ሞባይል ስልኮቻችን ለጤናችን?!

0

መታሰቢያ ካሳዬ

የስኳር፣ የደም ግፊትና የልብ ህመም ችግርዎን በሞባይልዎ መቆጣጠር ይችላሉ
የሞባይል ስልክ ጨረሮች የወንዶችን የወሊድ ብቃት ይቀንሳሉ

Mobile phone ኤሌክሳንድር ግርሃም ቤል ስልክን ፈልስፎ ለዓለም ሲያበረክት ቴክኖሎጂው የሰዎች ለሰዎች ግንኙነትን ብቻ ሳይሆን የየዕለት ተግባራቸውን ለማቅለልና ለማቀላጠፍ የሚረዳ አጋራቸው ይሆናል የሚል ግምት አልነበረውም፡፡ ሰዎችን እርስ በእርስ በድምፅ በማገናኘት የተጀመረው የስልክ ቴክኖሎጂ፤ በወቅቱ እንደ ተዓምር ነበር የታየው፡፡
ቴክኖሎጂው ቀስ በቀስም እየተሻሻለና እያደገ ሄደ፡፡ አሁን ቴክኖሎጂው ሰዎች የዕለት የጤና ሁኔታቸውን የሚከታተሉበት የቅርብ ዶክተራቸው እስከመሆን ደርሷል፡፡
ዓለም አቀፍ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ዩኒየን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 5 ቢሊዮን የሚጠጋ የዓለማችን ህዝብ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡
ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከሚሰጧቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል የሰዎችን የዕለት ተዕለት ተግባራት ቀላል፣ ምቹና የተቀላጠፈ ማድረግ፣ መልዕክቶችን በቀላሉ ለመላክና ለመቀበል ማስቻል፣ መረጃዎችን በፍጥነት ማድረስ፣ እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ካሉ ድርጅቶች ጋር የሚኖረንን የሥራ ግንኙነት ምቹና ቀልጣፋ ማድረግ ጥቂቶቹ ሲሆኑ እድሜ ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች! ዛሬ ለገበያ የሚቀርቡት የተንቀሳቃሽ ስልክ ቴክኖሎጂዎች የተጠቃሚውን የጤና ሁኔታ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሆነዋል፡፡
የስኳር፣ የደም ግፊትና የልብ ህመም ችግርን በተንቀሳቃሽ ስልክ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመስራት ስልክን ተንቀሳቃሽ የግል ሐኪም አድርገውታል፡፡ ይሁን እንጂ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ይኸው ተንቀሳቃሽ ስልክ፤ በአጠቃቀም ችግርና በራሱ በቴክኖሎጂው ተፈጥሮአዊ ባህርይ ምክንያት የሚያስከትላቸው አደገኛ የጤና ችግሮችም አሉ፡
ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለተጠቃሚው እጅግ አደገኛ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች መካከል ጨረሩ በቅድሚያ ይጠቀሳል፡፡ የሬዲዮ ሲግናልን ይዘው የሚረጩት ጨረሮቹ ለጤና እጅግ አደገኛ ችግሮችን ያስከትላሉ፡፡ በሞባይል ስልክ አጠቃቀም ወቅት ስልኩ ተግባሩን እንዲከውን የሚያደርጉት ጨረሮች በቅድሚያ የሞባይል ስልኩን አንቴና ያገኙታል፡፡ ይህ አንቴና ደግሞ የስልክ ተጠቃሚው በሚነጋገርበት ወቅት ከጆሮ ግንዱ ስር በመሆን መልዕክቱን እንዲቀበል የሚያደርገው ነው፡፡ ቦታው ከአንጎላችን ጋር ተቀራራቢ ከመሆኑ አንጻር ደግሞ በሞባይል ስልኩ አንቴና ለሚረጩት ጨረሮች በቀላሉ ተጠቂ ይሆናል፡፡ በዚህ ሳቢያም የአንጎላችን የነርቭ ሥርዓት በጨረር ሊጎዳና ለከፍተኛ ጉዳት ሊጋለጥ እንደሚችል Environmental Health Perspectives የተሰኘ የጥናትና ምርምር መፅሔት ዘግቧል፡፡ በሞባይል ስልክ የሚለቀቀው ጨረር ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች መካከል ካንሰር፣ ከፍተኛ የልብ ህመም ተጠቃሽ ሲሆኑ ጨረሩ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኘውንና አንጎላችንን ከተለያዩ መርዛማ ኬሚካሎችና ያልተፈለጉ ንጥረ ነገሮች የሚጠብቀውን “ብለድ ብሬይን ባርየር” የተባለውን ክፍል ሊጎዳውና ከጥቅም ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል የምርምር መፅሄቱ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሞባይል ስልክ የሚለቀቀው ጨረር የወንዶችን የወሊድ ብቃት እንደሚቀንሰውና ለስንፈተ ወሲብ ሊያጋልጥ እንደሚችል መረጃው አመልክቷል፡፡ የተጠቃሚው ለጨረሩ ተጋልጦ የመቆየት መጠንና የመጋለጥ ዓይነቱ የሚደርስበትን የጉዳት መጠንም እንደሚወስነው መረጃው ገልጿል፡፡
ሞባይል ስልኮች የጤና ጠንቅ በሆኑ ባክቴሪያዎች የተበከሉ ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ በአሜሪካ የተደረገ አንድ ጥናት እንደገለፀው፤ በሞባይል ስልክ ቀፎዎች ላይ የተገኙት ባክቴሪያዎች እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ በእጅ ንክኪ አሊያም በትንፋሽ ሊተላለፉ የሚችሉ አደገኛ የበሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች በስልክ ቀፎዎቹ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሞባይል ቀፎ አምራች ኩባንያዎች ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በስልክ ቀፎ መሸፈኛዎች ላይ ፀረ ባክቴሪያ ሽፋኖችን በመለጠፍ ባክቴሪያዎቹ ወደቀፎው በሚተላለፉበት ወቅት የጤና ጠንቅነታቸውን ያስቀረዋል፡፡
ለሞባይል ስልክ አጠቃቀም የሚረዱ ነጥቦች
በሞባይል ስልኮች ጨረር በከፍተኛ መጠን መጋለጥ የጤና ሥጋት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ስለዚህም በተቻለ መጠን ለሞባይል ስልኮች ጨረር የምንጋለጥበትን ሁኔታ መቀነስ ይገባል፡፡ ለዚህም በተቻለ መጠን መልዕክቶችን በፅሁፍ መልዕክት (SMS) መቀባበል የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይመከራል፡፡
የሞባይል ስልኮችን እንደ ጡት ባሉ አካባቢዎች ከመያዝ መቆጠብ፡፡ ወንዶች የተጣበቀ ሱሪ ለብሰው ሞባይል ስልኮቻቸውን በሱሪ ኪሳቸው ውስጥ ሲይዙ ጥሪ በሚያሰማበት ወቅት ከስልኩ የሚወጣው ጨረር በወንዶች የፆታዊ አካላት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ስልኮችን በእጅ ቦርሳና ሰፋ ባሉ ልብሶች፡- ኮት፣ ጃኬትና መሰል አልባሳት መያዝ በስልክ ጨረር ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ሊያስቀር ይችላል፡፡
ሞባይል ስልኮቻችን የበርካታ ባክቴሪያዎች መራቢያና የበሽታ አምጪ ቫይረሶች መከማቻ ስለሚሆኑ እጃችንን በንፁህ ውሃና በሳሙና ሳንታጠብ ከመመገብ መቆጠብ፣ ስልኮቻችንን በየጊዜው በአልኮል እንዲሁም በፀረ ባክቴሪያና በማፅጃ ኬሚካሎች በማፅዳት በበሽታ ከመያዝ ራሳችንን ልንታደግ እንደምንችል ጥናቱ አመልክቷል፡፡

Spread the love
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.