ሥነ ወሲብ ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ እና መሰረታዊ ከምንላቸው ምግብ፣ ልብስና፣ መጠለያ ቀጥሎ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይነገራል፡፡ ከጥንት ዘመን ባቢሎናዊያን፣ ግሪካውያን ሮማውያንና ከዛ ቀጥሎ በተነሱ መንግስታት ጭምር የስነ ወሲብ ችግርን ለመፍታት ከባህላዊ ሕክምና ጀምሮ የተለያዩ ወይኖችን በማስጠመቅና በማስቀመም ለችግራቸው መፍትሔ ለማምጣት ብዙ ደክመዋል፡፡ ምስራቃውያኑ ደግሞ አንዳንድ የባህር ምግቦችን ለወሲብ ማነቃቂያነት ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ እስካሁንም ይህንን መንገድ የሚጠቀሙ አገራትና ሕዝቦች በቁጥር በርካታ ናቸው፡፡

በኛ ሀገር በገጠር የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ እናቶች ባይማሩም የራሳቸውን መላ ፈልገው እስከዛሬ ድረስ ለወሲብ ማነቃቂያነት (ማበረታቻነት) የተለያዩ ዘዴዎች ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህም መካከል ባሏ ከእርሻ ስራው ደክሞት ሲመጣ ድፍን ምስር በብረትምጣድ ትቀቅልና በላዩ ላይ ጨው በትና ታወርደዋለች፡፡ ለእግሩ ውሃ አሙቃ ከተለቃለቀ በኋላ ያንን የድፍን ምስር ንፍሮ እየበላ ጠላውን በላዩ ላይ ያወራርዳል፡፡ ከተወሰነ ቆይታ በኃላ የድሮው ባህላችን የስንዴ፣ የገብስ( ከተገኘ የጤፍ) እንጀራ ሶስት አጥፋ በትሪ አድርጋ እቤት ካፈራው ወጥ ጋር ታቀርባለች፡፡ ከራት በኋላ የአበሻ አረቄ አቅርባ ‹‹በሉ ጠጡ›› ትላለች፡፤ ከዚህ በኋላ ባልና ሚስት ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ፍቅር በቋንቋቸው ያወድሷታል፡፡

ይሁን እንጂ ዓለም በሳይንሱ ዘርፍ እያደገች ስትመጣ ደግሞ አመጋገባችንን በካሎሪና በመቶኛ በመቀመር የስነ ወሲብ መፍትሔ የሚባለውን የአመጋገብ ስርዓት አስቀመጡ፡፡ አንድ ሰው ከትዳር አጋሩ ጋር ጥሩ የወሲብ ጊዜ ለማሳለፍ ከፈለገ የጓሮ አትክልቶችን 10%፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬ 10%፣ ጮማ 5% እንዲሁም ሀይል ሰጪ ምግቦች 75% መመገብ እንዳለበት ሲመክሩ ይደመጣል፡፡ ለመሆኑ ወሲብ ይሄን ያህል ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሳይንሱስ የወሲብን ጥቅም እንዴት ይገልፀዋል?

ወሲብና ጥቅሙ

ሚዛናዊ የሆነ ወሲብ የሚፈፅሙ ሰዎች ሰውነታቸው ጀርም ለመከላከል የሚኖረው ሃይል እንደሚጨምር የፔኒስሊቫኒያ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡ ከጀርም በተጨማሪ ቫይረስና ባክቴሪያ የመሳሰሉ በሽታዎችን የመከላከል አቅማችንን በእጅጉ እንደሚያበረታው ይናገራሉ፡፡

በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በተደረገው ጥናት መሰረት በሳምንት አንዴና ሁለቴ ወሲብ የሚፈፅሙ ሰዎች ከማይፈፅሙት ሰዎች የተሻለ በሽታን የመከላከል አቅም እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን ደስተኞችና ዘላቂነት ያለው ህይወት ለመምራት፣ ተገቢ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ከአነቃቂ መድኃኒቶች መታቀብና የትዳር እቅድ ከሌላችሁ ኮንዶም መጠቀም ተገቢ ነው ሲል ይኸው ጥናት አክሎ ይገልፃል፡፡

በወሲብ ጊዜ የደም ዝውውር የሚፋጠን ከመሆኑም የተነሳ ሰውነታችን ለማነቃቃት፣ ብሎም ድብርትን በመግፈፍ ለሰውነታችን ጤና ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ሌላው ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚገጥሟቸውን ከፍተኛ የሕመም ስሜት በማስታገስ ደረጃም ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ በዓለማችን ላይ 30 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች በዚህ ወቅት ከፍተኛ የሕመም ስሜት እንደሚከሰትባቸው የሚታወቅ ሲሆን ካገቡ በኋላ ግን መፍትሔ እንደሚያገኙ ይነገራል፡፡

በቅርቡ በተደረገ ጥናት ደግሞ ወሲብ የደም ግፊትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ መድኃኒት መሆኑን የገለፁት የአማይ ዌልነስ ሲኢኦ ዶክተር ጆሴፍ ጄ ፒንዞኔ፣ በዚህ ላይ ጥልቅ ምርምር ማድረጋቸውን ፅፈዋል፡፡ እኚሁ ዶክተር እንደሚሉት ወሲብ ከአካላዊ እንቅስቃሴ ተለይቶ መታየት የለበትም ይላሉ፡፡ ምክንያት ብለው ያቀረቡት ደግሞ በወሲብ ጊዜ በደቂቃ አምስት ካሎሪ መጠቀማችን ሲሆን ይህ ደግሞ ለጡንቻዎቻችን እንቅስቃሴና ለልብ ምታችን የራሱ ድርሻ ስላለው ነው፡፡

ወሲብ የኤስትሮጂንና ቴስቶትሮን መጠን ተመጣጣኝ (Balance) እንዲሆን ሲረዳ በልብ በሽታ የመሞት አጋጣሚንም ይቀንሰዋል፡፡ እንዲሁም ሴቶች በወሲባዊ መነቃቃት ወቅት የእግር ሕመም፣ ራስ ምታትና ጭንቀታቸውን በእጅጉ እንደሚቀንስላቸው ከጥናቱ መረዳት ተችሏል፡፡

የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው ሰዎች፤ በተለይ ደግሞ በውጥረት የተነሳ ለእንቅልፍ ማጣት ችግር የሚጋለጡ ሴቶች በወሲብ ጊዜ አእምሯቸው ራሱን እንደሚያድስና በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ምክንያት እንደሚሆንም ይነገራል፡፡

ጥያቄ ከቀረበላቸው 26ሺ ባለትዳር ሴቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሲመልሱ ‹‹ ወሲብ ከፈፀሙ በኋላ በስራቸውም ሆነ በእለት ውሎአቸው ደስተኛ ሆነው እንደሚያሳልፉ›› ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ብዙ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት የወሲብ ችግር ምንጩ ከምግብ እጥረት ወይም ማህበራዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ዋናው ምክንያት የሚሆነው  የስነ ልቦና ችግር ስለሆነ ባለሙያዎችን ማማከር ተገቢ ይሆናል ባይ ናቸው፡፡ አሊያ ግን ስነ ወሲብ ችግር ምናልባትም ለቤት መፍረስ መንስኤ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.