በወሲብ ጊዜ ከደስታ ይልቅ ህመም፣ ከሰላም ይልቅ ጭንቀት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን የሚያስተናግዱ ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳም ፍቅራቸውና ትዳራቸው የተናጋ፣ ወንድን ወደ መጥላት የተሸጋገሩ ሴቶች አሉ፡፡ የወር አበባዋን ማየት እንዳቆመችና በተለምዶው አባባል የማረጫ ዕድሜዋ ላይ እንደተገኘች አልማዝ (ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሟ የተቀየረው)፣ ወሲብ በምትፈፅምበት ወቅት ህመም ይሰማት የጀመረው ብዙም ሳይቆይ እንደሆነ ነው የምትናገረው፡፡

‹‹ከባለቤቴ ጋር ግንኙነት ሳደርግ በውስጤ ስለት ያለው ቢላ ዘልቆ እንደገባ ነው የሚሰማኝ፡፡ ከጎበኘኋቸው የህክምና ባለሙያዎች የሚታዘዙልኝ ቅባቶች ስቃዬን ቢቀንሱልኝም ለሀፍረት መጋለጤ፣ ራሴን መጠራጠሬ፣ ለግንኙነት ስዘጋጅ መሸበሬ አልቀረም..›› ትላለች፡፡

አልማዝ እየተሰማት ባለው ህመምና እሱን ተከትሎም የተቆጣጠራት ፍራቻ ለስምንት ዓመታት አብሯት የቆየ ነው፡፡ የመራቢያን አካል ስለሚያጠናክረውና ስለሚያፍታታው የህክምና ስፖርት ዘግይታ መረዳቷን ነው የምትናገረው፡፡ ዱባይ በመመላለስ ህክምናዋን እንደተከታተለች የምትናገረው አልማዝ የተአምር ያህል በራሷ ላይ ለውጥ ተመልክታለች፡፡

በህክምና ሳይንስ አጠራሩ ‹‹ዲ ስፓራውኒያ›› የሚባለው ቃል፣ ከግሪክ የተወረሰና ትርጉሙም በሚገባ ያልተጣጣመ ወይም ያልገጠመ እንደማለት ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ታዲያ በወሲብ ወቅትና በኋላ ላይ በሴቶች የመራቢያ አካል ላይ የሚፈጠረውን ህመም ለመግለጽ ቃሉን ይጠቁመበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ሚሊዮኖች ሴቶች በዚህ ችግር እንደሚሰቃዩ ነው የሚነገረው፡፡ ችግሩ ወሲባዊ ፍላጎትንና በኋላም የሚገኘውን እርካታ የሚከለክል ነው፡፡ ብሎም የሕይወትን መሰረታዊ ጣዕም በመንፈግ ችግሩን ያጎላዋል፡፡ የወር አበባቸውን ማየት ላቆሙት ሴቶች ደግሞ፣ ከዕድሜ ጋር ከሚደረግ ሩጫ ጋር መውደቃቸውን እንዲቀበሉ የሚያደርግ ስነ ልቦናዊ ችግር ከማስከተሉም ባለፈ የሰውት ቅርፅን ሊያበላሽ እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በርካታ ሴቶች በመረጡት ዝምታ፣ ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታ ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡ በእርግጥ እንደ ገበና የሚቆጠሩትን መሰል ጉዳት ለአደባባይ ማብቃት ባልተለመደባት ሀገራችን ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡

ዲያፓሪውኒያ ምንድነው?

ዲስፓሪውኒያ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን፣ በተለየ ሁኔታ የወር አበባ ማየት ባቆሙ/ባረጡ ሴቶች ላይ የሚከሰት ችግር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በጥናት በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሩብ ያህል ሴቶች፣ በወሲብ ወቅት ህመም የሚሰማቸው ሴቶች እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡ ህመሙ አነስ ካለው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ስቃይ የሚደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ ስሜቶችም ማቃጠል፣ ውጋትና መጠዝጠዝ ናቸው፡፡
የህመሞቹ መከሰቻ የሀፍረት ሥጋ ውጪኛው ክፍል ላይ እና የዳሌ አጥንት ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ሴቶች ከመራቢያ አካል ነርቭ በሚያገናኘው ቱቦ ላይ ምቾት ማጣት ይከሰትባቸዋል፡፡ ከዚህም በወሲብ ወቅት መታመሙ በሂደት የሚመጣ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ስለ ወሲብ ማሰብ ጭምር የማይፈልጉና ራሳቸውን ከዚህ ተፈጥሯዊ ተግባር የሚያርቁ ናቸው፡፡

መነሻ ምክንያቶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ልንቀበላቸው ከምንችላቸው የችግሩ ምክንያቶች መካከል የመጀመሪያው የሆርሞን ለውጥ ሲሆን፣ እንዲሁም ከስሜት ጋር የተያያዙት ድብርት እና ስጋት ደግሞ ሌሎቹ ናቸው፡፡ በመሀከላቸው የዕድሜ ዘመን ለሚገኙ ሴቶች፣ የመራቢያ አካል መመንመን (Vaginal atrophy) በወሲብ ወቅት ለሚፈጠር ህመም ሌላውና ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ በባለሙያዎች ይወሰዳል፡፡

ከስነ ልቦና እና ከስሜት ጋር የተያያዙት ታሪኮቻችንም ወደ ኋላ ለሚመጣው የግንኙነት ወቅት ህመም፣ መነሻ ስለመሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በመሰረታዊነት የተለዩትም አስገድዶ መደፈር፣ ጭንቀትና ድብርት፣ የጥፋተኝነት ስሜት ወሲብን በህመም የታጀበ የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ እንዲሁም በማህፀን ውስጥ የሚከሰት ህመም ምልክትም ሊሆን ይችላል፡፡

ህክምናው ምንድን ነው?

የማህፀን ሐኪሞች በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ናቸው፡፡ ችግሩ በእርግጥም የአንድ ወቅት ብቻ እንዳልሆነና እርዳታ እንደሚያስፈልግሽ ስታምኚ ለሀፍረትና ለመሸማቀቅ ቦታ ሊኖርሽ አይገባም፡፡ ከሌሎቹ ጉዳዮችሽ በላይ ቅድሚያ የምትጪው ጤናሽ በመሆኑ፡፡ ስለዚህ ስለህመም ስሜቱ በቀጥታ ለሐኪም በግልፅ መንገር ይኖርብሻል፡፡ በተለይ እንዴት ጀመረሽ? የት እና መቼ ነው የህመም ስሜቱ የሚሰማሽ? ከስቃዩ ለመውጣት በራስሽ የምትወስጃቸው እርምጃዎች ምንድናቸው? የማህፀን ሕክምና ታሪክሽ እና ስትወልጂ ስለነበሩ ሁኔታዎችና ከፍቅር አጋርሽ ጋር ስላለሽ ግንኙነት ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ሊቀርቡልሽ ይችላሉ፡፡ አስፈላጊው ነገርም ራስን ለዕርዳታው ዝግጁ ማድረግ ይሆናል፡፡ አልማዝን ለመሰሉ በወሲብ መደሰት ለሚፈልጉ ሴቶች ግን የማይሳካ ተግባር ይሆናል፡፡ ለሁለቱ ተጣማሪዎች በዚህ ወቅት ሰውነቶቻቸውን በሚፈልጉት መንገድ ምላሽ መስጠት ሳይችል ሲቀር መመልከት ትልቁ የጭንቀታቸውና የፍራቻቸው ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ከመልካሞቹ የትዳር አጋሮች በመሰል ወቅት ድጋፎቻቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ከባለሙያ የሚሰጠውን እርዳታ በጋራ ከመከታተል ጀምሮ በከባዱ ጊዜ ጭምር አጋርነታቸውን ያሳያሉ፡፡ ይሄ በኋላ ላይ ለሚፈለገው ውጤት መሰረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉና ከአካል ጉዳት ጋር የሚኖሩ ሴቶች የወሲብ ወቅት ህመምን እንደሚያዳብሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ብዙዎቹንም ለተፈጥሯዊው ተግባር ፍላጎት ወደማጣት ይመራቸዋል፡፡ የህክክና ባለሙያዎች ግን አሁንም የአካል ጉት ወይም ሰፊ ፆታዊ ጥቃት ብቻቸውን የችግሩ ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ ያስረዳሉ፡፡ በተደጋጋሚ በመራቢያ አካል ላይ ምርመራ በማድረግ ችግር እንደ ሌለባቸው የተነገራቸው ሰዎች ጭምር በህመሙ ሲሰቃዩ መመልከት የተለመደ በህመሙ ሲሰቃዩ መመልከት የተለመደ በመሆኑ፡፡ እርዳታዎቹ መድሃኒቶች፣ ቴራፒዎችንና ራስን መንከባከብን ሊያጠቃልሉ ይችላሉ፡፡

– ቅባቶች፡- ምንም አይነት ሆርሞን በውስጣቸው የሌለ ቅባቶችና ማለስለሻዎች፣ በግንኙነት ወቅት በሚፈጠር መተሻሸት ሳቢያ የሚከሰትን ህመም ይቀንሳሉ፡፡ ቅባቶቹ ከግንኙነት በፊት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለረዥም ጊዜ መፍትሄ ዘወትር የምንጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ሰዎች የሚስማማቸውን መርጠው ለመጠቀም ረዥም ጊዜ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ ከአትክልቶች የሚዘጋጁት ዘይቶች ውድ የሚባሉት አማራጮች ናቸው፡፡

– የግንኙነት ልምዶችን መቀየር፡- ከመደበኞቹና ህመም ከሚያስከትሉት የግንኙነት መንገዶች ለየት ያሉ ተግባሮችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ከጓደኛ ጋር መመካከር የተሻለውን ለመምረጥ ጠቃሚ ነው፡፡

– ንፅህናን በተለየ ሁኔታ መጠበቅ፡- የተለየ ሽታ ያላቸውን ሳሙናዎችንና ቅባቶችን በማስወገድ፣ የመራቢያ አካልን ንፅህና በውሃና በንፁህ ውሃ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ መጠበቅ በባለሙያዎች የሚቀርብ አማራጭ ነው፡፡ ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ልብሶችን መምረጥና ሰውነትን ምቾት ከሚነሱ ልብሶች ማራቅም ጠቃሚ ነው፡፡

– ሌሎች አማራጮች መመልከት፡- ወሲብ ጡንቻዎችን የማጠንከርና የደም ዝውውር ስርዓትን የማሳለጥ ሚና አለው፡፡ ታዲያ ግንኙነቱ የስቃይ ምክንያት ሲሆን ሌሎች አማራጮችን መመልከት ሳይኖርብን አይቀርም ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡

– ቀዶ ጥገና፡- በራሳችን መፍትሄ  ብለን የጀመርናቸው ነገሮች አልሳካ ካሉን ቀዶ ጥገና በአማራጭነት ቀርቧል፡፡ ህክምናው በመራቢያ አካል አካባቢ የተወሰኑ የሰውነት አካላትን በማስወገድ የሚከናወን ነው፡፡ ቀዶ ጥገናው ብዙ ጊዜ የስነ ልቦናውና የመድሃኒት ህክምናው ውጤታማ መሆን ሳይችል ሲቀር የሚገባበት ነው፡፡

– ካውንስሊንግ፡- ስሜትና ስነልቦና ላይ ትኩረት አድርጎ በባለሙያዎች የሚሰጥ ህክምና ነው፡፡ መሰረት ከሌለው ስጋት ጀምሮ ከጓደኛ ጋር ያለው መጥፎ ስሜት በወሲብ ወቅት ለሚፈጠረው ህመም ሌላው መነሻ እንደሀነ ይነገራል፡፡ ይሄ ደግሞ በቀጥታ ትዳርን ወይም የፍቅር ግንኙነትን ሊረብሽ ይችላል፤ ስለዚህ ከሰለጠኑ የምክር ባለሙያዎችና ቴራፒስቶች ጋር ስለጉዳዩ በግልፅ ማውራቱ ብዙ ይረዳል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.