የቂጥኝ በሽታ አገራችን መቼ ከባሕር ማዶ እንደመጣ በግልጽ ባይታወቅም አንዳንድ ጽሁፎች እንደሚገልጹት ከግራኝ መሐመድ ጦርነት በኋላ እሱን ለመከላከል ከመጡት የፖርቱጋል ወታደሮች ጋር በ16ኚው ዘመን መጣ የሚሉ አሉ። ከዚያ ተከትለው በመጡት በተለይ በ18ኛውና 19ኛው አመታት በመስፋፋትና በመሸታ ቤት ብዛትና የሴተኛ አዳሪዎች መበራከት የተነሳ በከተሞች ከትልልቅ እስከ ተራው ሕዝብ ውርዴ ነኝ የማይል ሰው የማይገኝበት ደረጃ ተደረሰ።
_
የሚደንቀው ነገር በአማርኛው ተናጋሪ ቅጥኝና ፈንጣጣ የተለያዩ በሽታ መጠሪያ ሲሆኑ በትግሪኛ ተናጋሪውና ለዚያ አቃራቢ በሆኑት አማርኛ ተናጋሪዎች ግን ቂጥኝ ፍንጣጣ ይባላል ባንዳንድ ትግሪኛ ተናጋሪ አካባቢዎችም ሀበ ፈረንጂ ወይም የፈረንጅ ይባል ነበር። የሚገመው ነገር ደግሞ የ18ኛው ክፍለ ዘመን የሸዋው ንጉስ ወልደ ጊዮርጊስ ወሰን ሰገድ ያስደረሱትና አሁን ተሰርቆ ለንደን የብሪቲሽ ላይብረሪ የሚገኝ የሕክና መጵሐፍ የተለያዩ የፈንጣጣ በሽታዎች ለምሳሌ ክፉኛ ፈንጣጣ ፣ የአዳል ፈንጣጣ ወዘተ የበሽታ ስሞች ይገኙበታል። ነገር ግን ዝርዝር መግለጫው በቂ ባለመሆኑ የተለያዩት በሽታዎች ምንንን እንደሚያመለክቱ በጥራት አይታወቅም። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚገምቱት ያዳል ፈንጣጣ ይባል የነበሩው ከዚያን ዘመን በኋላ ቂጥኝ ተብሎ የሚጠራው የአባለ ዘር በሽታ ነው ይላሉ።
_
በኦሮሚኛ ቂጥኝ ከ18ኛው ዘመን ወዲህ ፋንዶ በሚባል ስም ይጠራል። በዚያን ዘመን ግን የቂጥኝ በሽታ በኦሮሚኛ ተናጋሪው ህዝብ ብዙም ይታይ ስላልነበር በሽታው ከሰሜን ወደ ደቡብ የተዛመተው ዘግይቶ ነው ተብሎ ይገመታል።
_
በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ቂጥኝ መያዝ የተለመደ ሆኖ ቂጥኝ ይዞኛል ማለት እንደ ጉንፋን ይዞኛል ሆኖ የሚያሳፍር እስከ መሆን ደርሶ ነበር። ብዙዎችም በወሲብ ሳይሆን ከታመመ ዶሮ መብላት ጋር ስለሚያያይዙት ዶሮ ሲገዛ በደምብ ኮክኒው ተመርምሮ ደህና ሆኖ ሲገኝ ነበር። የቀድሞ የመሀል አገር አባቶች ደሞ ቂጥኝን አገራችን አምጥቶ የዘራው ጣሊያን ሊያመክነንና ሊያጠፋን አስቦ ነው ይሉ ነበር።
_
በባሕል ሐኪሞቻችን ቂጥኝ በተለያዩ እጽዋት ሕክምና ይሰጥ ነበር። ከነዚህ ሁሉ ፍቱን ነው ተብሎ የሚታወቀው ጦቢያ የሚባል ቁጥቋጦ ቅርፊት ከታማሚው መግል ጋር ተጨቅጭቆ በማጠጣት ነበር። ለበቂ ፈውስነቱ ግን የጥናት መረጃ የለንም። እንደያካባቢው ቁልቋል ፣ እንዶድ ፣ ሚጫሚጬ ፣ ብሳና ፣ ቀጨሞና ኮሶ ወዘተ ለቂጥኝ ጠቀሜታ ይውሉ ነበር። ታሪኩ ብዙ ስለሆነ የባሕል ሕክምና አዋቂያችንን Fekadu Fullas እንዲረዳን ተማጥኜ አፌን በዳቦ አብሱ እላለሁ።

Dr. Abebe Haregewoin
_______________________

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.