washing handእጅን መታጠብና በንጽህና መያዝ ከኢንፌክሽን እና በሽታ ዋነኛ የመከላከያ ዘዴ ነው። እጅን መታጠብ በጣም ቀላል ተግባር ሲሆን የኢንፌክሽን እና በሽታ ስርጭት በቤታችን፣ በሥራ ቦታ፣ ህፃናት በሚውሉበት ቦታ እና ሆስፒታሎች አካባቢ በሽታን በመግታት/በመከላከል ይጠቅመናል። ንጽህ እጅ ከሰው ወደ ሰው እና በአካባቢያችን የጀርም ስርጭትን ይገታል።

እጃችንን መታጠብ ያለብን መቸ ነው?
– ምግብ ከማዘጋጀታችን በፊት፣ በምናዘጋጅበት ወቅት እና ካዘጋጀን በኃላ
– ምግብ ከመመገባችን በፊት
– የታመመን ሰው ከመንከባከባችን በፊት እና በኃላ
– ቁስልን ከማከማችን በፊት እና በኃላ
– ሽንት ቤት ከተጠቀምን በኃላ
– ዳይፐር ከቀየርን እና ሽንት ቤት የተጠቀመን ህፃን ካጠብን በኃላ
– አፍንጫችንን ከነካን፣ ሳል ካሳለን ወይም ካስነጠስን በኃላ
– እንሰሳትን፣ የእንሰሳትን ምግብ እና እንሰሳት የተፀዳድትን ከነካን በኃላ
– የቆሻሻ ማጠራቀሚያ/መጣያ ከነካን በኃላ ናቸው።

ትክክለኛው የእጅ አስተጣጠብ መንገድ እንዴት ነው?
– እጅዎን በንጽህ የቧንቧ ውሀ ይታጠቡት/ ያርሱት ከዚያም ቧንቧውን ይዝጉትና ሳሙና ይጠቀሙ
– አረፋ እስከሚኖረው ሳሙናውን እና እጅዎን በደንብ ይሹት የእጅዎን ጀርባና የጣትዎን መሀል እና ጥፍርዎን በሳሙና አረፋ ማሸትዎን አይዘንጉ።
– ቢያንስ ለ 20 ሰከንድ እጅዎን በማሸት ወይም በመፈተግ ይታጠቡት
– እጅዎን በንጽህ የቧንቧ ውሀ ያለቅልቁት
– እጅዎን በንጽህ ፎጣ ወይም አየር ያድርቁት

ንጽህ ውሀና ሳሙና በሌለበት ቦታ እጃችንን እንዴት እናጸዳለን?
እጅዎን በሳሙና እና በንጽህ ውሀ መታጠብ በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን በቁጥር ለመቀነስ ተመራጭ ዘዴ ሲሆን ንጽህ ውሀ በሌለበት አጋጣሚ ግን ከአልኮል የተሠራ የእጅ ማጽጃዎችን መጠቀም ተገቢ ነው። የአልኮል መጠናቸውም እስከ 60% ቢደርስ ይመከራል። ከአልኮል የሚሰሩ የእጅ መጽጃዎች በእጅ ላይ ያሉ በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን በቁጥር ቢቀንሳቸውም ሁሉንም አይነት ተህዋሲያንን ግን ሙሉ ለሙሉ እንደማያጠፋቸው ልብ ማለት ይገባል።
በመጨረሻም እጅን በንጽህና መያዝ ጀርሞች እንዳይራቡና በበሽታ እንዳንያዝ ለመከላከል አንድና ዋነኛው መንገድ ነው። ብዙ በሽታዎች እጅን በውሀና ሳሙና ባለመታጠብ የሚከሰቱ ናቸው። ሲዲሲ(CDC) የተባለ ድርጅት እንደሚመክረው ከሆነ እጅን በትክክለኛው መንገድ መታጠብ/ማጽዳት በበሽታ እንዳንያዝና ለሌሎች በሽታ እንዳናስተላልፍ የመከላከያ ዘዴ ነው።

ጤና ይስጥልኝ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.