የኤስትሮጅን ንጥረ ቅመም (ሆርሞን) ሴትነትን ከመወሰን በተጨማሪ በተለያየ መልክ የሚገለፅ ተፅዕኖ አለው፡፡ ይህ ሆርሞን በሰውነት ውስጥ ከሚፈለገው መጠን በላይ ሲመረት ወይም ዝቅተኛ ሲሆን፣ አልያም ጭራሹን ሳይመረት ሲቀር የተለያዩ የጤና ችግሮችን ያስከትላል፡፡ በኤስትሮጂን ሆርሞን (ንጥረ ቅመም) ምንነት፣ በጥቅሙ፣ እሱን ተከትለው በሚከሰቱ የጤና ችግሮችና በመፍትሄያቸው ዙሪያ አንድ የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስትን አነጋግረንልዎታል፡፡

Making-Love

ጥያቄ፡ኤስትሮጂን ሆርሞን (ንጥረ ቅመም) ምንድነው? የሚመረተውስ እንዴት ነው?

ዶ/ር፡- ኤስትሮጂን ሆርሞን በሴቶች ሰውነት ውስጥ ከሚመነጩ ሆርሞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ሆርሞን ጋር የመተጋገዝ ስራ የሚያከናውን ፕሮጀስትሮን የሚባል ንጥረ ቅመም አለ፡፡ እነዚህ ንጥረ ቅመሞች በስነ ተዋልዶ ጤና ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ የምናተኩረው በኤስትሮጂን ንጥረ ቅመም ላይ በመሆኑ፣ ይህ ንጥረ ቅመም በተፈጥሮ የሚመነጭ ነው፡፡ ሆርሞኑ E, E2 እና E3 ተብለው በሶት ይከፈላሉ፡፡ የሚመነጨውም በአብዛኛው በሴቶች የዕንቁላል ማፍሪያ ክፍል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በእርግዝና ወቅት በእንግዴ ልጅ አማካኝነት፣ ንጥረ ቅመሙ የሚመረትበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆርሞኑ የሚመረተው ሴቶች ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ ነው፡፡

በደም ውስጥ ከሚገኙ ቅባቶች አንዱ የሆነው ኮሌስትሮል፣ በተለያዩ አብላይ ኢንዛይሞች አማካኝነት በቅድሚያ አንድርስቶንና ቴስቴስትሮን ወደተባለ የወንድነት ሆርሞኖች ይለውጣል፡፡ ቀጥሎም የተለያዩ የኤስትሮጂን ንጥረ ቅመም አይነቶች ይመረታል፡፡ የመመረት መጠናቸውም የአንዲትን ሴት የወር አበባ ዑደትን ተከትሎ ይለያያል፡፡ በተለይም በወር አበባ መምጫ 12ኛውና 13ኛው ቀን አካባቢና የሁለተኛው ወር አበባ ሊመጣ ሲል የኤስትሮጂን ምርቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የወር አበባን ለአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

  1. ደም የሚታይበት ጊዜ
  2. እንቁላል ከመውጣቱ በፊት ያለው ጊዜ
  3. እንቁላል የምትወጣበት ጊዜ እና
  4. እንቁላል ከወጣ በኋላ ያሉት ጊዜያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የአስትሮጂን መጠን ከፍ የሚልበትና ዝቅ የሚልበት ሁኔታ አለ፡፡ መጠናቸውን በተመለከተ እንቁላል ሊወጣ ሲል 380 ማይክሮ ግራም ሲሆን፣ በሚቀጥለው የወር አበባ ጊዜ ደግሞ 250 ማይክሮ ግራም ዝቅ ይላል፡፡ መጠኑ ሲቀንስ እስከ 36 ማይክሮ ግራም ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

አንዲት ሴት በፅንስ ላይ እያለች 7 ሚሊየን የሚሆኑ ዕንቁላሎች በተፈጥሮ ይኖሯታል፡፡ በውልደት ጊዜ የዕንቁላል መጠኑ ከ1 እስከ 2 ሚሊየን ዝቅ ይላል፡፡ ይህ ቁጥር ከውልደት በኋላ በየጊዜው እየቀነሰ በመሄድ፣ በ14ኛ ዕድሜዋ አካባቢ ከ300 እስከ 400 ሺ ይደርሳል፡፡ ወደ ጉርምስና ዕድሜዋ ስትገባ የኤስትሮጂን ሆርሞን በሚፈለገው መጠን መመረት ይጀምራል፡፡ ይህ ሁሉ ትዕዛዝ የሚመጣው ከአእምሮ ነው፡፡

አዕምሮ ውስጥ ሃይፓታለመስ እና ፒቱታሪ ግላንድ የሚባሉ ክፍሎች አሉ፡፡ ቀጥሎም የእንቁላል መስሪያው ክፍል አለ፡፡ እነዚህ ሶስት የአካል ክፍሎች በቅንጅት በመስራት፣ አዕምሮ በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በጉርምስና ዕድሜ ላይ እንቁላል ጊዜውን ጠብቆ መምረት ይጀምራል፡፡ የተሟላ ጤንነት ላይ ያለች ሴት በየወሩ በግራ እና በቀኝ ሁለት እንቁላሎችን ታኮርታለች፡፡

የተመረተው እንቁላል እንደወጣ ከወንድ ዘር ፍሬ ጋር ከተገናኘ ፅንስ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ፅንስ ከሌለ የተዘጋጀው የማህፀን ግድግዳ፣ በሚቀጥለው 28 ቀን የንጥረ ቅመሞች ድጋፍ ስለማይኖረው ይፈርስና ደም ሆኖ ይወጣል፡፡ አንዲት ሴት በየወሩ መጠኑ ከ3 እስከ 80 ሚሊ ሊትር ሊሆን የሚችል የወር አበባ ታያለች፡፡ የወር አበባ ዑደቱ የሚከናወነው፣ በኤስትሮጅንና በፕሮስቴስትሮን ሆርሞኖች መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡

 

ጥያቄ፡ኤስትሮጂን ከላይ ከተገለፁት ተግባራት ባሻገር ሌሎች ጠቀሜታዎች ካሉት ብናይ?

ዶ/ር፡- ኤስትሮጂን የሚባለው ንጥረ ቅመም፣ የወር አበባ ዑደትን የተሳካ ለማድረግ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር ሌሎች ጥቅሞችም አሉት፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትን ቀጥለን እናያለን፡፡

– በጡቶቿ ላይ በጉርምስና ዕድሜዋ ላይ ለውጦች እንዲመጡ ያደርጋል፤

– በጡት ውስጥ የወተት ማምረቻ ቧንቧዎች እንዲወፍሩና እንዲበዙ ያደርጋል፤

– የጡት ጫፍ ጥቁር እንዲልና የተለየ ቀለም እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፤

– በብብትና በብልት አካባቢ ፀጉር እንዲወጣ የሚያደርግ ነው፤

– የወር አበባ ዑደት እንዲጀመር የሚያደርግ ነው፤

– አንዲት ሴት የሴትነት አካላዊ ቅርፅ እንዲኖት ያደርጋል፤

– በሴቶች ጡትና መቀመጫቸው አካባቢ የቅባት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

– ሴቶች ድምፃቸው ቀጭን እንዲሆን ያደርጋል፤

– በሰውነታቸው ላይ ሴቶች ፀጉር እንዳይኖራቸውና የጭንቅላታቸው ፀጉር ግን እየበዛና እየተለቀ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡

– ማህፀን መጠኑን ጠብቆና ዳብሮ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ ኤስትሮጂን ሆርሞን ለሴቶች ከላይ የዘረዘርናቸውን ጥቅሞች ያስገኝላቸዋል፡፡

 

ጥያቄ፡የኤስትሮጂን ሆርሞንን መጣባት እንዲከሰት የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድናቸው?

ዶ/ር፡- የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ዋና ዋና የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡

– ዕድሜ በመግፋቱ ምክንያት በቂ የኤስትሮጂን መጠን አለመመረቱ፤

– ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በደም አማካኝነት የሚመጡ ኢንፌክሽኖች የዕንቁላል ማኳራቸውን ማጥቃታቸው፤

– በቀዶ ህክምና ኦቫሪ ሲወጣ፤

– በተፈጥሮ ኦቫሪው ኤስትሮጂን ማምረት አለመቻሉ፤

 

ጥያቄ፡የኤስትሮጂን ሆርሞን መዛባት መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር፡- ተለዋዋጭ የሰውነት ሙቀት፣ ላብ ጥምቅ ጥምቅ ማድረግ፣ የወር አበባ መዛባት፣ የብልት መድረቅ፣ የአጥንት መሳሳት፣ በወሲብ ወቅት ህመም መከሰትና የሆድ መነፋት በቀዳሚነት የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡

 

ጥያቄ፡ከሴቶች ጡት ማነስ እና ፀጉር ዕድገት ጋር የኤስትሮጂን ንጥረ ቅመም ያለው ግንኙነት ምን ይሆን?

ዶ/ር፡- የጡት ማነስም ሆነ መተለቅ ቀጥታ ከኤስትሮጂን ሆርሞን ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም፡፡ ኤስትሮጂን አንዱ መንስኤ ይሁን እንጂ ሌሎች ሆርሞኖች በተጣጣመ መልኩ የማይሰሩ ወይም ደግሞ መጠናቸውን የማይጠብቁ ከሆነ የአስትሮጂንን ጤናማ ተግባር ያበላሹታል፡፡ ስለዚህ የአንዲት ሴት ሆርሞን መጠኑ ከፍ ካለ ፂም ሊኖራት ይችላል፤ ስለዚህ የጡት ማነስ (መተለቅ) የፀጉር ዕድገት መቀጨጭና የሴትነት መለያ ባህሪያት መዛባት የሚከሰተው፣ በኤስትሮጂን ማነስና በሌሎች ሆርሞኖች መብዛት ምክንያት ነው፡፡

 

ጥያቄ፡የኤስትሮጂን ንጥረ ቅመም ከወሲብ ፍላጎት መቀነስ /መብዛት/ ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ አለ?

ዶ/ር፡- በእርግጥም ይገናኛል፡፡ የኤስትሮጂንና የቴስቴስትሮን ንጥረ ቅመሞች አለመመጣጠን፣ በሴቶችም በወንዶችም የወሲብ ፍላጎት መቀነስና መጨመር ሁኔታዎችን ያሳያል፡፡ ሆርሞኑ ብቻውን ሳይሆን በአካባቢ ሁኔታዎችና ከበሽታዎች ጋር በተገናኘ መልኩ፣ በሴቶች የወሲብ ፍላጎት ማጣት ላይ አልያም መብዛት ምክንያት ይሆናል፡፡

 

ጥያቄ፡የንጥረ ቅመሙ አለጊዜው መመረት፣ ማነስና መብዛትን ተከትለው የሚከሰቱ የጤና ችግሮች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር፡- ዕድሜያቸው ከ10 በላይ ሲሆን የጉልምስና ምልክት መታየት ሲገባው አስቀድሞ በ5 እና በ6 ዕድሜያቸው ጡት ማውጣት፣ ዳሌአቸው ሰፋ ማለትና የወር አበባ መታየት ቢያጋጥማቸው ይሄ የኤስትሮጂን መጠን በተፈጥሮ በብዛት መመረቱን ያሳያል፡፡ አልያም ደግሞ ሳይታወቅ በመድሃኒት መልክ ኤስትሮጂን ሆርሞን ከውጭ መወሰዱን ያመላክታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኤስትሮጂን ማነስ ካለ ደግሞ የጉርምስና ዕድሜያቸው ይዘገያል፡፡ ይህም ማለት 18 ዓመታቸው ድረስ ጡታቸው ላያድግና የወር አበባ ላያዩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኤስትሮጂን ሆርሞን መብዛት በሚከሰትበት ወቅት፣ የወር አበባ መብዛትና መርዘም እንዲሁም የማህፀን ዕጢዎችና የተለያዩ ቦታዎች ላይ ፀጉር የመውጣት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ እንደዚሁም የማህፀን ግድግዳ እና የኦቫሪ ካንሰር ይከሰታል፡፡ በሰውነት ውስጥ የቴስቴስትሮን ሆርሞን በብዛት ስለሚመረት፣ የቅርፅ መበላሸትን በተለይም የወንድነት ባህሪን መላበስ፣ ያልተፈለገ ቦታ ላይ ፀጉር መውጣት እና ድምፅ እንደ ወንድ የመወፈር ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ሆርሞኑ በማይመረትበት ጊዜ ደግሞ ሌሎች ችግሮችን ያስከትላል፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት በ51 ዓመቷ የወር አበባ ማቆም ሲገባት በ28 እና በ30 ዕድሜዋ የወር አበባ ሊጠፋባት ይችላል፡፡ ከዕድሜ የቀደመ የዕንቁላል ማፍሪያ አካል ስራውን የማቆም ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት መውለድ አይችሉም፡፡ ያለማቋረጥ ትኩሳትና በብዛት ላብ የመፈጠር ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በረጅም ጊዜ የአጥንት መሳሳትና የልብ ነክ ጤና ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ እንደዚሁም የአጥንት ጥንካሬ ማጣት፣ ከዕድሜ ቀድመው የእርጅና ምልክቶች እና ከዕድሜ የቀደመ ማረጥ ይከሰታል፡፡

 

ጥያቄ፡በንጥረ ቅመሙ አለመመረት ወይም የመጠን ማዛባት የበለጠ ተጋላጭ የሚሆኑ ሴቶች ይኖሩ ይሆን?

ዶ/ር፡- ይኖራሉ፡፡ የሥራ ውጥረት ያለባቸው፣ ለረጅም ጊዜ የሚሮጡ፣ በትላልቅ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያሉ ሴቶች ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የስኳር፣ የቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ የጭንቅላት ዕጢዎች፣ የእንቅርትና መሰል ለረጅም ጊዜ የሰውነት ጤናን የሚያውኩ በሽታዎች ሴቶችን የኤስትሮጅን ሆርሞን መዛባት ያስከትላሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የወር አበባ ዑደት መዛባትም ሊፈጠርባቸው ይችላል፡፡ ሌላው የዕንቁላል ማፍሪያው አካባቢ ያለው ክፍል በጨረር፣ በኢንፌክሽን በዘር የሚተላለፍ የጤና ችግር ያጋጠማቸው ሴቶችም፣ የሆርሞን አለመመረት ወይም የመጠን መዛባት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡

 

ጥያቄ፡የሆርሞን መዛባቱን ለማረጋገጥ የሚዳረጉ ምርመራዎች ምንድናቸው?

ዶ/ር፡-በደም አማካይነት የሆርሞን ምርመራ በማድረግ ማነሱንም ሆነ ከሚጠበቀው መጠን በላይ መመረቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኤስትሮጅን ሆርሞን መዛባትን ተከትሎ፣ ሌሎች የጤና ችግሮች መከሰታቸውንና ያስከተሉት ጉዳት መኖሩን ለማወቅ የአልትራ ሳውንድ ምርመራ እናደርጋለን፡፡

 

ጥያቄ፡ከኤስትሮጂን ሆርሞን ሚዛን መሳት ጋር በተያያዙ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄው ምንድነው?

ዶ/ር፡- ከሁሉም የሚቀድመው የሆርሞን ባለመመረት አልያም ደግሞ ከመጠን መዛባት ጋር በተያያዘ፣ የሚከሰቱ የጤና ባለሙያን ማማከር ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡ ሐኪሙ በሚያደርገው ሁሉ አቀፍ ምርመራ ችግሩ ከተለየ በኋላ የመውለድ ችግር ከሆነ፣ የወር አበባ መቋረጥና ሌሎች መሰል ችግሮች ከሆኑ እንደየባህሪያቸው በህክምናው የሚሰጡ መፍትሄዎች አሉ፡፡ በሌላም በኩል የወር አበባ መዛባት ካለ የሆርሞን ችግር ብቻውን ሳይሆን፣ ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋር የሚቆራኝበት ሁኔታ ስላለ የሌሎች ጤና ችግሮች ምርመራ ተደርጎ መፍትሄ ይሰጠዋል፡፡

የኤስትሮጅን ሆርሞን ማነስ ሲኖር በመድሃኒት መልክ የኤስትሮጅን ሆርሞን በመስጠት እናክማለን፡፡ በአጠቃላይ ከሆርሞን መዛባት ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች በህክምና መፍትሄ የመስጠት ሥራ በመስራት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.