ከሥጋ ብስና ጐመን በጤና!

0

bc9a180aa6e0c1cc9dccee2505ce17d6_Mጮማ ከቀዩ፣ ጥብስ ከጥሬው፣ ዳቢት ከሻኛው የሚማረጥባቸው… እስቲ ከረሜላ አውጣለት፣ ጥብሱ ለጋ ይሁን፣ ትንሽ ደረቅ ይበል… ቸኮሌት ጥብስ አድርገው… እየተባለ ትዕዛዝ የሚሰጥባቸው የከተማችን ሥጋ ቤቶች እንደ ደንበኞቻቸው ሁሉ እነሱም የ55 ቀናት የፆም ቆይታቸውን አጠናቀው  ከሥጋ ጋር ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል። ቅባት የናፈቃቸው የሥጋ ቤቶቹ መስቀያዎችና መከታተፊያዎች ሁሉ ዕለቱን በጉጉት የሚጠብቁ ይመስላሉ፡፡ በአዲሱ ገበያ፣ በዶሮ ማነቂያ፣ በስቴዲየም ዙሪያ፣ በልደታ አካባቢ ያሉ ሥጋ ቤቶች በራቸውን ከፍተው መቀባባትና መወላወል ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የናፈቁትንና የናፈቃቸውን ደንበኛ ተቀብለው ለማስተናገድ መጓጓታቸው ያስታውቃል፡፡

በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠውና ለ55 ተከታታይ ቀናት የሚዘልቀው የሁዳዴ ፆም ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡

ለሁለት ወራት ከሥጋና ከእንስሳት ተዋጽኦዎች ታቅቦ የከረመው ህዝበ ክርስቲያን ለወራት ተለይቶአቸው የከረመውን ሥጋ ነክ ምግቦች ዛሬ ሌሊቱን አንስቶ መመገብ ይጀምራል፡፡ የቅዳም ስሁር እየተባለ በሚጠራው በዛሬው ዕለት ሌሊቱን በበርበሬና በቅመም ትክን ብላ ተሰርታ በቅቤ ያበደች የዶሮ ወጥ ለፆሙ መግደፊያ በአብዛኛው ክርስቲያን ቤት ገበታ ላይ አትጠፋም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች ግን ይሄን ዓይነቱን አመጋገብ አይመክሩም። ይሄ ጤናማ ለሆነው የምግብ ስልቀጣ ሂደት እጅግ አደገኛ እንደሆነና የምግብ ስልቀጣ ስርአቱ የሚከናወንባቸው የሰውነታችን ክፍሎችን ሊጐዳ የሚችል ልማድ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ሥርጭቱ እየጨመረ የሄደው የአንጀት ካንሰር በሽታም መንስኤ ይህ አይነቱ ሥርዓት አልባና የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ። የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶክተር አብርሃም ፋሲል ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ የአንጀት ካንሰር ህመም ከአንጀት የውስጠኛው ክፍል ከሚገኝ አንድ ሴል የሚጀምርና ከመደበኛው የሴል መራባት ሂደት በተዛባ መልኩ በከፍተኛ ፍጥነት በመራባት ምክንያት የሚፈጠር አደገኛ በሽታ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሽታው ሥጋን አዘውትረው የሚመገቡና ቅባት ነክ ምግቦች ከገበታቸው ላይ የማይጠፋ ሰዎችን የሚያጠቃ ነው ብለዋል፡፡ በሽታው በአብዛኛው የትልቁን አንጀት የግራውን ክፍል በተለይም ወደ አይነምድር መውጫ አካባቢ ያለውን የትልቁ አንጀት ክፍል ያጠቃል ያሉት ሃኪሙ፤ ዕድሜያቸው ከሃምሳ አመት በላይ የሆነ ሲጋራ አጫሾችና አልኮል አዘውታሪዎች፣ ሥጋና ቅባት ነክ ምግቦችን አዘውትረው ከሚመገቡ ሰዎች ቀጥሎ የበሽታው ተጠቂ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ምግብ በአንጀታችን ውስጥ የስልቀጣ ሂደቱን ሲያከናውን የተለያዩ ሂደቶችን ያልፋል ያሉት ሃኪሙ፤ በእነዚህ የስልቀጣ ሂደቶች ውስጥ በሚያልፍበት ጊዜ የሚፈጠሩና አንጀታችንን ለተለያዩ ችግሮች የሚዳርጉ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ በተለይ አንጀታችን እንዲህ እንዳሁኑ ከሥጋና ቅባት ነክ ምግቦች ርቆ ከሰነበተ በኋላ በድንገት ቅባትና ቅመም የበዛባቸውን ምግቦች በመመገብ አደጋ ልንፈጥርበት አይገባም፡፡ እንዲህ ያለው አመጋገብ በአንጀታችን ላይ ድንገተኛ ችግርና ጉዳት ሊፈጥርበት ስለሚችል ቀስ በቀስና በማለማመድ ሊሆን ይገባል፡፡ በተፈጥሮአቸው ቅባት ነክ ምግቦችና ሥጋ በአንጀታችን ውስጥ ለምግብ ስልቀጣ ሂደቱ የሚወስዱት ጊዜ ከአትክልቶችና ሌሎች የፆም ምግቦች የበዛና ረዘም ያለ በመሆኑ የምግብ መፈጨት ችግርም ሊከሰት ይችላል ብለዋል፡፡

የአንጀት ካንሰር በሽታ የሥጋ አዘውታሪዎች ላይ በስፋት የሚታይ ችግር መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው፤ በሽታው የተከሰተባቸው ሰዎች የሚታዩባዋቸው ምልክቶች እንዳሉና ምልክቶቹ በታዩ ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ሃኪም ቤት በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የአንጀት ካንሰር በሽታ ምልክቶች ናቸው በማለት ዶክተር አብርሃም ከጠቀሷቸው ነገሮች መካከል ንፍጥ መሰል ነገር የተቀላቀለበት ለስላሳ አይነ ምድር፣ ደም የቀላቀለ ተቅማጥ፣ የማስማጥ ስሜት መኖር፣ የድካም ስሜት፣ ክብደት መቀነስ፣ የደም ማነስና አይነ ምድር በሚቀመጡበት ጊዜ የመጨነቅና ሰገራ እምቢ የማለት ስሜት መኖር ዋንኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይ ዕድሜያቸው ከሃምሳ አመት በላይ የሆናቸው ሰዎች የዚህ አይነት ምልክቶች ባጋጠሟቸው ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ሃኪም ቤት መሄድ እንደሚገባቸውም ሃኪሙ ተናግረዋል፡፡

የአንጀት ካንሰር ህመም ሥር ከመስደዱና በሽታው ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከመሰራጨቱ በፊት ከተደረሰበት በቀዶ ህክምና በካንሰሩ ሳቢያ የተጐዳውን የአንጀት ክፍል ቆርጦ በማውጣትና በማስወገድ ከበሽታው መዳን ይቻላል፡፡ የካንሰሩ ሴል የደረሰበት አካባቢ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተቆርጦ መወገድ ይኖርበታል፤ ያለበለዚያ የቀረው ክፍል ዕድገቱን በመቀጠል ለዳግም ችግር ያጋልጣል። የአንጀት ካንሰር ህመም በወቅቱ ተደርሶበት ሕክምና ካልተደረገ የካንሰር ሴሉ የመራባት ሂደቱን አፋጥኖ፣ ከአንጀት አልፎ በአካባቢው ያሉትን ክፍሎች በማጥቃትና በደም አማካይነት ወደ ጉበትና ሳንባ በመዛመት፣ ለሞት ሊዳርግ የሚችል አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ሥጋ የዋጋው ውድነት ከሚያደርስብን የኢኮኖሚ ችግር በላይ በጤናችን ላይ ይህን አይነቱን ችግርና ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ፣ ቢቀር ምን ይጐዳን ይሆን? “ከሥጋ ብስና ጐመን በጤና” አይደለ ተረቱስ!!

 

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.