡ እንደነሱ አባባል፣ የሳይንስ ምርምር ለሚያደርጉ ድርጅቶች ክብር ቢኖራቸውም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሳው ጥያቄ፣ የጥናቱ ውጤት ግልፅ ስላልሆነ (በነሱ አባባል ነው፣ የኢ-ሲጋራ በተያያዘ ያሉ ንግድ ቤቶችን ጠቅላላ መዝጋት ተገቢ ነው ወይ? ብለው ነበር፡፡ ሰለዚህ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በኢንዱስትሪ ጠበቆች ተፅዕመፐ አማካኝነት፣ ያሰቡትን ማድረግ ሰላልቻሉ፣ የወሰዱት አማራጭ ሁኔታው በዝግታ እንዲታይ ነው፡፡

መንግሥት ተቀየረና፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሪዚዳንት ሲተኩ፣ በ ኢ-ሲጋራዎች ማጣፈጫዎች ላይ ሊወሰድ የነበረው ጠበቅ ያለ ህግ አስከ 2021 ድረስ አይሰራም ወይም አይጀመርም ብለው አስታወቁ፡፡ ሰውየው፣ እንደዚህ አይነቶችን ህግጋት ሲሽሩ ወይም ሲያዘገዩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ እንግዲህ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ማንበብ፣ ህጉ ተፈፃሚ ቢሆን፣ ማጠፈጨዎቹ ቢከለከሉ ኖሮ የሚያስብል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ አትራፊዎች፣ በመንግሥት ህግጋት ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ አንድ ምሳሌ ይሆናል፡፡

ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን እንደሚጠቀሰው፣ ይህንን ኢ-ሰጃራ የሚጠቀሙ ሰዎች በከፍተኛ ቁጥር እየታመሙ፣ ህይወታቸውም እያለፈ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በጎሽ ድረ ገፅ፣ ስለዚህ ጉዳይ ቀደም ብለን ለማስጠንቀቅ ሞክረናል፡፡ ይህ ፅሁፍ አስከወጣበት እስካለፈው ሳምንት ድረስ፣ ይህን ቬፒንግ ከሚጠቀሙ ሰዎች፣ 805 ታመው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፣ 16 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ ነው የሚመስለው፡፡

የህመምና የሞት ምክንያቱን ለማጣራት፣ ትልቁ የዜና አውታር ኤን ቢ ሲ፣ በራሱ ለቦራቶሮች ጥናት ያካሂዳል፡፡ አይ አገር! (የዜና አውታር ራሱ ጥናት የሚያደርግበት፤ ምክንያቱም ኢንዱስትሪው አትራፊ ስለሆነም አይታመንም)፡፡ የኛ አገር ጋዜጠኛ ተብየዎች፣ ጥናቱ ቀርቶ በመረጃ የተደገፈ፣ ግራ ቀኙን ያዳመጠ ዜና ቢያስተላልፉ፣ ምሬትና ጥላቻው በቀነሰ ነበር፡፡ አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ሲደባለቅ ነው ነገር የተበላሸው፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያ ሌላ ይባል የለ፡፡ ይህ የኔ አስተያየት ነው፡፡ ልተንፍስ ብዬ ነው፡፡

ወደ ጥናቱ ልመልሳችሁ፡፡ በዚህ ጥናት፣ በጎዳና ላይ የሚሸጡ ማጣፈጨዎችን ናሙና ሰበሰቡ፡፡ እናም ከጎዳና ላይ ከሚሸጡት የተሰበሰቡት ናሙናዎች በሙሉ፣ ሲመረመሩ፣ ያም ለተባይ ማጥፊያ የሚውሉ ኬሚካሎች በውስጣቸው ይኖር ይሆን ተብሎ ነው፡፡ ታዲያ ሁሉም ከጎዳና የተሰበሰቡት ናሙናዎች፣ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ለፈንገስ ማጥፊያ የሚውል ኬሚካል ስሙም ማይክሎቡታኒል የተባለ ኮምፓውንድ ይገኝባቸዋል፡፡ አሁን ልብ በሉ፣ ይህ ኮምፓውንድ በእሳት ሲለኮስ ወደ ሀይድሮጀን ሳያናይድ ወደ ተባለ ኬሚካል ይቀየራል፡፡ ሳያናይድ፣ የምታውቁ ከሆነ፣ በትንሹ እንኳን ሰዎች ከተጋለጡ ለሕይወት እልፈት የሚዳርግ፣ ምን አግደረደረኝ፣ ሰው የሚገድል ኮምፓውንድ ነው፡፡ የዛሬ ስንት አመታት፣ በኢትዮጵያ፣ ወጣቶች ላመኑበት ትግል ሲታገሉ፣ ከተያዙ ሚስጥር እንዳያወጡ ሳያናይድ እየዋጡ ራሳቸውን ያጠፉ ነበር፡፡ ይባላል፡፡ የደርግ መርማሪዎችም ይህንን ያውቁ ኖሮ፣ ያሠሩት ሰው እልም ስልም ሲልባቸው፣ ሎሚ ይግቱ ነበር፡፡ መርዝ ውጦ ይሆናል ብለው ነው፡፡ ይሄኛውን በደንብ አውቃለሁ፡፡

በሌላ ጥናት፣ ሌላ ድርጅት፣ መንገድ ዳር በህግ ወጥ (ብላክ ማርኬት) የሚሸጡና ከፋብሪካ የሚወጡ ሀሽሽ (ማሪዋና) ያለባቸውን ማጣፈጫዎች በመመርመር ያገኙት፣ በብላክ ማርኬት ከሚሸጡት፣ ከአስራ አምስት ናሙናዎቸ በአስራ ሶስቱ ቫይታሚን ኢ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በጭስ መልክ ሲገባ፣ ይህ ቫይታሚን ኢ ለህመም ይዳርጋሉ ከሚባሉት ኮምፓውንዶች አንዱ ነው፡፡ በሚዋጥ መልክ ለአንዳንድ በሽታዎች የሚታዘዝ ነው፡፡ እኔም የማዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ግን በጭስ አይደለም፡፡ ከነዚህ ናሙናዎች በአስሩ ደግሞ፣ ያ ከላይ የተጠቀሰው ማይክሎቡታኒል ተገኝቶባቸዋል፡፡ ልብ ካላችሁ ይህ ኮምፓውንድ ሲቃጠል ወደ ሳያናይድ ይቀየራል፡፡ እኔም ካገር በፊት፣ ይህ ቬፒንግ የሚባል አደገኛ ነው፤ ልጆቻችሁ እንደፋሽን አድርገው እንዳይጀምሩት ብዬ ለማስጠንቀቅ ሞክሬ ነበር፡፡ አሁን ግን ይኸው መረጃው፡፡ ሰው እንዴት መርዝ ያጨሳል? እንደ ኤንቢሲ ዜና ባላሥልጣኖች አባባል፣ አጣፈጩ ቅመም ላዩ ላይ፣ ሳያናይድ አለበት የሚል ማስታወቂያ ቢለጥፍበት ኖሮ የሚገዛ አይኖርም ነበር ይላሉ፡፡ ውነት ነው፡፡ ይህም ሆኖ፣ ከላይ በተጠቀሱት ህሙማንና ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች፣ ጉዳት የደረሰባቸው በዚህ ኮምፓውንድ ነው ተብሎ ተነጥሎ የቀረበ ኬሚካል እሰካሁን አልተገኘም፡፡ ሰለዚህ ነገሩን የበለጠ አደገኛ ያደርገዋል፡፡ በሉ፣ ደንገጣችሁም፣ አሰባችሁም፣ መልሳችሁ አስተምሩ፡፡ አካፍሉ፣ ፌስ ቡክ ላይ ያለውን ገፅም ላይክ አድርጉ፡፡ ለፀሐፊ ሞራል ይሠጣል፡፡​

አዲሱ አጫጫስ ሰዎችን ወዲያውኑ ማጨስ ጀምሯል

ባለፈው፣ በጎሽ ድረ ገፅ፣ vaping (e-cigarette) ተብሎ ስሚጠራው አዲሰ ጭስ የማጨስ ተግባር ትምህርት ለመሥጠት ሞክረናል፡፡ ይህ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ የሆነ ህመም በአጫሾቹ ላይ ማሳየት ሰለጀመረ፣ የየሰቴት የጤና ቢሮዎች ለጤና ባላሙያተኞች ማሳሰቢያና መምሪያ እንዲልኩ አስግድዷቸዋል፡፡
ሁኔታው እንዲህ ነው፡፡ ከነሀሴ 21 ጀምሮ አንድ መቶ በሚሆኑ ሰዎች በጣም ከባድ የሆነ የሳምባ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታሎች ለህክምና የዘለቁ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ከበሽታው ጥንካሬ ብዛት የአርቴፊሻል መተንፈሻ ማሽን ላይ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ማለት በራሳቸው መተንፈስ ሰላልቻሉ ነው፡፡ ሁሉም በሽተኞች ሲጠየቁ፣ በዚህ ቬፒንግ ውስጥ ኒኮቲን ወይም ማሪዋና (ሀሽሽ) ያለበት ጭስ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ እንደ ፋሽን ሆኖ  ኤሌክትሪክ ሲጋራ(e-cigarette) ተብሎ በሚጠራው አጫጫስ ሁኔታ ብዙ አሳሳቢ ሁኔታዎች መከሰታቸው የታወቀ ቢሆንም፣ አሁን በነዚህ መቶ ሰዎች ላይ የታየው ግን በጣም አደገኛ ነው፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ይህ የአጫጫስ ዘዴ ለወጣቶች በማስታወቂያ መልክ በመቅረቡ፣ መንግሥትና ተቆርቋሪዎች ተቃውሞና ክትትል እያደረጉ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ፣ እነዚህ የታመሙ ሰዎች የታመሙት በማጨሻው ቁሳቁስ ምክንያት ይሆን፣ ወይም የሚጨሰው ነገር ባልተጠበቀ ሁኔታ ለጤና አስጊ በሆኑ ኬሚካሎቹ የተናካካ ይሁን አልታወቀም፡፡ ለማንኛውም፣ ይህ አዲስ ነገር ለጤና አስጊ መሆኑ ስለሚታወቅ፣ ወላጅና ቤተዘመድ የሚያውቋቸው ልጆችና ዘመዶቻቸው ይህን ልምድ እንዳያነሱ አስቀድሞ መምከርና መከላከል አስፈላጊ ነው፡፡
በዚህ አጫጫስ ለህክምና የቀረቡ ሰዎች የተሰማቸው ስሜትና የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ራስ ምታት፣ የደረት ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መዘጋት፣ ድካም፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ትኩሳት፣ ሳል፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት ክብደት መቀነስን ይጨምራሉ፡፡
እንግዲህ ከዚህ ውጭ በዘላቂነት የሚያሰከትላቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያም ከጊዜ በኋላ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ይህ አሳሳቢ የጤና ጠንቅ ስለሆነ ላልሰማ አካፍሉ፡፡ ለውይይት መነሻ እንዲሆን በማለት አጠር ያለ አቀራረብ መርጠናል፡፡

Gosh Health

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.