love_hearts_pair-3840x2160ዓይንሽ አርፎበታል። ፍቅር አስይዞሻል። እናም በሆነ አጋጣሚ መነጋገር ጀመራችሁ። ከመነጋገር አልፋችሁ ግንኙነት ለመመስረት እየሞከራችሁ ነው። ግንኙነታችሁ እንዲጠነክር ትፈልግያለሽ። የእሱ ስሜት ግን ላንቺ ግልጽ አይደለም። ከልቡ ይውደድሽ፣ አይውደድሽ የምታውቂው ነገር የለም። ሆኖም በየጊዜው እርስ በርስ የሚጋጩ ምልክቶችን ይሰጥሻል። “እወድሻለሁ” እያለ፣ የሚወድ ሰው የማያደርገውን ነገር ሲያደርግ ታይዋለሽ። ቁርጥ የሆነ አቋም የለውም። ሁልጊዜ ስለፍቅራችሁ የሚያወራው እያቅማማ ነው። የወሲብ ነገር ሲነሳ ግን አቋሙ ግልጽ ነው። የሥጋ ጥብስ እንደ ሸተተው ውሻ ለሀጩን ያዝረከርካል። አንቺን ለመብዳት የማይወጣው ተራራ የለም። ለመበዳት ፈቃደኛ ሳትሆኚ ስትቀሪ ግን አኩርፎ ለተወሰነ ጊዜ አያናግርሽም። ግራ ያጋባሻል። “ይሄ ሰው የሚፈልግኝ ለወሲብ ሞግዚትነት ነው ወይስ ለቁምነገር?” በማለት ራስሽን ትጠይቂያለሽ። ይህ ጽሑፍ ለጥያቄሽ ምላሽ ይዞ ቀርቧል።

ፍቅረኛሽ የሚከተሉትን ምልክቶች ደጋግሞ ካሳየሽ፣ አንቺ ከልብሽ እንደምትወጅው እሱም ከልቡ እንደማይወድሽ በርግጠኝነት ልታውቂ ይገባል። በርግጥ እነዚህ ምልክቶች በማነኛውም ቦታ፣ በማነኛውም ሰዓት፣ ለሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች ላይሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ ወንዶች የሚያዘወትሯቸው ምልክቶች ስለሆኑና ብዙ ጥናት ስለተደረገባቸው፣ ከእውነት የራቁ አይደሉም።

የከነፍሽለት ልጅ የማይወድሽ ከሆነ፦

1) ብዙ ጊዜ ስልክ ስትደውዪለት በ24 ሰዓታት ውስጥ አይመልስልሽም። ጥፋቱን ለመደበቅ የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባል። አንቺም ምክንያቶቹን አምነሽ በመቀበል ሁለተኛ ዕድል ትሰጭዋለሽ። ዳግመኛ ዕድል እንደምትሰጭው ስለሚያውቅና ይቅርታሽን ስለማትነፍጊው፣ ይህን አድራጎቱን ሁሌም ይደጋግመዋል።

ማወቅ ያለብሽ ነገር፦ ይህ ሰው 24 ሰዓታት ሙሉ ቢዚ የሚያደርገው ሥራ እስከሌለው ድረስ ለስልክ ጥሪሽ ምላሽ የማይሰጥበት ምክንያት የለውም። ዋነኛ ምክንያቱ ከአንቺ ለመራቅ የሚያደርገው ጥረት ነው።

2) ከጓደኞችሽና ከቤተሰብሽ ጋር ለመገናኘትና ለመተዋወቅ ጊዜ የለውም። የእሱንም ጓደኞች ሆነ ቤተሰብ ከአንቺ ጋር አያስተዋውቅም። “ዓይናፋር ሆኖ ነው፤ ግንኙነታችን ገና ስላልጠነከረ ይሆናል” እያለሽ ጊዜ ትሰጭው ይሆናል። እሱ ግን የፈለገውን ያህል ጊዜ ቢወሰድ፣ በጓደኝነት ብዙ ጊዜ አብራችሁ ብታሳልፉም የመለወጥ አዝማሚያ አያሳይም። ለጊዜያዊ ወሲባዊ ደስታ ወይም ላልጠበቀ ግንኙነት ብቻ ነው አንቺን የሚፈልግሽ። ሀብት ካለሽ፣ ለሀብትሽ፤ ዝና ካለሽ፣ ለዝናሽ ብሎም ይሆናል ካንቺ ርቆ የማይርቀው።
3) ለአንቺ አስቀድሞ ቀጠሮ መያዝ አይችልም። ከሳምንት ወይም ከወር አስቀድመሽ የሆነ ነገር ከእሱ ጋር ለማድረግ ዕቅድ ስትይዢ፣ ምክንያት ፈጥሮ እንደማይመቸው ወይም ቀጠሮ አስቀድሞ መያዝ እንደማይችል ይነግርሻል። ከልቡ ስለማይወድሽ እንጂ ላንቺ አስቀድሞ ቀጥሮ የማይዝበት ምክንያት ውሱን ነው። ከልቡ ከወደደሽማ አንቺ ሳትጠይቂው እሱ ራሱ ነው ዕቅድ አውጪ የሚሆነው።

4) የሚደውልልሽ ወይም አንቺን ፍለጋ የሚመጣው የምትተኚበት ሰዓት ሲደርስ ብቻ ነው። አንቺን የሚያስታውሰው ስካር ሲያሸንፈው ነው። ለማስመሰል አበባ ይዞልሽ ብቅ ይላል። ወይም እንደለመደው በጣፋጭ ቃላት ሊያታትልልሽ ይሞክራል። አንቺም “ባይወደኝ ኖሮ አበባ ይዞልኝ ይመጣል? ባይወደኝ እንደዚህ እንደሚወደኝ ይነግረኛል?” በማለት ራስሽን ታታልያለሽ።

5) ስለሁሉም ነገር ግልጽ ሆኖ አያወያይሽም። አንዳንዴ ይወድሻል። አንዳንዴ እንደማያውቅሽ ይሆናል። ከአንቺ ጋር ላለመገናኘት ምክንያት እየፈጠረ ራሱን ያርቃል። እንደማይወድሽ ወይም እንደማይፈልግሽ ግን አይነግርሽም። ከአንቺ የሚፈልገው የጠበቀ ግንኙነት ሳይሆን፤ ምንም ነገር ሳይጠበቅበት፣ በፈለገው ሰዓት ተገናኝቶሽ፣ ባልፈለገው ሰዓት ደግሞ ርቆሽ፤ በፈለገው ሰዓት በድቶሽ፣ ባልፈለገው ሰዓት ከሌላ ሴት ጋር እንዳሻው የሚዳራበትንና የሚፈነጥዝበትን ግንኙነት ነው።

እነዚህንና ሌሎች ምልክቶችን የምትወጂው ሰው ደጋግሞ ካሳየሽ፣ ብዙም ጊዜሽን ባታባክኚ ጥሩ ነው። በተለይ ይህን ሰው በልብሽ ለትዳር ካጨሽው፣ አቋምሽን አስተካክዪ። ምክንያቱም እሱ አንቺን የሚፈልገው ለጊዜያዊ የፍቅር ግንኙነት ነው፤ ዘለቄታ ላለው፣ ትዳርን ለሚያሳስብ ግንኙነት አይደለም። በዚህ አቋሙ የምትስማሚ ከሆንሽ ግን ግንኙነቱን ብትቀጥይ የከፋ ችግር ላያስከትል ይችላል። ሆኖም ግን እንደዚህ ኃላፊነትን ለመቀበል ከሚያፈገፍግ ሰው ጋር ልቅ የሆነ ግንኙነትን ስትመሰርቺ መጠንቀቅ ይኖርብሻል። ለምሳሌ ብታረግዢ፣ ከሱ ይልቅ የምትጎጂው አንቺ ነሽ።

(እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው፣ ወንዶች ለሴቶች የሚያሳይዋቸው “የአልፈልግሽም” ምልክቶች፣ ሴቶችም ለወንዶች የሚያሳይዋቸው “የአልፈልግህም” ምልክቶች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። “አንተ ትወዳታለህ እሷ ግን …” የሚለውን ጽሑፍ ይመልከቱ።)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.